እናቴ የሆነ ነገር ለማዘዝ ስታስብ የመማሪያ መጽሐፍ ወይም ደብተር ይዤ ታየኛለች፡፡ ‹‹አይ ይሄን ወረቀት!›› ትላለች፡፡ በተለይም የግብርና ሥራ እንዲሰራ ታዝዤ ‹‹እያጠናሁ ነው›› ካልኩ ‹‹የሚበላውን ሥራ ትተህ የማይበላ ወረቀት ታቀፍ!›› እያለች ቆጣ ትላለች፡፡ የጎረቤት ሰዎች ደግሞ ‹‹ተይው እንጂ! እሱ እኮ ተምሮ ነገ አንቀባሮ ይይዝሻል›› ሲሏት ‹‹ኡኡቴ! ወረቀት አይበላ!›› ትላለች፡፡
እናቴ ‹‹ወረቀት አይበላ!›› የምትለው ስላልተማረች ነው፡፡ ወረቀት ለእሷ ከግዑዝ አካልነቱ ያለፈ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ ዓለም እዚህ የደረሰችው በወረቀት (ትምህርት) መሆኑን ልትረዳ አትችልም፡፡ ሲጀመር ዓለም ማለት ለእርሷ በጣም ከሰፋ እስከ ወረዳችን እና ዞን ድረስ ያለው ነው፡፡ ኑሮ ማለትም እያረሱ መብላት ነው፡፡ ሥልጣኔ ማለትም ከአንዳንድ የፋብሪካ ውጤት የቤት ዕቃዎች (ለዚያውም አትወዳቸውም) እና ከእጅ ስልክ (ለዚያውም ቅርብ ጊዜ) ያለፈ አይደለም፡፡ እናም በልጅነቴ ደጋግማ ‹‹ወረቀት አይበላ!›› ትለኝ ነበር፡፡ የሚበላ ማለት ለእርሷ በዓይን የሚታየው የግብርና ምርት ነው፡፡
በወቅቱ ካለመማር እና ካለማወቅ የመጣ ነው ብየ ያለፍኩት ይህ የእናቴ ንግግር ዛሬ ግን ትንቢት መስሎ እየታየኝ ነው፡፡ በእርግጥ አይነቱ ይለያያል፡፡ አሁን ላይ እናቴ እንዳለችው ወረቀት የማይበላ ሆኗል፤ ችግሩ ግን ወረቀት የማይበላ የሆነው ወረቀት ብቻ ሆኖ እንዲቀር ስላደረግነው ነው፡፡ የወረቀቱ ንድፈ ሃሳቦች ወደ መሬት የማይወርዱ መሆናቸው ነው፡፡ የትምህርት ደረጃዎች ቢደራረቡም የወረቀት ክምር ብቻ መሆናቸው ነው። ወደ ሥልጣኔ ሊወስዱን አልቻሉም፡፡ ምርታማ ሊያደርጉን አልቻሉም፡፡ እንዲያውም ያልተማረ የሚባለው ማህበረሰብ ከሚሠራቸው ሥራዎች በታች እየሆኑ ነው፡፡ ዛሬ በድህነት የሚሳቅበትና የሚቀለድበት የተማረ የሚባለው መደብ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ድህነቱ ብቻ አይደለም ችግሩ፤ የተማረ የሚባለው የሃሳብም ድሃ በመሆኑ ነው ሀገሪቱ ከትርምስ አልወጣ ያለችው፡፡ አሁን ላይ ‹‹ያልተማሩ›› ይባሉ የነበሩት ወገኖች ሀገር ሲተራመስ እያዩ ‹‹መማር እንዲህ ከሆነ…›› እያሉ ነው፡፡
ከዚህ በፊት እንዳልነው፤ ሰኔ እና ሀምሌ በመጣ ቁጥር የተመራቂ ተማሪዎችን ብዛት እናያለን፡፡ የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች በፎቶና በድግስ ያጥለቀልቁታል፡፡ ምን ምርምር እንደሠሩ ግን አይታወቅም፡፡ የታቀፉት ወረቀቱን ብቻ ነው፡፡ የማይበላ ወረቀት ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተመራቂ ከዚህ ወር ጀምሮ ሥራ ፍለጋ ይኳትናል። ትምህርቱ ተግባር ተኮር ስላልነበረ ወረቀቱን የፀሐይ መከላከያ አድርጎ ሥራ ይፈልጋል፡፡ በመጨረሻም ምን ይሆናል? በልማዳዊ መንገድ ‹‹ያልተማሩ›› ያልናቸው አያት ቅድመ አያቶቻችን የፈጠሩትን ሥራ ይሠራል ማለት ነው፡፡ በዚያ ልማዳዊ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎችም ኑሮን በማሸነፍ ውጤታማ ሆነዋል፡፡
ጎበዝ ተማሪ የምባል ነበርኩ፡፡ በወቅቱ አስፈሪ የነበረውን የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ስወስድ እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ ስጋት አልነበረብንም፡፡ በጥሩ ውጤት ወደ መሰናዶ አለፍኩ፡፡ አንዳንድ ውጤት ያልመጣላቸው የአካባቢያችን ልጆች ተሸማቀቁ፡፡ ሕይወት ይቀጥላልና በየፍጭርጭራቸው መፍጨርጨር ጀመሩ፡፡ ምን አደረጉ? ሥራ ሳይመርጡ መሥራት ጀመሩ፡፡ ከትንሽ ነገር ተነስተው ትልቅ ነገር ላይ ደረሱ፡፡ ዛሬ በአካባቢው የሚሸማቀቁት እነርሱ ሳይሆኑ እኛ ነን፡፡ የአካባቢው ሰው ‹‹መኪና አልገዛህም? ቤት የለህም?›› እያለ ይጠይቀናል። ምክንያቱም እነዚያ ያኔ በወረቀት የበለጥናቸው ልጆች ቤትና መኪና አላቸው፡፡
የትምህርት ሥርዓታችን ተግባር ተኮር አይደለም። ወደ ሥራ ፈጠራ አይወስድም፡፡ እንኳን ወደ ሥራ ፈጠራና ቴክኖሎጂ መውሰድ ይቀርና ንድፈ ሃሳቡን እንኳን በሥርዓት የሚያሰርጽ አይደለም፡፡ እውቀት (የተሸመደደ ነገር) ላይ እንጂ አመለካከት (attitude) ላይ ትኩረት አይደረግም፡፡ በራስ ማሰብ፣ በራስ ማሰላሰልና የራስን አተያይ ለማዳበር የሚያግዝ አይደለም፡፡
በሌላ በኩል ከዘመኑ ጋር እየሄድን አይደለም፡፡ አሁን የምንማረው ትምህርት ከዘመነ ኢንተርኔት በፊት በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን በነበረ ልማድ ነው። ተግባር ንድፈ ሃሳብን ቀድሞታል፡፡ መምህሩ በክፍል ውስጥ የሚያስተምረው ትምህርት ዘመኑ ከደረሰበት ጋር ሲነፃፀር ኋላቀር ልማድ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ይሄኛው የኢትዮጵያ ብቻ ችግር ስላልሆነ እንለፈው፡፡
በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስናይ ግን ከተግባር በላይ ወረቀት ላይ ትኩረት እየተደረገ ነው፡፡ ሦስትና አራት ዲግሪ መደራረብ ብቻውን ለውጥ አያመጣም፡፡ የወረቀት ክምር ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ ወደ ተግባር ከቀየሩት አንድ ዲግሪ ሕይወትን ይለውጣል፡፡ የሥራ ሂደቶችና አሠራሮችም ተግባር ተኮር ይሁኑ፡፡
በነገራችን ላይ የሥራ ልማዳችንን ዘመን እና የኑሮ ውድነት ቀይሮታል፡፡ ስንፍና ካልሆነ በስቀተር በዚህ ዘመን ሥራ የሚንቅ አይኖርም፡፡ ኑሮ አስገድዶት የትኛውንም ነገር እየሠራ ነው፡፡ የዘመኑ ሁኔታ ደግሞ ያ ነገር እንደ ነውር እንዳይታይ አድርጎታል፡፡ አሁን ትልቁ ክብር በምንም አይነት ሥራ ይሰማራ ኑሮውን ያሸነፈ ሆኖ መገኘት ነው፡፡
ለምሳሌ፤ ቀደም ባለው ዘመን ሸማኔ አሁን ያለውን ክብር አልነበረውም፤ እንዲያውም እንደ ነውር ሁሉ ይታይ ነበር፡፡ ዛሬ ግን እንደ ሽሮ ሜዳ ሸማኔ የሚከበር የለም፡፡ ከአንድ ባለሦስት ዲግሪ ተቀጣሪ ደሞዝተኛ የሽሮ ሜዳ ነጋዴ ክብር አለው፡፡ ኑሮውን ያሸንፋል፡፡ ከአንዲት ባለሦስት ዲግሪ መምህርት አንዲት የቀጨኔ ሸክላ ሰሪ የተሻለ ገቢ አላት፡፡ ከአንድ የመጀመሪያ ደረጃ መምህር አንድ ጫማ የሚያጸዳ (ሊስትሮ) የተሻለ ገቢ ይኖረው ይሆናል፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው የዘመኑ ዓውድ ሰውን የሚያስከብረው የሚያገኘው ገቢ እንጂ የሥራው አይነት አይደለም፡፡ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ አደገ ወይም ተሻሻለ የሚባለው የደረጃ ዕድገት ሲያገኝ ወይም ደሞዝ ሲጨመርለት ሳይሆን የሆነች ትንሽ ንግድ ነገር ሲጀምር ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ኑሮን ማሸነፍ የሚቻለው በዚያ በኩል ነው፡፡
ይህ ሥልጣኔ ነው፤ በዘመን ሂደት የመጣ መሻሻል ነው። ብዙዎች የማይችሉትን፣ ጥቂት ሰዎች ብቻ የታደሉትን ከጭቃ ሸክላ መሥራትን ማክበር ሥልጣኔ ነው፡፡ ቀጭንነቱ በዓይን እንኳን ለማየት የሚያስቸግረውን ከጥጥ የተሠራ ድር ወደ ልብስነት መቀየር ልናደንቀውና ልንገረምበት የሚገባ ጥበብ እንጂ መጀመሪያውኑም ልንሳለቅበት የሚገባ አልነበረም፡፡
የወረቀት ትምህርታችን እንዲህ አይነት የአባቶቻ ችንንና እናቶቻችንን የጥበብ ሥራዎች ወደ ዘመናዊ መቀየር ሲገባው የዚያው የልማዳዊው አሠራር ጥገኛ ሆኖ ቀረ። የዲግሪ የትምህርት ደረጃ ይዞ ኑሮን ለማሸነፍ ሥርዓተ ትምህርት ከመቀረጹ በፊት የነበሩ ሥራዎችን ለመሥራት ይገደዳል፡፡
በነገራችን ላይ የመማር ዋናው ስኬት ኑሮን ማሸነፍ ብቻ መሆን አልነበረበትም፡፡ ኑሮን ድሮም ቢሆን አራሽ ገበሬን የሚያክል አይኖርም፡፡ ችግሩ ግን መማራችን የገንዛቤ ለውጥ (ሥልጣኔ) አለማምጣቱ ነው፡፡ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ማምጣት እንኳን ባይችል በሰላም መኖር የምንችል ዜጎች እንኳን እንድንሆን አላደረገንም፡፡ ትምህርቱ ወረቀት ብቻ ሆኗል፡፡
ድሮ እንደ ክብር ይታይ የነበረው የዲግሪው ወረቀት ምነው ዛሬ ዋጋ አጣ? የሚለው ነው አሁን ሊያሳስበን የሚገባው፡፡ ምነው ወረቀት ብቻ ሆኖ ቀረ? እንዴት ከወረቀት ወደ ዳቦ እንቀይረው? የተማረ ሥራ ፈጣሪ መሆን ሲገባው እንዴት ያልተማሩት ወደፈጠሩት ሥራ ተመለስን? ትራክተርና ኮምባይነር መፍጠር ቢያቅተን እንዴት በበሬ ከሚያርስ ገበሬ በታች ሆንን? እንዴት በአስተሳሰብ እንኳን መሻል አቃተን?
የወረቀት ዲግሪዎቻችን የሥልጣኔ ግርማ ሞገስ ይኑራቸው!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም