ሀገር የጋራ ናት፡፡ ዜጎች በጋራ የሚያንጿት፤ በጋራ የሚገነቧትና በጋራ የሚያለሟት፡፡ ሀገር የጋራ ቤት ናት፡፡ ስትዘም በጋራ የሚያቃኗት፤ ጉድፏን የሚያነሱላት ፤ አቧራዋን የሚያራግፉላትና ገበናዋን የሚደብቁላት፡፡
ኢትዮጵያውያንም በሀገራቸው በመጣ ቀልድ አያውቁም፡፡ አጥንታቸውን ይከሰክሳሉ፤ ደማቸውን ያፈሳሉ፤ ሕይወታቸን ይገብራሉ፡፡ ሕይወታቸውን ሰውተው ጭምር የሀገራቸውን ዳር ድንበር ያስከብራሉ፤ ሉዓላዊነቷን ያስጠብቃሉ፤ ባዕዳን ወራሪን አሳፍረው ይመልሳሉ፡፡ በሀገራቸው ላይ በመጣ ላይም በአንድነት ይቆማሉ፡፡ ምንም ዓይነት ልዩነት ቢኖራቸውም በሀገር ጉዳይ ላይ ግን በአንድነት ከመቆም አያግዳቸውም፡፡
ይህ የቆየ ኢትዮጵያዊ እሴት ግን አሁን ላይ ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ በተለይም ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያለውን የፖለቲካ ባህል ስናይ በጎ ሥራ ሠርቶ ሀገር እና ሕዝብን ከመጥቀም ይልቅ የራስን ጥቅም፤ ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅ የራስን ስሜት፤ ከሀገር ህልውና የፓርቲ ህልውናን ማስቀደም ላይ ትኩረት የሚደረግበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የጋራ ቤታችን የሆነችው ኢትዮጵያ ክብሯ ዝቅ እንዲል፤ የጋራ አስተሳሰብ እንዲቀዛቀዝ አልፎ ተርፎም በማያባራ ጦርነት ውስጥ እንድንዘልቅ አድርጎን ቆይቷል፡፡
ተበላሽቶ የቆየው የፖለቲካ ሥርዓታችን ለሀገር በጎ ማሰብና አለፍ ሲልም ችግሮቻችንን በጋራ ከመቅረፍ በጋራ ችግሮችን መቀፍቀፍ ላይ እንድንጠመድ አድርጎናል፡፡ በጋራ ቆሞ ሕዝብና ሀገርን ከመጥቀም ሀገር በትብብር እንዳትቆም የጥላቻ መርዝ መንዛት ነው፡፡ ተባብሮ ተደጋገፎ ሀገርን ማቆም ፖለቲከኞቻችን በሩቁ የሚሸሹት ጸበል ሆኖም ይታያል፡፡
ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች የመለያየት እንጂ የአንድነት ተምሳሌት ሆነው አልኖሩም። በሀገራችን ፖለቲካ ሲታሰብ ከአብሮነት ይልቅ መለያየት፤ ከመደጋገፍ ይልቅ መገፋፋት፤ ከውይይት ይልቅ መነቋቆር፤ አብሮ ከመቆም ይልቅ አብሮ መውደቅ አመዛኙን ሥፍራ ይዞ ቆይቷል፡፡
የፖለቲካ ትልቁ ጉድለት ከሸፍጥ ጋር መቆራኘቱ ነው፡፡ ፖለቲከኛ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ በጎ ሥራ መሥራት የተከለከለ ይመስላል፡፡ ይልቁንም ሴራ መተንተንና መንግሥትን መውቀስ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ጥንካሬ መለኪያ ተድርጎ እየተወሰደ ሀገር ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አሳጥቷል፡፡ ይባሱንም ሀገርን በማያራምድ አጀንዳ ሰቅዘው የኋሊት እንድትጓዝ አድርገዋል፡፡
የአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እሳቤ የሚመነጨው በተገኘው አማራጭ ሁሉ ወደ ሥልጣን መምጣት እንጂ ባላቸው ጊዜ ለሕዝብ እና ለሀገር በጎ መሥራት አይደለም፡፡ እነደነዚህ አይነቶቹ እነሱ ሥልጣን ካልያዙ በስተቀር ሀገር የሌለች ይመስል በእያንዳንዱ ጉዳይ ከወቀሳና ማጣጣል በስተቀር አባሎቻቸውን አስተባብረው ይህ ነው የሚባል ሀገራዊ ሥራ ሲሠሩ አይታዩም፡፡ ብዙዎችም መኖራቸው የሚታወቀው የምርጫ ዘመቻ ሲመጣ ብቻ ነው፡፡
በየዘመናቱ የነበሩ ገዢ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ከዚህ የተለየ እሳቤ አልነበራቸውም፡፡ ተፎካካሪን እንደ ጠላት ማየትና ማሳደድ ለዓመታት የተፀናወተን ልማድ ነው፡፡ አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሠረት ገና ከጅምሩ አጥፍቶና አንቋሾ፤ ጥላቻ ዘርቶና አኮስምኖ የራሱን ስብዕና ለመገንባት ሲሞክር ማየት የተለመደ ነው፡፡
በጋራ ሰርቶ ኢትዮጵያን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ከማላቀቅ ይልቅ እኔ ብቻ ስገዛ እኖራለሁ በሚል መታበይ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይመሠረቱ ፤ ከተመሠረቱም በኋላ እንዳይጠነክሩና ስር እንዳይሰዱ መንግሥታዊ ሥልጣንን ጭምር በመጠቀም የማዋከብና የማሳደድ ተግባር ውስጥ መግባት የተለመደ የፖለቲካ ባህላችን ነበር፡፡
ዛሬ ግን ሁኔታዎች እየተለወጡ ይመስላል፡፡ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ቁጭ ብለው በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመወያየትና አብሮ የመወሰን አዲስ አስተሳሰብ እየተመለከትን ነው። ሰሞኑንም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰብሳቢነት በሀገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና ተወካዮች በጋራ ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይም መክረዋል፡፡
ይህም ገዢው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመተባበር፤ የመመካከር፤ የመከባበርና የመፎካከር አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያደርግ ነው፡፡
ሀገር ሰላም የምትሆነው፤ የምታድገውና የምትለማው መተባበር ሲኖር ነው፡፡ መተባበር ካለ ቋጥኙ ይናዳል፤ ተራራው ይደረመሳል፤ አቀበቱ ቁልቁለት ይሆናል፡፡ አሁን የሚታየውም የሀገራችን ችግር ተወግዶ ሰላሟ የተረጋገጠ፤ ልማቷ የተፋጠነ እና ክብርና ሞገሷ የጸና ሀገር ለትውልድ ማስረከብ ይቻላል፡፡
መመካከርም ካለ በረባ ባልረባው መጋጨትና ነፍጥ ማንሳት ይቀራል፡፡ መከባበርም ከሰፈነ አንዱ ወደ ፊት ሄዶ ሌላው ወደ ኋላ እንዳይቀር፤ አንዱ የሀገር ባለቤት ሆኖ ሌላው ባዕድ እንዳይሆን በማድረግ ሁሉም ለሀገሩ ልማት በጋራ እንዲረባረብ በር ይከፍታል፡፡
ስለሆነም የጋራ ቤታችን የሆነችው ኢትዮጵያ ሰላሟ እንዲሰፍንና ብልጽግናዋም እንዲረጋገጥ በገዢው ፓርቲና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ዙርያ አብሮ የመሥራቱ ባህሉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም