ለኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ወገኖቻችን በሁሉም አይነት ድጋፍ ልንደርስላቸው ይገባል!

ኢትዮጵያ የተለያዩ መልክዓ ምድር ባለቤትነቷ ለዜጎቿ ካለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ባሻገር፤ በጋን ጠብቆ በሚከሰት ድርቅ፣ የክረምት መግባትን ተከትሎም በሚፈጠር ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ዜጎች በንብረታቸው፣ በአካላቸውና በሕይወታቸው ላይ ከፍ ያለን ጉዳት ሲያስተናግዱ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ረገድ ከብዙዎች አዕምሮ ከማይጠፋው የ77ቱ ድርቅ እና የብዙዎችን ልብ የሰበረው የድሬው የጎርፍ አደጋ ከበዙት አደጋዎች ውስጥ እንደ አብነት የሚጠቀሱ ናቸው።

እነዚህ በድርቅም ይሁን በጎርፍ አልያም በሌላ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ጉዳዮች ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎች ታዲያ ዘርፈ ብዙ ምክንያት ያላቸውን ያህል፤ በዜጎች ላይም መልከ ብዙ ጉዳትን ሲያስከትሉ ኖረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የወገን ደራሽ ወገን መሆኑንም ያሳዩ፣ የኢትዮጵያውያንን የሰብዓዊነት ልክ የገለጡ ክስተቶችም ናቸው፡፡ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሥራችንንም በመጠኑም ቢሆን የገለጡ ናቸው፡፡

በዚህ መልኩ በተለያዩ ጊዜያት ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የእሳት፣ የመሬት መንሸራተትና መሰል አደጋዎች ሲከሰቱ፤ እነዚህ አደጋዎችን የዜጎችን ንብረት ሲያወድሙ፤ ከቤት ንብረታቸው ሲያፈናቅሉ፤ ለአካል ጉዳት ሲዳርጉ፤ ሲከፋም ውድና ተኪ የሌላትን ሕይወታቸውን ሲነጥቁ ኖረዋል፡፡ ከሰሞኑም በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የደረሰው ድንገተኛ የመሬት ናዳ (መንሸራተት) አደጋ የእነዚህ አስከፊ ሀገራዊ ክስተቶች ሌላው ጠባሳ ሆናል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በዚህ አደጋ ከ260 የሚልቁ ወገኖች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ በተደረገው የነፍስ አድን ሥራ ዘጠኝ ያህል ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ እና ከ194 በላይ አስከሬኖችን ማውጣት ተችሏል፡፡ በሕይወት የተረፉትም ሆስፒታል ገብተው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ በአደጋው ምክንያት 600 የሚሆኑ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው በመፈናቀላቸው፤ ለእነዚህ ወገኖች የዕለት ደራሽ ምግብ እና መጠለያ ማቅረብ የግድ ብሏል፡፡ በዚህ መሠረትም የዞኑ አደጋ ስጋት አመራር፣ ከሌሎች የፌዴራል እና የክልሉ የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን፣ እነዚህ ወገኖች አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ለአብነት ያህል፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንን ዋቢ አድርጎ ከትናንት በስቲያ ባሰራጨው መረጃ መሠረት፤ የፌደራል መንግሥት በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በኩል ከሦስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች 520 ኩንታል ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እርዳታ አቅርቧል፡፡

ከዚህም ባሻገር አንዱ ጥቅል ለአምስት ሰው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል በድምሩ 100 ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ጥቅል ለእነዚህ ወገኖች እንዲደርስ አድርጓል፡፡ 100 የመጠለያ ድንኳኖችም ተተክለዋል፡፡ በእነዚህ እና መሰል ድጋፍም የፌዴራሉ መንግሥት በኮሚሽኑ አማካኝነት በጥቅሉ አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ ችሏል፡፡

በዚህ መልኩ በፌዴራሉ መንግሥት ከሚቀርበው ድጋፍ ባሻገር፣ የክልሉ መንግሥት፣ የዞኑ አስተዳደር፣ ወረዳው እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን እያደረጉ ይገኛል፡፡ ለአብነትም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትናንትናው እለት ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ የብር እና የቁሳቁስ የሰብዓዊ ድጋፍ ወደቦታው ልኳል፡፡

ይሁን እንጂ ጉዳቱ ከሀብት ውድመት ባሻገር ከፍ ያለ ሰብዓዊ እና ሥነልቦናዊ ብሎም ማኅበራዊ ቀውስ ያደረሰ እንደመሆኑ፤ እነዚህን ወገኖች ካጋጠማቸው ችግር እንዲያገግሙና እንዲወጡ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ የዜጎችን ተሳትፎና ድጋፍ ይፈልጋል፡፡

ካለው ነባራዊ ሁኔታ አካያ የሕይወት አድን ተግባሩ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በሕይወት የተረፉትን የማሳከም፣ የተፈናቀሉትን የመደገፍና አለፍ ሲልም መልሶ የማቋቋም፤ ችግሩ ከፍ ያለ ማኅበራዊና ሥነልቡናዊ ጫናና ቀውስን ያሳደረ እንደመሆኑም ኅብረተሰቡ ከዚህ ጫና መውጣት የሚችልበትን ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ፤… ከሁሉም ዜጎች የሚጠበቅ ሰብዓዊ ኃላፊነት ነው፡፡

ዛሬ ላይ እነዚህን ወገኖች ለማገዝ (በነፍስ አድን ቡድንም ይሁን በሰብዓዊ ድጋፍ) ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እንዲሁም ከአጎራባች ክልሎች እና ዞኖች የተውጣጡ ባለሙያዎች በስፍራው በመገኘት የሚቻላቸውን እያደረጉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ፣ የነፍስ አድን ሥራውም ሆነ የሰብዓዊ ድጋፍ ተግባሩ ከፍ ያለ አቅምና ትብብርን የሚጠይቅ እንደመሆኑ፤ ሁሉም ዜጋ ይሄን ተገንዝቦ የኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ወገኖችን ከደረሰባቸው ዘርፈ ብዙ ሰቆቃ ለመታደግ ሰብዓዊነቱን ሊገልጽላቸው ይገባል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን አንድም በስፍራው ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊው የጥንቃቄ ሥራ ሊከናወን እና ይሄንኑ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ይገባል፡፡ በሌላ በኩል፣ በሌሎች አካባቢዎችም መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ ቀድሞ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በመለየት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ተግባርን መፈጸም፤ ከተከሰተም ፈጥኖ ችግሩን መቆጣጠርና ፈጣን የአደጋ ጊዜ ምላሽ መስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ይጠበቃል!

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You