ፓርቲዎች ለሕዝቦች አብሮነትና ተጠቃሚነት ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል!

ከሦስት ሺህ ዓመታት የሚልቅ ታሪክ ባለቤት ኢትዮጵያ ከፍ ብላ በታሪክም፣ በኪነሕንጻና ኪነጥበብም፣ በባህልና እሴትም፣… ለመገለጧ ምክንያት የሆኑት ኢትዮጵያውያን፣ በዚህ በሺህ ዘመናት ጉዟቸው ውስጥ ከፍ ያለ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ብሎም ጠንካራ ሥነልቦናዊ ጥምረትን ፈጥረዋል፡፡ ይሄ ከፍ ያለው ጥምረትም ነው ኢትዮጵያን በሁሉም መስክና መልክ ክፍ ብላ በነጻነት ዘመናትን እንድትሻገር ያስቻላት፡፡

ይሁን እንጂ በአንድም በሌላም ምክንያት፣ በተለይም በየዘመኑ የሚነሱ ፖለቲካ አዘል ጥያቄዎችና ፖለቲከኞች አሠራር ሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ እንከኖች መከሰታቸው አልቀረም፡፡ እነዚህ ጥያቆዎች እና ፖለቲካዊ ክስተቶችም፣ ኢትዮጵያውያን በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ውስጥ ቅሬታን፣ አለፍ ሲልም መከፋፈልን የሚፈጥሩ ግጭቶችን ሲያስከትሉ ኖረዋል፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ከሚለያዩዋቸው ይልቅ በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሯቸው አያሌ ጉዳዮች ባለቤት እንደመሆናቸው፣ በየጊዜው ለሚነሱ ከፋፋይ ምክንያቶች ጆሮ ሳይሰጡ፣ ሥርዓቶችን በሚመሩ ግለሰቦች ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችና ግጭቶች ሳያቃቅሯቸው፣ ሰላምና ፍቅርን አስበልጠው፣ እና ከመለያየት ይልቅ አንድነትን መርጠው ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡

ይሄ ማለት ግን ዛሬም የቂምና ቁርሾ መንገድን፣ የመለያየትና የመከፋፈል ስሌትን ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት (ግለሰቦችና ቡድኖች) የሉም ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ ግጭቶችን እንደ ቂም ማባባሻ አድርገው በዜጎች መካከል መቃቃር እንዲነግስ የሚተጉ የመኖራቸውን ያህል፤ ራሳቸውን በዘመናት ሂደት ኢትዮጵያን ጠብቀው ያኖሩ የሀገር ጠባቂዎች አድርገው በመሳል ሌሎች የሚሏቸው አካላት የሀገር ባለቤትነት ስሜት እንዳይሰማቸው ለማድረግ የሚጥሩ አካላትም (ግለሰቦችና ቡድኖች) አሉ፡፡

በተመሳሳይ መልኩ፣ የኢትዮጵያ ከፍታ እና ብልጽግና የሚያማቸው የውጭና የውስጥ ኃይሎች ተናብበው ሲሠሩበት በቆዩት ኢትዮጵያን ከፋፍሎ የማሳነስ ስልት እሳቤ ውስጥ ተጠምዶ ለሕዝብ ጥቅም ቆሜያለሁ በሚል ካባ ሲሠራ የኖረውን እና በሕዝቦች ክንድ የከሸፈን አካሄድ ዛሬም ድረስ በልባቸው ይዘው ኢትዮጵያን በማሳነስ ውስጥ የራሳቸውን ሕልውና ለመገንባት የሚጥሩ ኃይሎችም (ቡድኖችና ግለሰቦች) አሉ፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ብዝሃነቷ ተጋርዶባቸው በአንድ መልክ እንድትሳል የሚጥሩ ኃይሎችም እንዲሁ አልታጡም፡፡

እነዚህ ሁሉ እሳቤዎች ታዲያ ኢትዮጵያን የሚያሳንሱ፣ ኢትዮጵያውያንም ተከፋፍለው አቅም እንዲያጡ የሚያደርጉ እንጂ፤ ኢትዮጵያውያን በኅብር በደመቀው አንድነታቸው ታግዘው የኅብረት ክንዳቸውን፣ እውቀትና አቅማቸውን ተጠቅመው ኢትዮጵያን እንዲያበለጽጉና ከፍ እንዲያደርጉ፣ ለራሳቸውም ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነትንና ልዕልናን እንዲጎናጸፉ የሚያደርጓቸው አይደሉም፡፡

