78 ዓመታትን በስኬት የዘለቀው ተቋም

 ዜና ትንታኔ

ተቋሙ ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦን አበርክቷል:: ኢትዮጵያ ከሌሎች ዓለም ሀገራት ጋር በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች ዘርፎች መልካም ግንኙነት እንዲኖራት አድርጓል:: የ 78 ዓመት የእድሜ ባለጸጋው አንጋፋ ተቋም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ::

በቅርቡም የአቪዬሽን ኦስካር ተብሎ በሚጠራው የስካይትራክስ መድረክ ለሰባተኛ ጊዜ የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ በመባል ክብርን ተቀዳጅቷል:: የአፍሪካ ምርጥ የቢዝነስ ክፍል የኢኮኖሚ ክፍል አየር መንገድ ለስድስተኛ ጊዜ እንዲሁም በአፍሪካ የኢኮኖሚ ክፍል ምርጥ ምግብ አገልግሎት ሰጪ አየር መንገድ በመባል ተደራራቢ ዕውቅና ተቀናጅቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ2016 በጀት ዓመት ሰባት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ፣ 17 ነጥብ አንድ ሚሊዮን መንገደኞችን ማጓጓዙ፣ 754 ሺህ 681 ቶን ካርጎ ማጓጓዙ፣ አምስት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ወደ ሥራ ማስገባቱ እና ሌሎች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው:: የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ስኬታማ ሆኖ የዘለቀበትን ምክንያት ዙሪያ ምሁራን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የአፍሪካ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንተኙ ላውረንስ ፍሪማን በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዙ ጊዜ ተጉዣለሁ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን በርካታ ጥቅሞች አለው:: አየር መንገዱ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባለፈም ለመላ አፍሪካውያን ኢኮኖሚያዊ እድገት አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በአፍሪካ አንደኛ አየር መንገድ ሆኖ እውቅና አግኝቷል። ይህም በአፍሪካ ውስጥ ሊተገበር የሚችል ብዙ ተጨማሪ አቅም እንዳለ ማሳያ ነው:: የኢትዮጵያ አየር መንገድ 139 ዓለም አቀፍ የመንገደኞች መዳረሻዎች አሉት:: ከእነዚህ ውስጥ 63ቱ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው:: ይህ የሚያሳየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው ይላሉ::

ተንታኙ እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢትዮጵያ እና ለአካባቢው የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሆኖ ሳለ በኤርትራ ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን የሚደረገው ስም ማጥፋት አየር መንገዱን ለማዳከም፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻከር ያለመ ስለመሆኑ ያስረዳሉ::

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ላይ የሚካሄደው የስም ማጥፋት ዘመቻም ማንንም የሚጠቅም ባለመሆኑ መስተካከል እንዳለበት ይገልጻሉ::

ባለፉት ዓመታት እንኳን የነበረው ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ገቢ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል:: አየር መንገዱ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ጉልህ ሚና አለው ይላሉ::

ሌላኛው የኢኮኖሚ ባለሙያ እና የፖሊሲ አማካሪው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር በቱሪዝም፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በሌሎች ዘርፎች ያላት ግንኙነትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው ይላሉ::

እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፣ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን እያስፋፋ ነው:: ይህ ደግሞ ተጨማሪ ቱሪስቶችን ወደ ሀገሪቱ ለመሳብና የንግድ ሥርዓቱን ለማስፋፋት እንደሚያግዝ ይናገራሉ::

ለአብነት በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የንግድ እቃዎች በአብዛኛው በባቡር እና በአውሮፕላን ነው የሚጓጓዙት:: ለዚህ ደግሞ በአፍሪካ ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ የተደራጃ የአየር መንገድ መሠረተ ልማት ያለው ሀገር ስለሌለ ትልቁን ድርሻ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይወስዳል ሲሉ ያስረዳሉ::

በኮቪድ ጊዜም የህክምና ግብዓቶችን ጨምሮ ሌሎች የካርጎ ጭነቶችን ሲያጓጉዝ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደነበር ያስታውሳሉ::

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቬሽን ዩኒቨርሲቲ መክፈቱ፣ የጥገና ቦታቸውን በማስፋፋት የሌሎች ሀገራትን አውሮፕላን ጭምር መጠገን መጀመራቸው እና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን መሥራታቸው የሚበረታታ ነው ይላሉ::

አየር መንገዱ በቀጣይ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር በመጨመር፣ የተቋሙን ሠራተኞች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማሳደግ፣ መዳረሻ ሀገራትን በማስፋፋት እና ሌሎች ሥራዎችን በትኩረት በመሥራት ስኬታማነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ያስረዳሉ::

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለ78 ዓመታት በስኬት ተጉዟል:: በቀጣይም እድገቱን ለማፋጠን የሚረዱትን በርካታ ሥራዎች እያከናወነ ነው ይላሉ::

አየር መንግዱ እያደገ የመጣውን የአየር ትራንስፖርት ፍላጎት ለማሟላት 125 አውሮፕላኖችን አዟል:: ካዘዛቸው 125 የአውሮፕላኖች መካከል 105ቱ የታዘዙት በታህሳስና የካቲት 2016 ዓ.ም ሲሆን፤ 20ዎቹ ቀደም ብለው የታዘዙ መሆናቸውን ይናገራሉ::

የ105ቱ አውሮፕላኖች የመረከቢያ ጊዜ እ.ኤ.አ ከ2027 እስከ 2030 ባሉት ጊዜ ውስጥ መሆኑን በመግለጽ፤ በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ ቀደም ብለው ከታዘዙት 20 አውሮፕላኖች መካከል 16ቱን ወደ ሥራ ለማስገባት እና 20 ሚሊዮን መንገደኞችን ለመጓጓዝ አቅዶ እየሠራ መሆኑን ያስረዳሉ::

ከዚያ ወደህ ከፍተኛ የሆነ የአውሮፕላን ፍላጎት ቢኖርም አውሮፕላን በፍጥነት ማግኘት ፈተና ስለመሆኑ ያመላክታሉ:: በሌላ በኩል በግንባታ ላይ ያሉ አምስት የአውሮፕላን ማረፊያዎችን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቅቅ እየሠራ ሲሆን፤ አውሮፕላን ማረፊያዎቹ ያቤሎ፣ ሚዛን አማን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎሬ መቱ እና የነገሌ ቦረና መሆናቸውን ያስረዳሉ::

ሥራ አስፈጻሚው እንደሚሉት፣ የያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ 54 በመቶ፣ የሚዛን አማን አውሮፕላን ግንባታ ደግሞ 64 በመቶ ደርሷል:: ግንባታቸውንም ታህሳስ 2017 ዓ.ም ላይ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ይላሉ::

የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራ ተጀምሮ በጸጥታ ምክንያት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግንባታው ተጀምሮ መጋቢት 2017 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሠራ ስለመሆኑ ይናገራሉ::

የነገሌ ቦረና አውሮፕላን ማረፊያም መጋቢት ላይ የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ ጎሬ መቱ የአውሮፕላን ማረፊያም ደግሞ አንድ ዓመት ጊዜ ሊወስድ ይችላል ይላሉ::

የመንገደኛ መስተናገጃ ተርሚናል እና የአውሮፕላን መንደርደሪያ ግንባታን በሚመለከት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ቀደም ሲል ከተጀመሩት አምስት የሀገር ውስጥ መንገደኞች መስተናገጃ ተርሚናሎች መካከል ጎዴና ጂንካ ተጠናቀው ተመርቀዋል:: ሮቤ ግንባታው ተጠናቆ ምረቃ እየጠበቀ ነው::

የደምቢዶሎ፣ የነቀመት፣ የአክሱም፣ እና የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ የአውሮፕላን መንደርደሪያዎች ማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቀው ሥራ ላይ ስለመዋላቸውም አንስተዋል:: በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ደረጃ ለማሻሻልና የሚጎሏቸውን መሠረተ ልማት ለማሟላት እንዲሁም የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሀገር ውስጥ ተርሚናሉ ላይ ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራ ለመሥራት በጀት ስለመመደቡ ይገልጻሉ::

አዳዲስ የመንገደኛ ተርሚናል ለመገንባት የታሰበባቸው ቦታዎች ሽሬ፣ ነቀምትና ደምቢዶሎ ሲሆኑ፤ በወላይታ ሶዶ ደግሞ አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት እንቅስቃሴ ጀምረናል ይላሉ:: በተያዘው በጀት ዓመት አምስት ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን መዳረሻዎችን ለመጨመር ታቅዶ አንዱ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ በቀጣይ ጊዜያት ይገባሉ:: ከዚህ በተጨማሪም ጥናት ላይ የተመሠረተ አዳዲስ ጣቢያዎች እንከፍታለን ሲሉ ይናገራሉ::

የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለማሳደግ፣ ለማዘመን እና እያደገ የመጣውን የአየር ትራንስፖርት ፍላጎት ለማሳካት በትኩረት እንደሚሠሩ ጠቁመዋል:: ምሁራኑ በሰጡት አስተያየትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጪዎቹ ዓመታት በአፍሪካም ሆነ በዓለም ግንባር ቀደም ተጠቃሽና ስኬታማ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን ይገልጻሉ::

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25  /2016 ዓ.ም

Recommended For You