‹‹ደራርቱ ቱሉ የሥልጠናና ምርምር ኢንስቲትዩት የመሮጫ መም ችግርን ይቀርፋል›› -አትሌት ቀነኒሳ በቀለ

በኦሮሚያ ክልል መንግሥት በሱሉልታ ተገንብቶ ባለፈው ሐሙስ ለምርቃት የበቃው ደራርቱ ቱሉ የስፖርት ማሠልጠኛ እና ምርምር አካዳሚ በኢትዮጵያ ስፖርት ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት በተለያየ መንገድ ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል። ከነዚህም መካከል ከማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ ከተተኪ ስፖርተኞች፣ ስፖርቱን በጥናትና ምርምር በመደገፍ፣ ስፖርት ቱሪዝምን ከማሳደግ እና የገቢ ምንጭ ከማድረግ አንጻር የሚታዩት ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡

ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ በተገኘበት ወቅት፤ የአካዳሚው መገንባት ለክልሉ እንዲሁም ለሀገር ስፖርት ብዙ የሚያቃልላቸው ችግሮች እንዳሉ ማስተዋሉን ገልጿል። ጀግናዋና የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት የኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር ባለድል አትሌት ደራርቱ ቱሉ የተሰየመው አካዳሚው፤ የኦሊምፒክን እና የፊፋን ደረጃ በማሟላት በዘመናዊ ሁኔታ ተገንብቷል። አካዳሚው በ16 ስፖርቶች 800 ሠልጣኞችን የመቀበል አቅም ያለው ሲሆን፤ የመሮጫ መም፣ የእግር ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስ እና የቅርጫት ኳስ ሜዳን አካቷል፡፡

ይኸውም በተጠቀሱት ስፖርቶች ወጣትና ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት በተጨማሪ በኢትዮጵያ የሚታየውን የስፖርት ማዘውተሪያ ችግር በማቃለል የድርሻውን ይወጣል። ኢትዮጵያ በምትወዳደርባቸው ዓለም አቀፍና አሕጉር አቀፍ የስፖርት ውድድሮች የእግር ኳስ ሜዳ እና የመሮጫ መም እጦት ለብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅት ፈታኝ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።ቀናት ብቻ ለቀሩት የፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድንም ከዚሁ ጋር በተያያዘ እየተፈተነ መሆኑን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል።

በመሆኑም የአካዳሚው መገንባት ችግሩን ከመቅረፍ አልፎ ኢትዮጵያ አሕጉር አቀፍ ውድድሮችን እንድታዘጋጅም ጭምር ዕድል እንደሚፈጥር ይታመናል። የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ባለድሉ አትሌት ቀነኒሳ በቀለም ትልቅና ዘመናዊ የሆነ የስፖርት አካዳሚ መገንባቱ ለአትሌቲክስ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው አስተያየቱን ይሰጣል። በዚህ ደረጃ ይሠራል ብሎ ያልጠበቀው አካዳሚው ሱሉልታ ላይ መገንባቱ የሚያስገኘው ጥቅም ከፍተኛ በመሆኑ አዲሱ ትውልድ በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል። ተቋሙ እንደ ሀገርም አስፈላጊ በመሆኑ ሠልጣኞች ከረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ታሪክ ጋር ተያይዞ በሞራልና በመነሳሳት እንዲሠለጥኑም ያደርጋቸዋል።

እንደ ቀነኒሳ አስተያየት፣ በአካዳሚው የተሠራው ጥራቱን የጠበቀ የመሮጫ መም (ትራክ) ቀነኒሳ በአካባቢው ካስገነባውና በብቸኝነት የሀገር ውስጥና የተለያዩ ዓለም መጥተው ለሚሠሩ አትሌቶች በሚሰጠው አገልግሎት ብዛት ለተጎዳው የመሮጫ መም ጫና ይቀንሳል።አትሌቶች እንደ አማራጭ የሚሠሩበት በማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ጀግናው አትሌት ያስረዳል። በተጨማሪም በርካታ አትሌቶች በስፍራው ባለው ተስማሚ አየር ዝግጅት በማድረግ በሀገር ደረጃ ውጤታማ ለመሆን ያስችላል። ወጣት ሠልጣኞች ከአትሌት ደራርቱ ቱሉ ድል አድራጊነት ልምድ በመውሰድ እንዲጠቀሙበትና ታሪኳን መልሶ እንደሚጽፉም ይታመናል። ከዚህ በፊት የተሠራውን ታሪክ በምርምር ለመደገፍና ተተኪውን ትውልድ በስፖርት ጠንካራ አድርጎ ለማሠልጠንም የአጋጣሚው የሚጫወተው ሚና የጎላ ይሆናል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፣ አካዳሚውን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ካነሱት ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የቀድሞቹ ውጤታማ አትሌቶች በየጫካውና ገደላገደሉ ልምምድ እየሠሩ ሀገርን ማስጠራት መቻላቸውን ነው። አሁን ያሉት አትሌቶች ደግሞ በአካዳሚ ውስጥ በእውቀት እና በሥልጠና በመታገዝ ውጤታማ ለመሆን እድል ያገኛሉ።

በኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ማዘውተሪያና ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ ግርማዬ ለታ፤ አካዳሚው የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሁሉም ክልሎች አንድ ደረጃውን የጠበቀ አካዳሚ እንዲገነባ በሰጡት መመሪያ መሠረት መጀመሩን ያስታውሳሉ። በዚህም ጨረታ ወጥቶ በ2008 ዓም ከአሸናፊው ኮንትራክተር ጋር ውል ታስሮ ወደ ሥራ ተገብቷል። የፕሮጀክቱ ሥራ ከተጀመረ በኋላም በበርካታ ችግሮች ውስጥ አልፏል፤ መጀመሪያ 700 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ ነበር። ይሁን እንጂ ሥራው በተለያዩ ችግሮች በመጓተቱና በየወቅቱ የሚታየው የግንባታ እቃዎች ዋጋ መናር ታክሎበት ከ1ነጥብ5 ቢሊዮን ብር በላይ ፈጅቶ ተጠናቋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት የአምስት ስፖርቶች የሥልጠና ማኑዋልም ተዘጋጅቷል፡፡

አካዳሚው በ30 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈና የቤት ውስጥ፣ የመም እና የሜዳ ላይ ስፖርቶችን ማካሄድ በሚያስችል ሁኔታ እንደተሰራም ያስረዳሉ። ጂምናዝየሙም ደረጃውን ጠብቆ የተገነባና ጥራታቸውን በጠበቁ ቁሳቁሶች ከጣሊያን ተገዝተው ሊሟሉለት ችለዋል። ስፍራው የተመቸ የአየር ንብረትን በመያዙ የውጪ ሃገር አትሌቶችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማድረግ ለሀገር ገጽታና ስፖርት ቱሪዝም ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል። በተጨማሪም አካዳሚው የተሟላ በመሆኑ አሕጉርና ዓለም አቀፍ ስፖርት ጉባኤዎችን ማካሄድ ይቻላል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You