በብዙ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ አገልግሎቱን የሚሰጡ ሠራተኞች ሲቆጡና ሲያመናጭቁ ማየት የተለመደ ነው:: ምንም እንኳን ግልምጫና ስድብ ትክክል ባይሆንም፤ ቢያንስ ግን ተገልጋዩ ያለአግባብ ልስተናገድ ብሎ ካስቸገረ በኋላ አይሻልም? እንዴት የዱቤ ይቆጣሉ? መጀመሪያ ልቆጣህና የአንተ ጥፋት በኋላ ይደርሳል የሚሉ ነው እኮ የሚመስለው!
ችግሩ ያለው የፀጥታና የሥነ ምግባር ኃላፊነት ያለባቸው ላይ ጭምር ነው:: ለምሳሌ፤ አንዳንድ ፖሊሶች አስቀድመው ይቆጣሉ:: ባለጉዳዩ ሥነ ሥርዓት ያለው እና በሠለጠነ መንገድ የሚያናግር ከሆነ ከቁጣ መጀመር ምን ይሉታል?
ይሄ ማለት ግን ተገልጋይ ላይ ችግር የለም ማለት አይደለም:: አናዳጅ ብቻ ሳይሆን ከማናደድ አልፎ ሊያስቁ የሚችሉ ሰዎች አሉ:: ከዚህ በፊት በሌላ ጽሑፍ የተጠቀምኩት አንድ ገጠመኝ ልጥቀስ::
ከዓመታት በፊት በአዋሽ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ ውስጥ ያስተዋልኩት ነው:: ደንበኞች የሚስተናገዱት በትኬት ቁጥር ነው:: የትኬቱ ቁጥር የተጠራ ተረኛ ወደተጠራበት መስኮት ሄዶ ይስተናገዳል:: አንድ ተገልጋይ የያዘው ትኬት ቁጥር ሳይጠራ ተነሳና ሠራተኛ ወደሌለው ባዶ መስኮት ሄደ:: የሰውየው ወደዚያ መሄድ ግራ የገባው ከባዶው መስኮት ጎን ያለው የባንኩ ሠራተኛ ‹‹ና›› አለው:: ተገልጋዩም ‹‹ና›› ወዳለው የባንክ ሠራተኛ ሄደና የሞላውን ቅጽ ለባንክ ሠራተኛው (ቴለር) ለመስጠት እጁን ሰነዘረ::፡ ሠራተኛውም ‹‹አይ! ምናልባት ብር ለመዘርዘር ወይም ለሌላ ቀላል ጉዳይ መስሎኝ ነው፤ ለመገልገል ከሆነ ቁጥርህ ሲጠራ ነው›› አለው:: ደንበኛው ‹‹አስተናግደኝ!›› አለ:: የባንኩ ሠራተኛ ትኬቱን ተቀብሎ ሲያይ ገና ብዙ ይቀረዋል:: ‹‹አይቻልም›› ብሎ ከለከለው:: ደንበኛው ‹‹ታዲያ ለምን ጠራኸኝ?›› ብሎ ተቆጣ:: የባንክ ሠራተኛውም በትዕግስት ማስረዳት ጀመረ:: ‹‹የጠራሁህ ለሌላ ጉዳይ መስሎኝ ነው፤ በዚያ ላይ ሰው በሌለው መስኮት ነው የሄድክ፤ እዚያ ማንም ሊያስተናግድህ አይችልም፤ ባልጠራህ ባዶ መስኮት ጋ ምን ልትሠራ ነበር?›› አለው:: ደንበኛው ጭራሽ ባሰበት::
ለመገልገል የገባው ደንበኛው ሙሉ በሙሉ ጥፋቱ የራሱ ሆኖ ሳለ ቁጣውም የራሱ ሆነ:: ጭራሽ እንዲያውም የተቋማት ሠራተኞችን ዝርክርክርነት ሁሉ እየጠቀሰ ይሳደብ ጀመር:: ልክ እሱ የሠለጠነ ይመስል እንደ ሀገር ያለው አሠራር ያልሠለጠነ መሆኑን በቁጭት ይናገራል::
አንዳንዱ ንዴቱን ቻል አድርጎ ይስቃል፤ አንዳንዱም እየታዘበ ዝም ይላል:: እርግጥ ነው በተቋማት ውስጥ ብዙ የተዝረከረከ አሠራር አለ፤ ግን ይሄ ሰውየ እነዚህ ሰዎች የመተቸት ሞራል አለው? ሠራተኛው ብቻ እንጂ ተገልጋዩ ሥነ ሥርዓት መያዝ የለበትም ማለት ነው? ይሄ ሰውየ እኮ የዚያን ሁሉ ተገልጋይ ሰዓት እያባከነ ነው፤ በዚያ ላይ የአሠራር ደንብም እየጣሰ ነው:: የትኬት ቁጥር ያስፈለገው እኮ መተራመስ እንዳይኖርና ሥራውን የተቀላጠፈ ለማድረግ ነው፤ አሁን ይሄን ሰውየ ምን ይሉታል እንግዲህ?
በኋላ የባንክ ሠራተኛውም ትዕግስቱ እያለቀ መጣ:: ወደ አላስፈላጊ ክርክር ውስጥ ገቡ:: የዚህን ጊዜ ሌሎች ተገልጋዮች ጣልቃ እየገቡ መገላገል ጀመሩ:: የባንክ ሠራተኛው ዝም በል ሲባል ዝም አለ:: ተገልጋዩ ግን ቁጣውን ያወርደው ጀመር:: በኋላ የባንክ ሠራተኛው ጭራሽ እየሳቀ ያበሽቀው ጀመር:: በነገራችን ላይ ነገሮችን ንቆ መተው ትልቅ ጥቅም አለው:: ያንን ተሳዳቢውን በጣም ነው የሚያናድደው:: ሠራተኛው ሥራውን መሥራት ጀመረ:: ባለጉዳዩ ሲለፈልፍ ቆይቶ ትቶት ወጣ:: ግልግል ሆነ ማለት ነው!
