ሥልጣኔ ከራስ ሲጀምር ፣ ቤተሰብ አካባቢና ሀገር ይዘምናል:: መሠልጠንን ባህል ያደረገ ትውልድ ሲበዛ ደግሞ መልካም እሴቶች ይበረክታሉ፣ የማህበረሰቡ አመለካከትም በአንድ ይቃኛል:: ዛሬ ዓለማችን ለደረሰችበት የዘመን ቴክኖሎጂ አንዱ ለእያንዳንዱ፣ ሌላውም ለብዙሃኑ ያደረገው አስተዋጽኦ ውጤቱን አልቆታል :: ሥልጣኔን አምኖ ለውጥን ከራስ የጀመረ ትውልድ የሚያደርገውን ሁሉ ጠንቅቆ ያውቃልና::
ብዙዎች እንደሚስማሙበት ሥልጣኔ ማለት የሠለጠነ ባህል ወይም ህብረተሰብ ማለት ነው:: እኛ አልፈን በተጓዝናቸው ዘመናት ሁሉ የሥልጣኔ ዐሻራዎቻችን አብረውን ነበሩ:: ጊዜው በሚዋጀውና ትውልዱ በሚሸከመው አቅም ልክም የራሳችን ቀለም ሲንጸባረቅ፣ ሲደምቅ ቆይቷል::
ይህ እውነት ከማንነታችን ተሻግሮ አፍሪካዊ፣ ብሎም ዓለምአቀፋዊ ምልክታችን እንደሆነ ዘልቋል:: እንዲህ መሆኑ ከሌሎች ሲለየንና ሲያኮራን የቆየ ቢሆንም ‹‹ስም ብቻውን›› ሀውልት እንደማይሆን ግን ቆይተንም ቢሆን ተረድተናል::
ዛሬ በቆምንበት ዘመን ደግሞ ለሥልጣኔው ግንባር ቀደም ከምንባለው ኢትዮጵያውያን ዓለም ብዙ ቢጠብቅ አያስገርምም:: እንዴትና ለምን የሚል ጠያቂ ቢኖር ደግሞ ምላሹ በብዙ ሊመነዘር ይችላል:: ኢትዮጵያ የሥልጣኔዎች ሁሉ መነሻ፣ የዘመናዊነት ጥንስሰ ስለመሆኗ አፍን ሞልቶ መናገር አያሳፍርምና::
በተለያዩ ጊዜያት ስለ ኢትዮጵያ ቀደምትነት የጻፉ የውጭ ሀገራት ዜጎች ይህች ሀገር አሁን ለምንገኝበት ሥልጣኔ በር ከፋች ስለመሆኗ በእማኝነት አረጋግጠዋል:: መላው ዓለም ሥልጣኔ ይሉትን ቃል በወጉ በማያውቀው ቀዳማዊ ዘመን አክሱም ላሊበላን ያቆመ፣ የራሱን ፊደል የቀረጸ፣ በብቸኛ የዘመን ቀመር የቆጠረ፣ ፋሲል ግንብን የመሰሉ ኪነህንጻዎችን ያነጸ፣ ትውልድ ታላቋን ኢትዮጵያ አድምቋት አልፏል::
ዛሬ ከዘመናት በኋላ ይህች ሀገር ልትደርስበት የሚቻላትን ዘመናዊነት ሌሎች ሀገራት ቀድመው ተቆናጠውታል:: በአባቶቹ ታሪክ ‹‹ነበር››ን የሙጥኝ ብሎ የቀጠለው ትውልድ ዳናውን ይዞ አለመከተሉ ዛሬ ኢትዮጵያ ለምትጠራበት የኋላቀርነት ስያሜ አይነተኛ ምክንያት ሆኗል::
ሥልጣኔ በድርጊት ብቻ አይገለጽም:: ዘመናዊነት የሚለካው ከራስ በሚነሳ አመለካካት ጭምር እንጂ:: ውጫዊ ዕድገት በሚታይበት አቋም ውስጣዊ ማንነት አብሮ ካልበለጸገ ደግሞ ዕድገት በእኩል ሊፈጥንና ሊሮጥ አይችልም::
ሥልጣኔን ባህሉ ያደረገ ትውልድ ሁሌም ከስህተቱ ይማራል:: መቼም ቢሆን በራሱ የአዕምሮ ትዕዛዝ ይገዛልና የሌሎችን አስታዋሽነት አይሻም:: ሥልጣኔን ከራሱ ያራቀ ፣ ዘመናዊነትን ሊቀበል የሸሸ ቢኖር ደግሞ መቼም ከስህተት አያልፍምና ከቅጣትና ጸጸት ጋር ሊኖር ግድ ይለዋል::
አብዛኞቻችን ከዕድገታችን ማነስና ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተያይዞ ተለምዷዊ አኗኗርን ፈጥነን ለመተው ስንቸገር ይስተዋላል:: የዘመናዊነት ኑሮ አጠገባችን እያለ እንኳን የኖርንበትን ልማድ ለመተው አቅም አናጣለን:: ይህ እውነት ከፍ ሲል ደግሞ ከራስ አልፎ ለአካባቢ ብሎም ለሀገር ጠንቅ ሲሆን ይታያል::
ተደጋግሞ እንደሚባለው ሥልጣኔ ከአእምሮ ካልመነጨ ዕድገቱ ሙሉ ሆኖ አይቆምም :: አስቀድሞ አስተሳሰብ ላይ ያልተሠራ ዘመናዊነትም በተግባር የሚተረጎም አይሆንም:: በትንሹ አንድ ምሳሌ ላንሳ፤ ስለቆሻሻ አወጋገዳችን:: ተገቢው ገንዳ በወጉ ተቀምጦ ለዓይን የሚከብድ ቆሻሻን በገንዳው ዙሪያ ጥሎ መሄድ ከኋላቀርነትም በላይ ሕገወጥነት ነው:: እንዲህ መሆኑ ግን ከሕግ ተጠያቂነት አያስጥልም:: ዘመናዊነት የገባው ትውልድ ለሕገወጥነት አይዳረግም:: የሚሠራውን ያውቃልና ሁሌም ለሕግና መመሪያ ተገዢ ነው::
አጥፊና ሕግን ተጻራሪ በሌለበት ማስጠንቃቂያ፤ ቅጣትና እስር ይሏቸው አጋጣሚዎች አይኖሩም:: በሥልጣኔ አምኖ ለዘመናዊነት የሚገዛ ትውልድ ደግሞ በትናንሽ ተራ ጉዳይ ተጠያቂ የመሆን አጋጣሚው የጠበበ ነው:: ሕግን የሚያከብር ትውልድ በበዛ ቁጥር ሀገር ትለማለች:: ሕዝብም በዘመናዊነት ጎዳና ተራምዶ በሥልጣኔ መስመር ያብባል::
ከጥቂት ጊዜ ወዲህ በመዲናችን አዲስ አበባ እየታየ ያለው ለውጥ የዘመናዊነት አንዱ መገለጫ ነው:: አሮጌው በአዲስ መተካቱ፣ ለዓይኖች መልካም እይታ መፈጠሩና ፈጣን የሥራ ባህል መዳበሩም በመልካም ጎን የሚታይ እውነታ ነው::
ከዚሁ ለውጥ ጋር ተያይዞ በርካቶች የሥራ ዕድል አግኝተዋል:: አዳዲስ ተግባራዊ ለውጦችም ተስተውለዋል::
ይህ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰበት የሀገር ሀብት በአግባቡ ተጠብቆ ለትውልድ ያልፍ ዘንድ የእያንዳንዱ ነዋሪ ሃላፊነትና ግዴታ መሆኑ አያጠያይቅም:: እነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ሥራ ሲጀምሩ ሊያጋጥም የሚችል የጥንቃቄ ጉድለት ታዲያ ‹‹ግዴለሽነት›› ተብሎ ብቻ የሚታለፍ አይሆንም::
ዘመናዊነትን ተከትሎ ሥልጣኔን የሚተገብር እንዳለ ሁሉ ለዚህ ደንብ ተገዢ የማይሆን ማንነት ሊኖር እንደሚችልም ይገመታል:: ጥፋት ከመፈጸሙ አስቀድሞ ማስተማርና ማስጠንቀቅ ያለ ቢሆንም ደንቡን ተላልፎ ድርጊቱን የሚፈጽም አካል ሲገኝ ደግሞ ተገቢው ቅጣት ሊተገበር የግድ ይላል::
ሰሞኑን ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ የሚኖር የሀብት አጠቃቀምና ሕግን በሚጥሱት ላይ የሚከተለው የቅጣት አወሳሰን ደንብ ይፋ ሆኗል:: የከተማዋ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣንን ጨምሮ የከተማዋ ትራፊክ ማኔጅመንት በየግላቸው ያወጡት ጠንከር ያለ ሕግ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆንም ተጠቅሷል::
በከተማዋ የኮሪደር ልማትና በተሠሩ መንገዶች ላይ ሕግ ተጥሶ ሲገኝ ዕውን የሚሆነው ሕግ ታዲያ አሽከርካሪዎችና እግረኞች ላይ ጭምር የሚተገበር ነው:: እግረኞች፣ አሽከርካሪዎችና ብስክሌተኞች በጋራ ለሚጠቀሙበት መንገድ በእኩል ተናበው በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ በደንቡ ላይ ተጠቅሷል::
ከዚሁ የመንገድ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚኖር የሕግ ጥሰት በአግባቡ የሚዳኝ ሲሆን ቆሻሻን ባልተገባ ቦታ ጥሎ የሚገኝ ማንኛውም ሰው በተቀመጠው ደንብና መመሪያ መሠረት የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልበት ተገልጧል::
ወደቀደመው መነሻችን እንመለስ ፣ ሥልጣኔን ወዳነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ:: ዘመናዊነትን ተግባራዊ ባደረግንበት በአሁኑ ዘመን እንደቀድሞው ማንነታችን በወጉ ያልተከተለን ሥልጣኔ ዛሬ ለዕድገታችን ሳንካ ሆኖ እየፈተነን ይገኛል:: በአንዱ እጃችን ሠርተን በሌላው የምናጠፋበት አጉል ልማድም እየተዋረሰን መሆኑን መደበቅ አይቻልም::
ይህ በአስተሳሰብ የመዘመን እውነት አስቀደሞ ገብቶን ቢሆን ዛሬ ደንብና መመሪያ ወጥቶልን ‹‹በአድርግ፣ አታድርግ›› ሕግ ባልተያዝን ነበር:: ከድርጊቶቻችን ጋር ዘመናዊነትን አውቀን ተግብረነው ቢሆን ለቅጣትና እሱን ይዞ ለሚከተለው ችግርም ባልተጋለጥን ነበር::
የቀደመው ሥልጣኔያችንን ማውራት ፣ መተረኩ ብቻ ለእንደኛ አይነቱ ማንነት ጥቅሙ የሳሳ ነው:: ይልቁንስ የፊቱን ታሪካችንን ይዘን፣ የራሳችንን ዐሻራ አኑረን ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ እሴት ብናተርፍ ለሁላችንም የሚበጅ ይሆናል::
እኛ በትናንቱ ደማቅ ታሪካችን ስንኮፈስ የዛኔ ጭራ የተባሉ ሀገራት ዛሬ ቀድመውን ሄደዋል:: ‹‹ሙያ በልብ›› እንዲሉ እነሱ የእኛን ታሪክ መነሻ አድርገው የጀመሩት የሥልጣኔ ጉዞ ፍሬው አብቦ ማንነታቸው ተለውጧል::
አሁንም ቢሆን ካለፈው ልምዳችን ተምረን ውስጣችንን ካዘመንን ማንነታችን የማይለወጥበት፣ ታሪካችን የማይቀየርበት ምክንያት የለም:: በየአጋጣሚው ራሳችንን ለስህተት ዳርገን ፣ በሚወጣብን ደንብና መመሪያ ከመታሰር ይልቅ ሥልጣኔን ወደራሳችን አምጥተን ዘመናዊነትን መተግበር ይቻለናል::
ዛሬም ትናንትናን የነበርን ሕዝቦች ማንነታችን ቀጥሏል:: አብሮን የኖረው የጥንካሬ ዐሻራ ቀለሙ ሳይፈዝ እንዲቀጥል ታሪካችንን ሳንረሳ ሥልጣኔያችንን ልናነሳው፣ መዘመናችንን ልናድሰው ይገባል::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም