“እንደ ሀገር ያጣነውን ነገር ለመጠገን የኃይማኖት አስተምህሮ አስፈላጊ ነው”  ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፡- እንደ ሀገር ያጣነውን ነገር ለመጠገን የተባበረ ክንድ እና የኃይማኖት አስተምህሮ አስፈላጊ በመሆኑ ጉባዔው ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ።

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔና የእውቅና መድረክ ትናንትና ሲካሄድ እንደገለጹት፤ የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ ያለብንን ኃላፊነት ልንወጣ ይገባል። እንደ ሀገር ያጣነውን ነገር ለመጠገን የተባበረ ክንድ እና የኃይማኖት አስተምህሮ አስፈላጊ በመሆኑ ጉባዔው ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል።

በኃይማኖቶች መካከል የአብሮነት እሴትን ሊያጠናክሩ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ገልጸው፤ የኃይማኖት ተቋማት ለሀገራዊ የሠላም ግንባታ ከፍተኛ ሚና አላቸው። በኃይማኖቶች መካከል የአብሮነት እሴትን ሊሸረሽሩ የሚችሉት ጉዳዮችን መከላከል ከኃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ስራ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ፣ የኃይማኖት አባቶች በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው ተሰሚነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው ምዕመናንን ስለ ሰላምና አንድነት በማስተማር ሀገራዊ ወሳኝ ጊዜያትን ለማለፍ የላቀ ሚና መጫወታቸውንም አንስተዋል።

ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና አንድነት የኃይማኖት አባቶች መንፈሳዊ ድጋፍና የተባበረ ክንድ ያስፈልጋልም ብለዋል። የኃይማኖት ተቋማት ልዕልና እና ክብር ተጠብቆ እንዲቆይ ሁል ጊዜም ጥረት እንደሚፈልግም አስገንዝበዋል።

የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ኸይረደን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ኢትዮጵያ በተፈተነችባቸው ጊዜያት ሁሉ አብረው የተፈተኑ የእምነት ብቻ ሳይሆን የማንነትም መገለጫ ጭምር መሆናቸውን ተናግረዋል። ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ ከፈተና ጀርባ ተስፋ መኖሩን ያመላክቱን ውድ ተቋማት ናቸውም ብለዋል።

የኃይማኖት ተቋማት ለሠላም ግንባታና ለዘላቂ አንድነት ለማዋል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ሥራዎችን በአብሮነት እየሠራ መሆን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የተቋማቱን አቅም ለዘላቂ አንድነት የማዋል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

እስካሁን ድረስም ያለማንም ትዕዛዝ ለሠላም፣ ለአብሮነትና ለዘላቂ አንድነት እየሠሩ ላሉት የኃይማኖት ተቋማት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የጉባዔው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ሊቀጳጳስ አባ ጎርጎርዮስ ጉባዔው ባለፈው በጀት ዓመት በጉባዔው የበላይ ጠባቂ አባቶችና በጠቅላላ ጉባዔው የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነትንና አደራን ለመፈጸም በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ተናግረዋል።

የሰላምና መከባበር እሴትን የሚገነቡ እንዲሁም የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቀነስ የሚረዱ የተለያዩ የምክክር መድረኮች፣ ሥልጠናዎችና አውደ ጥናቶችን በማካሄድ የተሳታፊዎችን ግንዛቤ የሚያጎለብቱ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል። በቀጣይም ተመሳሳይ ተግባራትን በመፈጸም እንደ ሀገር የተቀመጡ ዕቅዶችን ለማሳካት ጉባዔው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚበረክትም አመላክተዋል።

ጉባዔው አባል የኃይማኖት ተቋማትን በማስተባበር ስለሰላም፣ ስለ አብሮነት፣ ስለ ይቅርታ፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ በጎ ምግባርና ስለ መልካም እሴቶች በመደበኛነት ለማስተማር በሚያደርገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት አዎንታዊ ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉለትም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኃይማኖት ተቋማቱ ጉባዔ በበጀት ዓመቱ ላከናወናቸው ተግባራት ከጎኑ ለነበሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እውቅናና ሽልማት ያበረከተ ሲሆን፣ በመርሐ ግብሩ አባል የኃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ምዕመናንና አጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ሀምሌ 26 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You