ኢትዮጵያውያን በመከፋፈል ውስጥ አይጠነክሩም፤ ኢትዮጵያውያን በመጠላላትና በቂም በቀል ውስጥ ኅብረትና አንድነታቸውን፣ ፍቅርና መተሳሰባቸውን አይገነቡም፡፡ ይሄን እውነት ደግሞ አይደሉም ኢትዮጵያውያን (ሕዝቡ)፣ አያሌ ዘመናትን ሊያጋጯቸውና ሊከፋፍሏቸው የጣሩ ኃይሎችም በወጉ ይገነዘቡታል፡፡ ለዚህም ነው ሊያጋጩት ሲጥሩ ስለ ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መቆሙ፡፡ ሊያለያዩት ሲታትሩም ለአብሮነቱ ዋጋ መክፈሉ፡፡

ዛሬም ቢሆን ሕዝቡ የሚፈልገው ፖለቲካውም ሆነ ፖለቲከኞች በየዘመናቱ የሚፈጥሩት ችግር ወደ እሱ እንዲራገፍና ዋጋ እንዲከፍልበት ሳይሆን፤ ሁሉም ስለ ሕዝብ ሰላምና ልማት፣ ስለ ሀገር ደህንነትና ልዕልና፣ በጥቅሉም ሕዝቦች በጋራ ኖረው፣ በጋራ ሠርተውና በልጽገው በጋራ ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሠራ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ መንግሥት ዘመናትን ሲንከባለሉ የመጡና ለሕዝቦች ሰላም፣ ልማትና አብሮነት እንቅፋት እየሆኑ ያሉ ችግሮች ጠርተው እንዲፈቱ ለማስቻል ዜጎች ቁጭ ብለው የሚመክሩበትን አውድ አመቻችቶ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለሕዝቦች የልማትና የመልካም አስተዳደር እውን መሆን ይበጃሉ ያላቸውን ጉዳዮች የሕዝቦችን ጥያቄ ማዕከል አድርጎ መልስ እየሰጠ ይገኛል፡፡ አሁንም ችግሮችን እየለየ መፍትሄ መስጠት የሚያስችሉ ርምጃዎችን እየወሰደ ነው፡፡

በዚህ ረገድ እንደ መንግሥት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚበረታቱና ኃላፊነት ወስዶ ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና አብሮነት ይበጃሉ ያላቸውን ሥራዎች መከወን መቻሉም ሊያስመሰግነው የሚገባ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ስር የሰደዱ ችግሮች በመንግሥት ጥረት ብቻ በሚፈለገው ልክ ለፍሬ ይበቃሉ ብሎ አይታመንም፡፡ ይበቃሉ ቢባል እንኳን የተራዘመ ጊዜን መውሰዳቸው የግድ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ጥረት በተቃራኒው የሚቀነቀኑ አፍራሽ፣ ከፋፋይ እና የሕዝቦችን ጥቅም፣ የሀገርንም ሕልውና የዘነጉ አጀንዳዎችን የሚያራምዱ ኃይሎች አሉና፡፡

ታዲያ ይሄን አጀንዳ ከመቀልበስ አኳያ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ፓርቲዎች የሕዝብን ሃሳብና ፍላጎት ይዘው የሚታገሉ ከመሆናቸው አንጻር፤ አካሄድና እሳቤያቸው ሁሉ እነዚህን አፍራሽ እሳቤዎች በልካቸው የተገነዘበ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡

በመሆኑም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትኩረትና ሥራ፣ የሕዝቦችን ሰላምና አብሮነት የሚያጸና፣ በቀጣይ አስተዳድራታለሁ ስለሚሏት ሀገር ክብርና ሉዓላዊነት፣ እንዲሁም እመራዋለሁ ስለሚሉት ሕዝብ ጥቅልና ክብር፣ በጥቅሉም ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ሁለንተናዊ ልዕልናና ብልጽግና እውን መሆን ላይ ሊሆን ያስፈልጋል!

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You