የሚወሰልቱ ሰዎችን የሚያድነው የሴቶች የስለላ ቡድን – “ፎኒክስ ስኳድ”

 

በፔሩ የሚወሰልቱ ሰዎችን አድኖ የሚይዘውና በሴቶች ብቻ የተዋቀረው ቡድን የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ስቧል። ራሳቸውን “ፎኒክስ ስኳድ” ብለው የሚጠሩት የቡድኑ አባላት ከደንበኞቻቸው የሚቀርብላቸውን ጥያቄ ተቀብለው በሰአታት ውስጥ ወሳኝ መረጃን የማቅረብ ክህሎት አላቸው ተብሏል።

“ፎኒክስ ስኳድ” በደቡብ አሜሪካዋ ሀገር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተለያዩ መሣሪያዎችና ብልሃት የተሞላባቸው ዘዴዎች ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠቱን ጀሲካ ሜሊና የተባለችው የቡድኑ መሪ ትናገራለች።

የትዳር አጋራቸው ታማኝነት የሚከነክናቸው የፔሩ ነዋሪዎች ወደነጀሲካ ቢሮ በመምጣት አጣሩልኝ ብሎ በጠየቀ በሠአታት ውስጥ ምላሽ እንደሚያገኙም ነው የተገለጸው።

የቡድኑ አባላት ድብቅ ካሜራዎችን እና የቆዩ የስለላ ሥራ ጥበቦችን ይጠቀማሉ፤ ጉዳዩ ከበድ ያለ ከመሰላቸውም ድሮን እስከመጠቀም ይደርሳሉ።

“ፎኒክስ ስኳድ” የውስልትና አጣሩልኝ ጥያቄ የሚያቀርቡ ወንዶችንም ሆነ ሴቶች ያለአድልኦ የሚያስተናግዱ ቢሆንም ሁሉም አባላቱ ሴቶች ናቸው።

“የራሴን የስለላ ቡድን ሳቋቁም ሴቶችን ብቻ በአባልነት ለማካተት የወሰንኩት ሴቶች የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ ስላመንኩ ነው” ትላለች መስራቿ ጀሲካ ሜሊና ከላ ሪፐብሊካ ጋዜጣ ጋር ባደረገችው ቆይታ።

ሴቶች ምንም ሳይታወቅባቸው፤ ገጽታቸውን በፍጥነት ቀያይረው ውስብስብ የሚመስልን ነገር በፍጥነት መፍታት እንደሚችሉም በማከል።

“ፎኒክስ ስኳድ” የተቋቋመው ፍቺ እየፈለጉ ለፍርድ ቤት የሚያቀርቡት ታማኝነት ያለው ማስረጃ ያጡ ሰዎችን ችግር ለመፍታት ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You