ፈገግታ… የህይወት ምንጭ ጠብታ…የሰው ልጆች ሁሉ ውስጣዊ ልምላሜ ነው። የጥርስን ነጸብራቅ ፊት ላይ ያስቀምጣል። ደስታን እያፈካ ሀዘንን ያከስማል። ከስጦታዎችም ሁሉ ትልቁ ስጦታ ይኼን ለመስጠትና ለመቀበል መታደል ነው። እንዲህ አይነት ሰዎችም ከማንም በላይ ለልባችን ቅርብ ሆነው ይታያሉ። እነርሱ ተጨንቀው ወልደው ፈገግታን ለኛ ይሰጡናል። ባኮረፈች ዓለም ውስጥ ፈገግታና ሳቅን መፍጠር እጅግ ፈታኙ ቅጽበት ነው። እናም መመረጥን ይሻል።
በእያንዳንዱ ድራማዊ መድረኮች ላይ ትወናን እንመለከታለን። ተውኖ ለማስለቀስ ምናልባትም የተዋጣለት አስመሳይ መሆንና ማስመሰል በቂ ሊሆን ይችላል። በትወና ውስጥ አስመስሎ ብቻ ማሳቅ ግን አይቻልም። ለዚህም ነው በዓለማችን ላይ ከተመለከትናቸው እልፍ ተዋንያን መሀከል ጥቂቱ ብቻ ሳቅን መፍጠር የሚችሉ ኮሜዲያን ሆነው የምናያቸው። እነርሱ ማለት በደስታና በሳቅ የሚያቀጣጥሉን የህይወታችን ማጣፈጫ ቅመሞች ናቸውና በተመለከትናቸው ቁጥር የፈገግታ ሱስ ያሲዙናል። ውስጣዊ ስሜታችን ከቀልዶቻቸው ጫፍ ጋር ስለሚተሳሰርም እድሜ ዘመናችንን ሁሉ እንድናስታውሳቸው የሚያደርግ ተፈጥሯዊ መስተጋብር መሀከላችን ይፈጠራል። ታዲያ በዚህ ሁሉ መሀከል፣ ለዚህ ሁሉ ነገር እናት ለመሆን መቻል ማለት እንዴትስ ያለው መታደልና መመረጥ ቢኖረው ነው?
በአንድ ማኅበረሰብ ቤተሰብ ውስጥ እናትነት ለአንዲት ሴት ብቻ የሚሰጥ ጸጋ እንደመሆኑ በሀገራችን የኮሜዲ መድረክ ላይ እናትነቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተቀበለች እንቁም ታይታለች። “የኮሜዲ እናት!” ተብሎ ከተጠራ ይህች እናት ማን እንደሆነች ለማወቅ ማሰብ አይጠበቅም። አሻሚነት ኖሮትም አያከራክርም። ምክንያቱም ብቸኛዋ ሴት ሆና በብዙ የወንዶች ስብስብ ውስጥ ድንገት ብቅ በማለት የእናትነቱን ማዕረግ የወሰደች፤ ከእንግዳዘር ነጋ ሌላ ሴት የለችምና።
በእንቁ ባለ ጥበብ የአልማዝ ፈርጥ አጊጣና አምራ ድንገት መሀል ላይ የተገኘች አዲስና ክብርት እንግዳ ነበረች። የአንደኛው ዘመን የሳቅ እናትና የፈገግታ ቀዳማዊት እመቤት ነበረች። እናም ታዲያ አንድም በድንቅ ችሎታዋ ሁለትም በቀዳማይነቷ “የኮሜዲ እናት” የሚል ስያሜን ለማግኘት በቃች። ምን ሠርታ ታወቀች? ከተባለ እርሷ ያልሠራችው የለምና…
እንግዳ ዘር የፈገግታ ጥኡም ፍሬ…ቀድማ የበቀለች፣ ቀድማም የደረሰች የኮሜዲው እናት፣ የሳቅ ደምስር ነበረች። ብዙ ሰዎች እርሷን ለመመልከት ሲሉ ተጋፍተው መድረክ ታድመዋል። ብዙ ሰዎችም የራዲዮናቸውን አንቴና እያዞሩ ከፍተው ድምጿን ለመስማት ተቻኩለዋል። ዛሬ እንግዳዘር ነጋ የምትተውንበት ድራማ ይታያል በማለት ተሰባስበው ከቴሌቪዥኖቻቸው መስኮት ፊት ተኮልኩለው ጠብቀዋል። ምክንያቱም እሷ ፈጠራን ትችልበታለች። እየፈጠረችም በቀልዶቿ ሙሉ አዳራሹን ያለ እረፍት ታንከተክተዋለች። በመድረክ፣ በራዲዮና በቴሌቪዥን ስትተውን ደግሞ ቢያዩዋትም ሆነ ቢሰሟት ስሜት ባክኖ ከመሬት ጠብ አይልም። በዚህም በዚያም ቀልብን ሰውራ ታፈዛለች። በእነዚሁ ዘርፈ ብዙ ድንቅ ችሎታዋ ምትሀተኛም ጭምር ናት። ከዚያው ላይ ደግሞ የሕዝብን መውደድ ደርቦላት፤ በሕዝብ ፊት እንደ ንጉስ ጌጥ አብረቅርቃ ታይታለች። ይህች ታላቅ የጥበብ ሰው እንደዚህም ሆና በአንደኛው የኋላ ዘመን ታሪክ ውስጥ ነበረች። አንጋፋዋ አርቲስት እንግዳዘር ነጋ…
የሰው ልጅ ሁሉ የራሱ ብቻ የሆኑ በርካታ የህይወት ምዕራፎች ይኖሩታል። እንደማንነቱ ሁሉ በብዙ ክፍሎች የታጨቁ ብዙ ገጾችንም ይደጉሳል። እንደቻለው ሁሉም ህይወቱን ይጽፋታል። እንደጻፈውም ይነበብለታል። በመነሻው ጀምሮም በመጨረሻው ያሳርጋል። የኢትዮጵያን የኮሜዲ መድረክ ስንገልጥ ከፊት እንግዳዘር ነጋን እናገኛለን። በእንግዳዘር ውስጥም እኚህኑ ባለምዕራፍ ገጾችን እንመለከታለን። ምናልባትም ደግሞ የድጓሱ መጀመሪያና መጨረሻ “ገድለ እንግዳዘር” የሚል አርዕስትም እናገኝ ይሆናል። የመጀመሪያው ምዕራፍ በመጀመሪያውም ገጽ ላይ እንግዳዘር ነጋ በ1944ዓ.ም በደብረማርቆስ ከተማ ውስጥ ተወለደች ብሎ ይጀምራል። ሰሜናዊቷ የጓጃም ምድር፣ የደብረማርቆስ የፍቅር አየር ከወዲያው ጠራት። በዚያም ተወልዳ የመጀመሪያውን ምዕራፍ አንድ ገለጠች። የብቃቷ እንቡጥ ፍሬ ያሸተበት የመጀመሪያው ገጽ ልጅነቷ ነበር።
ስለ ጥበብ ተጋድሎዋ የሚጀምረው ወጣት መስላ በታየችበት ወቅት ሳይሆን ገና ታዳጊ ሆና በኖረችባቸው ዓመታት ውስጥ ነበር። በጊዜው ልጅነቷን የተመለከቱ ሁሉ ውበቷ የጥበብ ጽራር እንደነበረ ያውቃሉ። ፊቷ ላይ ካሉት አፍንጫና ዓይኖቿ ይልቅ አንዳች የጥበብ ዓይነስብ እንደተቀመጠባት ይታይ ነበር። ልጅነቷ ላይ ብዙ የጥበብ ገጾች ስለመኖራቸው በርካቶች ያወሱታል። በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ በአስኳላ የቀለም ትምህርት ቤቶች ተገኘች። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቅችውም በተወለደችበት የደብረማርቆስ ከተማ ውስጥ ነበር። በቀጣይም የትውልድ ቀዬዋን ለቃ ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ አመራች። ወደ መምህራን ኮሌጅ በመግባትም በጥሳ ወጣች።
ሁለተኛው የህይወት ምዕራፏም የሚጀምረው ከዚሁ ቀጥሎ ነበር። የኑሮ እንጀራዋም በተማረችበት የመምህርነት ሙያ ላይ አረፈ። ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር በመምህርነት ስታገለግል ድፍን 11 ዓመታት ተቆጠሩ። በኋላም በኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ውስጥ ተቀጥራ መሥራት ጀመረች። ለተወሰኑ ጊዜያት ስታገለግል ከሰነበተች በኋላም ወደ ሦስተኛው ምዕራፍ ከመሸጋገሪያ መንገዷ ጋር ተገናኘች። በ1979ዓ.ም ወሳኙን የህይወት ምዕራፍ የከፈተችበት ቁልፍ ነበር። እንግዳዘር ነጋ በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ውስጥ የመሥራት ዕድሉን አገኘች፡፡
ከልጅነቷ አንስቶ በውስጧ የተሸከመችው ጥበብ በውስጧ ቢኖርም እንዲሁ በአጋጣሚዎች ካልሆነ በስተቀር ራሷን ለማሳየት የሚሆን አጋጣሚ አላገኘችም። እናም አሁን በትክክለኛው ጊዜና ቦታ መገኛት ካለባት ቦታ የተገኘችው ገና አሁን ነበር። እዚህ ስፍራ ላይ ያላትን ለማውጣት አመቺ ከመሆኑም ውስጧን ለመረዳት ቅርብ የሆኑ ሰዎችንም ጭምር ለመገናኘት ቻለች። በወቅቱም አለባቸው ተካ፣ አስረስ በቀለ እና ልመንህ በተቋሙ ውስጥና በመላው ሀገሪቱ በዋናነትም በኮሜዲው ተወዳጅነትን ያተረፉበት ነበር። ከእነዚህም ጋር አብሮ ወደመሥራት የሚያስገባው ግዙፍ በር ተከፈተላት። የመጀመሪያዋ ሴት ኮሜዲያን ሆናም በቴሌቪዥንና በራዲዮ ብቅ አለች። ብዙዎችም ያላትንና ያመጣችውን አዲስ ነገር ወደዱላት። አደነቁላት። በጥቂት ጊዜያት ውስጥም የዝና ማማው ላይ ወጣች። በዚያን ጊዜ ሴቷ ኮሜዲያን ከተባለ እሷም እንግዳዘር ነጋ ነበረች። እዚህ ቤት ውስጥም የክብር ዘውዷን እንደደፋች ለ20 ዓመታት ያህል ዘልቃለች፡፡
ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የነበረው የእሁድ መዝናኛ ዝግጅት ለአፍታም ቢሆን እንግዳዘርን አይዘነጋም። በዚያም ሰሞን ላይ ጀማሪ ሆነው በጥበብ ጉዞ ከጀመሩትና በአሁኑ ሰዓት ከአንጋፋዎቹ ተርታ ከተሰለፉት መሀከል አንዱ ሰይፉ ፋንታሁን ነበር። በወቅቱ የሙያ ትምህርት ቤቱ ከሆኑት አንዷ ናት። በተለያዩ ጭውውትና ድራማዎችም አብረው ለመሥራት ችለዋል። እርሷ የራሷ ብቻም ሳትሆን በነበረችባቸው ጊዜያት አብረው ለሠሩ ሁሉ ደማቅ ጮራ ነበረች። ኮሜዲውን የተሸከሙት ድራማና ጭውውቶች እንደ አደይ አበባ የፈኩበት ጊዜ ነበር። እንግዳዘር ነጋ፣ ክበበው ገዳ፣ አለባቸው ተካ፣ ደረጀ ኃይሌ፣ ሀብሬ ምትኩ፣ ተስፋዬ ካሳ፣ አለልኝ መኳንት፣ አበበ በለውና አስረስ እንዲሁም ሌሎች ዘመን አይሽሬ በዘመንም አይተኬ ጥምረትና ውህደት ነበሩ።
በበዓላትና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ላይ የሚያቀርቧቸው ጭውውቶች በሳቅ ነብስን የሚዘሩም ነበሩ። ታዳሚው ከየመቀመጫው እየተነሳ ሁሉ ሆዱን ይዞ ያነፍራል። የእንግዳዘርና የአስረስ በቀለ ጥምረት ደግሞ የተለየ ነበር። በአንደኛው መድረክ እንግዳዘር ለወራት ወንድሟ ጋር ከአሜሪካ ደርሳ የተመለሰችውን የንግስትን ገጸ ባህሪ ትጫወታለች። አስረስ በቀለ ደግሞ ባላገር ዘመዷ ሸዋንግዛውን ነበር። ከጨዋታቸው መሀልም ሸዋንግዛው ስለአሜሪካው ወንድሟ ስለ ጴጥሮስ ይጠይቃታል።
…
“ጴ…ጥ…ሮስ! ትላለህ…በእነርሱ ፒተር ነው የሚባለው። አሁን ለምሳሌ ሙሉ ጎጃምን ታውቃታለህ?”
“አዎ!”
“እሷን አሁን ኤም ጂ ነው የሚሏት። …ደግሞ ያ ማነው…ዮሐንስን ታውቀዋለህ? እሱም ጆኒ ነው የሚባለው፡፡” ትለዋለች።
“ቆይ ይህቺ አማሪካን ስም ስትገለባብጥ ነው እንዴ የምትኖረው! ..አሁን እንግዲ ጉድ ላመጣልሽ ነው። እኔ አሁን ስሜ ሸዋንግዛው ነው ታዲያ እስቲ አማሪካን እኔን አሁን ማን ብላ ነው የምትጠራው?”
“ማ አንተን?”
“አዎ”
ጥቂት አሰብ አደረገችና “አንተን…አንተንማ ማን መሰለህ… ሸዋ ፊንገር ነው የምትልህ! …”
…
በሌላ የጥያቄና መልስ ጭውውታቸው ደግሞ ከአሜሪካን የተመለሱ ባልና ሚስት ሆነው ይተውናሉ። በአንድ መድረክ ላይም እንግዳ በመሆን ሁለቱም ከመድረክ ላይ ይወጣሉ። ጠያቂውም “አሜሪካን እንዴት አገኛችኋት?” በማለት ሲጠይቅ፡፡
“አሜሪካንን እኛ አይደለንም ያገኘናት። ማነው ይኼ…ኮሎምበስ ነው ያገኛት፡፡”
“እንግሊዝኛ ይችላሉ?”
…
“ኦፍኮረስ….ያ!…ኢቭን…የስ..” አንድ በአንድ የሚያውቋቸውን ቃላት ያንጠባጥቡታል።
ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር እልፍ የሴት ጠቢባን ወጥተው እጃችንን ከአፋችን ላይ አስደርበውናል። ዛሬ እንዳሉ ሁሉ ትናንትም ነበሩ። በአንደኛው ነገር ላይ ግን የመጀመሪያዋ ሴት ለመባል የቻሉ ጥቂት ናቸው። ከእነርሱም አንዷ እንግዳዘር ነጋ ናት። በሀገራችን የኮሜዲ መድረክ ላይ የትኛዎቹም ሴቶች ሳይወጡበት በፊት ቀድማ ታይታበታለች። “የመጀመሪያዋ ሴት ኮሜዲያን” የሚለውንም ቀዳማይ የክብር አርማ ተቀበለች። በነበራት የ20 ዓመታት ቆይታዋ የሠራቻቸው ሥራዎች ዛሬም ድረስ ከብዙዎች የተለየች እንድትሆን አድርጓታል።
በጭውውትና በድራማው ውስጥ በእርሷ ልክ ወርቃማ ዘመናትን የተቀዳጀ ያለ አይመስልም። አብዛኛዎቹን ድራማና ጭውውቶችን ጽፋ የምታዘጋጀው እራሷ እንግዳዘር ነበረች። የትወና ብቃቷና አድማጭ ተመልካቹን የማዝናናት ልዩ ተሰጥኦዋ ደግሞ ጥርስ የማያስከድን ነበር። ብዙዎች “የኮሜዲ እናት” ብለው እንዲጠሯት ያስገደዳቸውም ይኼው ነበር። ዳሩ እንዲህ ይሁን እንጂ፤ የእርሷ ነገር ግን “ጅብ ካለፈ ውሻ ጮኸ” ዓይነት ነው፡፡
የእንግዳዘርን የችሎታዋን ልክና የውለታዋን ቁና የተረዱ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለእርሷ ከማውራት አይቦዝኑም። በተለይ ደግሞ የሥራ ባልደረባዋ የነበሩት ከማንም በላይ ያውቋታል። ከእነዚህም አንዱ አስረስ በቀለ ነው። አልሆንልህ እያለው ጊዜን ሲጠባበቅ ቢቆይም ለረዥም ጊዜያት ስለ እንግዳዘር ነጋ አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ሲያስብ ቆይቷል። እርሷን ለመዘከር የሚሆን አንድ የጥበብ ምሽት የማዘጋጀት ትልቅ ፍላጎት እንዳለው በአጋጣሚዎች ለብዙ ወዳጆቹ አጫውቶም ነበር።
አንደኛው ምዕራፍ ተዘግቶ ሌላም ይገለጣል። ከአንደኛው የህይወት ገጽ ወደሌላኛው እየተሸጋገሩ በሄዱ ቁጥርም ወደ አንድ ነገር እየቀረቡ መሆኑ ግልጽ ነው። አርቲስቷ እንግዳዘር ነጋ የምዕራፍ ሦስት ጀንበሯ ጠልቆ ከአራተኛውና ከመጨረሻው የህይወት ምዕራፍ ላይ ተገለጠች። ሁሉንም የሰው ልጆች አንድ የሚያደርገውም ምናልባትም ይኼኛው ምዕራፍ ነው። በምዕራፍ አንድ የመጣ ሁሉ የመጨረሻውን የምድር ቆይታውን አጠናቆ በምዕራፍ አራት ተመልሶ መሄዱ ግድ ነው። “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” የሚለውን የፈጣሪን ቃልና የተፈጥሮን ህግ ጥሶ ለማምለጥ የሚቻለው አንድም የሰው ልጅ የለምና።
በስንብቱም ስጋና አጥንቱን ለመጣበት አፈር መልሶ ይሰጣል። ነብሱንም ለሰጠው ፈጣሪው ያስረክባል። ታላቁን ስምና ሥራውን ግን ለሰው ልጆች በስጦታ ያበረክትለታል። ከአፈሩ ከፍ ብሎ ከመቃብር በላይ የሚታየውም በዚሁ ስጦታው ነው። በህይወት ሳሉ ለመስጠት ያልታደሉም ከሞት ወዲያ ከአንዲት የድንጋይ ሐውልት በስተቀር ሌላ ምንም አይኖራቸውም። ለሰጡቱ ደግሞ ከሞት ወዲያም ህይወት አለ። ሠርተው ያለፉት ሥራ ሁሉ በሚመጣው ትውልድ አደባባይ ላይ የሚቆም የጀግንነትና የመታሰቢያ ሐውልት ሆኖ ይታይላቸዋል። ይህን ለማድረግ የሚችሉ ግን ከብዙ መሀከል ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ከእነርሱም እንደ እንግዳዘር ነጋ ያሉቱ ብቻ ናቸው። አርቲስት እንግዳዘር ነጋም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አራተኛውን ምዕራፏ በአውሮፓውያኑ 2004ዓ.ም በድንገት ተዘጋ። ታላላቆች ግን መጀመሪያ እንጂ የሚያልቅ መጨረሻ የላቸውም።
ተገልጦና ተነቦ ከሚያልቀው አራተኛው ምዕራፍ በኋላ ለዘለዓለም በቃላት የማይገለጽ፣ ህልቁ መሳፍርት ገጾች የታጨቁበትና ከምድር እስከሰማይ የሚረዝመው አምስተኛው ምዕራፍ ይቀጥላል፤ ግን ደግሞ አያቆምም። ከዚህ ምዕራፍ ላይ የሚደርሱ አሁንም እንደ እንግዳዘር ያሉት ብቻ ናቸው።
የባለውለታዋ ውለታ ለማስታወስ ምናልባትም የተደረጉ አንዳንድ መልካም ነገሮች ተቀምጠዋል። ስምን ከሰማይ በታች ካለ የምድር ጥላ ላይ ከማሳረፍ በላይ ምን አለና? እንግዳዘር ነጋ ዛሬ ላይ ከአንድ ባንክ ደጃፍ ላይ ግዙፍ ሥራዋ ከስሟ ጋር አቁሞላታል። የኮሜዲው እናት ናትና፤ እናት ባንክም በአዲስ አበባ ተክለሃይማኖት ሰፈር ውስጥ ያለውን ቅርንጫፉን በስሟ ሰይሞታል።
አርቲስት እንግዳዘር ቅርንጫፍ…የእርሷ የጥበብ ህይወትና የአምስተኛው ምዕራፏ ግንድም ከአፈር በላይ ሆኖ በስር ላይ ሌላ ስር እያበቀለ ቅርንጫፎቿን እንደ ሰማይ ክዋክብት፣ እንደ ምድር አሸዋም እያበዛው ይሄዳል። እንደ ወንዝ ዳር ቄጤማ፣ እንደ ጸደይ አበባም ያለመልመዋል። የፈገግታ እናትነቷም በአምስተኛው ሌላ ምዕራፍ በእልፍ ገጾች ሲገለጥ ይሄዳል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም