“ኢትዮጵያን ከርዳታ ጠባቂነት የሚያወጣት የዜጎች ሥራ ድምር ውጤት ነው” -ነገሠ ነገዎ -የገዳ ቱለማ ሐዩ

የዛሬው የዘመን እንግዳችን የገዳ ቱለማ ሐዩ ነገሠ ነገዎ ይባላሉ። የተወለዱት ዝቋላ ተራራው ስር ሲሆን፣ ኦዳ ጂዳ ደግሞ የቀበሌያቸው መጠሪያ ነው። በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ሊበን ጩቃላ ወረዳ፣ አዱላላ ከተማ መኖሪያቸውን ያደረጉት እንግዳችን ዛሬ የ70 ዓመት አዛውንት ናቸው። ፊደል የቆጠሩት እዛው ባሉበት ቀበሌ ሕዝባዊ የኑሮ እድገት በሚባል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው ነው።

ይሁንና በዚያ ትምህርት ቤት ብዙም ሳይቆዩ ወደ ቢሾፍቱ አቀኑ። በዚያም አፄ ልብነድንግል ትምህርት ቤት ገብተው በትውልድ ቀዬያቸው ጀምረውት የነበረውን የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ቀጠሉ።

እዚያም የጀመሩትን የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተረጋግተው ለመማር አልታደሉም። ምክንያቱም ተጠግተውት ይማሩበት የነበረው ሰው በዝውውር ምክንያት ወደ አዲስ አበባ አቀኑ። በዚያን ጊዜ እርሳቸውን ተከትለው ወደአዲስ አበባ ማቅናት ግድ ነበርና ተከትለዋቸው ተጓዙ። በዚያም ሽሮ ሜዳ በሚገኘው በቀድሞ አጠራሩ አማሐ ደስታ ትምህርት ቤት በመግባት የጀመሩትን የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ቀጠሉ። ይሁንና በትምህርት ቤቱ ብዙም አልቆዩም፤ አንድ ዓመት ብቻ ተምረው አምሰተኛ ክፍል ላይ አቆሙ።

በትምህርት ከዚያ በላይ መሄድ ስላልቻሉ ወደ ትውልድ ስፍራቸው ተመልሰው አባታቸውን በሥራ ሲያገለግሉ ቆይተው ትዳር መሥርተው መኖር ጀመሩ። ምንም እንኳ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ባያጠናቅቁም የዛሬው የዘመን እንግዳችን የጥልቅ ዕውቀት ባለቤት ናቸው። የተለያዩ ሃሳቦችን በማንሳትም መካሪ እና የገዳ ሥርዓትን አስተማሪም ናቸው።

ዛሬ ልጆች ወልደው የልጅ ልጅ ለማየትም በቅተዋል። እንግዳችን ባሉበት ቀበሌም ሆነ ወረዳ በማኅበራዊ ጉዳይ በመሳተፍና የተጣላን በማስታረቅም ሆነ በመምከር የድርሻቸውን እያገለገሉ ነው። በማኅበረሰቡ አባላት መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችንም በሽምግልና በመፍታት ላይ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅትም በሚኖሩበት በአዱላላ ከተማ የአባትነትና የሐዩነት ድርሻቸውን በመወጣት ላይም ናቸው። በሐዩነት እና አባ ገዳዎችንም እያስተማሩ የገዳ ሥርዓት እንዲከበር እየመከሩ ይገኛሉ።

እርሳቸው ወደ ገዳ ሥርዓት ውስጥ ከገቡ 24 ዓመት ያህል ሆኗቸዋል። ከዚያም ለስምንት ዓመት በአባ ገዳነት አገልግለው ለቀጣዩ አስረክበዋል። ከቆይታ በኋላ ደግሞ የገዳ ቱለማ ሐዩ ሆነው ሕዝቡን እንዲያስተምሩ ከሌላው አቻቸው ጋር በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። አዲስ ዘመንም እኚህን በአባትነትም በገዳ ሥርዓት አስተማሪነትም ትውልዱን እያነጹ ያሉትን ሐዩ (የቀድሞ አባ ገዳ) ነገሠ ነገዎ የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርጎ አቅርቧቸዋል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኗ ይታመናል፤ ነገር ግን እስካሁን በሌሎች ስትደገፍና ርዳታ ስትጠብቅ ቆይታለች፤ ይህ ለምን የሆነ ይመስልዎታል?

ሐዩ ነገሰሠ፡- በመሠረቱ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ሆና የሌሎች ሀገራትን እጅ መጠበቅ የለባትም። ምክንያቱም አሁን ጊዜው እንደድሮ አይደለም። ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ትከተለው የነበረ የአስተራረስ ዘዴ ምናልባት የሌሎችን ርዳታ እንድትጠብቅና አልፋም እንድትለምን የሚያስደርጋት አይነት ነው ሊባል ይችል ይሆናል። ምክንያቱም ድሮ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ይታረስ የነበረው በበሬ ነው። በበሬ ማረስ ደግሞ ብዙ ድካም አለው። ልፋቱና ውጣ ውረዱ ይብዛ እንጂ ውጤቱም የዚያን ያህል አጥጋቢ አይደለም።

አሁን ብዙ ቦታ በሚባል ደረጃ እየታረሰ ያለው በትራክተር ነው፤ እርሻዎቹም ኩታ ገጠም በመሆናቸው ለዚህ የአስተራረስ ዘዴ ምቹ እየሆኑ ነው። ለምሳሌ ብጠቀስልሽ እኔ ያለሁበት የኦሮሚያ ክልል ብዙ ለውጦች አሉ። አርሲ እና ባሌን ብንወስድ በአሁኑ ወቅት በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቨስተሮችም ሆኑ አርሶ አደሮች እርሻቸውን የሚያርሱት እንዳልኩሽ በትራክተር ነው። እኔ ያለሁበትም ዞን እንዲሁ እየታረሰ ያለው በትራክተር ነው።

ሌላው ኢትዮጵያ እንደሚታወቀው ለግብርና ሥራ ምቹ የሆነ የአየር ፀባይ ያላት ከመሆኑም በተጨማሪ መሬቱም ውሃውም አልጠፋም። ይህንን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የግብርና ሥራዎች በተለይ በአትክልት ምርት ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ አጥጋቢ ነው። የአትክልት ልማት በራሱ ሰፊ በመሆኑ ለየአካባቢው ሕዝብ የመጥቀሙን ያህል ለሀገርም ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው።

እንደ እኔ እምነት በአሁኑ ወቅት ሁሉም ቢሆን እዛው ጤፉ ላይ ወይም በቆሎው ላይ ተቸክሎ መቆየትን አይፈልግም፤ አትክልቱንም በማምረት ከልማቱ ተጠቃሚ እየሆነ ነው። ነገር ግን ይህ ብቻውን በቂ ነው ማለቴ አይደለም። ከዚህ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆንና ሀገርንም ለመጥቀም በተሰጠን የተፈጥሮ ፀጋ ለመጠቀም ትውልዱ አሁንም ለሥራ መትጋት ይጠበቅበታል። በሀገራችን በርካታ ወንዞች አሉ። ለምሳሌ አዋሽን ተከትሎ የተለያዩ አትክልቶች እና ፍራፍሬዎችን ማምረት ቢቻል ከፍተኛ ጥቅም ያለው ነው። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ነው። ሥራ ሠርቶ መለወጥ ለተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ የተሰጠ ስጦታ አይደለም። መሥራት የሚችል ሁሉ ሠርቶ መለወጥ አለበት። ኢትዮጵያን ከርዳታ ጠባቂነት የሚያወጣት የዜጎች ሥራ ድምር ውጤት ነው፤ ስለዚህም ትውልዱ ሊሠራ ይገባል።

ይህ እንደሚቻል ደግሞ በዓይናችን አይተናል፤ በጆሯችንም ሰምተናል። ኢትዮጵያ በመስኖ የስንዴ ምርት ማልማት ጀምራለች፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ያመረተችውንም ወደውጭ ሀገር መላክ ጀምራለች። ይህ መሆን እንደሚችል ትውልዱ በዓይኑ አይቷል። ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻልም በተግባር ተመልክቷልና ከገባበት ሰመመን መንቃት ችሏል። ይህ ተግባር ተጠናክሮ ቢቀጥልና ትውልዱም የሥራ ባሕሉን እያዳበረ ቢመጣ ኢትዮጵያ አትለምንም፤ ርዳታ ጠባቂም አትሆንም።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ነፃ ሀገር መሆኗ እውን ነው፤ ነገር ግን ርዳታ እና ድጋፍ ትሻለች፤ ከልመና በመውጣት ክብሯን እንድታስጠብቅ ለወጣቱ ምን ይላሉ?

ሐዩ ነገሠ፡– ልመና ሰውን ያሳንሳል፤ ያዋርዳልም። ያለፈ ክብር ኖሮ ቢሆን እንኳ ከዛ ክብር ዝቅ ያስደርጋል። በልመና መዝለቅ አይቻልም። ምክንያቱም ክብርን የሚያሳንስ ነው። በሀገር ደረጃ የሚታየውን ጠባቂነት መቀየር ይቻላል። በአሁኑ ወቅት ጊዜው ተሻሽሏል። ያንን አጋጣሚ ለመጠቀም በተለይ ወጣቱ ክፍል ወደሥራ መግባት አለበት። የሚሠራው ለሌላው ሳይሆን ለራሱ ነው። ለራሱ በሠራው ጥሩ ሥራ ሀገር ትጠቀማለች። ሀገሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጣት ስም የእርሱ ስም መሆኑን መዘንጋት የለበትም። ሀገርህ ለማኝ ናት መባልን ደግሞ የሚፈልግ ያለ አይመስለኝም። ራሷን የቻለች ነፃ ሀገር እንድትሆን የማይፈልግ አለ ብዬ አላስብም።

ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች የእርሻ ማሳ እያለ ከማረስ ይልቅ ወደከተማ በመሰደድ እጃቸውን ንጹሕ አድርገው መቀመጥን ይመርጣሉ። ሥራ መሥራት ቢፈልግ በእኔ እምነት ያጣው ነገር የለም። ተደራጅቶ መንግሥትን ቢጠይቅ ምቹ ሁኔታን የማይፈጥርለት ማንም የለም። ምክንያቱም ሀገር ከልመና መውጣት የምትችለው ዜጎቿ ጠንክረው መሥራት ሲችሉ ነው፤ ሌላ አዲስ ነገር የለውም።

መንግሥት ደግሞ ተደራጅቶ ለሚመጣ ወጣት ቦታ በመስጠት እስኪቋቋም ድረስ ክትትል ሊያደርግለት ይገባዋል። ቦታ እና ገንዘብ መስጠት ብቻ ሳይሆን በተፈጠረለት ምቹ ሁኔታ ምን እያደረገ ነው ሲልም ቁጥጥር ሊያድርግበት ይገባል።

እውነት ለመናገር በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ክልሎች እየተደረገ ያለው የልማት ሥራ የሚያስገርም ነው። ለምሳሌ በየአቅጣጫው የዶሮ እርባታ ተስፋፍቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን የተሻሻሉ የከብቶች ዝርያ ወደማኅበረሰቡ በመቅረብ ላይ ነው። ይህ አይነቱ ሥራ የሚበረታታ ነው። ሥራ የለም ለሚል አካል ከዚህ አይነት የሥራ ዘርፍ ሌላ ምን ሊመጣ ይችላል?

እንደ ቀላል መታየት የሌለበት ነገር በሀገራችን በዶሮ እርባታም ሆነ በእንስሳት፣ አትክልትና ፍራፍሬ እየተካሔደ ያለው ልማት ነው። ሰው በዘርፉ በመሰማራቱ ኢኮኖሚው ያድጋል። በትክክልም በልቶ ማደር ይችላል። በልቶ ማደር ከተቻለ ደግሞ በምግብ ራስን መቻል ተጀመረ ማለት ነው። ስለዚህ በተለይ ወጣቱ ክፍል ለመሥራትና ለመለወጥ ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል። ለዚያ ደግሞ ሥራን መምረጥ አይኖርበትም። ይሁንና ሥራን መናቅ እንደሌለባቸው የሚያስችል ግንዛቤም ከመንግሥት በኩል ቢሰጥ ጥሩ ነው እላለሁ።

ሀገራችን ሁልጊዜ በርዳታና በድጋፍ እኖራለሁ ብትል ራሱ ድጋፍ ሰጪው አካል ይሰለቻታል። እውነት ለመናገር ከዚህ ቀደም የተለየዩ ሀገራት ለሀገራችን ድጋፍ አድርገዋል። የርዳታ ስንዴም ሰጥተውናል። ሀገራችንም ከችግሯ የተነሳ ባለፉት ዘመናት ከብዙዎች ብዙ ነገር ጠብቃም ጥቂት ነገር አግኝታለች። በልመና የትም መድረስ አይቻልም። የእስከዛሬው ልምድ የሚያሳየው ይህንኑ ነው።

በግለሰብ ደረጃም የሚታየው እንዲሁ ነው። ልመና የልብ የሚያደርስ አይደለም። ሥራ ፈትቶ እስኪላክለት የሚጠብቅ አካል ያሻውን እና የሚያስፈልገውን ሁሉ ማድረግ አይችልም። የራሱን ፍላጎት ለማሟላት የራሱ ጥረት የግድ ነው።

ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ራሷን ለመቻል ጥረት ማድረግ አለባት፤ ጥረቱ የሚለካው ደግሞ በልጆቿ አማካይነት ነው። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በመልማት ላይ ትገኛለች። ለልመና የሚዳርገን ምንም ምክንያት ያለ አይመስለኝም። ያለው የአየር ሁኔታም ቢሆን የትኛውንም ልማት ለማካሔድ ምቹ ነው። የሚያስፈልገን ነገር ቢኖር ሠላም ነው። ፈጣሪ ሠላምን በሀገራችን ያስፍንልን እንጂ የጠፋ ነገር የለም።

በአሁኑ ወቅት በየአካባቢው እየተተከለ ያለው ችግኝ በራሱ የአየር ሁኔታውን የበለጠ ተስማሚ እያደረገ ነው። ቀደም ሲል ተራቁተው የቆዩ ጋራና ሸንተረሩ በሙሉ በመለወጥ ላይ ይገኛል። በየመስኩ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ ነው። ቀድሞ የሌለውን አይነት ምርትም እያመረትን ነው። በመሆኑም ሀገራችን ከዚህ በኋላ ለልመና ራሷን አሳልፋ መስጠት የለባትም እላለሁ። ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ የሌላውን አካል ርዳታ የምትጠብቅ ከሆነ ስሟ የሚያጎድፍ ይሆናል። ርዳታ የመጠበቅ አስተሳሰብ መቅረት አለበት።

አዲስ ዘመን፡- እንዴት ማስቀረት ይቻላል?

ሐዩ ነገሠ፡- ለትውልዱ በተለይ ለወጣቶቹ የምመከረው ነገር ቢኖር ልመና አዋራጅ እና ክብር የሚያሳጣ በመሆኑ ሥራ እንዳይንቁ ነው። ጠንክረው የሚሠሩ ከሆነ በጥረታቸው የተሻለ ቦታ መድረስ ስለሚችሉ ለራሳቸውም ሆነ ለሀገራቸው አለኝታ መሆን ይችላሉ። ሥራ አለመናቅ የሚጀመረው ደግሞ አሁን ሀገራችን ውስጥ እየተከናወነ ያለ ትልልቅ ሐሳብ አለ፤ ይኸውም ዶሮ ማርባት፣ ንብ ማነብ፣ ከብት ማደለብም ሆነ አትክልት ማልማት በጥሩ ሁኔታ የተጀመረ በመሆኑ እዛ ላይ እየተደራጀ መሥራት ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- በየትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ተረጂነት ወይም ልመና ስም የሚያጎድፍ ነው፤ እርስዎ ይህን እንዴት ይመለከቱታል?

ሐዩ ነገሰ፡– ጉዳዩን ከመጀመሪያው ለመግለጽ ያህል ለምሳሌ አንድ ሰው ሊቸግረው ይችላል። ከችግሩ ሊወጣ የሚችልበትን ዘዴ በአካባቢው ያሉ ሰዎች መክረው የተቸገረ ሰው ራሱን እንዲችል ይታገዛል፤ በኦሮሞ ባሕልም ይህ አይነቱ ድጋፍ ይደረጋል። ለምሳሌ ሊያርስ የሚችልበት በሬ በመስጠት ካለበት ችግር እንዲወጣ ይደረጋል። የምትታለብ ላም በመስጠትም ያንን ክፉ ጊዜ እንዲያልፍ ይረዳል። እንዲያ የሚደረገው ግን እንዲቋቋም እንጂ ለሁልጊዜው ተረጂ እንዲሆን አይደለም። ይህ ሁሉ ድጋፍ ተደርጎ ራሱን ሳይችል ቀርቶ እየዞረ የሚለምን መሆን የለበትም። ይህ በባሕሉ አስነዋሪ በመሆኑ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም። እንዲያውም ለማኝ ተብሎ ይጠራል። ምክንያቱም ሰው ለፍቶ ጥሮ ግሮ ራሱን መቻል አለበት የሚል እምነት አለ። ምክንያቱም ማኅበረሰቡ በልመና የሚመጣ ገንዘብም ሆነ ንብረት ዘለቄታ ያለው እንዳልሆነ ስለሚያውቅ ከዚያ ፈጥኖ እንዲወጣ የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የኦሮሞ ባሕልም ልመናን የሚጠየፍ መሆኑ ነው።

ልመና አንድን ግለሰብን ሆነ ሀገርን ዝቅ የሚያደርግ ነው። የሚለምን አካል ክብር የለውም። እንዳልኩት በአንድ አጋጣሚ ተቸግሮ ሊሆን ይችላል፤ ለዚያ ችግር መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ባሕል በእያንዳንዱ ብሔር እንደሚኖር ሁሉ በኦሮሞም በጥቅል እንደ ሀገርም ይኖራል፤ በሚደረገው ድጋፍ ተበረታቶ ራስን ማቋቋም የማይፈልግ አካል ካለ ያው ስያሜው ለማኝ ነው የሚሆነው፤ መለመን ደግሞ የሚያሳፍር በመሆኑ ከዚህ ውስጥ ለመውጣት ሥራ ፍቱን መድኃኒት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ልመናም ሆነ ርዳታ መጠበቅ ኢትዮጵያንም ሆነ ዜጎቿን አይመጥንም፤ እርስዎ በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?

ሐዩ ነገሠ፡- አንዳንዴ ልመናን ወይም ርዳታ መጠበቅ ባሕል የሚሆንበት ጊዜ አለ፤ መሥራት እየተቻለ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣን ድጋፍ እንደመብት መጠበቅ የሚታይበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ በሙስሊሙም መስጂድ አካባቢ፣ በክርስቲያኑ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ እጃቸውን ለልመና የሚዘረጉ ግለሰቦች በእኔ እይታ ሁልጊዜ ስለቸገራቸው ብቻ ሳይሆን ልመናውን ባሕል አድርገው ዝም ብለው ሳይሠሩ በቀላሉ ለመብላት በመፈለግ ነው።

በእርግጥ ድጋፍ ሊደረግላቸው የተገቡ እንዳሉ የሚዘነጋ አይደለም። እርግጥ እንደየብሔሩና እንደየሃይማኖቱ መረዳዳት አለ፤ ከርዳታ ፈጥኖ ወጥቶ የራስን ሥራ መሥራት ደግሞ የግድ ነው። ልመናን ባሕል አድርጎ መቀጠል ከግለሰቡ አልፎ ሀገርንም የሚጎዳ ነው።

መንግሥት ደግሞ በዚህ በየዘርፉ ለዜጋው ሥራ ለመፍጠር እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚመሰገን ነው። ወጣቱን በተለያየ ማኅበር እያደራጀ እና በተለያየ መስክ የሥራ ክህሎት እንዲኖራቸው ሥልጠና በመስጠት የየራሳቸውን ሥራ እንዲሠሩ በማበረታታት ላይ ይገኛል። እንዲህ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ባለበት በዚህ ጊዜ ትውልዱ በመሥራት ራሱንም ሀገሩንም መለወጥ ይችላል።

ኢትዮጵያም ከርዳታ ጠባቂነት ሆነ ከልመና ልትወጣ የምትችለው በልጆቿ አማካይነት ነው እንጂ ሌላ ሊመጣ የሚችል ተዓምር አይኖርም። ስለዚህ መንግሥት ምቹ ሁኔታን እያመቻቸ ባለበት በዚህ ጊዜ ሥራን ባለመናቅ መሥራት ፋይዳው ለሁሉም ወገን ነው። ለሥራ ደግሞ የግድ ሙሉ አካል መሆን አይጠበቅም፤ ማየት የተሳነውም ሆነ አካሉ የተጎዳ በሚፈጠረው ምቹ ሁኔታ መሥራት ይችላል። ለሁሉም አንድ አይነት ሥራ መስጠት ሳይሆን እንደየችሎታው መሥራት በሚችለው ላይ ማሰማራት ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ ሥራ የለም የሚል አቤቱታ ከትውልዱ ይደመጣል፤ እርስዎ ትውልዱ ሥራ እንዳይንቅ ምን ይመክራሉ?

ሐዩ ነገሠ፡- ትውልዱ ሥራ እንዳይንቅ ይህን አስተሳሰቡን ለመቀየር ግንዛቤ ማስጨበጥ በመጀመሪያ ተገቢ ነው እላለሁ። ለጊዜው የተፈጠረለትን የሥራ ዕድል ወደጎን ሳይል ተጠቃሚ ለመሆን መትጋት አለበት። ሥራ የሌላቸው ወጣቶችም ሆኑ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ተደራጅቶ መሥራት፣ ሲጠናከር ደግሞ ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ ጊዜ የሚፈቅድ ጉዳይ ነው። የተደራጀ አካል በብዙ ሁኔታ በመንግሥት ሲደገፍ እናስተውላለን። ይህ መልካም የሆነ ነገር ነው። ነገር ግን ሁልጊዜ ሲደገፍ መኖር የለበትም። ራሱን ችሎ ደግሞ ለሌሎችም መትረፍ መቻል አለበት ባይ ነኝ። ይህ አይነት አካሔድ ካለ ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝቅ የሚያደርጋትን የተረጂነት ሁኔታዋን መቀየር ትችላለች።

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ኢትዮጵያ ራሷን በምግብ እንድትችል ግብርና ላይ ጠንከር ያለ ሥራ እያከናወነ ነው፤ ይህን እንዴት አዩት?

ሐዩ ነገሠ፡– እውነት ለመናገር እኔ ይህንን ያየሁት በመደነቅ ነው። ይህ አይነት አሠራር ቀደም ሲል አላየሁም። ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር ቀደም ሲል የነበረንን ብዙ እንስሳ ነው። እሱ ግን ካለብን ድህነት ሊያስቀረን አልቻለም፤ ምክንያቱም ከብቱ ብዙ ይሁን እንጂ ዝርያው አነስተኛ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ መጠቀም አልተቻለም ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን መንግሥት የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችንም ሆነ ጫጩቶችን ከውጭ አገር ድረስ በማስመጣት በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ውጤታማ እንዲሆኑ እያደረገ ነው። ይህ በራሱ አገራችንን ራሷን እንድትችል ሊያደርጋት ከሚችለው መካከል ተጠቃሽ ነው።

በእህል በኩልም ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ወደአርሶ አደሩ በማድረሱ በኩል ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውም መልካም የሚባል ጅማሬ ነው። ይህ አቅርቦት ቀደም ሲል በሥራ ላይ ላለ አካል ብቻ ሳይሆን ሥራ አጥ ለሆኑትም በማደራጀት ወደሥራ እንዲገባ ማድረግ ተገቢ ነው እላለሁ።

አዲስ ዘመን፡-ትውልዱ እንደ እርስዎ ያሉ አባ ገዳዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችንም ሆነ የሃይማኖት አባትን ምክር የመስማት ፈቃደኛነቱ እየቀረ ነው፤ ለዚህ መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?

ሐዩ ነገሰ፡- እውነት ነው፤ ትውልዱ የታላላቁን ምክር ቸል ብሏል። ነገር ግን ሁሉም የየራሱ እና የየአካባቢው ባሕል እና እሴት አለው። በዚያ ባሕል ውስጥ ሽማግሌም ታላቅም ይከበራል። በሀገራችን በየትኛውም አካባቢ ያለ ባሕልም ሆነ የትኛውም እምነት እናትና አባት እንዲከበሩ የሚያዝ ነው። የየሃይማኖት አባቶች ቃልም እንዲደመጥ የሚያዝ ነው። ለምሳሌ በባሕላችንም ሆነ በሃይማኖቱ ረገድ አትሥራ የሚልም ሆነ ታላላቆችህን አታክብር የሚል ሕግም አስተምሕሮም የለም። ይሁንና እንደተባለው ትውልዱ ያንን ልማዳዊ ሕግ ላለማክበር ገሸሽ ሲል ይስተዋላል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የራሱን ነገር ቸል ብሎ ወደውጪው ባሕል በማዘንበሉ ነው።

ነገር ግን በባሕላችንም ሆነ መልካም በሆኑ እሴቶቻችን ውስጥ የሌለውን አፈንጋጭነት እንዳይቀጥሉ መምከር ከእኛ አይነቱ የሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅ ነው። ልጅን ከመሠረቱ መጥፎውን ከጥሩ እንዲለይ የምናስተምር ከሆነ ባስተማርነው ያድጋልና ያንን እናድርግ እላለሁ። ይህን የምናደርግ ከሆነ የተሻለ ትውልድን ማፍራት እንችላለን።

የሃይማኖት አባቶች እና አባ ገዳዎች የየራሳቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው። ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል አባገዳዎችም ሆኑ ሐዩዎችም በየቦታው አለን፤ ትውልዱን ማስተማር እንችላለን፤ አሁንም ቢሆን እያስተማርንና እየመከርንም እንገኛለን። ሥራ ፈትቶ የሚለምነውን አካል ልመና የሚያስጸይፍ ተግባር መሆኑን አስረግጠን ማስገንዘብ ይጠበቅብናል ባይ ነኝ።

በተለይ ከሰዎች መጠበቅ አዋራጅም በራስ አለመተማመንንም የሚፈጥር በመሆኑ እና ሥልጡንነት አለመሆኑን ማስረዳት አለብን። ሁሉም እንደየአቅሙ ተደራጅቶም ሆነ በግሉ መሥራት የሚያስከብር መሆኑን ማሳወቅም ከእኛ ይጠበቃል። በእርግጥ ባሕላችንም የሚለው ይህንኑ ነው። አባ ገዳዎች ይህንን ማስተማር አለብን። ሐዩዎችም ይህንን ማስገንዘብ አለብን። ሌሎችን እንዲሁ የሚያስተምሩና የሚመክሩ ከሆነ የማይለወጥ ነገር የለም። ሁሉም መልካም ይሆናል።

ትንሽ እኛን እየጎዳን ያለው ነገር ትውልዱ የራሱ የሆኑ መልካም እሴቶችን ትቶ የማይበጀውንና አጥፊ የሆነውን የውጭ ባሕል ላይ መጠመዱ ነው። ትውልዱ ወደራሱ ማንነት ይመለስ። የራሱ የሆነ የሚያኮራ ባሕል ባለቤት ነው። የጣለውን መልካሙን ማንነት ያንሳ፤ እምነቱን ያጠንክር። እናት እና አባቱን ቢያክብር፤ ታላቅ እና ታናሽ ደግሞ እርስ በእርስ ቢከባበሩ፤ አንደኛው የሌላኛውን አብሮነት ቢወድድ ሀገራችን ሠላም ትሆናለች።

በአሁኑ ወቅት ሰውን እያጨካከነ ያለው ነገር ምንድን ነው? ያልሽኝ እንደሆነ ድሮ ልጆቻችን ሬሳ አያዩም፤ በአካባቢያችን አንድ ሰው ከሞተ ግብዓተ መሬቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንጀራ አይበላም። አሁን እሱ ነገር የለም። ሰው እርሱ በእርሱ ሲተራረድ እየታየ ነው። አንዱ በወንድሙ ላይ እጁን ለማንሳት ችግር የለበትም። ሞት ርካሽ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ክፉ ክፉውን ለማየት የሚያስችል ልብ እየተፈጠረ ነው። ይህ ግን እልቂትን እንጂ ኑሮን የሚያሳምር አይደለም። ለዚህም ነው ትውልዱ ምክር የሚያስፈልገው እላለሁ። የሚመክር ካለ የሚመለስ ትውልድ አለ። ኢትዮጵያ የብዙኃን ሀገር ናት። ስለዚህም ትውልዱን እንደየብሔረሰቡ ባሕልና እሴት ማስተማር ለውጥን ማምጣት ያስችላል።

አዲስ ዘመን፡- በኦሮሚያና በአማራ ክልል እየተስተዋለ ያለ የሠላም መታጣት አለ፤ ሠላም እንዲመጣ እርስዎ ምን ይላሉ?

ሐዩ ነገሠ፡- እርግጥ ነው ጦርነት ማንንም አይጠቅምም። ጦርነት የሰውን ልጅ ሕይወት ይቀጥፋል። እልቂትን ያመጣል። በየትኛውም ክልል ያለ አካል የሚፈልገው ነገር ሊኖረው ይችላል። ያንን ለማግኘት ግን ጦር መስበቅ አይጠበቅበትም። ሠላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄውን ማቅረብ ይኖርበታል እንጂ ለጦርነት ራሱን ማዘጋጀት ለማንም አይበጅም።

ሁሉም ነገር መልስ አለው። የሚፈለገውን ነገር ወደውይይት ማምጣት አንዱ ሲሆን፣ ለዚያ ጉዳይ ደግሞ በውይይት መፍትሔ ማምጣት አስፈላጊ ነው። በጥላቻ እና በጦርነት አሁንም ቢሆን የሚመጣ ሠላምም ሆነ ተፈላጊው ጉዳይ አይኖርም። ምርጫው ጦርነትና እርስ በእርስ መፋለም ከሆነ ውጤቱ ሞት፣ ጉስቁልና እና የከፋ ጉዳት ነው።

ይህ ችግር ደግሞ የሚመጣው ጦርነት ፈላጊው አካል ላይ ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ ላይም ጭምር ነው። ከፍ ሲል ደግሞ የባሰ ችግር ውስጥ የምትገባ ሀገራችን ናት። ስለዚህ ይህ ችግር እየባሰ እና እየከፋ እንዳይሄድ ሁሉም ጥቂት ስለትውልዱም ሆነ ስለሀገሩ ቆም ብሎ ቢያስብ መልካም ነው። ጥያቄ ካለውም ወደፊት ለፊት በማምጣት በጉዳዩ ላይ ቢመካከር መልካም ነው። የሃይማኖት አባት እንደ ሃይማኖት አባትነቱ፣ ሽማግሌውም እንደ ሽማግሌነቱ፣ ቤተሰብ እንደቤተሰብነቱ ቢመካከር፣ ቢወያይና የየድርሻውን ቢወጣ ይህ ሠላም መታጣት ይቀርና ሠላም መስፈን ይችላል። ከመገዳደል በመመካከር መፍትሔ መፈለግ ብዙ ርቀት አብሮ ለመሄድ የሚያስችል ነው። እግዚአብሔር ደግሞ ለሀገራችን ሰላም ይስጣት እላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አጀንዳ የማሰባሰቡን ሥራ እየሠራ ይገኛል፤ ሕዝቡ ወደውይይቱና ምክክሩ እንዲመጣ ምን ይመክራሉ?

ሐዩ ነገሰ፡- የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን እናውቃለን፤ ቀደም ባለው ምክክር ላይ ነበርንበትም። እኔ ባለሁበት ወረዳም እንደተባለው ከመቶ ያላነሰ ሰው ወክለን ልከናል። ሊደረግ ያለው ምክክር መልካምን ነገር ይዞ የሚመጣ ነውና ይቀጥል የሚል አስተያየት አለኝ። ምክንያቱም የተመካከረ ሰው እንዲሁ በከንቱ ጊዜውን አይጠፋም። አንድ ውጤት ላይ ይደርሳል የሚል እምነት አለኝ።

የማይመካከር፣ የሆድ የሆዱን የማይገልጥ፣ ምስጢሩን የሚደብቅ እና ችግሩን የማይናገር አካል፣ ለችግሩ ምንም አይነት መፍትሔ አይገኝለትም። ስለዚህ የምክክር ኮሚሽኑ ሥራውን እየሠራ ነው፤ እኛም ለውጤታማነቱ ድጋፍ ልናደርግለት ይገባል። ይህ ሁሉ ድካምና ልፋት ለኢትዮጵያ ሠላም ሲባል ነው፤ ኢትዮጵያ ሠላም ሆነች ማለት ደግሞ ለሁላችንም መልካም የሆነ ነውና ኮሚሽኑ ይጠንክር እላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ከሰሞኑን በሀገር ደረጃ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለ የኮሪደር ሥራ አለ፤ ይህን የልማት ሥራ እንዴት አዩት?

ሐዩ ነገሰ፡- ይህ ሥራ በእኔ በኩል ታይቶ የማይታወቅ ነው፤ እኔ ስሰማ እንዲህ አይነቱ ሥራ በውጭ ሀገር ያለ ነው። ይህ አይነት ሥራ እኛ ዘንድ መምጣቱ በጣም የሚያስደስት ነው። ይህ ነገር በእኔ እምነት ከጨለማ ወደብርሃን፣ ከጠባብ መንገድ ወደ ሰፊ መንገድ እንደመሸጋገር የሚቆጠር ነው። ደግሞም ነው። ከደሳሳ እና ጭንቅንቅ መኖሪያ ወደ ተሟላ መኖሪያ መሸጋገር ነው። ይህ አይነቱ ሥራ እኛ ኢትዮጵያውንም እንደአውሮፓና አሜሪካ በተሻለ መንገድ እና ቤት መኖር የሚያስችልንን ጉዞ መጀመራችን የሚያመላክት ነው። ይህ ደግሞ የሚያኮራ ተግባር ነው።

በእርግጥ መልካሙን እና የተሻለውን ለመያዝ ጉዳት ይኖራል። የሰዎች ቤት ፈርሷል፤ ይህ ደግሞ ሰዎችን ሊያሳዝን የሚችል ነው። ይሁንና ለዚህም ጉዳይ መፍትሔ እየተሰጠ የሚሠራ በመሆኑ የሚጋጥመንን ፈተና በመታገስና በመመካከር በማለፍ ወደተሻለው ኑሮ መሸጋገር ያስፈልጋል። ይህ የአዲስ አበባ ተሞክሮ እኔ ወደምኖርበት ወደቢሾፍቱ አካባቢም እየመጣ ነውና በዚህ ደስተኛ ነኝ። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በእድገት ጎዳና መሆኗ ደስ የሚያሰኝ ተግባር ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

አዲስ ዘመን፡- እንግዳችን ስለሆኑ በጣም አመሰግናለሁ።

ሐዩ ነገሰ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You