ተፈጥሯዊ የፊት ቆዳ መጠበቂያ ምርቶች

ዲክራ ሸኪብ ትባላለች:: ዲክራ ተወልዳ ያደገችው በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል በድሬዳዋ ከተማ ነው። ተፈጥሯዊ ግብዓቶችን በመጠቀም ፊትን መንከባከብና ማስዋብ የሚያስችሉ የቆዳ መጠበቂያ ምርቶችን አዘጋጅታ ለገበያ እንደምታቀርብ ትናገራለች። ‹‹እኔ ባደግኩበት የምሥራቁ ክፍል በተፈጥሯዊ ግብዓቶች ቆዳን መንከባከብ የተለመደ ነው›› ስትል ጠቅሳ፣ ይህም ግብዓቶቹን ለማዘጋጀት መነሻ እንደሆናት ትገልጻለች።

የጉዞ አስጎብኚ ባለሙያ እንደነበረች ትናገራለች። ትዳር መሥርታ የልጆች እናት ስትሆን፣ ቤት ውስጥ በመሆን ልጆቿን ለማሳደግ ትወስናለች። ይህን ጊዜም በፌስቡክ የማኅበራዊ ገጽ ላይ በቤት ውስጥ ሆነው ልጆቻቸውን ለሚያሳድጉ እናቶች በተፈጥሯዊ ግብዓቶች እንዴት የፊታቸውን ቆዳ መንከባከብ እንደሚችሉ ልምዷን ማጋራት ውስጥ ገባች።

‹‹አብዛኛዎቹ ሴቶች ራሳቸውን መንከባከብ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ግብዓቱን ከየት እንደሚያመጡት እና እንዴት ማዘጋጀት እንደሚጀምሩም አያውቁም›› የምትለው ዲክራ፤ እነዚህን ተፈጥሯዊ ግብዓቶች ከድሬዳዋ በማምጣት ከአራት ዓመት በፊት ቤቷ ውስጥ ማዘጋጀት መጀመሯን ታስታውሳለች።

እሷ እንዳለችው፤ በድሬዳዋ የፊት ቆዳን በመንከባከብ በኩል በስፋት የሚታወቀው ቀሲል ወይም የቆርቆራ ዛፍ ነው። ፍሬው የሚበላ ሲሆን፣ የቅጠሉ ዱቄት ደግሞ ከውሃ ጋር እንዲቀላቀል ይደረጋል፤ ይህን ጊዜም አረፋ ያወጣል፤ አረፋውም ሳሙናን በመተካት ፊትን ለመታጠብ፣ ቆዳን ለማፅዳት እንዲሁም ለፀጉር እንክብካቤ ይውላል።

‹‹ወደሀገር ውስጥ የሚገቡ የተለያዩ የቆዳ መጠበቂያ ምርቶች በገበያው ላይ ቢገኙም፣ የሶማሌ ሴቶች ግን ይህ ዕፅዋት ፊትን ለመንከባከብ በእጅጉ ይመርጡታል። ብዙዎች አሁን ተፈጥሯዊ መንከባከቢያዎችን ትተው ለተለያዩ ኬሚካሎች እየተጋለጡ ነው›› ስትል ታብራራለች።

እሷ ግን ይህን ዕፅዋት ነው ለቆዳ መጠበቂያነት እንዲውል የምታደርገው። ይህን የማደርግበት ዋና ዓላማ ከውጭ ለሚመጡ ምርቶች የምናወጣውን ወጪ ለመቀነስ እና እየተረሳ የመጣውን በባሕላዊና ተፈጥሯዊ የቆዳ መጠበቂያ ዘዴ ለማስታወስ ነው›› ትላለች ::

በማኅበራዊ ገጽ ከተለያዩ እናቶች ጋር ልምድ በመለዋወጥ የጀመረችው ይህ ተፈጥሯዊ ፊት የመንከባከቢያ ዘዴ የማዘጋጀት ሥራ፣ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ነው የተናገረችው። ይህን ዘዴ የተጠቀሙ ብዙዎች ለውጥ ማየታቸውንም ትጠቅሳለች። ዲክራ የፊት መንከባከቢያ ምርቶች እንዴት ይዘጋጃሉ በሚል በበይነ መረብ የሚሰጡ ተከታታይ ትምህርቶችን በመከታተልም ልምዷን ማሳደግ ትላለች ።

አሁን ላይ ‹‹ዚክራ ናቹራል›› በሚል ስያሜ ከተፈጥሯዊ ግብዓቶች የሚዘጋጁ ከአራት በላይ የፊት ቆዳ መንከባከቢያ ምርቶችን እንደምታዘጋጅ ጠቁማለች። እነዚህም አንድ የፊቱን ቆዳ ለመንከባከብ የሚፈልግ ሰው ሊያውቃቸው የሚገቡ ግብዓቶች መሆናቸውን ጠቅሳለች። ‹‹ለፊታችን ከሚያስፈልጉን ምርቶች የመጀመሪያው ፊትን የሚያፀዳው ነው፣ ፊት ከፀዳ በኋላ ደግሞ ለቆዳችን እርጥበት የሚሰጥ ግብዓት ያስፈልገናል። ሌላው የፀሐይ መከላከያ ሲሆን፣ ከዚያም የፊታችንን ቆዳ ጥርት የሚያደርጉ ውሕዶችን መጠቀም እንችላለን ›› ስትል ታብራራለች።

ሳሙናን ተክቶ ፊትን ለማፅዳት የሚውለው ቀሲል፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሌላ መጠሪያ እንዳለውም ዲክራ ትገልጻለች። ቀሲል በውስጡ የቫይታሚን ሲ ንጥረነገር እንዳለው ጠቅሳ፣ ፊትን የማፅዳት እና የማፍካት ባሕሪ እንዳለው ነው ያመለከተችው። ሌላኛው ምርት የጽጌሬዳ አበባ ውሃ መሆኑንም ጠቁማ፣ ይህ ውሃ ፊት እርጥበት እንዲኖረው እና በተለያዩ ባክቴሪያዎች አማካኝነት ፊታችን ላይ የሚወጡ እንከኖችን ለመከላከል ይጠቅማል ትላለች።

ዲክራ ከምታዘጋጃቸው የፊት መንከባከቢያ ውሕዶች ውስጥ ከሌሎች ውሕዶች ጋር ተቀይጦ የሚዘጋጀው በማዕድን የበለጸገ የሸክላ አፈር ይጠቀሳል፤ ይህን ግብዓት በመጠቀም በኩል ግብፅ፣ ሞሮኮ እና አንዳንድ የዓረብ ሀገራት በስፋት እንደሚጠቀሙበት ይጠቀሳል፤ ግብዓቱም ባሕርና ደለል ያለበት አካባቢ ይገኛል ።

እሷም ይህንን ምርት ከእነዚህ ሀገራት በማስመጣት ከሀገር ውስጥ ዕፅዋቶች ጋር በመደባለቅ ታዘጋጃለች። ‹‹በማዕድን የበለጸገ የሸክላ አፈር በሀገራችን ቢገኝም፣ ለፊት ቆዳ መንከባከቢያነት ለመዋል የተለያዩ ሂደቶችን ማለፍና በዘርፉ ባለሙያዎች ተመርምሮ መረጋገጥ እንደሚኖርበትም አስገንዝባለች።

የእርድ ውሕድም ታዘጋጃለች። ይህንን ግብዓት ብዙዎች ይጠቀሙበታል። ከተለያዩ ግብዓቶች ጋር በመደባለቅ ነው ውሕዱን የምታዘጋጀው። ውሕዱ በፀሐይ ለተጎዳ ፊት፣ ብጉር ላለባቸው ሰዎች እና ፊትን ለማፍካት ያገለግላል።

ፊትን ለማለስለስ የሚውለው የፊት ቅባትም ታዘጋጃለች። ይህንንም ከወይን ፍሬ ዘይት፣ ከአልመንድ ፍሬ እና ከሌሎች ግብዓቶች ነው የምታዘጋጀው። ቅባቱ ፊታችን ላይ የሚገኘውን ተፈጥሯዊ ወዝ የሚተካ መሆኑን ጠቅሳ፣ የተለያዩ ውሕዶችን ከተጠቀምን በኋላ ሊከሰት የሚችለውን ድርቀት ለመከላከል እንደሚጠቅመም ጠቁማለች።

ዲክራ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ የሆነውን ቀሲል 150 ግራም በ300 ብር እና 300 ግራም በ500 ብር ለገበያ ታቀርባለች። ይህም ለረጅም ጊዜ የሚያገልግል መሆኑን ጠቅሳ፣ በጥቅል መልክ የሚዘጋጀውን የቆዳ መንከባከቢያ ለደንበኞቿ የምታቀርበው በቆዳቸው አይነት ላይ ምክር ከሰጠች በኋላ መሆኑንም ትናገራለች። በጥቅሉ በሁለት ሺህ 200 ብር የሚሸጠው ግብዓት ለሦስት ወር ያህል እንደሚያገለግልም ገልጻለች።

ቀሲል በየእለቱ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችልና ውሕዶችን የያዘው ጥቅል ደግሞ በሳምንት ለሦስት ቀናት መወሰድ እንዳለበትም ተጠቃሚዎቿን ትመክራለች። የፊት መንከባከቢያዎቹ የሚያመጡት ለውጥ እንደየሰው የፊት ሁኔታ እንደሚለያየም ጠቅሳ፣ ከሁለት ሳምንት ጀምሮ እስከ ሦስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ግን ለውጥ እንደሚታይ ጠቁማለች።

ዲክራ አሁን ላይ በሀገር ውስጥ ከሚገኝ የቆዳ እንክብካቤ ማሠልጠኛ ተቋም ትምህርት በመውሰድ እውቅና አግኝታለች። ወደፊትም በተፈጥሯዊ ግብዓት የምታዘጋጃቸውን የቆዳ መንከባከቢያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁ ለማድረግ እንደምትሠራም እንዲሁም የቆዳ መንከባከቢያ ማዕከል ለመክፈት ማቀዷን ጠቁማለች።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You