መንግሥት ከሰሞኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ይፋ አድርጓል፡፡ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወሰንበት የውጭ ምንዛሬ የገበያ ሥርዓት መሸጋገሩ ተጠቃሽ ነው።
ወደ ተግባር የገባው የውጭ ምንዛሬ የገበያ ሥርዓት ላኪዎች እና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው ማስቀረት ያስችላቸዋል። ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንደሚያሻሽልም የሚጠበቅ ነው።
ወደ ውጭ የሚደረግ የካፒታል ሂሳብ ፍሰት የተገደበ ቢሆንም፤ የውጭ ምንዛሪ ገበያው ለገቢ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ነጻ መደረጉን መንግሥት አሳውቋል።
በጥቅሉ ውሳኔው የውጭ ምንዛሬ በአቅርቦትና ፍላጎትን ለማመጣጠን፤ የገቢና የወጪ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ዋጋ ከገበያ ጋር እንዲጣጣም እና የሀገሪቱን የዕዳ ክፍያ ሚዛን ለማስተካከል ይረዳል የተባለለት ነው።
ለመሆኑ የውጭ ምንዛሪን ገበያው እንዲወስነው ማድረግ ምን ፋይዳ አለው? ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮችና መሻገሪያ መንገዶችስ ምንድን ናቸው?
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር)፤ እንደሀገር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፈተና ሆኖ መቆየቱን ያነሳሉ። በዚህም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማሟት፣ ገቢ ምርቶችን ለማስመጣትና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳብ እክል ሲፈጥር እንደቆየ ያብራራሉ።
ምርቶችን ከውጭ የሚያስመጡ ነጋዴዎችም የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ጥቁር ገበያን እንዲጠቀሙ ተገድደው እንደነበረ ጠቁመው፤ ይህም የትርፍ ህዳጋቸው እንዲጠብና ማህበረሰቡ ላይም የዋጋ ንረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል ይላሉ።
የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ በገበያ መወሰን ባንኮች የዶላር አቅርቦት እንዲኖር እና በሕገወጥ የምንዛሬ አቅራቢዎች ዘንድ ገበያው ጋር ያለው ሰፊ ልዩነት እንዲጠብ ለማድረግ ያስችላል ያሉት ይንገስ ዶ/ር፤ ወደውጭ የሚላኩ ምርቶችን ዋጋ እንዲጨምር እንደሚያግዝም ያብራራሉ።
ፖሊሲውን በታሰበው ልክ መተግበር ከተቻለ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲያድግ ያደርጋል የሚሉት ይንገስ (ዶ/ር)፤ ወጪ ንግድን በማበረታታትም ከፍተኛ የዶላር ክምችት እንዲኖር ያደርጋል። ነጋዴዎችም በቀላሉ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ ያስችላል ይላሉ።
ይሁን እንጂ የዶላር ዋጋ መጨመርን ምክንያት በማድረግ ሀገራዊ ምርትና አገልግሎቶች ላይ አላግባብ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር መንግሥት ጠንካራ የቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባው ይጠቁማሉ።
ሀገሪቱ ላይ የሚታየው የፖለቲካ ትኩሳትና የሰላም እጦት ተንቀሳቅሶ ለመሥራትም ሆነ ምርትና ምርማነት ላይ እክል በመፍጠር ለትግበራው እንቅፋት ሊሆን የሚችልበት እድል ሰፊ ነው የሚሉት ምሁሩ፤ ሀገራዊ ፖለቲካው ላይ በሚኖር ልዩነት ምክንያትም ከውጪ የሚላከው ገንዘብም በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ሊያደርግ እንደሚችል ይጠቁማሉ።
መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ማስፈንና በብድር እና በርዳታ የተገኘው ሀብትም የሀገር ኢኮኖሚና የሕዝቡን ሕይወት መቀየር በሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ መዋል የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሠራባቸው የሚችሉ ተግባራት መሆን እንዳለባቸውም ያስረዳሉ። በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ሀብታሙ ለገሰ ከላይ በተነሳው ሃሳብ ይስማማሉ።
ሆኖም የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ በገበያ እንዲወሰን መደረጉም ጥቅምም ስጋቶችም ይኖሩታል የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ ስኬታማነቱም መንግሥት በሚወስዳቸው ርምጃዎችና በፋይናንስ ተቋማት ጥንካሬ ይወሰናል ባይ ናቸው።
መንግሥት እና ብሔራዊ ባንክ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ለንግድ ባንኮች የሚያጋሩ ከሆነ ወደ ኢንቨስትመንት የሚገቡ ባለሀብቶችና ከውጭ ዕቃ የሚያስመጡ ነጋዴዎች በቀላሉ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ያስችላቸዋል። ይህም የምርቶችና የአገልግሎቶች ዋጋ እየቀነሰ እንዲሄድ ሊያደርግ የሚችል መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ነገር ግን ከዚህ በፊት እንደነበረው በባንክ በቂ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ሳይቻል ቀርቶ ወደ ሕገወጥ ምንዛሬ ገበያ የሚሄዱ ከሆነ የዋጋ ንረቱ ሊባባስ የሚችልበት ዕድል መኖሩንም በስጋትነት ያነሳሉ።
ብሔራዊ ባንክ በብድርም ሆነ በሌላም መንገድ ከሚያገኘው ዶላር ላይ ቢያንስ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንኳን ወደኢኮኖሚው እንዲገባ ቢያደርግ ነጋዴዎች በቂ ዶላር እንዲያገኙና ጥቁር ገበያው እንዲሸነፍ ማድረግ ይቻላል ሲሉም ያስረዳሉ።
ይህም ገበያውን በሂደት የሚያረጋጋ፤ ኢንቨስተሮችን የሚያበረታታ እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ ወደሀገር የሚላከውን የውጭ ምንዛሪም እንዲያድግ የሚያደርግ ነው ይላሉ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ባንኮች የውጭ ምንዛሪን በራሳቸው እንዲፈልጉ የሚተው ከሆነ ግን ጥቁር ገበያው እንዲጨምርና የዋጋ ንረቱም እንዲባባስ ያደርጋል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።
የብር ዋጋ እንዲቀንስ ካደረጉ ምክንያት አንዱ ኢኮኖሚው ከሚያመርተው በላይ ከፍተኛ ብር መኖር ነው የሚሉት ባለሙያው፤ ኢኮኖሚው ላይ ብሔራዊ ባንክ የጀመረውን ሰነዶችን ለንግድ ባንኮች እየሸጠ ገበያ ውስጥ ያለውን ገንዘብ የመሰብሰብ ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት ይመክራሉ።
እነዚህን ርምጃዎች በአፋጣኝ መውሰድ ካልተቻለ ግን ማህበረሰቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ስጋት አላቸው። የፋይናንስ ተቋማት ከሚያከናውኑት ሥራ ጎን ለጎን አስፈጻሚ አካላት የቁጥርና ክትትል ሥራውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ይጠቅሳሉ።
ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ማህበረሰቡ ላይ ጫና እንዳይፈጠር የነዳጅ ድጎማ ሥርዓቱን ማሳደግ እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ማህበረሰቦች አስፈላጊውን ድጎማ ማድረግ እንደሚኖርበት ያብራራሉ። በረጅም ጊዜ ደግሞ የግል ዘርፉ የማይገባባቸውን እና ማህበረሰቡ በዋናነት የሚቀምባቸው ዘርፎች እየለየ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ማድረግ እና በሂደትም የግሉ ዘርፍ እንዲረከበው መሥራት ይጠበቅበታል ይላሉ።
እንደባለሙያዎቹ ማብራሪያ፤ የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ በገበያ መወሰን ጥቅም እንዳለው ሁሉ ስጋቶችም ይኖሩታል። ይህም መንግሥት በሚወስዳቸው ጠንካራ የቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት ላይ ይወሰናል። በመሆኑም መንግሥት የውጭ ምንዛሬ የገበያ ሥርዓት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል ማድረግ ይገባዋል።
የሚገኙ ርዳታና ብድሮችንም ቀጣይነት ያለው ሀብት ሊያፈሩ በሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ ማዋል ያስፈልጋል። ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ምርትና ምርማትን ማሳደግ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን እንዲሁም የወጪ ንግድ ሥርዓትን ማጠናከርም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሀምሌ 26 /2016 ዓ.ም