እንግዲህ አንዳንዱ ሰው እንዲህ ነው:: የባንክ ሠራተኛው ጨዋ ባይሆን ኖሮ፣ ነገሩን ንቆ ባይተወው ኖሮ እነዚህ ሰዎች እስከመደባደብ ይደርሱ ነበር:: ሲደባደቡ ያየ ሰው ጥፋቱ የማን እንደሆነ ካላወቀ በሁለቱም ይፈርድ ነበር:: አንዳንድ ሰዎች በጣም ግርም ይላሉ:: ከይቅርታ ይልቅ ስድብ ይገዛቸዋል:: ይቅርታ ሲባሉ የተፈሩ ይመስላቸዋል::
ምንም እንኳን ችግሩ ያለው ከሁለቱም (ከአገልጋይም ከተገልጋይም) ቢሆንም ታጋሽነትና የሠለጠነ አሠራር የሚጠበቀው ግን ከአገልግሎት ሰጪዎች ነው:: ምክንያቱም ኃላፊነት ላይ የተቀመጡት የተሻለ ብቃት ኖሯቸው ነው:: ተወዳድረው ነው:: ሀገራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ነው:: ሀገራዊ ኃላፊነት ሲባል የግድ በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ብቻ መሆን የለበትም:: የአንድ ተቋም የጥበቃ ሠራተኛ ለዚያ ሥራ ኃላፊ ነው:: ሥራውም ሀገራዊ ሥራ ነው:: ሀገረ መንግሥት ሲባል የግድ ዳር ድንበሩ ብቻ አይደለም:: የአሠራር መዋቅሩ ጭምር ነው:: ስለዚህ አንድ ሀገር ሠለጠነች የሚባለው የአሠራር ሂደቱ የሠለጠነ ሲሆን ነው::
ሰዎች ሥነ ምግባርን መማር ያለባቸው በኃላፊነት ላይ ካሉ ሰዎች ነው:: በአገራችን የምናየው ነገር ግን በቁጣ መጀመር ነው:: ከአንድ ሳምንት በፊት ከግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ጋር በተያያዘ ጉዳይ አንድ የቀበሌ አገልግሎት ተቋም ሄጄ ነበር:: እርግጥ ነው በግሌ ለማማረር የሚያበቃ መጉላላት አላጋጠመኝም:: ያስተዋልኩት ችግርም የዚያ ቢሮ ሠራተኞች የተለየ ችግር ሳይሆን እንደ ሀገር የሠለጠነ አሠራር ባለመስረጹ ያጋጠመ ነው::
የተሰጠው ቅጽ ግልጽነት የለውም:: መጠይቆቹ አሻሚ ናቸው:: ቅጹን የሚሞሉ ሰዎች ‹‹እዚህ ላይ ምንድነው የሚሞላ?›› እያሉ አገልግሎት ሰጪዎችን ለመጠየቅ ይገደዳሉ:: ይህኔ ነበር በሁለቱም በኩል መሰለቻቸት የሚታየው:: አገልግሎት ሰጪዎቹ ሥራ እያቋረጡ ያን ሁሉ ሰው ማስረዳት ይሰለቻቸዋል:: ተገልጋዮች ደግሞ በግምት ቢሞሉት በኋላ ‹‹ትክክል አይደላችሁም›› ሊባሉ ነው::
በሌላው በጣም በተደጋጋሚ የማስተውለው ችግር ግን የትኛው ጉዳይ የት እንደሆነ አለማወቅ ነው:: አገልግሎት ሰጪዎች ሲጠየቁ ባለጉዳዩ የዚያ ቢሮ ነዋሪ የሆነ ይመስል ‹‹እንዴት ይሄን አታውቅም?›› የሚል ድምጸት ባለው ቁጣ ‹‹ማነው እዚህ ነው ያለህ?›› ብለው ይቆጣሉ:: ባለጉዳዩ የጠየቀውን ቢሮ በትህትና ከመጠቆም ይልቅ እነርሱ ጋ አለመሆኑን ብቻ በቁጣ የሚናገሩ አሉ:: ምንም እንኳን እንዲህ የሚያደርጉት በጣም ጥቂቶች ቢሆኑም በእነዚህ ጥቂቶች ምክንያት ግን ተቋሙ ይወቀሳል:: ተቋሙ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሀገራዊ አገልግሎቱም ይወቀሳል::
በሥራ ጫና ምክንያት መሰላቸት እንደሚኖር ይታመናል:: አንዳንዶቹ ግን በሚያስቅ ሁኔታ ወንበራቸው ላይ ጀርባቸውን አስደግፈው እያሽከረከሩ ስልካቸውን በመጎርጎር ላይ ሆነው ነው ባለጉዳይ ሲመጣ በቁጣ የሚጀምሩት:: ታዲያ እነዚህ አያናድዱም?
ቢቻል ሁሉንም በትዕግስትና በትህትና ማስተናገድ፤ ሰው ናችሁና በሥራ ጫና ምክንያት መዋከብ ቢኖርም ቢያንስ ግን በሠለጠነ መንገድ የሚስተናገደውን ሁሉ ባታደነባብሩ:: የቅድመ ቁጣ አገልግሎት አትስጡ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም