ኢትዮጵያ በፓሪስ!

የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ትናንት ምሽት በይፋ ተጀምሯል። በኦሊምፒክ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስታዲየም ውጪ የመክፈቻው ሥነ ሥርዓቱ ሲካሄድ፤ የተሳታፊ ሀገራት ልኡኮች የፓሪስ እምብርት በሆነው ሴይን ወንዝ በጀልባ በመጓዝ ሰንደቅዓላማቸውን ይዘው ሀገራቸውን አስተዋውቀዋል።

የ50 ሜትር ነፃ ቀዘፋ የውሃ ዋና ተወዳዳሪዋ ሊና አለማየሁ እና የ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ተወዳዳሪው አትሌት ምስጋና ዋቁማ የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ከፊት አንግበው በመክፈቻ ሥነሥርዓቱ ልዑኩን መርተዋል።

በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ከ120 ሀገራት በላይ መሪዎች ወይም ተወካዮቻቸው የተገኙ ሲሆን፣ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም በመክፈቻው ለመታደም ከትናንት በስቲያ ከኢትዮጵያ ከልዑኩ ጋር ፓሪስ መግባታቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ በአትሌቲክስና ውሃ ዋና 35 ስፖርተኞችን የምታሳትፍ ሲሆን፣ በመካከለኛና ረጅም ርቀት እንዲሁም የማራቶን ውድድሮች በርካታ ሜዳሊያ ያስመዘግባሉ ተብሎ ከሚጠበቁ ሀገራትም አንዷ ነች።

ፓሪስ ለኢትዮጵያ 15ኛ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በተሳተፈችባቸው ኦሊምፒኮች ስኬታማ በሆነችበት አትሌቲክስ 23 የወርቅ፣ 12 የብርና 23 የነሐስ በአጠቃላይ 58 ሜዳሊያ አስመዝግባለች።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You