የቡና ቀጥታ ግብይት አማራጩ ውጤቶች

ከ2011 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ወደ ውጭ ከተላከ ቡና የተገኘ የውጭ ምንዛሪ (በዶላር)

ኢትዮጵያ የቡና መገኛና ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና የምታመርት ብትሆንም፣ ወደ ውጭ የምትልከው ቡና በመጠንም ሆነ በሚያስገኘው ገቢ አጥጋቢ እንዳልሆነ በስፋት ይገለጻል፡፡ ለዚህም የቡና ምርትና ምርታማነት አለመሻሻል፣ የጥራት ሁኔታና የግብይት ሥርዓቱ የተንዛዛ መሆን በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው፡፡

እነዚህን የዘርፉ ማነቆ የተባሉ ችግሮችን ለመፍታትም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ተቋማዊ ሪፎርም ከማድረግ ጀምሮ ለዘርፉ ዕድገት ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም እየተመዘገበ ያለው አበረታች ውጤት ቡና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት በኩል ተጠቃሽ ሆኖ እንዲቀጥል በሚያስችል ቁመና ላይ እንዲገኝ አድርጓታል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን መረጃ እንዳስታወቀው፤ በግብይት ሂደት ያለውን የተንዛዛ አሰራር በመቅረፍና የተለያዩ የግብይት አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ ዘርፉ አበረታች ውጤት እንዲያስመዘግብ ማድረግ ተችሏል፡፡ ባለስልጣኑ ተግባራዊ ካደረጋቸው የግብይት አማራጮች መካከልም የቀጥታ ገበያ ትስስር አንዱ ሲሆን፤ ይህም አስቀድሞ የነበረውን የተንዛዛ የግብይት ሂደት በማስቀረት አቅራቢውንና ላኪውን በቀጥታ ማገናኘት ያስቻለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የተሻለ የቡና መጠን ለውጭ ገበያ በመላክ የተሻለ ገቢ እያገኘች ነው፡፡ በቀጣይም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም ጥራት ላይ በመሥራት ቡናን በስፋት ለዓለም ገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ ለማምጣት እየተሰራ ነው፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶክተር) እንዳሉት፤ ቀጥታ የገበያ ትስስር የሚባለው የግብይት አማራጭ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ ለውጦች ታይተዋል፡፡ የግብይት አማራጩ በላኪና በአቅራቢ መካከል የሚደረገውን ግንኙነት ከውክልና በማውጣት በቀጥታ እንዲሆን ማድረግ አስችሏል። የግብይት አማራጩ አቅራቢና ላኪው ፊት ለፊት ተገናኝተው ቡናውን አይተውና ለይተው መገበያየት የሚችሉበት ነው፡፡ አዋጭና ተመራጭ በመሆኑም በኤክስፖርት እንዲሁም በገቢ መጠን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት የተገኘው የውጭ ምንዛሪና የተላከው የቡና መጠን ከዚህ ቀደም ሲላክ ከነበረው የቡና መጠንና የገቢ መጠን ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት ነው፡፡ ከዓመታዊ ገቢና ከተላከ የቡና መጠን ባለፈም በየወሩ ወደ ውጭ ገበያ የሚላከው የቡና መጠንና የገቢ መጠንም እንዲጨምርና በየዓመቱ መጨረሻም የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ አስችሏል፡፡ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው የቡና መጠን 90 በመቶ ያህሉ በቀጥታ የገበያ ትስስር የግብይት አማራጭ የተላከ ሲሆን፤ ይህም የግብይት አማራጩ ውጤታማ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ይህ የግብይት አማራጭ በዋናነት የተንዛዛውን የግብይት ሥርዓት እንዲቀንስ በማድረግ፣ የተሻለ መጠንና ጥራት ያለው ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲገባ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ይህን ወደ ማዕከላዊ ገበያ የገባ ቡና በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክም ሰፊ ዕድል ፈጥሯል። በመሆኑም በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም ብቻ ለመጀመሪያ ጊዜ 46 ሺ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ ቀርቧል፡፡ ይህ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተላከው የቡና መጠን ኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ተገኝቶ የማያውቅ የመጀመሪያው ክብረ ወሰን /ሪኮርድ/ ነው፡፡

ወደ ውጭ ገበያ ከተላከው 46 ሺ ቶን ቡና 218 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህ በአንድ ወር የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢም እስካሁን በወር ከተገኘው ገቢ ከፍተኛው መሆን ችሏል፡፡

አጠቃላይ በ2016 በጀት ዓመት ለዓለም ገበያ የቀረበው የቡና መጠን 298 ሺ 500 ቶን ሲሆን፤ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢም አንድ ነጥብ 43 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 50 ሺ ቶን ቡና ጭማሪ ያለውና በገቢም ከፍተኛ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የሃያ በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ሌሎች መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይህ ውጤት የተመዘገበው ደግሞ እንደ ሀገርም እንደ ዓለም አቀፍ ሁኔታም በርካታ ችግሮች ባጋጠሙበት ወቅት መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ቀይ ባህር የተዘጋበት፣ የኮንቴነር እጥረት በስፋት ያጋጠመበት፣ በርካታ የመርከብ ችግሮች የገጠሙበትና የሎጅስቲክስ እጥረት ጎልቶ የወጣበት ወቅት መሆኑን አብራርተዋል። እነዚህን ሁሉ ችግሮች በመቋቋም በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ችግሮችን መፍትሔ በማፈላለግ ማለፍ የተቻለ ሲሆን፤ በተለይም ቀይ ባህር ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ቡና በአውሮፕላን ካርጎ መላክ እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡

አማራጭ ግብይቱ በቂ ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ እንዲገባ ከማድረግ ባለፈ ከፍተኛ ጥራት ያለው የቡና ምርት እንዲቀርብ ትልቅ ድርሻ እንደነበረውም ተጠቅሷል፡፡ በተለይም በነጋዴው እጅ ላይ ያለውን ቡና በወቅቱ ለቡና ገዢ ሀገራት መላክ የሚቻልበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ፤ የግብይት አማራጩ ለሀገር ካስገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ግኝት በላይ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻለ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም አንድ ኪሎ ግራም ቀይ እሸት ቡና ከ10 እስከ 12 ብር ሲሸጥ የነበረ ሲሆን፤ የቀጥታ የገበያ ትስስር የግብይት አማራጭ ተግባራዊ በመደረጉ ምክንያት አንድ ኪሎ ቡና ከ60 እስከ 70 ብር በመሸጥ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆን ችሏል፡፡

ከዚህ ቀደም በተደረገ ዳሰሳ ወደ ውጭ ገበያ ከሚላክ ቡና የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝት አርሶ አደሩ ጋር የሚደርሰው 40 በመቶ ያለው ብቻ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን ከ60 እስከ 80 በመቶ አርሶ አደሩ ኪስ ይገባል፡፡ ይህም ማለት አርሶ አደሩ አንድ ኪሎ ቀይ እሸት ቡና ሲሸጥበት ከነበረው ስድስት ብር ወደ ስልሳና ሰባ ብር መድረሱ ነው፡፡ ይህም በቀጥታ የገበያ ትስስር የግብይት አማራጭ የተገኘ ውጤት ነው፡፡

ከግብይት አማራጮች በተጨማሪ ነባር ገበያዎችን አጠናክሮ በማስቀጠልና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን በማፈላለግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያ ቡና በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተደራሽ ሆኗል፡፡ ከአውሮፓና አሜሪካ በተጨማሪ ወደ መካከለኛው ምስራቅና ሩቅ ምስራቅ /ኤዢያ / ሀገሮችም ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት ተልኳል፡፡

ለአብነትም ቻይና ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በዓመት ከአስር ሺ ቶን ቡና በላይ ገዝታ አታውቅም፡፡ ይሁንና በ2016 በጀት ዓመት 25 ሺ ቶን ቡና በቀጥታ ወደ ቻይና ተልኳል፡፡ ሳውድ አረቢያ ከ55 ሺ ቶን በላይ ኢትዮጵያ ቡናን በቀጥታ ግብይት ተገበያይታለች። የኢትዮጵያን ቡና በከፍተኛ መጠን በመግዛት የሚታወቁት አምስት ሀገራት አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ጃፓንና ሳውድ አረቢያ ናቸው፡፡ በዘንድሮ በጀት ዓመት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና በመውሰድ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ሳውድ አረቢያ ናት፡፡

ኢትዮጵያ ከ60 በላይ ለሆኑ የዓለም ሀገራት ቡና ትልካለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ለዓለም ገበያ እያቀረበች ያለችው ቡና በምርት መጠን እንዲሁም በጥራት የተለየ መሆኑን የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህም የተለያዩ ሀገራት የኢትዮጵያን ቡና የመቀበል ፍላጎት እንዲያሳዩ ምክንያት ከሆኑት መካከል መሆኑ ተመልክቷል፡፡

እነዚህና መሰል መነሻ ምክንያቶች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ቡና በከፍተኛ መጠን ወደ ውጭ ገበያ ተልኮ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በማምጣት የቡና ምርት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አስችለዋል፡፡ ለዚህ ውጤትም የቡና ባለቤት ከሆነው አርሶ አደር ጀምሮ አቅራቢውና ላኪው የአንበሳውን ድርሻ ወስደው በትጋትና በታማኝነት ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ ለተመዘገበው ውጤት ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡

አምራችና አቅራቢው እንዲሁም ላኪው ከሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ውጭ በሆነ መንገድ በቀጥታ ተገናኝተው መገበያየት የሚችሉበት ዕድል በመፈጠሩ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ቀጥታ የገበያ ትስስር የግብይት አማራጭ ከተጀመረበት ከሁለትና ሶስት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ገበያ የምትልከው ቡና በመጠንና በጥራት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን አስታውቀዋል። የሚከተለው ሰንጠረዥም ካለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ወዲህ የቡና ወጪ ንግድ በመጠንና በገቢ እያደገ መምጣቱን ያሳያል፡፡

የግብይት አማራጩ በምርትና ምርታማነት እንዲሁም በጥራት ካስመዘገበው ውጤት ባለፈ የቡናን ጥራት በማስጠበቅ፣ ብክነትን በማስቀረትና የተንዛዙ አሰራሮችን በማስወገድ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ምርትና ምርታማነትና ጥራት ላይ ትኩረት በመስጠት ከነባር ገበያዎች በተጨማሪ አዳዲስ የገበያ ዕድሎች እየመጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህን የገበያ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም በቀጣይ የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡ ለዚህም ባዛርና ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት ቡና ገዢ ሀገራት በቀጥታ ቡና መግዛት እንዲችሉ መሥራትና ከዚህ በበለጠ አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን ማስፋት ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለዓለም ገበያ የቀረበውና ለተገኘው የገቢ መጠን በዘርፉ የተሰራው የሪፎርም ሥራ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በሥራው ሂደት ግን ተግዳሮቶች ገጥመው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ የሎጅስቲክስና ሌሎች ችግሮች በተጨማሪ የኮንትሮ ባንድ ንግድም ፈታኝ ነበር፡፡ እንደ ሀገር ፈታኝ የሆነው የኮንትሮባንድ ንግድ በቡና ንግድ ላይ በስፋት ይስተዋላል፡፡ ባለስልጣኑ ችግሩን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረቶችን አድርጓል፡፡

ለአብነትም የቡና ሽኝት አሰራርን ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የታገዘና የተደገፈ ሥርዓትን እንዲከተል ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም ሲባል ቡና ከወረዳ ጀምሮ ሲሸኝ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በመሆኑ ከየት ተነስቶ የት መግባት እንዳለበት በተዘረጋው ሥርዓት ክትትል ይደረጋል፡፡ ስለዚህ ከሞላ ጎደል በቡና ንግድ ላይ የሚስተዋለውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመቀነስና ለመከላከል ተሞክሯል፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉትንም ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ባለስልጣኑ በሻይ ልማትና ግብይት ላይም ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ቡና ላይ የተገኘውን ተሞክሮ ወደ ሻይና ቅመማ ቅመም ማስፋት ተገቢ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ለቅመማ ቅመም ምርት ስትራቴጂ መዘጋጀቱን አመልክተው፣ የቅመማ ቅመም ግብይትና ጥራት ቁጥጥር አሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ዓመት ከፍተኛ መጠን ያለው የቅመማ ቅመም ምርት ወደ ዓለም ገበያ ማስገባት የሚቻልበት ሰፊ ዕድል እንዳለም ገልጸው፣ ለዚህም በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

እስካሁን ድረስ ከአምስት ሺ ሄክታር ማሳ ያልበለጠው የሻይ ምርት ልማት የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ30 ሺ ሄክታር በላይ ማሳ በሻይ ምርት መሸፈን እንደቻለ አመልክተዋል፡፡ የሻይ ምርት በከፍተኛ መጠን እያደገና የማምረት አቅምም እየሰፋ መምጣቱን ተናግረው፣ በቀጣይ ሶስት ዓመታት እንደ ቡና ሁሉ የሻይ ምርት መጠንም ከፍ እንደሚል ጠቁመዋል፡፡ ይህን ሁሉ ተከትሎም የዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ግኝትም የተሻለ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You