ቴክኖሎጂና አዲስ የፈጠራ ሥራ የሰው ልጆችን ሕይወት በብዙ አሻሽሏል፡፡ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከግብርና እና ከሌሎች ዘርፎች አንፃርም የሚሰጠውን ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ላሉና በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ደግሞ የቴክኖሎጂ ፋይዳ ከምንለው በላይ ትልቅ ነው።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል እንዳላት ሀገር ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት እያደረገች ትገኛለች። በሁሉም መስክ ማለትም የማኅበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል፣ ዘመናዊ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ግብርናን ዘመናዊ በማድረግ በምግብ እራስን ለመቻል፣ ለጤና ብሎም ለወታደራዊ አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂ መታገዝ የግድ ሆኗል።
በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አምስት ሚሊዮን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ አስጀምረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳይንስ ሙዚየም ኢንሼቲቩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት ኢንሼቲቩ ሠልጣኞችን ዘመኑን በዋጀው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል። የኢትዮጵያ የነገ ተስፋዎች የሆኑ ወጣቶችም ሥልጠናውን በጥሞና በመከታተል ሥራ ፈጣሪ፣ ኩባንያ ፈጣሪና በዓለም ገበያ ተወዳድረው የሚቀጠሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም ይህንን ትልቅ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ክህሎት በዲጂታል የታገዘ ማኅበረሰብ ለመፍጠር፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና ለመሰማራት ወሳኝ እየሆነ መጥቷል። ነገር ግን ኢትዮጵያ በተመሳሳይ የእድገት ደረጃ ጋር ካሉ አገራት ጭምር ስትወዳደር በዲጂታል ክህሎት ወደ ኋላ ቀርታለች። አዲሱ ትውልድ ተገቢው የዲጂታል ክህሎት ከሌለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን ካለመቻሉ ባሻገር እንደ ሀገርም እድገትን የሚጎዳ ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በዲጂታል ክህሎት ያለባትን ክፍተት ለመሙላት የመሠረታዊ ኮምፒውተር እውቀትና ሁለንተናዊ የዲጂታል ክህሎት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ ለወጣቶች ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ የአምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ ፕሮግራምም የኢትዮጵያ ወጣቶች ተገቢውን የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው ለማድረግ የተቀረጸ በመሆኑ ፋይዳው ከፍተኛ ነው።
አምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ “ኮደርስ” ፕሮግራም በኢትዮጵያ እና በተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ መንግሥታት መካከል በተደረገ ስምምነት የተነደፈ የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና መርሐ ግብር ነው። የመርሐ ግብሩ ዓላማ ወጣቱ ትውልድ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ የሚያስችለውን የዲጂታል ክህሎት እንዲኖረው ማስቻል ነው።
መርሐ ግብሩ ለሁሉም ተደራሽ የሆኑ የኦንላይን ኮርሶችንና ሌሎች ደጋፊ የሆኑ አገልግሎቶችን በማቅረብ እ.ኤ.አ በ2026 አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስ እና አንድሮይድ ልማት መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ማስታጠቅን ግብ ያደረገም ነው።
ዘመኑ ቴክኖሎጂ የሥራ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን የለውጥ አራማጅ የሆነበት ምዕራፍ ላይ ደርሷል። የሀገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በወጣቶች እጅ እንደሚሆንም ይታወቃል። የነገዋን ኢትዮጵያ የሚቀርፁት የፈጠራ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች እነዚህ ወጣቶች ናቸው። በመሆኑም የኢትዮ ኮደርስ ፕሮግራም ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በዲጂታል ሥነ ምሕዳሩ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችላቸውን ክህሎትና እውቀት በማስታጠቅ አዳዲስ ዕድሎች እንዲፈጠርላቸው እና ሀገራችን በቴክኖሎጂው መስክ ወደፊት እንድትገሰግስ በር የሚከፍት ነው የሚል እምነት አለኝ።
የኢትዮ ኮደርስ ፕሮግራም ወጣቶችን ለማብቃት፣ ፈጠራን ለማጎልበት እና የዲጂታል ዘመንን ግዙፍ አቅም ለመጠቀም እንደ ሀገር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ በመሆኑ የተጀመረው ኢንሼቲቭ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ተግባራዊ ሊሆን ይገባል እላለሁ።
እንደ ሀገር ምንም ያህል መሠረተ ልማት ቢገነባ፣ መተግበሪያዎች ቢለሙ፣ የሕግ ማዕቀፎች ቢረቀቁ፤ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ላይ ተመሥርተው የሚለሙ አፕሊኬሽኖችን የሚጠቀም ሰው ካልተፈጠረ የለሙትን መሠረተ ልማቶች ተጠቅሞ ያለውን ሃሳብ ወደ መተግበሪያ ለውጦ አገልግሎቶችን የሚያለማ የሰው ኃይል ከሌለን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እቅዱ በታለመለት ልክ ግቡን ሊመታ አይችልም።
ስለሆነም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን ለማስፋትና ለማስቀጠል የዲጂታል ዕውቀት እና ክህሎት ያለው በርካታ የሰው ኃይል ማዘጋጀትና ማብቃት የግድ ይለናል። በዚህ ረገድ ባለፉት የዲጂታል ስትራቴጂው ዓመታት ጥረቶች የነበሩ ቢሆንም በዘመቻ መልክ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያካትቱ የዲጂታል ክህሎት ፕሮግራሞች ተቀርጸው በስፋት አልተተገበሩም።
ይህም አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት እውን ከማድረግና የትራንስፎርሜሽኑን ቀጣይነት ከማረጋገጥ አንጻር ትልቅ ተፅዕኖ ያለው ጉዳይ ሆኗል። ለዚህም የአምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢኒሼቲቭ የወጣቶችን የዲጂታል ክህሎት በማሳደግ ረገድ አንዱ ምላሽ ሆኖ መምጣቱ ይባል የሚያሰኝ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ቴክኖሎጂ በትምህርት መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ማስተማር እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ቁጥሩ ከፍተኛ ለሆነ ሕዝብ ሕክምና ተደራሽ ማድረግ አይቻልም። በግብርናውም በቴክኖሎጂ ተጠቅመን ካልሠራን በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ መመገብ አይታሰብም፡፡ ትልቅ ቁጥር ያለው ሕዝብ ነው ያለውና ወደ እያንዳንዱ ቤት መድረስ የሚቻለው በቴክኖሎጂ ነው፡፡ ስለዚህ ከምንም በላይ እንደ ሀገር ለዘርፉ ትኩረት መስጠት የውዴታ ግዴታ ነው ብዬ አስባለሁ።
ቴክኖሎጂ በጥቂት የሰው ኃይልና ቦታ ትላልቅ ሥራዎች ለመሥራት ምቹ መሆኑ ዘርፉን በብዙ ተመራጭ እንደሚያደርገው እሙን ነው። በሚመጣው ዘመን ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ለቴክኖሎጂ ሥራና ምርምር ትልቅ ትኩረት ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በዘርፉ ለተሰማሩ ግለሰቦችና ተቋማት አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ መሥራት አለበት እላለሁ።
ያደጉትም ሆነ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቴክኖሎጂን በሚያስፈልጋቸው ዘርፎች እንደ አስፈላጊነቱ እየተጠቀሙበት ችግሮቻቸውን እየፈቱ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች። ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና፣ የጤና፣ የደኅንነት፣ እና መሰል ዘርፎችን አቅም ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል።
የተለያዩ ዓውደርዕዮች በማዘጋጀት በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦች የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎችን ማሳየት እንዲችሉ ዕድል መፍጠር ይስተዋላል ይህ የሚበረታታና ይበል የሚያሰኝ ነው። ነገር ግን በዘርፉ ዓለም ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አንፃር አሁንም እንደ ሀገር ያለንበት ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ አሁን ከተሰጠው በላይ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ይገባል።
ክብረአብ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም