የዋጋ ውድነት የትምህርት ጥራት ያመጣ ይሆን?

ወቅቱ ተማሪዎች የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዓመት ጨርሰው ቀጣዩን የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለቀጣዩ ክፍል የሚመዘገቡበት ነው። ታዲያ በዚህ የምዝገባ ወቅት በብዙ መንደሮች እየተሰማ የሚገኘው የክፍያ ነገር ነው። እንደሚታወቀው የክፍያ መጨመር በየዓመቱ በሐምሌና ነሐሴ ወር አጀንዳ ነው። የአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ዓመታዊ ክፍያ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኖ እንደነበር አይተናል።

እንግዲህ እዚህ ትምህርት ቤት የሚያስተምር አቅም ያለው ሀብታም ስለሆነ ለከፋዮች አያስጨንቃቸውም እንበል! ዋናው ጥያቄ ግን ያለው ሀገራዊ ፋይዳ ምንድነው? ከዚህ ትምህርት ቤት የሚወጡ ልጆች ምን የተለየ ነገር ያገኙ ይሆን? ቅጥ ያጣ ቅንጦትና ምቾት በበዛ ቁጥር አካባቢያቸውን የመመርመርና የማወቅ ዝንባሌያቸው አይቀንስም ወይ? የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እና አካባቢውን ያላወቀ ትውልድ ለሀገሩ ምን አይነት ችግር ፈቺ ምርምር ይሠራ ይሆን?

ምናልባት ይሄ የጥቂት ትምህርት ቤቶች (ምናልባትም የአንድ ትምህርት ቤት ብቻ) ሊሆን ይችላል። የዋጋ ውድነት እና ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች ግን ተደጋግመው ሲነገሩና ሲታዩ የቆዩ ናቸው።

እንደምናየውም፣ እንደምንሰማውም፤ የግል ትምህርት ቤት ተመራጭ ነው የሚባልበት ምክንያት ለትምህርት ጥራት ተብሎ ነው (ከግል ትምህርት ቤት የወጣ ተመራማሪ ባንሰማም)።

የግል ትምህርት ቤት ለሀብታም ልጆች የሆነበት ምክንያት ደግሞ ከመክፈል አቅም ጋር ተያይዞ ነው። ድሃ ወላጅ ለግል ትምህርት ቤት የሚሆን የመክፈል አቅም ስለሌለው የመንግሥት ትምህርት ቤት ያስገባል። ጉዳዩ ከክፍያ ጋር መሆኑ ነው ነገሩን የፉክክር ያደረገው። የሀብታምና የባለሥልጣን ልጆች ለስማቸው ክብር ሲባልም ቢሆን የግል ትምህርት ቤት ይገባሉ ማለት ነው።

እኔ ያልታየኝና ያልገባኝ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ‹‹አለ›› የተባለው የትምህርት ጥራት ነው። ምናልባት የተማርኩት የመንግሥት ትምህርት ቤት ስለሆነ የግሉን ስለማላውቀው ይሆናል። ለጊዜው ወላጅ ስላልሆንኩ ልጅ በማስተማርም በቅርበት አላየሁትም። ይሄ ማለት ግን ስለግል ትምህርት ቤቶች ምንም አላውቅም ማለት አይደለም። የሙያዬም ባሕሪ ነውና ተደጋጋሚ ሥራዎችን ሠርቻለሁ። ብዙ ነገሮችን ታዝቤያለሁ። በቅርበት ከማውቃቸው ጓደኞቼ ብዙ ገጠመኝ አስተውያለሁ። በትምህርት ቤቶች እየገባሁም ለማስተዋል ችያለሁ።

ለማንም ሰው ግልጽ ከሆነው ስያሜያቸው ልጀምር። የግል ትምህርት ቤት ሆኖ ሀገራዊ ስያሜ ያለው ብዙም አላጋጠመኝም። እንዲያውም የአንዳንዶቹ ቃሉን እንኳን ለመጥራት ማስታወሻ ለመያዝ የሚያስገድዱ ናቸው። ትርጉማቸውን ለማወቅም የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ወይም የኢንተርኔት መረብን መበርበር የሚያስገድዱ ናቸው። የሚገኘው ትርጉም አንድ የውጭ ሀገር ታሪክ ይነግረናል። ቃሉ ብቻ ሳይሆን ሀሳቡና ክስተቱ ራሱ የውጭ ይሆናል።

በሀገር ባለውለታዎች፣ በሀገር ውስጥ ቋንቋ፣ በሀገር ውስጥ ታሪክ፣ ሀገር ውስጥ በተከሰተ መልካም ክስተት ተሰይመው የሚታየው የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ ነው። የትምህርት ቤቱ ስም ራሱን ችሎ አንድ ነገር ያስተምራል። እቴጌ መነንም ሆነ የካቲት 12 የኢትዮጵያ ታሪክ እና የኢትዮጵያ ሰዎች ናቸው። ምኒልክ ትምህርት ቤትም ሆነ በላይ ዘለቀ ትምህርት ቤት የኢትዮጵያ መሪዎችና አርበኞች ናቸው። ኮከበ ጽባህም ሆነ ምሥራቅ ጎህ ኢትዮጵያዊ ስያሜ ያላቸው ናቸው።

እነዚህ ስያሜዎች ቀላልና ተራ ነገር አይደሉም። ለታዳጊ ሕጻናትና ልጆች ብዙ ነገር እያሳወቁ ነው። በየትኛውም አጋጣሚ የትምህርት ቤቶች ስም ሲጠራ  የባለታሪኮች ስም እየታወሰነው። አፌ ላይ የመጡትን ጠቀስኩ እንጂ የብዙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ስያሜ ሀገራዊ ስም ያለው ነው። እንግዲህ አንዱ የታዘብኩት ነገር ይሄ የስያሜ ልዩነት ነው። ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ልጆች፣ አድገው ሀገራቸውን ለሚያገለግሉ ልጆች የግል ትምህርት ቤት በሀገራዊ ስያሜ ቢሰየም ምን ችግር አለው? ወይስ ውጭ ሀገር ካሉ የስያሜው ባለቤቶችና ባለታሪኮች በማስታወቂያ መልክ የሚያገኙት ጥቅም አለ ይሆን?

ሌላው የግል ትምህርት ቤቶች ላይ በሰፊው የሚነሳው ሐሜት ትኩረታቸው የእንግሊዘኛ ቋንቋ ላይ መሆኑ ነው። ምንም ችግር የለውም! ነገሮችን ለመረዳት፣ ዓለም አቀፍ ሰው ለመሆን እንግሊዘኛ ወሳኝ ነው። ብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የእንግሊዘኛ ችሎታ የሚጠይቁ ናቸው። እንግሊዘኛ ፈጣን መሆን የማያከራክር ጥቅም አለው፤ እንዲያውም በዚህ ዘመን ግዴታ ነው። ቋንቋ የኢንተርኔት ቋንቋ ነው።

ችግሩ ግን እንግሊዘኛ ብቻውን ዕውቀት ነው ወይ? የሚለው ነው! የቋንቋ ጥቅም ለመግባባት ነው። እንግሊዘኛ ማወቅ ብቻውን የፊዚክስ ተመራማሪ አያደርግም። የኬሚስትሪ ሊቅ አያደርግም። የተፈጥሮን ምሥጢር ለመመርመር ሀገርኛ ነገሮችን ማወቅ የግድ ይላል። ‹‹አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ያስቀጣል›› በማለት የአገር ውስጥ ቋንቋን መጣል የትም አያደርስም።

ምናልባት ልጆቹ ትምህርት ሲጨርሱ ከአገር ውጭ እንዲሠሩ ይሆን? ለሀገራቸው እንዲያገለግሉ ከሆነ የሀገሩን ቋንቋና ባሕል አራግፎ የጣለ ትውልድ አገር ሊረከብ አይችልም። ለምሳሌ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ የሚሆን ከሆነ፤ ወይራ፣ ጽድ፣ ዋንዛ፣ እሬት፣ ፌጦ…… የመሳሰሉ አገር በቀል ሀብቶችን ማወቅ ነበረበት። የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪ የሚሆን ከሆነ፤ ዓድዋን፣ የገዳሥርዓትን፣ ሽምግልናን፣ አሸንዳን፣ ጨምበላላን ማወቅ አለበት። እነዚህን ነገሮች የሚያውቀው ከአካባቢው ሰዎች ነው። ከአካባቢው ተረትና ምሳሌዎች ነው። የአካባቢው ተረትና ምሳሌዎች፣ ተረኮች፣ ታሪኮች ደግሞ የተሰነዱት በእንግሊዘኛ ሳይሆን በሀገሩ ቋንቋዎች ነው። ከእነዚህ ነገሮች የራቀ ተማሪ የማያውቃትን ሀገር ነው የሚረከብ ማለት ነው።

እነዚህ ነገሮች የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ በብቃት እየተሰጡ ናቸው ማለቴ አይደለም። እንዲያውም ቢያንስ በእንግሊዘኛው እንኳን የግል ትምህርት ቤቶች ሊሻሉ ይችላሉ። የመንግሥት ትምህርት ቤት በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰማው ቅሬታ ግዴለሽነትና ክትትል ማጣት ነው። መምህሩ ከፈለገው ወር ሙሉ ክፍል ላይገባ ይችላል። ክፍል ውስጥ ገብቶም እንደፈለገው ቀልዶ ሊወጣ ይችላል። በዝርክርክነት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ ያለው ውድቀት ይከፋል። ዳሩ ግን ምን ዋጋ አለው! ከፍተኛ ቁጥጥር ቢያደርጉም የግል ትምህርት ቤቶች ልጆችን ከሀገራዊ ነገሮች እያራቋቸው ነው።

ትኩረቴን የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ያደረኩበት ምክንያት የጥራት ማሳያ ናቸው ሲባል ስለምሰማ ነው። የትኛው ምጡቅ ተመራማሪ እንደወጣ ስላልሰማሁ ነው። እንግሊዘኛ ላይ መራቀቅ ብቻውን ተመራማሪና የፈጠራ ሰው ሊያደርግ ስለማይችል ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የሀብታምና የባለሥልጣናት ልጆች ብቻ መሆኑ ነው። የሀብታምነት መለያው ጎበዝና ተመራማሪ ተማሪ ከመፍጠር ይልቅ የትምህርት ቤቱ ስም ብቻ መሆኑ ነው። የመንግሥት ባለሥልጣን የመንግሥትን ብቃት እያቆለጳጰሰ ልጁን የሚያስተምር ግን የግል ትምህርት ቤት ነው። በየደረሰበት ግን የመንግሥትን የትምህርት ጥራት ያወድሳል። ይሄ ባለሥልጣን የመንግሥትን የትምህርት ጥራት አያምንበትም ማለት ነው፤ ወይም ደግሞ የግል ትምህርት ቤት ብቻ የሚያስተምር ለስሙ ክብር ብቻ ነው ማለት ነው።

የግል ትምህርት ቤቶች ልዩነታችሁን በፈጠራችኋቸው ልጆች እውቀት አሳዩን! የዋጋ ውድነት ብቻውን የትምህርት ጥራት አያመጣም!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You