የመጀመሪያው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር (Home-Grown Economic Reform Program) ብዙ የፖሊሲ ሃሳቦችን በውስጡ ያካተተና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ዓላማዎችንና ግቦችን ያሳካ እንደነበር መንግሥት ሰሞኑን አስታውሶ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ደግሞ ቀሪ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እንደሚያስችል ገልጿል።
የመንግሥትን ኢንቨስትመንት ውጤታማነት በማሻሻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባት በመርሃ ግብሩ ትግበራ ከተቀመጡ ግቦች መካከል አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል። በሌላ በኩል ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ከተገነባባቸው አራት ዋና ዋና ምሰሶዎች መካከል አንዱ፣ ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ነው።
ኢትዮጵያ ሰሞኑን ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ ገብታለች። ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ዋና ዋና የፖሊሲ ርምጃዎችና የሚጠበቁ ሀገራዊ ፋይዳዎች መካከል አንዱ፣ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት (Floating Exchange Rate) ትግበራ ነው። ሀገሪቱ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ መግባቷ መገለፁን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት መሻሻሉን ይፋ አድርጓል። በዚህም የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት በገበያ ላይ ወደተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ተሸጋግሯል።
ይህ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል አንዱ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ እንደሆነ መንግሥት ገልጿል። አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት የውጭ ምንዛሬ ግኝትንና ክምችትን ሊጨምሩ የሚችሉ ልዩ ልዩ አሠራሮችን አስተዋውቋል። ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታን በመተው ላኪዎችና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው ማስቀረት የሚያስችላቸው በመሆኑ፣ ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በእጅጉ እንዲሻሻል ያደርጋል።
በአዲሱ አሠራር በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ከውጭ የሚላክላቸውን ሐዋላ፣ በውጭ ምንዛሪ የሚከፈል ደሞዝን/የኪራይ ገቢን እና ሌሎች ገቢዎችን የሚያስቀምጡባቸውን የውጭ ምንዛሪ ሂሳቦች እንዲከፍቱ፣ እንዲሁም እነዚህን የውጭ ምንዛሪ ሂሳቦች ተጠቅመው የውጭ አገልግሎት ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ ተፈቅዷል። መመዘኛውን የሚያሟሉ የውጭ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ (Ethiopian Securities Exchange) እንዲሳተፉ ተፈቅዷል። በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚሠሩ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን ሙሉ በሙሉ ለራሳቸው መያዝን ጨምሮ ልዩ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም መብት ተሰጥቷቸዋል።
ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች ካፈሩት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለራሳቸው ያስቀሩት የነበረው 40 በመቶ ወደ 50 በመቶ ከፍ ብሏል። ቀደም ሲል ባንኮች ለተለያዩ ገቢ ሸቀጦች የሚጠቀሙበት የውጭ ምንዛሪ አሠራርና አደላደል ደንቦች ቀሪ ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪም አሁን በሥራ ላይ ካሉና በባንኮች ከተቋቋሙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች (ForEx Bureaus) በተጨማሪ ባንክ ያልሆኑ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች (Independent ForEx Bureaus) ይቋቋማሉ፤ ለእነዚህ ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችም በገበያ ዋጋ የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ እንዲገዙና እንዲሸጡ የሥራ ፈቃድ ይሰጣቸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ስለውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያው በሰጡት ማብራሪያ፣ ማሻሻያው ለኢንቨስትመንት እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል። አቶ ማሞ እንዳስረዱት፣ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ፣ የሀገሪቱን የንግድ ሥርዓት ከአጎራባችና ከአቻ ሀገራት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
‹‹በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ከታላላቅ የአፍሪካ ኢኮኖሚዎችና በማደግ ላይ ከሚገኙ በርካታ ሀገራት መካከል የውጭ ምንዛሪ ቁጥጥር ሥርዓትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያለባት ሀገር ናት። ሀገሪቱ ከሕዝብ ብዛት፣ ከሠለጠነ የሰው ኃይል፣ ከተመጣጣኝና ከተወዳዳሪ ግብዓቶች (የሰው ጉልበት፣ መሬት)፣ ከተጠናከረ የአየር ትራንስፖርትና ከተሻሻለ ሎጂስቲክስ፣ ከኃይል አቅርቦት፣ ከተፈጥሮ ሀብትና ከማዕድናት አኳያ በብዙ መልኩ ለኢንቨስትመንት ምቹና ሳቢ ብትሆንም፣ እነዚህ ሁሉ ዕድሎች በአስቸጋሪና ጥብቅ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ምክንያት ውጤታማነታቸው የተጠበቀውን ያህል አልሆነም። ›› ብለዋል። ስለዚህ፣ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ለውጭ ኢንቨስተሮች ማነቆ ሆኖ የቆየውን አሠራር ለማስወገድና ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት እንደሚጠቅም አመልክተዋል።
አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ያበረታታል፤ የማምረት ሥራቸውን እንዲያስፋፉና የገበያ ድርሻቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል። በኢንዱስትሪና በፍጆታ ዕቃዎች ምርት ዘርፎች የተሠማሩ ተኪ ኢንዱስትሪዎች፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› በተሰኘው ንቅናቄ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ከማሻሻያው ተጠቃሚ ይሆናሉ።
እሳቸው እንደተናገሩት፣ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግሉን ዘርፍ ለማሳደግና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዘመን እንዲሁም ኢኮኖሚውን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ የተወሰዱ ሌሎች በርካታ የማሻሻያ ርምጃዎችን የሚደግፍና የሚያጠናክር ይሆናል። ከእነዚህም የማሻሻያ ርምጃዎች መካከል፣ ቀደም ሲል ለግል ዘርፍ/ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ የነበሩ ዘርፎችን (ለምሳሌ ቴሌኮም፣ ሎጂስቲክስ፣ ባንክ፣ ካፒታል ገበያ፣ ጅምላና ችርቻሮ ንግድ) ክፍት ማድረግ፣ የንግድ ማሳለጫ ሥርዓት ማሻሻል፣ የግል ዘርፍና በመንግሥት ፕሮጀክቶች በአጋርነት ማሳተፍ፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ማቋቋም … ይገኙባቸዋል። በእነዚህ ዘርፎች የተደረጉ ለውጦች ለግሉ ዘርፍና ለኢኮኖሚ ዕድገት አያሌ መልካም ዕድሎችን ቢከፍቱም፣ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲዎች ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች ማነቆ ሆነው በመገኘታቸው ማስተካከያ ማድረግ የግድ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ሌሎች የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ የወጡ በርካታ የለውጥ ርምጃዎችን ለማጠናከር እንደሚረዳ አቶ ማሞ ምህረቱ አስረድተዋል።
የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለሀገሪቱ ኢንቨስትመንት እድገት ማነቆ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ይፋ የተደረጉት አሠራሮች በኢንቨስትመንት ሥራ ውስጥ ቁልፍ ሚና ካላቸው ግብዓቶች መካከል አንዱ ለሆነው የውጭ ምንዛሬ ግኝትና ክምችት መጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የልማት እቅድና የመንግሥት ኢንቨስትመንት አስተዳደር የሥራ ክፍል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ በረከት ፍስሃጽዮን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው ለኢንቨስትመንት ማደግ በጎ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይገልፃሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፣ ቀደም ሲል የነበረው አሠራር ኢኮኖሚውን አንቆ የያዘ የውጭ ምንዛሪ አሠራር ሥርዓት ነበር። አዲሱ አሠራር ይህንን በመሻገር ውጤታማ የሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻልባቸውን ዘርፎች ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል። ይህም ለሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ይሆናል። የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ውጤቶችን በግብዓትነት የሚጠቀሙ አምራቾች ይኖራሉ። ሀገራዊ አቅምን በአግባቡ በመጠቀም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ሂደትን የሚያበረታታም ይሆናል።
የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ያበረታታል። የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ይዘዋቸው የሚመጡ እድሎችና መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉ መታወቅ አለበት። በሪፎርሙ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ የሚደረግ ከፍተኛ መጠን ያለው ፋይናንስ ይኖራል። በአጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያው ኢንቨስትመንቱን ያነቃቃዋል። ማሻሻያው የመንግሥትን ገቢ በማሳደግና የመንግሥት ወጭ አስተዳደርን በማዘመን የማኅበራዊና የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች እንዲጠናከሩ ያግዛል።
‹‹ማሻሻያው የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የማሳደግ አቅም ይኖረዋል። በሀገር ውስጥ አቅም ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶችን የማምረት እድል በመስጠት፣ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሰፊ እድል ይከፍታል፤ በዚህም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጠራል። ትክክለኛውን ዋጋ ይዞ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማረጋገጥ የተመጣጠነ የወጪና የገቢ ንግድ እንዲኖር ያደርጋል። ተወዳዳሪ መሆን መቻል ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመጠገን ይረዳል። ይህም የንግድ ሚዛን ጉድለትንና የክፍያ ሚዛንን ለማስተካከል ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በዚህም የተረጋጋ ኢኮኖሚ ይፈጠራል። በግሉ ዘርፍ ለይ የተመሠረተ ጠንካራ ነጻ ኢኮኖሚ ዋናው ማረጋገጫው በገበያ የተመሠረተ ዋጋ መኖሩ ነው›› በማለት ያብራራሉ።
ቀደም ሲል የነበሩ የማክሮ-ኢኮኖሚ መዛባቶችን ለማረም እና ኢኮኖሚው ያጋጠሙትን መዋቅራዊ ችግሮች ለመፍታት መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ሲደረጉ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ በረከት፣ አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አካል እንደሆነ ይገልፃሉ።
አቶ በረከት እንደሚያስረዱት፣ የውጪ ምንዛሪ አስተዳደርን የተመለከተው ጉዳይ የኢኮኖሚውን ዋነኛ ማነቆዎችን ለመፍታት መከናወን የነበረበት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል ነበር። በመጀመሪያው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ለማረም፣ የእዳ ጫናን ለማቃለል፣ የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ እና የኢኮኖሚ እድገት ምንጮችን ለማስፋት በተከናወኑ ሥራዎች ብዙ ውጤቶች ተገኝተዋል።
የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያው በሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር የሚተገበር ነው። ‹‹በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በድንገት የተከሰተ ሳይሆን ቀደም ሲል ሲተገበሩ ከነበሩት ጋር የሚያያዝና በሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ሊተገበር እቅድ የተያዘለት ነው›› በማለት ያስረዳሉ።
የፐብሊክ ፖሊሲ ጥናት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ በበኩላቸው፣ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያው ለሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ብሎም ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው ትልቅ እምርታን የሚያስገኝ ርምጃ እንደሆነ ይናገራሉ ‹‹ይህን ዓይነቱን አሠራር ካደጉት ሀገራት በተጨማሪ ብዙ የአፍሪካ ሀገራትም ይጠቀሙበታል። የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ያበረታታል። ከካፒታል ገበያው መጀመር እና ከውጭ ባንኮች መግባት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ኢንቨስተሮች ሊመጡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር ያደርጋል። ማሻሻያው ኢኮኖሚውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊጠቀምበት በሚችለው መንገድ ሊያራምደው ይችላል›› ይላሉ።
ማሻሻያው ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት የኮንትሮባንድ ስራዎችን፣ በተለይም ከሀገር ውስጥ የሚወጣውን ገንዘብ መቆጣጠር እንዲሁም ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን እንዳለበትም ይመክራሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም