ቢሾፍቱ:- ትናንት በቢሾፍቱ አሻም አፍሪካ ሆቴል የአርሶ አደሩን ምርታማነት በቴክኖሎጂ ለማዘመን በተሞከረባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በዕለቱ የኮመን ሴንስ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አማረ ሙጎሮ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ባለፉት አራት ዓመታት በአማራ በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ቴክኖሎጂን ከግብርናው ያዛመዱ ተግባራት ሲከውኑ ቆይተዋል፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር፤ ከብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ፤ ከግብርና ምርምርና ከሌሎችም ጋር በተደረገው ቅንጅት አርሶ አደሩ የዘመኑን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ጥረት መደረጉን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡
ቴክኖሎጂን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ በተደረገው ጥረት ግብርናን ከሜትሮሎጂ ጋር በማዛመድና ከማዛመድ ባሻገር ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ እንዲለመድና ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤ በተለይም ወቅታዊ የአየር ትንበያን ተጠቅሞ መረጃ በሞባይል መልዕክት ለአርሶ አደሩ ለማድረስ በተደረገው ሙከራ ምርት በወቅቱ እንዲሰበሰብና ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያዎቹ የሙከራ ዓመታት ከ3 ሺ በላይ አርሶ አደሮችን በቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ለማድረግ ሲቻል፤ በሚቀጥሉት ዓመታትም ቁጥሩን በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡
የገበሬዎች የህብረት ስራ ማህበራትን በቴክኖሎጂ ተደራሽ ለማድረግ በተደረገው ጥረትም የመሰረታዊ ማህበራትን ሙሉ ገጽታ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መረጃ ለማስተሳሰር ተችሏል ብለዋል፡፡ እንደአስተባባሪው ገለጻ፤ ፕሮጀክቱ ሲቋቋም 200 ሺ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ ሲሆን፤ እስካሁን በኔዘርላንድስ መንግስት ገንዘብ ድጋፍና በሞግ ኒገን ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ስራው ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በኦፖዚት ቴክኖሎጂ ሶሉሺን የግብርና ቴክኖሎጂ ሃላፊ አቶ ኤልያስ ጎሳዬ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት አርሶ አደሩን ከቴክኖሎጂ ጋር በማዛመድ ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ ሃላፊው ገለጻ፤ ግብርናውን ለማዘመን የፋይናንስ አስተዳደርን ጨምሮ አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን በአግባቡ ሸጠው ያለኪሳራ የሚገበያዩበትን ሥርዓት ለመዘርጋት ተሞክሯል፡፡ አርሶ አደሩ በኤሌክትሮኒክስ ኩፖን ተጠቅሞ ምርቱን ለፋብሪካዎች የሚያቀርብበትንና ወቅታዊ መረጃዎችን የሚለዋወጥበትን መንገድም ተግባራዊ መሆኑን ሃላፊው ገልጸዋል፡፡
ከቴክኖሎጂው አሰራር ጋር ተያይዞ የህብረት ስራ ማህበራት ምን ያህል ገዝተው እንደሚሸጡ ለመጠቆም የሚያስችል ቴክኖሎጂ ስለመተግበሩም ተናግረዋል፡፡ በተለይ አርሶ አደሩ ወቅታዊ የአየር ንብረት መረጃዎችን እንዲያገኝ ከሳተላይትና ከብሄራዊ ሜትሮሎጂ በመቀበል በስልክ መልዕክት ሲተላለፍ መቆየቱን ገልጸው፤ ይህም ግብርናውን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ እገዛ እንዳደረገ ጠቁመዋል፡፡ በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ እንደገለጹት፤ የሀገራችን ግብርና በዝናብ ውሃ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ይህ አይነቱ ቴክኖሎጂ መተግበሩ ጥቅሙን ያጎላዋል ብለዋል፡፡
በዕለቱ በቢሾፍቱ ከተማ አሻም ሆቴል በተደረገው ውይይት ላይ የግብርና ሚኒስቴር፤ የብሄራዊ ሜትሮሎጂ፤ የፌዴራል ህብረት ስራ ማህበራትና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 3/2011
መልካምስራ አፈወርቅ