ሚኒስቴሩ ዓመቱን ሙሉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ሊሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- ያለውን አቅም በማስተባበር የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ዓመቱን ሙሉ ለመሥራት እቅድ መያዙን የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለፁ።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር በትናንትናው ዕለት አስጀምሯል።

ሚኒስትሯ ሸዊት በመርሃግብሩ እንዳሉት፤ የባህል እና ስፖርት ሴክተር ከፍተኛ አቅም ያለው በመሆኑ የስፖርት ማህበራት እና የኪነ ጥበብ እንዲሁም የሥነ ጥበብ ማህበራት በማስተባበር በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመሥራት ታቅዷል።

የበጎ ፈቃድ ሥራዎች በክረምት ብቻ የሚሠራ ሳይሆን አቅምን በማስተባበር ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ ክልሎች ለመሥራት እንደታሰበ ጠቅሰዋል።

ችግኝ በመትከል፣ ደም በመለገስ እና የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ በመጀመር ዓመቱን ሙሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል።

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት እና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ወይዘሪት ሃይማኖት ግርማ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱት የበጎ ፈቃድ ሥራዎች መካከል በአማራ ክልል የአቅመ ደካሞችን ቤት መጠገን፣ መአድ ማጋራት እና ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እና ዩኒፎርም ድጋፍ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የማህበረሰቡን ችግር ተረድተው የብሔራዊ ቴአትር እና የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት አገልግሎት ሠራኞች ላደረጉት የበጎ ፈቃድ ሥራ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ አመስግነዋል።

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የባህል ክፍል አርቲስት ሰናይት ሃይለማሪያም መርሃ ግብሩ ላይ የተገኘች ሲሆን፤ በተለያየ ጊዜ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፏን ገልፃለች።

አሁንም የራሷን ዐሻራ ለማስቀመጥ ችግኝ መትከልዋን እና ለአራተኛ ጊዜ ደም መለገስዋን ተናግራለች።

የተጀመረው የበጎ ፈቃድ ተግባር ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል እና የተተከሉት ችግኞች በመንከባከብ፤ መልካም የሆነውን ሁሉ በማድረግ ሀገራችንን ወደ ጥሩ ደረጃ ማድረስ ይኖርብናል ብላለች።

መርሃ ግብሩ ላይ የዘርፉ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና በጎ ፈቃደኞች የተገኙ ሲሆን፤ የደም ልገሳ እና ችግኝ ተከላ አከናውነዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You