ከግጭት ምዕራፍ ወደ ሠላምና ልማት ምዕራፍ ለመሸጋገር!

እንደ ሀገር በ2016 በጀት ዓመት ለማከናወን የታቀዱ ተግባራት ተቋጭተው፤ የ2017 በጀት ዓመት ተግባራትን ወደመከወን ተገብቷል:: በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ የበዙ መልካም ተግባራትን ከውና ከፍ ያለ ውጤትና ስኬትን ማስመዝገብ የቻለችበት የበጀት ዓመትን ማሳለፏን ከተለያዩ ሪፖርቶች መገንዘብ ተችሏል::

በአንጻሩ፣ ከበዛው ስኬትና ውጤቷ ባሻገር የሚገለጹ፣ እዚህም እዚያም የሚታዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በሠላም መደፍረስ ታጅበው ሂደቱን ለመገዳደር መሞከራቸው አልቀረም:: እንደ አጠቃላይ ግን ስኬት ያለ ድካም፤ ውጤት ያለ ፈተና አይገኝምና፤ በፈተና ውስጥም ሆና ሀገር ከፍ ያለ አፈጻጸምን ማሳየት ችላለች::

እንደ ሀገር በተገኘው ውጤት ውስጥ የክልሎች ሚና ከፍ ያለ ነው:: በዚህ መልኩ በስኬትም ሆነ በፈተና ሂደቷ ውስጥ በሁለቱም ገጾቿ ቀድመው ከሚገለጹ ክልሎች መካከል አንዱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሲሆን፤ ክልሉ ባካሄደው ዓመታዊ ጉባኤው ላይ የዓመቱን አፈጻጸም እና የቀጣይ እቅዱን ከስኬትም ከፈተናዎቹም አኳያ ቃኝቶ አሰምቷል::

በወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለጨፌው ባቀረቡት የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በርካታ ጉዳዮችን አንስተዋል:: በማብራሪያቸው እንዳነሱትም፤ በክልሉ 123 ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል፤ በመስኖ ስንዴ 102 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል፤ በሩዝ ልማትም ቢሆን በ2015/16 ምርት ዘመን 32 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት የተቻለበት ነው::

ከዚህ በተጓዳኝ በኢንቨስትመንት 148 ቢሊዮን ካፒታል ያስመዘገቡ ሦስት ሺህ 757 ፕሮጀክቶች ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል:: ዘጠኝ ሺህ 654 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በሕዝብ ተሳትፎ፣ በመንግሥትና በልማት ድርጅቶች ትብብር ተሠርተው ተጠናቀዋል:: ከአራት ሺህ በላይ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፤ ለ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል:: ሙስናን ለመከላከል በተሠራው ሥራም ሊመዘበር የነበረ አምስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ማዳን ተችሏል::

ከዚህ ሁሉ ስኬት በተጓዳኝ ደግሞ ሠላም የክልሉ ትልቁ ተግዳሮት የነበረ ሲሆን፤ የልማት ሥራዎቹ ስኬታማ ተግባር የተከናወነውም በዚሁ ፈተና ውስጥ ተሆኖ ነው:: ይሁን እንጂ፣ ከልማት ተግባራቱ ጎን ለጎን የክልሉን ሠላም ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል:: በተለይ የክልሉን ሕዝብ ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የሠላምና የልማት ሥራዎች በመከናወናቸው ሠላምን ለማረጋገጥ በተከናወነ የሕግ ማስከበር ሥራ ውጤት ተገኝቷል:: እየተወሰደ ባለው ሠላምን የማስከበር ርምጃ ብሎም መንግሥት ለሠላም ባደረገው ተደጋጋሚ ጥሪ በመታገዝ በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት እጅ የሰጡ ሲሆን፤ እጅ የሰጡና የአሸባሪው ሸኔ አባላትን ወደ ኅብረተሰቡ በቀጥታ ከመቀላቀል ይልቅ በሦስት ዙር የተሐድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል::

ይሄን መሰሉ በልማቱም፣ በሠላሙም እየተገኘ ያለው ውጤት ደግሞ ለ2017 በጀት ዓመት እንደ ሀገር በተቀመጠው ግብ ውስጥ ክልሉም ከፍ ያለ ሚናውን ይወጣ ዘንድ የበኩሉን አበርክቶ የሚያደርግ ነው:: በመሆኑም ከልማት አኳያ፣ በ2017/18 የምርት ዘመን በበልግና በመኸር 12 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር በማልማት ከ379 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት፤ ከገቢን አኳያም 206 ነጥብ 08 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ውጥን ተይዟል::

ከዚህ በተጓዳኝ፣ ለሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠራል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ፤ ደረጃቸውም እንዲሻሻል ይደረጋል:: በሺህ ኪሎ ሜትሮች የሚለካ የአዳዲስ መንገድ ግንባታ እና ጥገና ተግባራት ይከናወናሉ:: በኢንቨስትመንት ዘርፉም ቢሆን 200 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 30 ሺህ ፕሮጀክቶችን በመቀበል ለአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል::

ይሄን መሰል የሕዝቦችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ታቅደው ሊሠሩም ሆነ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችለው ግን ከሁሉም በፊት ሠላም ሲኖር እና ሁሉም ዜጋ ለዚህ ተግባር ንቁ ተባባሪም፣ ተሳታፊም ሲሆን ነው:: በመሆኑም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የታቀዱ ተግባራት እንዲሳኩ ከታሰበ ሁሉም ኃይል ለሠላም ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ይጠበቅበታል::

ለዚህም ነው፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለጨፌው ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ “የታጠቁ ኃይሎች ከጥፋት መንገድ ተመልሰው የግጭትን ምዕራፍ መዝጋት አለብን” ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው:: ምክንያቱም፣ ልማቱ ሊፋጠንና የሚፈለገው ብልጽግና እውን ሊሆንና የዜጎችን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት እውን ማድረግ የሚቻለው፤ ሁሉም ከግጭት አስተሳሰብና ተግባር ወጥቶ፤ ለጋራ ልማት፣ ለጋራ ሠላም እና ለሁለንተናዊ ብልጽግና እውን መሆን ሲሠራ ነው:: በመሆኑም ከግጭት ምዕራፍ ወጥቶ ወደ የጋራ ሠላምና ልማት ምዕራፍ መሸጋገር የ2017 በጀት ዓመት የሁሉም ተግባር ሊሆን ይገባል!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም

Recommended For You