ሀገር በብዙ መልኩ ትወከላለች፤ ከፍ ብላም ትገለጣለች። ኢትዮጵያም በውስጥ ኢኮኖሚዋን የሚደጉሙ፤ በውጭም ገጽታዋን የሚገነቡና ተጽዕኖዋን የሚያበረቱ በርከት ያሉ ዲፕሎማቶች (በግለሰብም፣ በተቋምም) አሏት። ከእነዚህ የበዙ ማንነትን ገላጭና ተጽዕኖ ፈጣሪነትን ከሚያጎናጽፏት ተቋማት መካከል ደግሞ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተጠቃሽ ናቸው።
እነዚህ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከትናንት እስከ ዛሬ የዘለቀ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ብሎም ዲፕሎማሲያዊ አቅም መፍጠሪያ ሆነው ሲያገለግሉ ኖረዋል። በተለይ እንደ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ኃይል፣ በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሳሰሉት፤ የኢትዮጵያን ስምም መልክና ዓርማም ተላብሰው የሚንቀሳቀሱና የሚሠሩ ተቋማት ናቸው።
በዚህ ረገድ እነዚህ ተቋማት፣ በአንድ በኩል የሀገር ኢኮኖሚን ከመደጎም አንጻር ከፍ ያለ ድርሻን ይዘዋል። በዚህም ከሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ከኢንቨስትመንት፣ ከማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማት ተደራሽነት፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት፣ ከቴክኖሎጂ ተደራሽነትና ሽግግር፣ ከዲጂታላይዜሽን አኳያ የማይተካ ድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛል። ለልማትና መንግሥታዊ ተግባራትን ለመፈጸም የሚያስፈልግ ሀብት በማስገኘት በኩልም ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ያሉ ናቸው።
ለአብነት፣ በሀገሪቱ የሚገኙ አጠቃላይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሦስት ትሪሊዮን ብር የሚደርስ ሀብት ያፈሩ ሲሆን፤ ይህም ከሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት ድርሻቸው 15 በመቶ ይሸፍናል። በሀብት ደረጃም ቢሆን ሦስት ትሪሊዮን የሚደርስ ሀብት ባለቤት ናቸው። ይሄ ደግሞ በሀገር ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ እያበረከቱ ያለው ድርሻ ጉልህ መሆኑን ማሳያ ነው።
ከዚህ የሀገር ውስጥ ጉዳይ አበርክቷቸው ባሻገር፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት፣ ከቀጣናው፣ ከአህጉሪቱ ብሎ ከዓለም ሀገራት ጋር በሚኖራት ግንኙነት ከፍ ያለ ተጽዕኖን እንድትጎናጸፍ በማድረግ በኩል እየተወጡት ያለው ተግባር፤ እነዚህ ተቋማት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሰንደቅ ሆነው እንዲገለጡ እያስቻሏቸው ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮ ቴሌኮም ሀገራችን በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ሆና እንድትቀጥል እና የራሷን ዲጂታል ሥርዓት እውን እንድታደርግ በማስቻል በኩል ከፍ ያለ ዓለም አቀፋዊ ክብር እና እውቅናን እየተቸረ ያለ ተቋም ነው።
በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፉም ያሉ ተቋማት፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያለባትን የኃይል አቅርቦት ፍላጎት ክፍተት ለመሙላት ከሚያደርጉት ከፍ ያለ ሥራ ባሻገር፤ የኢትዮጵያን በጋራ ሠርቶ በጋራ የመበልጸግ መርህን በማሳካት ላይ ያሉ ናቸው። በዚህ ረገድ ለጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ሌሎችን ሀገራት ተደራሽ የሚያደርገው የኤሌክትሪክ ኃይል አንዱ ማሳያ ሲሆን፤ ይሄንኑ ሥራ ወደ ሌሎች የአህጉሪቱ ቀጣናዎች ብሎም አህጉራት ያሉ ሀገራት በማስፋት የኢትዮጵያን የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ያደረገ የዲፕሎማሲ መንገድ በእጅጉ እያሳለጠ ይገኛል።
ሌላው፣ ከሀገር አልፎ ለአህጉር ኩራት ሆኖ የተገለጠው ደግሞ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። ኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ስም እና ሰንደቅ ዓላማ ተሸክሞ ከሀገር ሀገር የሚንቀሳቀስ እና አህጉር አቆራርጦ የአየር መስመር ድር የፈጠረ አንጋፋ ተቋም ነው። አየር መንገዱ በዚህ ተግባሩ እንደ አህጉር የመጀመሪያው ደረጃ ላይ የተቀመጠ ምርጥ አየር መንገድ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን አሉ ከሚባሉ ምርጥ ቀዳሚ አየር መንገዶች መካከል አንዱ መሆን ችሏል።
አየር መንገዱ ለዚህ ከፍታ የበቃው ዝም ብሎ አይደለም። ይልቁንም በመሠረተ ልማት በኩል የሠራቸው ሥራዎች፣ በሕዝብ ማስተናገጃ ተርሚናል ግንባታ፣ በካርጎ አገልግሎቱ፣ እንዲሁም ዘመናዊ እና ግዙፍ አውሮፕላኖች ባለቤትነቱ እና እነዚህን አውሮፕላኖች በልካቸው ተገንዝቦ መጠቀም የሚያስችል ሁለንተናዊ አቅም ባለቤት በመሆኑም ጭምር ነው።
አየር መንገዱ ዛሬ ላይ በዓመት አስር ሚሊዮኖችን በምቾትና ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ እያስተናገደ ይገኛል። ደረጃውን የጠበቀና ደኅንነቱ የተጠበቀ የካርጎ አገልግሎቱም ቢሆን፣ የክፉ ቀን የዓለም ሕዝብ አለኝታነቱን ያረጋገጠለት ጭምር ነው። ለዚህ ደግሞ የኮቪድ ወቅት ተግባሩ ዘመን ተሻጋሪ ህያው አብነት ነው። ከዚህ ባሻገር የራሱን አብራሪዎች፣ ቴክኒሺያኖች፣ የበረራ ባለሙያዎች፣… ከማሰልጠን አልፎ፤ ለወንድም ጎረቤት ሀገራት ጭምር መሰል ባለሙያዎችን በማሰልጠን አቅም መሆን የቻለም ነው።
እነዚህ እና መሰል ተግባራት ሲታዩ፣ የኢትዮጵያ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በአንድ በኩል የሀገር ልማት እና ኢኮኖሚ አቅም ሆነው መዝለቃቸውን ለመናገር ያስችላል። በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ እና የዲፕሎማሲ መርሆዎቿን ገላጭ አቅም በመሆን እየሠሩ ያሉ ናቸው። በመሆኑም፣ እነዚህ ተቋማት በሁሉም መስክ ያላቸውን ሀገራዊ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አበርክቶዎች ከፍ አድርገው እንዲወጡ ማስቻል የተገባ ነው። ተቋማቱም የኢትዮጵያ የውስጥ አቅም፣ የውጭም የዲፕሎማሲ ልዕልናዋ ሰንደቅ መሆናቸውን ተገንዝበው ለላቀ ኃላፊነት ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም