“የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሀብት የሚፈስበት ብቻ ሳይሆን የሚታፈስበትም ይሆናል” ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር

ከሁለት ሺህ የሚልቁ ተቋማት የተፈጠሩለት ዘርፍ ነው። ከ100 በላይ የሚሆኑቱ ደግሞ በፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ደረጃ ዘምነዋል። ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሠልጣኞች በተቋማቱ ውስጥ በተለያዩ ደረጃ ሥልጠና ላይ ናቸው። ዘርፉ ከፍተኛ ሀብት የሚፈስበት ሆኗል። የነገዋ ኢትዮጵያ ከዚህም ዘርፍ በሚወጡ የሠለጠኑ እጆች የምትሠራ ሆናለች። የመንግሥት ዘርፉን የማጠናከር ቁርጠኝነትም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እስከማቋቋም ድረስ ዘልቋል። ይህ ዘርፍ ብዙዎች ትኩረት ያልሰጡት ነገር ግን ብዙ ሚሊዮኖች እየፈሩበት ያለው የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ነው።

ለመሆኑ መንግሥት ይሄንን ሁነኛ ዘርፍ ለማጠናከርና እንደ ጀርመን ያሉ ሀገራት ከደረሱበት ከፍታ ለማድረስ ምን እየሠራ ይሆን?፤ ፖሊሲዎቻችንና ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት በእርግጥስ ወደሚፈለገው ደረጃ ማድረስ የሚያስችሉ ናቸው? እነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች የቀረበላቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ዘርዘር ያለ ምላሽ ሰጥተውበታል። የሚኒስትሯ ሙሉ ቃለ ምልልስም እንዲህ ቀርቧል።

አዲስ ዘመን:- የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከቴክኒክና ሙያ ሥልጠና አንጻር ያሉት ተልዕኮዎች ምን እንደሆኑ ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ ሙፈሪሃት:- የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን ከቴክኒክና ሙያ ዘርፍ አንጻር በጣም ወሳኝ ተልዕኮ ነው ያለው። ይሄ ተልዕኮ አንድን ኢኮኖሚ ተወዳዳሪ የማድረግ ተልዕኮ ነው። መነሻው የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ቢሆንም እኛ ደግሞ የለየናቸው ጉዳዮች አሉ። የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ እንዲኖር በማድረግ ረገድ የራሱ የሆነ የማይተካ ድርሻ አለው። በሁለተኛ ደረጃም ማኅበራዊ ሁኔታዎቻችን የተሻሉና የጎለበቱ እንዲሆኑ ትልቅ ሚና እንዳለው ተመልከተናል። ዜጎችን የማስቻል ሁኔታውም ትልቅ ነው። በተለምዶ ማብቃት የሚባለው ማለት ነው። አንድ ሰው በአንድ ጉዳይ ላይ ክህሎትም እውቀትም ካለው በራሱ የመተማመኑና ብቃቱ ያደገ ይሆናል። ስለዚህ ይሄንን ተልዕኮ የመወጣት ኃላፊነት አለብን።

አዲስ ዘመን :- ለጠቀሷቸው ተልዕኮዎች መሳካት ምን ያህል ምቹ ፖሊሲ አለ ማለት ይቻላል

ወ/ሮ ሙፈሪሃት:- በፖሊሲ ደረጃ በቅርብ ጊዜ የወጣው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ የላቀ ግልጽነት ያለው ሆኗል። የሰው ኃይላችንን ለሀገር ውስጥም ይሁን ለዓለም አቀፍ ገበያ ብቁ አድርጎ ማዘጋጀት የሚያስችል እንደሆነም ማየት ይቻላል። ይሄም ብቻ አይደለም። ሀገር በቀል ለሆኑ እውቀቶችና ክህሎቶች ቦታ የሰጠ ፖሊሲ ነው። ከአሁን ቀደም በነበረው አካሄድ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፉ የሚታወቀው አነስተኛና መካከለኛ ሙያተኞችን ብቻ የሚያወጣ ዘርፍ ተደርጎ ነበር። ነገር ግን አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ፖሊሲ ዘርፉ የላቀ የብቃት ደረጃን የሚያጎናጽፍ እንዲሆን ተደርጎ እስከ ደረጃ 8 ድረስ ያደገ እንዲሆን ተደርጓል። በአጭር ጊዜ በተለይ ሪፎርሙን ተከትሎ የተከናወኑ ሥራዎች ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ትልቅ ሊባል የሚችል ነው። ወደተሻለ ደረጃም ለማድረስ የሚያስችል እንደሆነ መመልከት ይቻላል።

አዲስ ዘመን :- ዘርፉ በርካታ የሰው ኃይል ያለበት፣ በመንግሥት በኩልም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ላቅ ያለ እንደሆነ ተገልጿል። ለመሆኑ በዚህ ደረጃ ትኩረት ያገኘው ይህ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውና እንዲኖረው የሚፈለገው ድርሻ እንዴት ይገለጻል?

ወ/ሮ ሙፈሪሃት:- ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ኢኮኖሚው ተወዳዳሪ እንዲሆን የማስቻል ተልዕኮ አለው ስንል አንድም በዘርፉ በእያንዳንዱ ንዑስ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲኖረው በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና አለው ማለታችን ነው። በሁለተኛ ደረጃ በቴክኖሎጂ ሽግግር ያለው ሚና ተጠቃሽ ነው። ጠቅለል ተደርጎ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ወይንም ተቋማት በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸው ዐቢይ ሚና ምንድን ነው ተብሎ ቢጠየቅ፤ አንደኛው የሚሆነው የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ነው። ሌላኛው ደግሞ የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ መሥራት ነው። ለምሳሌ በ10 ዓመቱ የፍኖተ ብልጽፅግና ላይ የቅድሚያ ቅድሚያ የተሰጣቸው አምስት ዘርፎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው ግብርና ነው። የግብርናው ዘርፍ ተለምዷዊ በሆነ መንገድ በምንሠራው ሥራ የምንፈልገውን ሽግግር ማረጋገጥ አንችልም። ስለዚህ ነባሩን የሰው ኃይል፣ ተለምዷዊ በሆነ መንገድ ሥራ ሲሠራ የቆየውን አርሶ አደር፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን እንዲሁም አዳዲስ ወደ ዘርፉ መግባት የሚፈልጉ ዜጎችንና ኩባንያዎችን ለዘርፉ ብቁ የሆነ ክህሎት ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ትልቅ አቅም አላቸው።

በፌዴራል ደረጃ አምስት ለሚኒስቴሩ ተጠሪ የሆኑ የግብርና ኮሌጆች አሉን። እነዚህ ኮሌጆች የግብርናውን ዘርፍ የሰው ኃይል ፍላጎት የሚያሟሉ ናቸው። በእነዚህ ብቻ አንቆምም በክልል ደረጃም ለየክልሎቹ ተጠሪ የሆኑ 20 አካባቢ የግብርና ኮሌጆች አሉን። እነዚህ ኮሌጆችም በየአካባቢው የሠለጠነ የሰው ኃይል እንዲያፈሩ ይጠበቃል። አሁን ላይ ማሠልጠን ብቻ ሳይሆን የመመዘንም ሥራ እየሠራን ነው ያለነው። ማሠልጠን ማብቃትና መመዘን ማለቴ ነው። የምዘና ሥርዓቱ ላይ ለምሳሌ መመዘን የሚፈልጉ አርሶ አደሮችን እየመዘንን ነው ያለነው። ምዘና የሚጠቅመው ተመዛኞች የት ደረጃ ላይ ነው ያሉት ምን ይጎድላቸዋል የሚለውን ለመለየትና ቀጣይነት ያለው የማብቃት ሥራ ለመሥራት ነው። ይሄ የግብርና ዘርፉን ትራንስፎርሜሽን መሠረታዊ የሚባል ለውጥ እንዲያመጣ ካለው እምቅ አቅምም አንጻር ትርጉም ያለው ሚና ይጫወታል ማለት ነው።

አሁን እኛ እያየን ያለነው ይሄንን ጉዳይ እንዴት አድርገን በብቃትና በፍጥነት እንሂድበት የሚለውን ነው። ምክንያቱም ትልቅ ቁጥር ያለው የኅብረተሰበ ክፍል ነው በግብርናው ዘርፍ ተሰማርቶ የሚገኘው።

አዲስ ዘመን :- ከሪፎርም አንጻር በዘርፉ ምን እየተሠራ ነው?

ወ/ሮ ሙፈሪሃት:- በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች ናቸው እየተሠሩ ያሉት። ክህሎት ማሻሻል ያስችላሉ ያልናቸውን 11 አካባቢ የሪፎርም መስኮች ተመርጠው ሥራዎች እየተሠራባቸው ይገኛል። አንዱ የሥልጠና ፍላጎት መር እናድርገው የሚል ነው። ፍላጎት መር እናድርግ ስንል ከአምስቱ የቅድሚያ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች አንፃር የመቃኘት ሌላም ገበያ የሚፈልጋቸው ዘርፎች ካሉ እያየን እንሂድ የሚል ነው። ስለዚህ አንዱ ለግብርናው ከሰጠነው ትኩረት ጋር ይያያዛል።

በአምራች ዘርፉም (ማኑፋክቸሪንግ) በተለይም በኮንስትራክሽን፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ በጨርቃጨርቅ እና በግብርና ማቀነባበሪያ ላይ በትኩረት እየተሠራባቸው ያሉ ጉዳዮች አሉ። ሥርዓተ ትምህርቶቻችንም ይሁኑ ማሠልጠኛ መሣሪያዎቻችን ለወቅቱ በሚሆን ደረጃ የመከለስ ሥራ ሠርተናል። ተጨማሪ በሚያስፈልጉ ዘርፎች ላይ ደግሞ የግሉ ዘርፍና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት አሳትፈን አዳዲስ ሥርዓተ ትምህርት የማዘጋጀት ሥራ ሠርተናል። በዚህም ከ140 በላይ የሆኑ ሥርዓተ ትምህርቶችን በአዲስ መልክ የማዘጋጀት ሥራ ተሠርቷል። አብሮ ደግሞ ግን ለጎን የማሠልጠኛ መሣሪያዎችን የማዘጋጀት ሥራ ተሠርቷል ይህም በየጊዜው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

ቱሪዝምን ካየን ደግሞ ይህም እንደ ዘርፍ ትልቅ አቅም ተደርጎ የተለየ ነው። ይህንን ዘርፍ ለማዘመን የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ ሆኗል። ለቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት የዋጀ የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ሥራ ተሠርቷል። ከግል ዘርፉ ጋርም ከመቼውም በላይ ተቀራርበን ለመሥራት እየሞከርን ነው። በቱሪዝም የሙያ ዘርፍ ሥልጠናው እስከ ደረጃ ስምንት ድረስ ይሄዳል። በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ደረጃ ስምንት ማለት በተለምዶ የትምህርት ሥርዓት ፒኤችዲ የሚባለው ነው። ደረጃ ሰባት ደግሞ የማስተርስ፤ ደረጃ ስድስት የመጀመሪያ ዲግሪ ማለት ነው። ዘርፉ በየደረጃው እና በየእርከኑ በቂና ብቃት ያለው የሠለጠነ የሰው ኃይል በማዘጋጀት ረገድ ትልቅ ትርጉም ያለው አካሄድ ነው።

የቱሪዝም ዘርፉ ላይ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አነሳሽነት የለሙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ የመስተንግዶ ኢንዱስትሪ የሚባለው ዘርፍ ላይ ሆቴሎች ላይ የሚሰማራውን የሰው ኃይልን ጨምሮ የማሠልጠን እና የማዘጋጀት ሥራን እየሠራን ነው ያለነው። ይህም እንደ ሀገር የቅድሚያ ቅድሚያ ከሰጠናቸው ዘርፎች ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ማለት ነው። በአጠቃላይ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ታሳቢ ያደረገ የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትም እየሠራን ነው።

ሌላኛው የማዕድን ዘርፉ ነው። የማዕድን ዘርፉ የቅድሚያ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ ነው። የማዕድን ዘርፉ ለውጡን ተከትሎ ነው በዚህ ደረጃ ግልፅ በሆነ ፖሊሲ የተደገፈው። ስለዚህ ዝግጅት ይፈልጋል ማለት ነው። አንዱ ቅድም ያነሳሁት ፍላጎት መር የሆነ የክህሎት ልማት ሥራ ነው የምንሠራው ብለን ከአስራ አንዱ ሪፎርሞች አንዱ አድርገን ወስደነዋል። ልክ እንደዛው ሁሉ የየአካባቢውን የመልማት ፀጋን መሠረት ያደረገ የቴክኒክና ሙያ ሥርዓት አደረጃጃት ነው የፈጠርነው። በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ውስጥ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ተቋማት ማዕከላት እየተባሉ ይለያሉ። ፖሊቴክኒኮች ላቅ ያለ እርከን ያላቸው ናቸው። 110 የሚሆኑ ፖሊቴክኒኮች አሉን። ፖሊቴክኒኮች በየአካባቢው አንፃራዊ ጠቀሜታ ላይ የተመሠረተ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና እንዲሰጡ በሚያስችል አደረጃጀት ነው የተዋቀሩት። ለምሳሌ የተሻለ የቱሪዝም ሀብት ልማት ያለበት አካባቢ ላይ ያሉ ኮሌጆቻችን ከቱሪዝም ሀብት ልማት ጋር የተያያዙ ሙያዎች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ማለት ነው። የግብርና ሥራዎች የተሻለ ጠቀሜታ ያለው አካባቢ ከሆነ ደግሞ ግብርና እና ግብርና ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር ትኩረት ያደርጋሉ ማለት ነው። ስለዚህ የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት ካሉበት አካባቢ ሀብትና ፀጋ ጋር በጥልቅ የተቆራኙ እንዲሆኑ ይደረጋል ማለት ነው። ይሄ አካሄድ የየአካባቢውን አለኝታ በደንብ አድርጎ ለማውጣት ያስችላል። ኢኮኖሚያችንም የተሳሰረ ሆኖ እንዲገነባ ነው የሚፈለገው። የመወዳደር አቅማችንን ያሳድገዋል።

ለማደግና ለመለወጥ ወሳኙና አንዱ የሰው ሀብት ነው። የሰው ሀብት ልማቱን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በተናበበ መንገድ ማዘጋጀት ከተቻለ በአንድ በኩል ጥራት ያለው ዝግጀት ለማድረግ ያስችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የየአካባቢውን የመልማት ፀጋ ወቅታዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚነት እንዲኖር ያግዛል። ካለን ነገር ጀምረን ማልማት ስንችል በአካባቢው ላይ ያለው ጥቅም ላይ ሳይውል ቀርቶ የነበረው ሀብት መልማት ይጀምራል። ያ ደግሞ አካባቢውንም ኅብረተሰቡንም ተጠቃሚ ያደርጋል። በተመሳሳይ በአይሲቲ በኩልም እየተሠሩ ያሉ በርካታ ሥራዎች አሉ።

የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፉ በቴክኖሎጂ የታገዘ አልነበረም። በኮቪድ ጊዜ ተጨባጭ ፈተና ሆኖ ታይቷል። ዩኒቨርሲቲዎች በተሻለ ፍጥነት እራሳቸውን ወደ ማስተካከል ሲገቡና የትምህርት ሥርዓቶቻችን በድረገጽ ለመስጠት ሲሞክሩ፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ግን እሱን ማድረግ አልቻሉም። ከተግባር ተምረን ሃያ የሚሆኑ የቴክኒክና ሙያ ተቋሞቻችንን የተሟላ መሠረተ ልማት እንዲኖራቸው አድርገናል። ለሌሎችም በዚሁ እንቀጥላለን። በዚህ ደረጃ እየተሠራ ነው። በቁጥር ካየነው የግሉንና የመንግሥትን ጨምረን ከአጭር ሥልጠና ጀምሮ የሚሰጡት ሁለት ሺ ገደማ እየተጠጉ ናቸው። ሁሉንም ደረጃ በደረጃ ወደዛ ማሽጋገር ይጠይቃል። አሁን ላይ እየሠራን ያለነው የፖሊቴክኒኮችን አቅም መገንባት ላይ ነው። የፖሊቴክኒኮቹ አቅማቸው ሲገነባ በእነሱ ዙሪያና በአካባቢያቸው ያሉ በኮሌጅ ደረጃ ያሉ ተቋማትን ይዘው ይወጣሉ የሚል የትስስር ሥርዓትም ጭምር ተዘርግቶላቸው ነው እየተሠራ ያለው። በዚህ መልኩ የኢኮኖሚ እድገታችን የቅድሚያ ቅድሚያ ለሰጣቸው ዘርፎች የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ሥርዓቱን አዘጋጅቶ ለመሄድ ጥረት እየተደረገ ነው ያለው።

አዲስ ዘመን :- ከሪፎርም አንጻር ይሄንን ያህል ርቀት ከተሄደ፤ በመንግሥት በኩል ለዘርፉ ምን ያህል ሀብት እየተበጀተ ነው?

ወ/ሮ ሙፈሪሃት:- ዘርፉ በባሕሪው ከፍተኛ ካፒታል የሚፈልግ ነው። ምክንያቱም ብዙ ማሽነሪዎችን ይፈልጋል፤ ብዙ ወርክሾፕ መኖር አለባቸው፤ ጊዜውን የዋጀ መሆንም አለባቸው። ውድድሩን እንደምታውቁት በጣም ጠንካራ ነው። የእኛ ኢኮኖሚ ያለውን እምቅ አቅም እንዲያወጣ ከተፈለገ እዚህ ዘርፍ ላይ የሚሠራው ሥራ ወሳኝ ነው። ካለው ቋት በመመደብ ረገድ ደረጃ በደረጃ እያደገ የመጣ የሀብት ድልድል አለ። ያለፉት ሁለት ዓመታት እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከተቋቋምንበት ጊዜ ጀምሮ የሚደረጉ ጥረቶች አሉ፤ ነገር ግን ከአንድ ምንጭ ብቻ በሚገኝ ሀብት ይሄንን ዘርፍ ማሳደግ አይቻልም። በዚህም ምክንያት ከባለድርሻ አካላት ጋር ጠንከር ያለ ሥራ እንሠራለን። ቁጥራቸው ውስን ቢሆንም አቅድ ይዘን ስልት ነድፈን ባለድርሻ አካላቱን የማብዛትና የማስፋት ሥራ እየሠራን ነው ያለነው። በአንድ ቋት ሀብቶቹ እንዲሰባሰቡና ቅድሚያ ትኩረት ለተሰጣቸው በዘርፉ ውስጥ ለተለዩ የለውጥ ሥራዎች እንዲውሉ የማድረግ ስልት ተከትለን እየሠራን ነው።

ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርቡ መንግሥት ባደረገው ድርድር 200 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ባንክ በብድርም በእርዳታ መልክም ለማግኘት ጥረት ተደርጓል። የጀርመን ልማት ድርጅትም ዘርፉን ያግዛሉ። በቅርቡ ደግሞ የጣሊያን መንግሥትም ይሄን ዘርፍ ለማገዝ እየሠራ ነው። የአውሮፓ ኅብረትም መንገድ ላይ ነው ያለው። የመንግሥትን አቅም እና የልማት አጋሮቻችንን አቅም ተጠቅመን ነው እየሠራን ያለነው። እኛ ደግሞ እንደአቅጣጫ ይዘን እየሠራን ያለነው እራሳቸው የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ሀብት የማመንጨት ዕድል አላቸውና ያንን ተጠቅመው ሃብት ማመንጨት አለባቸው የሚል ነው። የወርክሾፖቻችንን አቅም ብዙዎቹ ከሥልጠና በላይ ነው። በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ የኢንዱስትሪ ደረጃ ላይ ያሉ ዘርፎች ሲቸገሩ እነሱን እያገዝን በትርፍ ሰዓት ደሞ ከሥራ ውጭ የሆኑ ማሽኖችን በትርፍ ዓይን ሳይሆን አገልግሎት በመስጠት ዓይን በሚገኝ ገቢ ራስን የመደጎም አቅጣጫ እንከተላለን። ይሄ ግን ዋና ተግባር አይሆንም።

በአጠቃላይ በእኛ እቅድ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እራሳቸውን መቻል አለባቸው የሚል አቅጣጫ ነው ያለን። በዚያ መርሕ እየሠሩም ነው ያሉት። በሪፎርሙ ያስቀመጥነው አቅጣጫ ሠልጣኞች ወደ ተቋም ከገቡበት ጀምሮ ወጥተው ሥራ የሚፈልጉ ሳይሆኑ በቆይታቸው ሂደት ሥራ እንዴት እንደሚፈጠር ተለማምደው እራሳቸው ኩባንያ መሥርተው መውጣት አለባቸው፤ መመረቂያቸው ወረቀት ሳይሆን ኩባንያ መመሥረት መሆን አለበት የሚል ነው። እንደዚህ ሲሆን ሥራና የቴክኒክና ሙያ ሥርዓቱ የተሳሰረ ይሆናል ማለት ነው። ያንን ልምምድ ለመሥራት የፈጠርናቸው ኩባንያዎች በጣም ባጭር ጊዜ በ100 ሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር የሥራ ትዕዛዝ ተቀብለው እየሠሩ ነው። የግብርና ኮሌጆቹም አግሮ ፕሮሰሲንግ ላይ ገብተዋል። ዘይት መጭመቅ፣ ማር ማምረት ጀምረዋል። የሐር ትል ልማት ላይም በስፋት ይሳተፋሉ። በጣም ቆንጆ ቆንጆ የሐር ምርት ውጤት የሆኑ አልባሳትን ማምረት ጀምረዋል።

በአጭር ጊዜ በተሠራው ሥራ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት አይተውት ሰምተውት የማያውቁትን የገንዘብ መጠን ማፍራት የቻሉበት ሁኔታ ውስጥ መግባት ጀምረዋል። የሁሉም የተጠቃለለ ሪፖርት ሲደርስ ማወቅ ይቻላል። ከላይ የጠቃቀስኳቸው ሥራዎች በተለይም በዚህኛው ዓመት ነው ተሟልቶ ወደ ሥራ እየገቡ ያሉት። ከእነዚህ ተቋሞቻችን በጀመሩት መንገድ ወደ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት እንጠብቃለን። ይሄ ሆኖም ኖሮም አያውቅም። አዲስ አበባ ላይ ያሉ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትንም ብናይ ተመሳሳይ አዳዲስ ምርቶችን ማፍራት ጀምረዋል። ሥራዎችን ተቀብለው መሥራት ጀምረዋል ብሎ መውሰድ ይቻላል።

የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ምን አይነት አተያይ ነው ያለው የሚለውን ለማየት ሞክረን ነበር። የእኛ ማኅበረሰብ በመስማት ብቻ ሳይሆን በማየትም ጭምር የሚያምን ማኅበረሰብ ነው። ስለዚህ የቴክኒክና ሙያ ተቋማቱ “ሆነው እንዲገኙ” እናድርግ የሚለውን የመጀመሪያ አቅጣጫ አድርገን ነው የያዝነው። በተግባር ሆነን እንገኝ ብለን የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ሥርዓቱን ከሥልጠና በላይ በሚል አጠቃላይ እሳቤ ተርጉመነዋል። ከሥልጠና በላይ ያልነውን ጉዳይ ወደ ተግባር ጠንቅቀን ወደ ሥራ እየቀየርን ስንሄድ የቴክኒክና ሙያ ተቋማቱ ሳቢ ይሆናሉ። ዋል አደር ያለውን አስተሳሰብ ለመቀየር በተጨባጭ እነዚህ ስፍራዎች ላይ የሚገኘውን ክህሎት እና እውቀት በፈለጉት ሰዓት የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉ ወርቃማ እጅ ያላቸውን ሰዎች በመጠቀም እየሠራን ነው። ዜጎች ይሄ ገብቷቸው እንዲወስኑ ለማድረግ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት እንደ ዘርፍ የሚሰጡትን ጥቅም ማሳየት የሚያስችል ሥራዎችን እንሥራ በሚል እነዚህ ተቋማት ከሀሳብ እስከ ምርት እስከ ምስለ ምርት የሚሄድ ሥራ እየተሠራባቸው ነው ያለው።

የቀደመውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመቀየር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሚያደርገው ውትወታ ብቻ የተሟላ ግንዛቤ ማስያዝ አይቻልም። አንተም ያልከውን አይነት የተዛባ ትርክትና በቴክኒክና ሥልጠና ዘርፍ ያለውን አስተሳሰብ በተወሰነ ደረጃ መስበር ጀምረናል ማለት እችላለሁኝ። ለምሳሌ አምና ያስመረቅናቸው ልጆች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት የነበራቸው ይሄንን ዘርፍ የመረጡና የሠለጠኑ ናቸው። ይሄ ዘርፉ ላይ ያለው የተዛባ ነገር እየተስተካከለ ነው ማለት ነው። የእኛ የኮሙኒኬሽን ሥራ ዋል አደር ያለውን ችግር በደንብ ለመቋቋም የሚያስችል እንዲሆን አድርጎ ከሚዲያ ጋር የነበረውን ሥራ ማጠናከር ይኖርብናል።

አዲስ ዘመን:- በርካታ ተቋማት ከቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የተመረቁትን ለመቅጠር ፍላጎት አይታይባቸውም። ይሔ ተግዳሮት እንዴት ነው እየታለፈ ያለው ?

ወ/ሮ ሙፈሪሃት:- ጥሩ ጥያቄ ነው። በግሉ ዘርፍ “ማሽን ይሰብራሉ፤ ማሽን ያበላሻሉ” የሚል ሪስክ ያለመውሰድ ጉዳዮች አሉ። ሁሉም የግል ዘርፍ ማለት ቢያስቸግርም ቀላል ባልሆነ ደረጃ እንደዛ አይነት ተግዳሮት አለ። እዛ አካባቢ ያለውን መረዳት ለማስተካከል እየጣርን ነው። ምክንያቱም ለጋራ ሀገር ኃላፊነት ተከፋፍሎ መሥራት ካልተቻለ ጥንቅቅ ያለ ያለቀ የሚባል ነገር የለም። ሰው በተግባር ሂደት ነው የሚገነባው። እዚህ ያገኘውን መሠረታዊ እውቀት ይዞ መግባት ሲችል ነው የሚገነባው። ይሄንን ችግር ለመሻገር አንዱ እየሠራን ያለነው ከግል ዘርፉ ጋር ተቀራርቦ መስራት ነው። ከንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጋር የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ።

በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የጀመርነው አንድ ሥራ አለ። ከቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ሥርዓቱ ጋር አብሮ የሚዛመድ የሰው ኃይል አሠልጥነን ወጣቶችን ኢንዱስትሪዎች ጋር እናስገባቸዋለን። ለወራት እዛ ይለማመዳሉ፤ አፈጻጸማቸውን እያሻሻሉ እያስተካከሉ ይሔዳሉ። መጨረሻ ላይ ይቀጠራሉ። በዚህ መንገድ 11 ከተሞች ላይ የጀመርነው ፕሮጀክት አለን። ተቀጣሪ የሆኑበት ሁኔታም አለ። በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ላይ ግን የተለየ ታሪክ ነው ያለው። ሠልጣኞች ሆቴሎች ጋር ሄደው ልምምድ ያደርጋሉ። ተመርቀው ከወጡ በኋላ ሳይሆን እስኪጨርሱ ሳይጠብቁም ይቀጠራሉ። በአንጻራዊነት በአገልግሎት ዘርፉ በኩል ያለው የተሻለ ነው። በማፋክቸሪንግ ዘርፉ ነው ቻሌንጅ ያለው፣ እሱን ደግሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው ደንብ አለ። ይሄ ደንብ የተባለውን ትስስር የሚፈጠርበትን መንገድ የሚያመቻች ነው።

አዲስ ዘመን :-በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የአሠልጣኞች ወይም የመምህራንን ብቃት እና ገቢያቸውንም ማሳደግ ወሳኝ ድርሻ አለውና ከዚህ አንጻር ምን እየተሠራ ነው?

ወ/ሮ ሙፈሪሃት:- ይሄም አንዱ የሪፎርም አጀንዳ ነው። ቀደም ሲል የተካሄዱ ጥናቶች አሉ። ተጨማሪ ዳሰሳዎችንም አድርገን የደረስንበት እኛ የምንገኝበት ቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ሥርዓት እያደገ ያለ ቢሆንም ሃገራት ከሄዱበት ርቀት አኳያ የማካካሻ ሥራ የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዳሉ ነው። እነዛን የማካካሻ ሥራዎች ለመሥራት የአሠልጣኙ ጉልበት እና ጥበብ በጣም ወሳኝ ነው ብለን ነው የተመለከትነው። የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችም አሉ። የዋሉ ያደሩ አዳዲስም የተፈጠሩም ሊኖሩ ይችላሉ። ይሄንን ማስተካከል ይኖርብናል።

አሠልጣኙ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ክህሎቶችን መታጠቅ ያስፈልገዋል። የመምህራን የአሠለጣጠን ዘይቤ ኢኖቬቲቭ የሆነ ነው። የምንሠራው ሥራ በዛ ደረጃ ትርጉም ያለው መሆን አለበት በሚል የተቀረጹ ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶች አሉ። ክረምት ላይ ሰፋ ያለ ሥልጠና እንሰጣለን ብለን ዝግጅት እያደረግን ነው ያለነው።

ከዛ ባሻገር ግን በመደበኛው የሥልጠና ፕሮግራሞች የማስተርስ፣ የፒኤችዲ ፕሮግራሞችን ጨምሮ ወይም በእኛ የሌቭል 7 እና 8 በሃገር ውስጥም በውጭም የአመራር ክህሎት ሥልጠናዎችን እየሰጠን ነው። መምህራንም ከደረጃ ወደ ደረጃ ማሸጋገር የሌቭል ሲ፣ ሌቭል ቢ፣ ሌቭል ኤ የሚባሉ የሥልጠና ሥርዓቶች አሉ። ከአንዱ እርከን ወደ አንዱ እርከን የሚሸጋገሩበት የቆየ የሥልጠና ሥርዓት አለ፤ እርሱንም ተግባራዊ እያደረግን ነው ያለነው።

ከኑሮ አኳያ መሻሻል አለባቸው ብለን የለየናቸው ጉዳዮች አሉ። የመንግሥት ደሞዝ እየጠበቁ፣ የመንግሥት ማሻሻያ እርከን እየጠበቁ መኖር በዚህ ዘርፍ ነውር ነው መሆን ያለበት፤ ቅድም እንዳነሳሁት ሌሎች የሌላቸውን ዕድል ይህ ዘርፍ አለው። የእንጨት ሥራ አሠልጣኝ የሆነ ሰው ለምሳሌ በሚጨምረውና በምትጨምረው እሴት ልክ ወደ እራሱ የሚሄድ ነገር ማምጣት ያስፈልጋል። በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ሥርዓት ውስጥ በደንብ እንዲጎለብት ማድረግ ያለብን እሴት እየጨመረ፣ ዘርፉንም እየጠቀመ እራሱንም እየጠቀመ የሚሄድበት ሥርዓት እንዲኖር ነው። የተጋ በትጋቱ ልክ የሚጠቀምበት ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ጀምረናል። አዲስ አበባ ለምሳሌ ወረድ ብላችሁ ብታዩ አንዳንድ ኮሌጆች አስራ አንዱንም ዘረ መሎች ተግባራዊ አድርገዋል። በተቋም ደረጃ እንደ ዊንጌት ያሉ ተቋሞቻችን ዓለም አቀፍ ሰርተፍኬት አግኝተዋል። ከተቋም አልፎ ደግሞ ወደ ግለሰብ አሠልጣኞቻችን እናሳድጋለን። እነዚህ አሠልጣኞች በዚህ ደረጃ ሰርቲፋይድ ከሆኑ የትኛውም የዓለም ጫፍ ላይ ሄደው መሥራት ይችላሉ ማለት ነው። ወደዛ ነው እየወሰድን ያለነው። ይሄ ሥራ የመምህራንን የአሠልጣኞችን ተነሳሽነት ንቃት እና በሂደት ውስጥ ተጠቃሚነት ይበልጥ እያጎለበተ ይሄዳል። እንደ አንድ የትኩረት አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራበት ነው ያለው። ሌሎችን ሲሠሩ ማውራት ይሻላል ። ሂደት ከምናገር ብዬ ነው።

አዲስ ዘመን :- የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናን ዘርፍ የዛሬ 10 ዓመት የት እንጠብቀው?

ወ/ሮ ሙፈሪሃት:- ጥሩ ማሰብ ጥሩ መመኘት እና ጥሩ መተለም በጣም ጥሩ ነው። እነዚህ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ሳይቆራረጡ በደንብ ከዳር መድረስ ከቻሉ ጨዋታ ለዋጭ የሆነ ዐሻራ ማኖር የሚችል ዘርፍ ነው ብዬ ነው የማስበው። በሰው ኃይልም ልማትም በቴክኖሎጂ ሽግግርም ኢትዮጵያን እንደ ሀገር በሁለት እግር የሚያቆሙ በርካታ ቴክኖሎጂዎች የሚወጡባቸው ማዕከላት ይሆናሉ። ብዙ ሚሊዮኖችን የሚለውጡና የሕይወት ትርጉም የሚሰጡ ማዕከላት ይሆናሉ። ዘርፉም እንደ ዘርፍ እንደዛ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እሴት ጨምሮ ተወዳዳሪ ሆኖ የሚወጣበትን ጉልበት የሚሰጥ ዘርፍ ይሆናል። በዚህ ሂደት ትርጉም ያላቸው ማኅበራዊ ኢኮኖሚያና ለፖለቲካዊ ስኬቶች እንዲሳኩ አስቻይም ዘርፍ ነው። እራሱ የዘርፉ ተቋማዊ ባሕሪ ማስቻል ነው። ግለሰብን ማስቻል፤ ቤተሰብን ማስቻል፤ ማኅበረሰብን ማስቻልና ተቋማትን ማስቻል ነውና። ይህን አስቻይነቱን በብቃት የተወጣ ዘርፍ መሆን ይችላል። ስለሆነም የኢትዮጵያ የእድገትና የመለወጥ ጉዞ ውስጥ ትርጉም ያለው አሻራ የሚያሳርፍ ዘርፍ ይሆናል። በአስር ዓመቱ በዚያ ደረጃ ልንጠብቀው እንችላለን። በአምስት ዓመት ውስጥ ደግሞ ዲጂታል ላይ ምን እናሳካለን ብለን ከወሰድን እራሳቸውን የቻሉ በራሳቸው ገቢ የሚተዳደሩ ለአሠልጣኞቻቸው ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ ሠልጣኞቻቸውን ተወዳዳሪ ያደረጉ የተበራከቱ ተቋማት ማየት ይቻላል ብዬ ነው የማስበው።

አዲስ ዘመን:- በመጨረሻም ያገናኘን የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ነውና ለዘርፉ ተዋንያን የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ዕድሉን ልስጥዎት።

ወ/ሮ ሙፈሪሀት:- መልካም እንግዲህ የዘርፉ ተዋንያን አንድም የገዘፈ ሚና ያላቸው መሆኑን ሁልጊዜ እንዲያስታውሱ አደራ ማለት እፈልጋለሁ። ሰዎች ዘርፉን ያስቀመጡት ቦታ ላይ ሳይሆን በዘርፉ ውስጥ የነቃ ሚና የሚጫወቱ አካላት ዘርፉ ውስጥ ያለውን ጉልበትና አቅም በደንብ ይገነዘባሉ ብዬ አምናለሁ። በጊዜያዊ የግንዛቤ ችግር ዘርፉን በተመለከተ የተለያየ አተያይና መረዳት ቢኖርም የዘርፉን እምቅ አቅም በማውጣት ረገድ ደግሞ ዘርፉ ውስጥ ያሉ ተዋንያን የማይተካ ድርሻ አላቸው። በግላቸውም እንደተቋምም ዘርፉ ውስጥ እንዳለ የቤተሰብ አባል የዘርፉን እምቅ አቅም በመግለጥ ሂደት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ አዕምሯቸውን፣ ልቦናቸውንና ወርቅ እጃቸውን አስተሳስረው የሚሠሩትን ሥራ በላቀ ትጋትና ጥራት መሥራት እንዲችሉ አደራ ማለት እፈልጋለሁኝ። እናንተ ያያችሁትን ብርሃን ሁሉም እንዲያይ በማድረግ ረገድ በተግባር እንገለጥ የሚል መልዕክት ነው ያለኝ።

አዲስ ዘመን :- ለሰጡኝ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ጊዜዎት እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።

ወ/ሮ ሙፈሪሃት:- እኔም በጣም ነው የማመሰግነው።

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You