የቃላት መርፌ

ቃላት መርፌ ናቸው። ቃላት ክር ናቸው። ቃላት ጨርቅና የመድኃኒት ጠብታም ናቸው። ሁሉም ነገር የሚጀምረውም ከቃል ነው። እኛ የሰው ልጆችም ብንሆን…በሚታየውም ሆነ በማይታየው ዓለም ውስጥ ቃላት እምቅ የስሜትና የመንፈስ ንጥረ አካላት ናቸው። ሰማይና ምድር እንኳን ያለ አንዳችም ካስማ ለመቆም የቻሉት በቃል ነው። ቃል ያክማል፣ ያድናል፣ ይገድላል። ደግሞም ያቆማል፣ ያስኬዳል፣ ይጥላል። ይረግማል ይመርቃል፣ ይሠራል ያጠፋል። ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ቃላት የሚያይሉበትና መግነጢሳዊ እሳተ ጎሞራ የሚሆኑበት ሌላ የተለየ ነገርም አለ።

ይኸውም የቃል መርፌ የሆነው ግጥማዊ የቃላት ዓለም ነው። “ከእንጨት መርጦ ለታቦት፤ ከሰው መርጦ ለሹመት” እንዲሉ ከቃላትም ተመርጦ ለግጥም ቤት ይውላሉ። እናም ከቃል በላይ የሆነው ቃል ግጥም ነው። በግጥም ቃላት ይቀደዳሉ። ቃላት ይሰፋሉ። ክርና መርፌ ተገናኝቶ….እንደ ጥጥ ይፈተላል። እንደ እንዝርት ይሾራል። እንደ ድውር ይደወራል። እየተጠለፈ ይገመዳል። ጥለት ነውናም ይቋጫል። በስተመጨረሻም እንደ ጋቢ ይደረባል። እንደ ሸማ ይለበሳል። ለዚህ ሁሉ ነገርም ግጥም ዘለዓለማዊ የነጻነት ዓለም መሆኑ ነው። የቋንቋ ሰዋሰው ያለጭንቅ እንደ ኬሻ ተነጥፎ ፍልስፍና አዘል ውበት ይፈስበታል። በምናባዊ አዲስ ቀለም ያልታየውን ያሳያል። በቃላት መርፌ የሚቆም ጥልቅ የውበት ሰገነት ነው። ነፃነቱም ሁሉ ውበትን ለመፍጠር እንጂ ውበትን ለመግደል አይደለም።

“የቃላት መርፌ” የሚለው አርዕስት አስቀድሞ ለብቻው ምን ሊነግረን ይችላል? የገባን ነገር እንዳለ ሆኖ የግጥምን ባህሪም ያመለክታል። መርፌ በዋናነትም ሁለት ዓይነት ናቸው፤ የሚሰፋ መርፌ እና የመድኃኒት ጠብታ የያዘ መርፌ ሊሆን ይችላል። የመጀመሪያው በባህሪው የተቀደደን ይሰፋል። ስፌቱም በግልጽ የሚታይ የክር መስመር ይኖረዋል። በዚህ ዓይነቱ ግጥም ውስጥም በባለመስመሩ ስንኞች ውስጥ ያለውን መልዕክትና የግጥም ሃሳብ በቀጥታ ፍቺ የምናገኝበት ነው። ምንም ዓይነት ፍካሬያዊ ትርጓሜ የለውም። ሸማኔው ገጣሚ ግጥሙን ያቀረበው በግልጽና ሁሉም በሚያውቃቸው የቃላት ክሮች በመሆኑ ክሩን ለማወቅ የተለየ ዕውቀት አያስፈልገውም። ሁለተኛው የቃላት መርፌ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ልክ እንደ ሐኪም መርፌ ያለ ነው። ስለመርፌው እንጂ መርፌው በውስጡ ስለያዘው መድኃኒት ለማወቅ ጠለቅ ያለ ዕውቀትን ይሻል።

ገጣሚው አብዝቶ ከተራቀቀበት ደግሞ ከቀማሪው በስተቀር ባለሙያው ሐኪም እንኳን የመድኃኒቱን ሳይንሳዊ ቀመር እንደማያውቀው ሁሉ ሊሆን ይችላል። ግጥሙ ቅኔ አዘል የቃላት መርፌ ይሆናል። በግላጭ የሚታየውን ሰሙን እንጂ ቅኔውን ማንም አይደርስበት ይሆናል። የሚስጥራዊነቱ ከጡዘቱ ሲደርስ ደግሞ በጊዜው ገጣሚው ብቻ የሚያውቀው እንደ ትንቢታዊ ያሉ ግጥሞችን ለማንሳት እንችላለን።

ግጥም የቃላት ግጥምጥምና ተራ ግጥም አይደለም። ገጣሚስ ማነው? ስንኞችን እየደረደረ ቃላትና ፊደላትን አመሳስሎ የገጠገጠ ሁሉ ገጣሚ አይደለም። እምቅ የቃላት ሀብት ስላለው ብቻም በቃላት ኳኳታ ገጣሚ አይኮንም። ግጥምን ስለወደዱ አሊያም ለስሜታችን ቅርብ ስለሆነም ገጣሚነት አይቀልም። ገጣሚ ማለት በቃላት ሀብት ተከቦ፣ በስሜት ባህር ጠልቆ፣ በዓይነ ህሊና ተመልክቶ፣ በጠቅላላ ዕውቀትና በአዕምሮ መጥቆ፣ ዓለምና ሕይወትን ተረድቶ የቃላት ፈጣሪ የመሆን ድምር ውጤት ነው። ገጣሚ ማለት የቃላትን መርፌ ጨብጦ ምኑ ላይ ወግቶ ምን መስጠት እንዳለበት የሚያውቅ ነው። ተሰጥኦ ካለ፤ ፍላጎት ተሰጥኦን ያበቅላልና በዚሁ ላይ እኚህን ማከል የግድ ነው። ስለ ግጥም በቂ ዕውቀት ሊኖር ያስፈልጋል። በትንሹ ቤት መድፋት፣ ቤት መምታት፣ የግጥም ቤት፣ የግጥም ዜማ፣ ቀለማትንና የመሳሰሉት መሠረታዊ ናቸው። የቃላት ምጣኔ፣ ቅኔ ሰምና ወርቅ፣ ምጸታዊና ዘይቤያዊ ቃላት ለሚሉት እንግዳ ሆነን ገጣሚነት አይኖርም።

ሥነ ግጥምና ኪነ ጥበብ… በቃላት መጠን፣ በቁጥርና በግዝፈት ግጥም ከአብዛኛዎቹ ትንሽና ታናሽ መስሎ ቢታይም፤ ግጥም ግን የአብዛኛዎቹ አባት ነው። አንዱን ከአንዱ ራሱን ከሌላው በማቆራኘት ደረጃ ወደር የለውም። ብዙ የኪነ ጥበብ ሥራዎችም የቆሙት በግጥም መሠረት ላይ ነው። ከነጭራሹ ያለግጥም እስትንፋስ አልባ ሙት መስለው የሚታዩም አሉ። ሙዚቃን ያለግጥም ለማሰብ ፈጽሞ አይቻልም። ለሙዚቃ ህልውና ወሳኝ የሆኑ ሁለት ነገሮች ግጥምና ዜማ ናቸው። ከሁለቱ መሀከልም የሙዚቃ የደም ዝውውር የሚካሄደው በግጥሙ ውስጥ ነው። ግጥም ከሌለ ደምም፣ ነብስም አይኖረውምና ሙት ነው እንደማለት ነው። የኛ የኢትዮጵያውያን ብቻ የሆኑት ሽለላ፣ ፉከራና ቀረርቶ የተገነቡት በግጥም ነው። ቃለ ተውኔት፣ ትውፊታዊ ቲያትሮች፣ በላ ልበልሃ፣ እንካ ሰላምቲያ እና መሰሎችም የግጥም ምንደኞች ናቸው።

በሥነ ጽሑፉ ውስጥም ሆነ በሙዚቃው ውስጥ ያሉት ሁለቱም ግጥም ቢሆኑም ልዩነት ግን አላቸው። ሥነ ጽሑፋዊ ግጥም እጅግ እምቅና በቅኔ ሰም ወርቅ የተድቦለቦለ የቃላት ቦንብ ማለት ነው። ሲደመጡ እንግዳና ጠጣርነት ይገዝፍባቸዋል። ኃይላቸው እንደመብረቅ የሚያስገመግምና አንዳንዴም የሚያስደነግጡ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱ ቃላት ለሥነ ጽሑፋዊ ግጥም ውበትና ግርማ ሞገስን የሚያጎናጽፉ ናቸው። ነገር ግን እኚህን በሙዚቃ ውስጥ መስማት ኮረታማ መንገድን በባዶ እግር እንደመሄድ ይሆናል። የሙዚቃ ጣዕሙ መልዕክቱ በቶሎ ከአዕምሮና ልብ ጋር ተዋህዶ ስሜትን መፍጠሩ ነው። “ይህ ደግሞ ምን ማለት ይሆን…” እያለ አድማጭ ትርጉሙን ፍለጋ መቃዠት የለብንም። ለሙዚቃ ሁሉም ሰው ሊረዳቸው የሚገባ ቀለል ያሉና ለዜማ አመቺ ቃላት መሆን አለባቸው። ቅኔም ሆነ ወጣ ያሉ ቃላትን አንጠቀምም ማለት አይደለም። ነገር ግን አመጣጥኖና በማይጎረብጥ መልኩ መጠቀሙ ለሙዚቃው ውበትን ይጨምራል። ከረር ካሉ ቃላት ይልቅም ለስለስ ያሉ ሰዋሰዋዊ ዘይቤያዎችን መጠቀም የተሻለ ነው።

ግጥም ድሮና ዘንድሮ…ግጥም በአምናና ካችምና በዘንድሮና በከርሞ መሀከል የሚያረጅ የሚሻግት ማንነት የለውም። እንደየጊዜው ክረምትና በጋ ቢፈራረቅበትም ሁሌም ግን ትኩስና የማይቀዘቅዝ ነው። ይሁንና ነፃነቱን በመጠቀም እንደየዘመናቱ የተቀላቀሉበት ነገሮች መኖሩ አልቀረም። የሰው ልጆችን ዕድሜ የያዘው ግጥም በተለይ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ የተካተቱበት አዳዲስ ነገሮችም አሉት። ለአብነትም ቀድሞ በነበሩት የግጥም ቤቶች ውስጥ “የፀጋዬ ቤት” የሚል ሌላ አንድ መጨመሩ ነው። የግጥም ቤቱ ዓይነት በስምንት ቀለማት የተዋቀረ አዲስ የግጥም ዓይነት ነው። ሎሬት ፀጋዬ ገ/ መድህን በግጥም መቅረዝ ላይ ይህን ታላቅ አበርክቶ በአበባ መልክ አኑሮት አልፏል። በአንድ ግጥም ውስጥ በፊደላት ቤት መድፋት፣ በቃላት ቤት መምታት የሚሉት ነገሮች ከወዳኞቹ የግጥም መሠረታዊያን መሀከል ናቸው። ግጥም ቤት ይመታ ዘንድ ከስንኞቹ የመጨረሻ ቃላት፣ ከቃላቱም የመጨረሻዎቹ ፊደላት መመሳሰል አለባቸው የሚለው ሕግ አሁን አሁን ላላ ብሏል። ምክንያቱ ደግሞ “በግጥም ቤት ለመምታት የግዴታ ቤት በመድፋት ብቻ ሳይሆን በዜማም ቤት መምታት ይቻላል” የሚል ነው። ይህም ማለት እንግዲህ ለምሳሌ ግጥሙ አራት ስንኞች ያሉትና የመጀመሪያው ስንኝ ቤት መድፊያም “ሮ” ብትሆን ቀጣዮቹ ሦስት ፊደላትም “ቶ፣ ኮ፣ ዞ” ወይንም “ሮ” ሊሆኑ ይችላሉ። ሳድስን ከሳድስ፣ ግዕዝም ከግዕዝ እንዲሁም ደግሞ ተመሳሳይ የዜማ ድምጸት ያላቸውን ቃላት ለመጠቀም ይቻላል የሚል ነው።

ከዚህኛው በተለየ መንገድ ደግሞ የአቀራረብ ለውጦችም ተከስተውበታል። አንደኛውም ግጥምን በጃዝ የተሰኘው ቄንጠኛ አቀራረብ ነው። ወጣቱ ክፍል በዚህ የአቀራረብ ስልት የተነደፈም ይመስላል። ገጣሚውም ግጥሙን ማራኪና ተወዳጅ ለማድረግ ከበስተጀርባ በሙዚቃ መሳሪያዎች እየታጀበ ወደ ኦርኬስትራነት ለመለወጥ የቀረው የለም። ከማንበብ ተጣልቶ ከግጥም ለራቀው ምናልባትም ጥሩ ማስታረቂያ መንገድ ይመስላል። አዳዲስ የግጥም ታዳሚያንና አፍቃሪያንንም የማፍራት ኃይል ይኖረዋል። ወትሮም ቢሆን ግጥም የሙዚቃ እናት ነበር። አሁን በመጣው የግጥም በጃዝ ደግሞ ይበልጥ ለሙዚቃ ቅርብ ሆኖ ታይቷል። አብዝቶ መቅረቡ ግን ቀስ በቀስ ሙዚቃው አስምጦ እንዳያስቀረው የርቀት ገደብ ያስፈልገዋል። ክፋት ባይኖረውም የበዛ ነገር ሁሉ አንዱን ማሳነሱ አይቀርምና የኋላ እንደማስቲሽ ተጣብቆ አለቅ፣ አልላቀቅ እንዳይሉ ነው ስጋቱ። ይህን መንገድ ብቻ ወደን ካለ እርሱ አልታይ ካለንም የመጻሕፍቱ ቤት መራቆትና ኦና መሆንም ይመጣል። ስለዚህም ሁሉንም እየመጠኑ ነው መደቆስ።

በግጥም ቤት ውስጥ አስፈሪ ጥላ እያጠላባቸው እንደ አዕዋፋት እየበረሩ ወደ በረሀው እየተሰደዱ ያሉ ነገሮች የሉም አንልም። በቀድሞዋ ኢትዮጵያ ሰማይና ምድር ላይ ሲበሩ የነበሩ ሥነቃላዊ ግጥሞች ዛሬ ከወዴት አሉ? ምናልባትም በየመጻሕፍቱ ውስጥ ታጭቀው ይገኙ ይሆናል። የቃሉ ትርጓሜ እንደሚያመላክተን ከትውልድ ትውልድ በቃል ሲተላለፉ የሚኖሩና የነበሩ ግጥሞች ናቸው። ታዲያ እኛስ ካለፉት ተቀብለን ለሚመጣው ለማስተላለፍ ያዘጋጀነው ምንስ አለን? ድንገት ያለንስ የትኛውን ነው የምንሰጠው? ልክ እንደ ዱላ ቅብብል የሰጡንን ብቻ? ወይንስ በነበረው ላይ የራሳችንን ጨምረን? ምናልባትም ደግሞ አብዛኛዎቻችን ጋር ያለው ነገር “ግጥም ሲጥም፤ እንደ ዶሮ ቅልጥም” የሚለው ባዶ ስልቻ ብቻ ይሆናል። ግጥም ከሞተ ሟቹ ግጥም ብቻውን አይደለም። ምሰሶው ወድቆ ግርግዳና ጣራው፣ ክዳንና ሳሩ ለብቻቸው የሚቆሙበት ቤት የለም። የግጥም መጀመሪያም ማኅበረሰቡ እንጂ የትኛውም ገጣሚ አልነበረም። ዛሬ ላይ ከማኅበረሰቡ ጉያ እንደ ጢስ እየተነኑና እንደ ንብ እየተመሙ የገጣሚያኑን ብዕር እንደ ቀፎ ወረው ታጭቀውበት ቆይተዋል። እየከፋም ሲሄድ ግጥም አዋቂ ብቻ ሳይሆን ሰሚም እየጠፋ የግጥም አፍቃሪ ያለህ ተብሏል። ባለሙያዎቹም ቢሆኑ ይህን ችግር መንግሎ ለመጣል ታግለዋል ለማለት ይከብዳል። ስለግጥም የሚያፋጩ ርዕሰ ጉዳዮች እየተነሱ አይወራባቸውም። በየሚዲያው ግጥም ካልሆነ በስተቀር ስለ ግጥም ግዙፍ ባህረ ሃሳብ ሲነሳ አይስተዋልም። ጥንታዊ እንደመሆኑ አዳዲስ ጥናትና ምርምሮች ብቅ አይሉም።

በገጣሚ ተጀምሮ በገጣሚ የሚያልቅ የግጥም ውበት የለም። የአንድ ግጥም ግማሽ ውበት የሚገኘው በአንባቢው ዘንድ ነው። አንድ ተመሳሳይ ግጥምን ባነበቡ ሁለት ሰዎች መሀከል ግጥሙን በእኩል ላንወደው እንችላለን። ከዕለታት በአንዱ ቀን እንዲህ ገጠመኝ። በአንድ የጥበብ ዝግጅት ላይ ነበር…“ቀጣዩን ጭውውት አቅራቢዎች ዝግጁ እስኪሆኑ ድረስ እስከዚያ አንዲት ግጥም ላቅርብላችሁ” በማለት መድረክ አጋፋሪው ለማንበብ ጀመረ። “አይ መርካቶ!” አለ። የማን ግጥም እንደሆነ ግን አልተናገረም። ደህና ለማንበብ ጀምሮም ከአራተኛው ስንኝ በኋላ ፍሬኑን እንደበጠሰ መኪና ስንኝ ከስንኙ፣ ቃሉን ከቃሉ ጋር እያተራመሰ ቀጠለ። ድምጸቱም ግራና ቀኝ ይዋዥቃል። አጠገቤ ተቀምጦ የነበረው ጓደኛዬ ከዚህ ቀደም በገጣሚው በሎሬት ፀጋዬ ገ/ መድህን የተነበበውን ይህንኑ “መርካቶ” የተሰኘውን ጣፋጭ ግጥሙን ሲያዳምጥ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ሰምቼው ነበር። ግን የመድረክ አጋፋሪው ግጥም ግራ እያጋባው ወደ ጆሮ ግንዴ ተጠግቶ “ይህን ግጥም ግን አውቀዋለሁ ልበል?” ነበር ያለኝ። በርግጥ እየቀለደም አልነበረም። ግጥምን የዝግጅት ጎዶሎ መሸፈኛ ከማድረጋችን በፊት ቢያንስ አስቀድመን ልናነበውና ቀድሞ የነበረውን ሞገስ ልንጠብቅለት ይገባል። ግጥም ቅጽበታዊ ስሜት እንደመሆኑ ሲበላሽም በቅጽበት ስህተት ነው። አንባቢያን ከማንበባችን በፊት ስለግጥሙ ማወቅ፣ ግጥሙንና ገጣሚውን በሚመጥን መንገድ ማቅረብ ይኖርብናል። ከአነባበብ ጉድለት ውበት ይጠፋል። ከቆንጆ አቀራረብም አዲስ ውበት ይፈጠራል።

አንባቢውም ውበትን በእነዚህ መንገዶቹ ለመፍጠር ይችላል…ድምጻችን እንደ ደረቅ መርፌ ጆሮን እንዳይዋጋ ከድምጻችን ጋር የሚሄድ ዜማ በመፍጠር ማራኪ ማድረግ። ቁጭ ላለው ታዳሚ ቁጭ ተብሎ አይነበብምና ቆሞ ማንበብ። ቆመው ሲያነቡም ያልዘገየም ያልተቅበዘበዘም መጠነኛ እንቅስቃሴ ማሳየት ያስፈልጋል። የፊታችንን ገጽታ የግጥሙን ስሜት ከፊት ላይ ማንጸባረቅ ተመልካቹን የሚስብ ነው። የድምጻችን ከፍታና ዝቅታ፣ ላይና ታች በምንልበት ጊዜ ከዜማ እንዳናፈነግጥ መጠንቀቅ ወሳኝ ነው። ትንፋሽ አወጣጥና አወሳሰድ ግጥሙን የዘነጋ መሆን የለበትም። አስቀድመን ጉሮሯችንን በመጠራረግ ከሳግ የጸዳ ማድረግ ብንችልም ቮካል ተመራጭ ነው። በምናነብበት ቋንቋ ቃላቱን አጥርቶ የመጥራት የአፍ ዳገት ቢኖር የግጥሙን የውበት ለዛ ማደብዘዙ አይቀርም። ግጥም የስንኝ ቋጠሮ ብቻ ሳይሆን የስሜት ቋጠሮም ጭምር ነውና የአድማጩን ስሜት ቋጥሮ ለመያዙ የአንባቢውም ችሎታ ወሳኝ ነገር ነው። ለሰው ብቻ ሳይሆን ለግላችን በምናነብበት ጊዜም የግጥሙ ውበት ጎልቶ እንዲታየን የምናነብበት ስልት ያስፈልገናል። ስናነብ እንደልቦለድ ጽሑፍ መሆን የለበትም። በአንድ ወቅት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበረው አብርሃም ሊንከን በግጥም ፍቅር የተለከፈ ነበር። ሲያነብም ከቤቱ አልጋ ላይ ወጥቶና በጀርባው ተንጋሎ እየጮኸ ነበር የሚያነበው። ገረዶቹን ጨምሮ እየተመለከቱና ያደመጡት ሁሉ እብደት መስሎ እየታያቸው በግራ መጋባት ይጠይቁትም ነበር። እርሱም “የማነበው ግጥም ደስታን የሚሰጠኝ ድምጼን አውጥቼ እንዲህ ሳነበው ነው” ሲል ነበር የሚመልስላቸው።

ስለ ቃላት መርፌ የማንሳታችን የመጨረሻ አንድ ነገር ቢኖር መርፌ ሙያን የሚጠይቅ የትንሽ ክቡር መሆኑ ነው። ትንሽ ነው ግን ደግሞ ለዓይን ከማነሱ ጋር በምንም የማይመጣጠነውን ትልቅ ነገር ይሠራል። ሕክምናን ተምሮ በቅጡ ያላወቀ ደረትን ቀዶ ልብን ለማከም አይነሳም። ሽመናውን የማያውቅ ሸማኔም ለመስፋት ጣቃውን አይቀድም። ሥራ እንደፈታ መነኩሴም ቆብን ቀዶ እንደመስፋት በጨዋታ የምንፈጽመው አይደለም። ግጥም ትልቁ የነፃነት ዓለም ቢሆንም ነፃነቱ በሙያዊ ዕውቀት ያልተደገፈ ከሆነ መጥፊያውን እናፈጥንለታለን። እንግዲህ “አሳን መብላት በብልሃት” እንዲሉ፤ ግጥምም ሙያዊ ነፍስያን የሚሹ ክፍልፍል ብልቶች አሉት። ደግሞም እንደ አሳው እሾሃም ነው። የቃላቱ መርፌ ካላወቁበት የሚያደማና የሚደማ እሾህ ነው። የጠለቀ ዕውቀትና የመጠቀ ብልሃት ያስፈልገዋል። በብዕር የቃላትን መርፌ ለማንሳት የሚነሳ ሁሉ ከሙያው መቅረዝ ላይ ጥበብን ከብልሃት ለማኖር ግድ ይለዋል።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You