ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡ የበርካታ መስህቦች ባለቤት ነች። ጥንታዊ ሥልጣኔና ሀገረ መንግሥት ያላት ቀደምትና የሰው ዘር መገኛ ጭምር ናት። በሀገሪቱ የአርኪዮሎጂ ፣ የፓሊዮንቶሎጂና ፓሊዮአንትሮፖሊጂ (መካነ ቅርሶች ጥናት) እንዲሁም የኢንታንጀብል (የማይዳሰሱ) ኢትኖግራፊ (የማህበረሰብ ባህል ጥናት) ቅርሶች ይገኛሉ። በታሪክ በባህል፣ በተፈጥሮ፣ በሥነ ፅሁፍ፣ በእምነት እንዲሁም በአያሌ ዘርፎች በአጭሩ ተዘርዝረው የማያልቁ የሰው ልጅ ሥልጣኔ አመላካች ሀብቶችን በውስጧ ይዛለች።
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሚመዘገቡ ቅርሶች (መስህቦች) ሁለት አይነት መልክ እንዳላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። እነዚህ ሀብቶች በሰው ልጅ ታሪክ፣ ሥልጣኔና ዛሬን የመድረስ ልህቀት ላይ እኩል ድርሻ እንደሚወስዱም ይገልፃሉ። የማይዳሰሱም ሆነ የሚዳሰሱ ቅርሶች በእኩል ደረጃ ሊጠበቁ፣ ሊለሙ ሊተዋወቁና የያዙት ፋይዳ ጎልቶ ሊወጣ እንደሚገባ እነዚሁ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች (እንደ አክሱም፣ የፋሲል ግንብ፣ የጢያ ትክል ድንጋይ እንዲሁም የመስቀል፣ ጥምቀት፣ ኢሬቻ፣ የጨምባላላ የመሰሉ) ሀብቶች ያላት ቀደምትና ታሪካዊ ሀገር ነች። ቅርሶቹ የተነጣጠሉ ሳይሆኑ አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር የሚመጋገቡ፣ አንዳቸው ለአንዳቸው በባህል እንዲሁም በእምነት የሚቆራኙ ሆነው እናገኛቸዋለን። ለምሳሌ ያህል በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት በማይዳሰስ የተመዘገበውን የመስቀል በዓል ብንመለከት በቀጥታ ከአክሱም፣ ከላሊበላ የሚዳሰሱ ቅርሶች ጋር የሚተሳሰር ሆኖ እናገኘዋለን። በመሆኑም ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት የሆኑ የማይዳሰሱ ቅርሶችን ስንጠብቅ፣ ስናለማና ስናስተዋውቅ በተመሳሳይ የሚዳሰሱ ሀብቶቻችንም እኩል እንክብካቤና አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረጋችንን ልንገነዘብ ይገባል።
በተመሳሳይ የማይዳሰሱ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች በራሳቸው ተዳሳሽ የሆነ እሴት እንዳላቸው ባለሙያዎች ይገልፃሉ። ይህንን እሴት ከሚወክሉት ውስጥ ደግሞ ባህላዊ አልባሳት፣ ምግቦች፣ ጌጠጣጌጦች እና መሰል ቁሳዊ ሀብቶች ይነሳሉ። ይህን ጉዳይ በዝርዝር ለመረዳት እንድንችል በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ዳሰሳዊ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪን አነጋግረናል።
አቶ ደምረው ዳኜ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የኢንታንጀብልና የኢትኖግራፊ ቅርሶች ተመራማሪ ናቸው። የኢትዮጵያ ቅርሶች የምርምር ጉዞ በሚለው ዓመታዊ የምርምር ጉባዔ ላይ ‹‹በማይዳሰስ ቅርስ ውስጥ የሚገኝ የሚዳሰሱ እሴቶች እይታ›› /Exploring Tangible Values in the Intangible/ በሚል ርእስ ጥናታዊ ዳሰሳ አቅርበው ነበር። የዝግጅት ክፍላችን ይህንን ርእሰ ጉዳይ በዝርዝር ሊመለከተው ወድዷል።
አቶ ደምረው እንደሚሉት፤ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርስ ስምምነት /the ICH Convention/ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርስ ጋር በተያያዘ በቀዳሚነት የተወሰደው እርምጃ እ.ኤ.አ በ1973 ቦሊቪያ በዓለም አቀፉ የኮፒራይት ኮንቬንሽን ውስጥ ፎክሎርን ለመጠበቅ የሚያስችል ፕሮቶኮል እንዲካተት ባቀረበችው ሃሳብ የተጀመረ መሆኑን ይናገራሉ። የቦሊቪያ ሃሳብ በጊዜው ስኬታማ ባይሆንም የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ልክ እንደ ተዳሳሽ (Tangible) ባህላዊ ቅርስ ትኩረት እንዲያገኝ ቀዳሚውን ግንዛቤ ለመፍጠር ያስቻለ መሆኑን ያስረዳሉ። ዩኔስኮ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ በ1972 ታንጀብል የሆኑትን የባህልና የተፈጥሮ ቅርስ ጥበቃ ኮንቬንሽንን መቀበሉንም ይገልፃሉ።
የኢንታንጀብልና የኢትኖግራፊ ቅርሶች ተመራማሪው እንደሚሉት፤ ዩኔስኮ በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርስ ጥበቃ ረገድ ቀዳሚ ሊባል የሚችለውን ርምጃ የወሰደው እ.ኤ.አ በ1982 መሆኑን ዋቢ መፅሀፍትን ጠቅሰው ያስረዳሉ። በዚህ ርምጃው ፎክሎርን ለመጠበቅ በሚል የኤክስፐርቶች ኮሚቴ ያቋቋመ መሆኑን አንስተው በድርጅቱ ውስጥ ቁሳዊ ያልሆኑ (የማይዳሰሱ) ቅርሶችን የሚከታተል የሥራ ክፍል /Section/ መመሥረቱን ያነሳሉ።
እንደ ተመራማሪው ገለፃ በ1982 በሜክሲኮ ከተማ የባህል ፖሊሲዎችን አስመልክቶ የተላለፈው ውሳኔ ባህል ለሚለው ጽንሰ ሃሳብ አዲስና ሁለገብ ትርጉም መስጠቱ የሰው ልጅ ቅርስ መገለጫው ታንጀብል ቅርስ ብቻ ሳይሆን ኢንታንጀብል ቅርስ ጭምር መሆኑን ግልጽ ያደረገ መሆኑን ያስረዳሉ። ዩኔስኮም ባህል አንድ ህብረተሰብ ወይም ማህበራዊ ቡድን ከሌላው ተለይቶ የሚታወቅበትን ማንነቱን ለመግለጽ የሚያገለግሉት መንፈሳዊ፣ ቁሳዊ፣ ምሁራዊና ስሜታዊ ገፅታዎችን ሁሉ የሚያጠቃልል ሰፊ ፅንሰ ሃሳብ መሆኑን በዝርዝር ማስቀመጡን ያስረዳሉ። ከዚህም በላይ ባህል ሥነ ጥበብንና ሥነ ፅሁፋዊ ብቻ ሳይሆን የአኗኗር ዘይቤዎችን፤ የሰው ልጅ መሠረታዊ መብቶችን፣ የእሴት ሥርዓቶችን፤ ልማዶችንና እምነቶችን ጭምር የሚያካትት መስክ እንደሆነ በትርጓሜው ማስፈሩን ይናገራሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ1997/98 የዘረጋው የሰው ልጅ አፋዊና ኢንታንጀብል ቅርስ ፕሮግራም (Proclamation of Masterpieces of Oral and Intangible Heritage of Humanity) አንዱና ተጠቃሽ ነበር የሚሉት አቶ ደምረው፤ በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት የተወሰኑ እና የተለየ እሴት እንዳላቸው የታመነባቸውና ነገር ግን የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን የአፋዊ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች የሆኑ የባህል መገለጫዎችን ዝርዝር ለመመዝገብ መቻሉን ይናገራሉ።
ቅርሶቹን የመጠበቅና የመንከባከብ ፋይዳ
በኢትዮጵያ ውስጥ በማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ ተካትተው የሚገኙ እሴቶችንም ሆነ በዓለማችን ላይ ያሉ የመስህብ ሀብቶችን መጠበቅና መንከባከብ በዓለም አቀፍ ሕግነት የተደነገገ መሆኑን የሚያነሱት ተመራማሪው፤ ይህም ቅርሶቹ በሚተገብሩዋቸው ማህበረሰቦችና ቡድኖች ውስጥ እየተተገበሩና ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ ህያው ሆነው መቀጠላቸው ማረጋገጥ እንደሚገባ ይናገራሉ።
‹‹የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን ከሚደርስባቸው ጥፋቶች ለመከላከል የተለያዩ ርምጃዎች እንዲወሰዱ ስምምነቱ ያስቀምጣል›› የሚሉት ተመራማሪው ከነዚህ መካከል ዋና ዋናዎቹ ቅርሶቹን መለየትና ያሉበትን ሁኔታ መረዳት፣ የቅርሶቹን አገልግሎትና ጠቀሜታ ለማስተዋወቅና ከጥፋት የመከላከያ ርምጃቸውን በእቅድና በፕሮግራም ውስጥ ለማካተት አጠቃላይ የመከላከያ /safeguarding/ ፖሊሲ ማዘጋጀት፣ ቅርሶቹን ከጥፋት የመከላከል ሥራ የሚሠራ ተገቢ ተቋም አካል ማቋቋም፤ ጥናትና ምርምሮችን ማበረታታትና ማካሄድ፣ ቅርሶቹን ከጥፋት ለመከላከል የሚያግዙ ሌሎች የሕግ ፣ የቴክኒክ የአስተዳደርና የፋይናንስ ርምጃዎችን ማለትም ለማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ማኔጅመንትና አስተላልፎ የሚያግዙ ማሠልጠኛዎችን መመስረት፣ ቅርሶችን ለመድረስ ወይም ለማየት የተቀመጡ ባህላዊ ክንውኖችን ሳይጣሱ ለእይታ ማቅረበ መሆኑ ይናገራሉ።
የማይዳሰሱ ቅርሶች ፋይዳ
ተመራማሪው ኢትዮጵያ በማይዳሰሱ የሰው ልጅ ወካይ ቅርሶችን ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱ ሀብቶቿን መጠበቅና በመንከባከብ በርካታ ፋይዳዎች ማግኘት እንደምትችል ይገልፃሉ። የመጀመሪያው ባህላዊ ቅርስ የሚገኘው ተጨባጭ እሴት ቅርሱን ወደ ቁስ ወይም ምርት በመለወጥ የሚገኝ ጠቀሜታ መሆኑን ያስረዳሉ። በዚህም ባህላዊ እሴቶችን የሚያንፀባርቁ እሴቶችን ወደ ምርትና ቁስነት በመቀየር ለጎብኚዎች በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ማስገኘት አንደሚቻል ያስረዳሉ። በምሳሌነትም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባህላዊ ምግቦች፣ አልባሳት እና የማህበረሰቦችን እሴቶች መገለጫ የሆኑ ጌጣጌጦች ያነሳሉ። እነዚህ ቁሳቁሶች ከመገለጫነት አልፈው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውም ጉልህ መሆኑን ይናገራሉ።
ከዓለም አቀፍ የቱሪዝም ገቢ 40 በመቶው ያክል ከማይዳሰሰው ባህላዊ ቅርስ ጋር በተያያዙ ከሚሰጡ አገልጎሎችና ጉብኝቶች እደሚገኝ በማስረጃነት የሚጠቅሱት አቶ ደምረው፤ በአጠቃላይ የቅርስ ጎብኚዎች /Heritage tourist/ ከሌሎች ቱሪስቶች የበለጠ ወጪ እደሚያወጡ እና በቀን ሲነጻጸርም እስከ 38 በመቶ ያክል የበለጠ መሆኑን ያስረዳሉ፣ በተመሳሳይ የቅርስ ጎብኚዎች /Heritage tourist/ ረጅም ቆይታ 22 በመቶ ያክል የበለጠ ቆይታ እደሚያደርጉ መረጃዎችን ጥቅሰው ያስረዳሉ። ይህም ማለት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የዓለማችን ሀገራት ቅርሶቻቸውን መንከባከባቸውና ማስተዋወቃቸው ዳጎስ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝላቸው ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልል ቀደም ሲል የማይዳሰሱ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርስ የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር አስመልክቶ የተጠና አንድ ጥናትን ዋቢ በማድረግ ተመራማሪው እንደሚያስረዱት፤ በአሸንዳ 105 ሺህ ያክል ቱሪስት እንደሚጎበኘው፣ አክሱም ጽዮንን 95 ሺህ ያክል ቱሪስት እንደሚጎበኘው፣ የመስቀል በዓል አከባበርን 40 ሺህ ያክል ቱሪስት እንደሚጎበኘውና ጥምቀትን 10 ሺህ ያክል ቱሪስት እንደሚጎበኘው ይገልፃሉ። ከዚህ መነሻ ብቻም የእሴቶቹን መጠበቅና መንከባከብ በእጅጉ አያሌ ጠቀሜታዎች እንደሚያስገኝ መረዳት ቀላል መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹ትግራይን ከሚጎበኘው የውጭ እና የሀገር ውስጥ ቱሪስት 60 በመቶ በመቶ ያክሉ ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስን እንደሚጎበኝ መረጃው ያመለክታል›› በማለት በምሳሌነት የሚያነሱት ተመራማሪው ከዚህ ቁጥር ተነስተን እያንዳንዱ ቱሪስት በአማካኝ በተለያዩ አገልግሎቶች የሚያወጣውን ትራንስፖርት፣ ምግብ፣ ማረፊያ፣ መዝናኛ ወዘተ ተርፈ ማስላት ብንችል ትልቅ ዋጋ ያለው ተጨባጭ ፋይዳዎችን እንደሚያስገኝ መገመት አያዳግትም ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የትውፊታዊ የእደጥበብ ሥራ ክህሎት ውጤቶች የሆኑትን ልዩ ልዩ የእደጥበባት ምርቶችን፣ የሸማ ሥራ፣ የአለላ ወይም የሰፌድ ሥራ፣ የነሀስ፣ የብርና የወርቅ ወዘተ ጌጣጌጦች ሥራን፣ የፈረስ ጭራ፣ የቆዳ እና የመሳሰሉትን ትውፊታዊ እደጥበብ ሥራ እውቀቶችን ወደ ሀብት በመለወጥ ለገበያ በማቅረብ የሚገኘው ትሩፋት ወይም ሀብት ሌላኛው የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርሶች የሚያስገኙት ተዳሳሽ እሴት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የኢንታንጀብልና የኢትኖግራፊ ቅርሶች ተመራማሪ አቶ ደምረው በማጠቃለያ ሃሳባቸው እንደገሚገልፁት፤ ከእያንዳንዱ የሚዳሰስ ቅርስ የማይዳሰስ ቅርስ አለ። በመሠረቱ የሚዳሰሰውን ቅርሱን የፈጠረው የማይዳሰስ በምንለው ምድብ ውስጥ የሚያርፈው እውቀትና ክህሎት ነው። ስለ አክሱም ሀውልት ግዝፈት ወይም ስለላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ሲታሰብ ‹‹እንዴት አድርገው ጠረቡት፣ ቀረጹት ወይ ደግሞ አቆሙት›› ብለን እናሰላስላለን የሚሉት ተመራማሪው፤ ከፊታችን የቆመውን ሀውልት ወይም ውቅር አብያተክርስቲያን የሠራው የዛን ዘመን የማይዳሰሰውን ፍልስፍና መሆኑን መገንዘብ እንደሚኖርብን ያስረዳሉ። በዚህም የተነሳ ለአሠራርና ለመግባባት ካልሆነ በስተቀር ሁለቱን ነጥሎ ማየት እንደማይቻልም ይገልፃሉ።
እንደ ተመራማሪው ሃሳብ፤ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ በራሱ የሚዳሰስ ወይም ተጨባጭ የሆኑ ውጤቶች ወይም ፋይዳዎችን ያስገኛል። በመጀመሪያ የማይዳሰሱ የሚባሉትን መመዝገብና መለየት ሲቻል፣ ማጥናትና ምርምር ማድረግ ሲጀመር ወደ ሚዳሰስ እሴትነት መለወጥ እንደሚጀመር መታወቅ እንዳለበት ያስረዳሉ። በመሆኑም የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርሱን በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ትርጉም ያለውና ተጨባጭ ጥቅም መስጠት ወደሚችልበት ሁኔታ መለወጥ ይገባል ሲሉ ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ፤ ለተግባራዊነቱም ተባብሮ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም