የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሩን ስኬት ወደ ላቀ አፈጻጸም ደረጃ ለማድረስ!

ኢትዮጵያ የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የችግኝ ተከላ እያካሄደች ትገኛለች። ሀገሪቱ በእዚህ ክረምት ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ ባለፈው ሰኔ ወር በይፋ ወደ ተከላው ገብታለች። የችግኝ ተከላውም በየክልሎቹና ከተማ አስተዳደሮቹ በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ ነው። ሰሞኑን የወጣ መረጃ እንዳመለከተውም፤ እስከ አሁን አራት ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።

የዘንድሮው የችግኝ ተከላ የእስከአሁን አፈጻጸም፣ በችግኝ ተከላው ለመትከል ከታቀደው የችግኝ መጠን ከግማሽ በላይ መትከል መቻሉን ያመለክታል። የክረምቱ ወቅት ገና እንደመግባቱ የችግኝ ተከላው አፈጻጸም በጥሩ አፈጻጸምነት ሊያዝ የሚችል ነው። አፈጻጸሙ በዚህ ደረጃ ላይ ለመገኘቱ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። ለችግኝ ተከላው አስቀድሞ የተደረገው በቂ ዝግጅት፣ ዝናቡ የሰጠ መሆኑ፣ ዜጎችን በችግኝ ተከላው በማስተባበር በኩል ጥሩ መሠራቱ የሚሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ባለፉት ዓመታት በችግኝ ተከላው ያካበቱት ልምድ ለእዚህ ዓመቱ የችግኝ ተ ከላ አስተዋጽኦ አበርክቷል ተብሎ ሊወሰድ ይችላል።

እንደሚታወቀው፤ ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ከዕቅድ በላይ ሠርታለች። በችግኝ ተከላውም 20 ሚሊዮን ዜጎቿን አሳትፋለች። በ2011 ዓ/ም በተጀመረው በዚህ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር እስከ አለፈው ዓመት ድረስ 32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል። በአንድ ጀንበር ለመትከል ከታቀደውም በላይ ሲተከል እንደነበርም ይታወቃል።

ዘንድሮ እስከ አሁን የተተከሉት ችግኞች ብዛት ሲታሰብ ይህ የመርሀ ግብሩ ያለፉት ዓመታት ትልቅ ስኬት በዘንድሮ የችግኝ ተከላ ከፍተኛ ተሞክሮ እንደሚያበረክት ይታመናል። ተሞክሮው በዚህ ዓመት የችግኝ ተከላም ያለፉትን ስኬታማ ተግባሮች መድገም እንደሚቻል ያመለክታል። ዜጎች ለችግኝ ተከላው በቀጣይም በስፋት የሚወጡባቸው ጊዜያት አሁንም ሰፊ ናቸው። እነዚህን ጊዜያት በአግባቡ በመጠቀም የችግኝ ተከላውን አስቀድሞ በማጠናቀቅ ስኬታማነቱን በሚገባ ማሳየት ይገባል።

ለብልህ አይነግሩም፤ ለአንበሳ አይመትሩም እንደሚባለው ኢትዮጵያውያን በችግኝ ተከላው ስማችሁ በደማቁ የተመዘገበ እንደመሆኑ በችግኝ ተከላው የሚያደርጉትን ርብርብ እንደሚያጠናክሩ ይጠበቃል። የችግኝ ተከላውን የምትመሩ አካላትም ችግኞቹን በወቅቱ በሚተከሉባቸው ሥፍራዎች በማድረስ፣ ሕዝቡን በማስተባበር ችግኞቹ ፈጥነው እንዲተከሉ ለማድረግ እስከ አሁን ከምታደርጉትም ጥረት በ ላይ ርብርብ ማድረግ ይኖርባችኋል።

በችግኝ ተከላው ስኬታማ መሆን የተቻለው ከእቅድ በላይ ችግኞችን በመትከል ፣ ሕዝቡንም ለእዚህ ታላቅ ሀገራዊ አጀንዳ ማሰለፍ በመቻልና በመሳሰሉት ብቻ አይደለም። ችግኝ ተከላው በአካባቢ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንዲችል በማድረግም ነው። ይህ ደግሞ የችግኝ እንክብካቤን የግድ ይላል። በዚህም በኩል ውጤታማ መሆን እየተቻለ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የችግኞች የጽድቀት መጠን እየጨመረ መምጣቱም ይህንኑ ይጠቁማል።

የችግኝ ተከላው ትሩፋቶች ገና ከወዲሁ መታየትም ጀምረዋል። መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ የሀገሪቱ የደን ሽፋን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከተጀመረበት የፈረንጆቹ 2019 ከነበረበት 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ወደ 23 ነጥብ ስድስት በመቶ ከፍ ብሏል። ይህ ሌላው የመርሃ ግብሩ ስኬት ትልቁ ማሳያ ነው። በመርሀ ግብሩ ከተተከሉ ችግኞች መካከል እንደ አቮካዶ ያሉ የፍራፍሬ ተክሎች ችግኞች ይገኙበታል። እነዚህ ችግኞች ለፍሬ ደርሰው ለውጭ ገበያ ለመቅረብ የበቁበት ሁኔታም ይታያል። ይህ ሁሉ የሚያመለክተው መርሀ ግብሩ ለአካባቢ አየር ንብረት መጠበቅ፣ ለምግብ ዋስትና መጠበቅ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ወዘተ. አስተዋጽኦ በማበርከት ግቡን ወደ መምታት እያመራ መሆኑን ነ ው።

እነዚህ ሁሉ ስኬቶች የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ በስኬት ለማጠናቀቅ ትልቅ አቅም ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል። የዘንድሮው የዝናብ ይዞታ ለችግኝ ተከላ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ይታመናል። ስለሆነም ይህን ምቹ ሁኔታም አሟጦ መጠቀምም ይገባል።

የክረምቱ ወቅት ገና እንደመያዙና በቀጣይም ችግኝ ለመትከል ሰፊ ጊዜ እንደመኖሩ በእቅድ የተቀመጡትን ችግኞች በሙሉ መትከል ይቻላል። ይህ ብቻም አይደለም፤ ይተከላሉ ተብለው ከሚጠበቁት ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችም በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ቀሪው ጊዜ እነዚህንም ችግኞች ለመትከል የሚያስችል እንደሚሆን ይታመናል። አሁን ያለነው ሀምሌ ወር አጋማሽ ላይ ነው፤ የክረምቱ ዝናብ እስከ መስከረም ድረስ ይዘለቃል ተብሎ ይታሰባል፤ በእነዚህ ጊዜያትም ችግኞችን መትከል ይቻላል፤ ጊዜ አለ በሚል መዘናጋት ውስጥ ባለመግባት ችግኞቹን አስቀድሞ መትከል ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን በእቅዱ ለመትከል ከተያዙት ችግኞችም በላይ ለመትከል፣ በችግኞች የመጽደቅ ምጣኔ ላይም የበለጠ ለውጥ ማምጣት፣ አጠቃላይ የአረንጓዴ ዐሻራ መርህ ግብሩን ስኬት ወደ ላቀ የአፈጸጸም ምዕራፍ ማድረስም ይቻላል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You