ይበል የሚያስብለው የብሔራዊ ባንክ ርምጃ፤

መንግሥት የዋጋ ግሽበቱንና እሱን ተከትሎ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ ነው።በፍላጎትንና አቅርቦትን ለማመጣጠን ምርትንና ምርታማነት ለማሻሻል የግብርና ሜካናዜሽን፣ ኩታ ገጠም ግብርናን፣ በመስኖ በመታገዝ በዓመት ሦስት ጊዜ ለማምረት፣ እንዲሁም በሌማት ትሩፋት ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም ይበል የሚያሰኝ የምርት እድገት የታየ ቢሆንም፣ የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያለ ትብታብ አመድ አፋሽ እያደረገው ይገኛል።

ይሄንንም ችግር ለመሻገር በሚል፣ ለአብነት በአዲስ አበባ አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ ለማገናኘት የገበያ ማዕከላትን በሁሉም የመዲናዋ መግቢያዎች በመገንባት፤ ለሸማች ሕብረት ሥራ ማህበራት ተዘዋዋሪ ፈንድ በማቅረብ እንዲሁም የሰንበት ገበያዎችን በማበረታታት ገበያውን ለማረጋጋት ጥረት ተደርጓል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የፊስካልና የሞኒተሪ ወይም የገንዘብ ፖሊሲውን ለመቃኘት ማሻሻያዎች እየተደረጉ ይገኛል።

ከፊስካል ፖሊሲ አንጻር መንግሥት ዕቅዱን፣ በጀቱን ወይም ገቢና ወጪውን የዋጋ ግሽበቱን ከማረጋጋት አኳያ ሲቃኝ፤ በኢኮኖሚው ውስጥ የገንዘብ ዝውውሩን፣ ስርጭቱን፣ መጠኑን፣ የውጭ ምንዛሬን ምንዛሬን በመተመን የገንዘብ ወይም የሞኒተሪ ፖሊሲውን ያሻሽላል። ይሄንን ለመረዳት ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ ያደረገውን የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ አዋጅ እንቃኝ።

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ ከአሥር ወራት ቀደም ብሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የዋጋ ንረት ላለፉት በርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ከባድ የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተና ሆኖ መቆየቱን አምነዋል። ‹‹ባለፉት አሥር ዓመታት የዋጋ ንረት በአማካይ ከ16 በመቶ በላይ ዕድገት አሳይቷል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ በአማካይ ከ30 በመቶ በላይ ዕድገት አሳይቷል። የዋጋ ንረት በደሃው የኅብረተሰብ ክፍል የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ብዙ ጉዳት አለው። የዋጋ ንረት ለረዥም ጊዜ በቆየ ቁጥር አሁን በኢትዮጵያ እንደሆነው ሥር የሰደደ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥጋት ይፈጥራል። የዋጋ ንረት ይኖራል የሚለው ሥጋት በራሱ ለዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት ይሆናል›› ሲሉ በዚያ መግለጫ ተናግረው ነበር።

በወቅቱም፣ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጥብቅ የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ቃል ገብተው ነበር። ከአምስት ወራት ቀደም ብሎ ደግሞ ከብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ባንኩ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ዋና ትኩረቱ አድርጎ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም በስድስት ወራት ውስጥ የዋጋ ንረት ምጣኔ ላይ አንፃራዊ ቅናሽ መመዝገቡን ተናግረው ነበር።

በዚህ ዙሪያ የተለያዩ ዘገባዎች እንዳመለከቱት፤ በወቅቱ ገዢው፣ ‹‹በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የብድር ዕድገት በ14 በመቶ ገተነዋል። ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ ብድርም በ75 በመቶ ቀንሰነዋል። ባንኮች ወደ እኛ ለብድር ሲመጡ የምናስከፍለውን ወለድ ምጣኔ ወደ 18 በመቶ አሳድገነዋል። የገንዘብ ሚኒስቴርም ጥብቅ የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲ መከተል ጀምሯል። የመንግሥት የሀብት አጠቃቀምን ከብክነት በፀዳ መንገድ ለመምራት የሚያስችሉ ጥብቅ አሠራሮች ተዘርግተዋል፤›› ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፤ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በወሬ ሳይሆን ተጨባጭ ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስረድተው ነበር።

ይሁን እንጂ እሳቸውም ሆኑ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ተጨባጭ ዕርምጃዎችን መውሰድ ስለመጀመራቸው ብዙ ቢናገሩም፣ ነገር ግን እስካሁንም የኢትዮጵያን ገበያ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ተጭኖት ይገኛል። በመሆኑም ይሄንን እውነት በመገንዘብ እና የተነገረውን ቃል ለመፈጸም ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣቸው አዳዲስ አዋጆችና የአሠራር ማሻሻያዎቹ የዋጋ ንረቱን በመሠረታዊነት የሚፈቱ ዕርምጃዎችን አካቶ ማቅረቡ ትልቅ ዕርምጃ ነው።

በተለይ አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ አዋጅ ከዚህ ቀደም ለረዥም ዓመታት ሲሠራበት የቆየና ለዋጋ ንረት ዋና መነሻ ነበር። በመሆኑም በቆየው አሠራር ላይ ጠበቅ ያለ የማሻሻያ ድንጋጌ ይዞ መቅረቡ የሚያስመሰግነው ነው።

በዚህ ረገድ የብሔራዊ ባንክ ግብ የፋይናንስና የዋጋ ንረትን ማረጋጋት እንደሆነ በመጥቀስ የሚንደረደረው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጡ አዋጆችም ይህንኑ ግብ ለማሳካት በሚያስችል መንገድ በየጊዜው ማሻሻያ ሲደረግባቸው መቆየቱን ያትታል። ብሔራዊ ባንክን መጀመሪያ ያቋቋመው ቻርተር ቁ.30/1955 ከወጣ በኋላ በ1955፣ በ1968፣ በ1986 እና በ2000 የወጡ የገንዘብና የባንክ አዋጆች መኖራቸውን ይጠቅሳል።

እነዚህ አዋጆች የወጡባቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዐውዶች የተለያዩ ቢሆንም፣ ለብሔራዊ ባንክ ቁልፍ ሚናና ተቋማዊ ህልውና ዕውቅና የሰጡ እንደነበሩ ይጠቁማል። የብሔራዊ ባንክን ሥልጣንና ኃላፊነት፣ የባንኩን አስተዳደር፣ ባንኩ ከሌሎች የመንግሥት አካላት ጋር የሚኖረውን ግንኙነትንም የሚወስኑ ሕጋዊ ማዕቀፎችን በግልጽ ያብራሩና ያስቀመጡ፣ የባንኩን ካፒታል ያሳደጉ እንደነበሩም ይገልጻል።

እነዚህ አዋጆች ብሔራዊ ባንኩ ከመንግሥት ጋር የነበረውን ግንኙነት በምን መንገድ እንደወሰኑ አንድ በአንድ ያብራራል። በ1955 ዓ.ም. የወጣው የገንዘብና የባንክ አዋጅ ባንኩ ከመንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት ሲዘረዝር፣ ባንኩ ለመንግሥት የሚሰጠው ቀጥታ ብድር መጠን መንግሥት ባለፈው ዓመት ከሰበሰበው ገቢ 15 በመቶ እንዳይበልጥ የሚያስገድድ ሲሆን፤ በብድሩ ላይ ከሦስት በመቶ ያልበለጠ ዓመታዊ ወለድ እንደሚከፈልበትና ብድሩ የበጀት ዓመቱ ባለቀ በስድስት ወራት ውስጥ መከፈል እንዳለበት ይደነግጋል።

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያውን ሲቀጥልም፣ በ1968 ዓ.ም. የወጣው የገንዘብና የባንክ ሥርዓት ቁጥጥር አዋጅ በበኩሉ፣ መንግሥት ከባንኩ የሚወስደውን የብድር መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ገቢ ከ25 በመቶ እንዳይበልጥ ከማድረግ ውጪ፤ የወለድ ተመኑም ሆነ የብድር መመለሻ ጊዜው ከ1963 ዓ.ም አዋጅ ጋር ተመሳሳይ እንዲሆን አድርጎታል ይላል። የ1963 ዓ.ም. ያለውን አዋጅ ይዘት ግን ሳይዘረዝር ነው ያለፈው።

ቀጥሎ የሚያነሳው በ1986 ዓ.ም. የወጣው የገንዘብና የባንክ አዋጅም ከብሔራዊ ባንክ የሚለቀቀው የቀጥታ ብድር መጠን መንግሥት ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሰበሰበው አማካይ ገቢ ከ15 በመቶ እንደማይበልጥ፣ ብድሩም በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ ማለቅ እንዳለበት፣ ወለዱንም ባንኩ በገበያ ዋጋ እንደሚወስን ያስቀመጠ እንደሆነ ረቂቅ አዋጁ ያመለክታል።

ቀጥሎ የመጣው ያለው አዋጅ ቁጥር 591/2000 ግን፣ ቀደም ሲል የወጡ አዋጆችን ያሻሻለ ሲሆን፣ የመንግሥትና የብሔራዊ ባንክ የብድር ግንኙነት ገደብ ባለው መንገድ እንዳይመራ ያደረገ መሆኑን በግልጽ ይጠቁማል። በ2000 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ባንኩ ለመንግሥትና ለፋይናንስ ተቋማት ብድር እንደሚሰጥ ከመግለጽ ውጪ ለመንግሥት በሚሰጠው ቀጥታ ብድር ላይ ግን ምንም ገደብ ሳይጥል በለሆሳስ ያለፈ የመጀመሪያው አዋጅ ነው ሲልም፣ አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ አዋጅ አስቀምጦታል። በመሆኑም ይህ በ2000 ዓ.ም. የወጣ አዋጅም ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን የሚቆጣጠርበትን አቅም ያዳከመ እንደነበር ጠቁሞ፣ አካሄዱ የዋጋ ንረትን አባባሽ መሆኑን ነው ያመለከተው።

ይህን ለመቀየር አዲስ የአዋጅ ማሻሻያ ማስፈለጉን የጠቆመው አዋጁ፣ በዚህም መሠረት፣ ‹‹በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 27 መሠረት ብሔራዊ ባንክ በጥሬ ገንዘብ ፍሰት ላይ የተመሠረተ ጊዜያዊ የኦቨር ድራፍት አገልግሎት ከ12 ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተመላሽ የሚደረግ ብድር ለፌዴራል መንግሥት ሊሰጥ ይችላል። የብድር መጠኑም ካለፉት ሦስት የበጀት ዓመታት አማካይ ዓመታዊ የፌዴራል መንግሥት የሀገር ውስጥ ገቢ ከ15 በመቶ መብለጥ የለበትም›› ሲል አዲስ የብድር ገደብ ደንግጎ አውጥቷል።

ይህ አዲስ የሕግ ማሻሻያ በኢትዮጵያ ያለቅጥ በተንሰራፋው የዋጋ ንረት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ስለመሆኑ ማብራሪያ የተጠየቁት የቀድሞ ከፍተኛ የባንክ የሥራ ኃላፊ የሆኑት አቶ እሸቱ ታዬ፣ የብሔራዊ ባንክ አቋም እንደ ዜጋም ሆነ እንደ ፋይናንስ ባለሙያ በእጅጉ የሚያስደስት ሆኖ እንዳገኙት ነው የተናገሩት።

‹‹ለረዥም ጊዜ ለመንግሥት በቀጥታም ሆነ ቀጥታ ባልሆነ መንገድ የሚሰጠው ብድር ገደብ እንዲበጅለት ሲጠየቅ ቆይቷል። ብሔራዊ ባንኩ በአዲሱ አዋጁ የመንግሥት የሦስት ዓመታትን ጥቅል የኢኮኖሚ ገቢ አይቼ ነው የዚያን 15 በመቶ ብድር የምሰጠው፣ ይህም ተንከባላይ አይደለም፣ ብድሩን ሲከፍል ብቻ ነው ተጨማሪ ብድር መጠየቅ የሚችለው ማለቱ በእኔ ግምት ደፋርና ለውጥ የሚያመጣ ድንጋጌ ነው፤›› ሲሉ ባለሙያው ተናግረዋል።

የብሔራዊ ባንክ አዋጅ ባንኩ ከመንግሥት፣ ከባንኮች፣ ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና የፋይናንስ ተቋማት ጋር እንዲሁም ከግለሰቦች ጋር ጭምር የሚኖረውን ግንኙነት የሚወስን እንደሆነ የጠቆሙት አቶ እሸቱ፤ አዲሱ ሕግ በትክክል ከተተገበረ ትርጉም ያለው ለውጥ በዋጋ ንረት ላይ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

አያይዘውም፣ “የባንኮችን የብድር ጣሪያ ከ14 በመቶ በላይ እንዳይሆን ብሔራዊ ባንክ ክልከላ አድርጎ ነበር። ይህን ያደረገው ደግሞ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እንደነበር አስታውቋል። ባንኮችን ብድር ከልክሎ መንግሥት በሚበደረው ገንዘብ ላይ ገደብ ካላስቀመጠ ግን ለዋጋ ግሽበቱ መሠረታዊ አባባሽ ምክንያት የመንግሥት ብድር ነው ተብሎ ይፈረጃል። አሁን ግን በባንኮች በኩል ግለሰቦች በሚያገኙት ብድር ላይ ቁጥጥር ከማድረግ ጎን ለጎን በመንግሥት አበዳደር ላይም ቁጥጥር አድርጓል። ይህ በሁለቱም መንገድ በመንግሥትም በግለሰቦችም ተበዳሪነት ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ ነው ማለት ነው። እስከ 2026 ባለው ዓመት ብሔራዊ ባንኩ የዋጋ ግሽበትን እስከ አሥር በመቶ ባለው አኃዝ ለማውረድ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት ታስቦ የወጣ አዋጅ ይመስለኛል›› በማለትም አቶ እሸቱ ሃሳባቸውን አክለዋል።

ብሔራዊ ባንክ፣ በአዲሱ አዋጅ የፌዴራል መንግሥት ከባንኩ የሚበደረውን ብድር መገደቡ በብዙዎች ዘንድ እየተደነቀ ቢሆንም፤ ከዚሁ ጎን ለጎን ግን ሥጋት የሚያነሱ ወገኖች አልጠፉም። ከእነዚህ አንዱ የሆኑት የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ዋሲሁን በላይ አዲሱ አዋጅ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ሊበደርባቸው የሚችልባቸው ምክንያቶች ተብለው የተዘረዘሩትን አመክንዮዎች ያጣቅሳሉ።

ለአብነትም፣ ‹‹መንግሥት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ማለትም ያልተጠበቀ የማኅበረሰብ ጤና፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ድርቅ ወይም አግባብነት ያለውን ሕግ መሠረት አድርጎ የታወጀ አጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በፌዴራል መንግሥት ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ጉልህ የውጭ ኢኮኖሚ ለውጦች በተከሰቱ ጊዜ ይህን ጊዜያዊ ችግር ለመቅረፍ ሲባል፣ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ ብድር ለመንግሥት የሚሰጥበትን አግባብ ደንግጓል›› ተብሎ የተቀመጠውን ንዑስ ድንጋጌ የሚያወሱት አቶ ዋሲሁን፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በእነዚህ ችግሮች ብዙ የምትፈተን እንደመሆኑም አዋጁ የመንግሥት ብድርን በሚመለከት ገደብ ካስቀመጠ በኋላ ይህን ሁሉ የመበደሪያ ቅድመ ሁኔታ መደርደሩ፣ በተጨባጭ የአዋጁ ገደብ ትርጉም ኖሮት እንዳይሠራ የሚያደርግ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ይሁን እንጂ እንደ ሀገር አሁን ላይ ካለው ተጨባጭ እውነት እና የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው እያመጣ ካለው ውጤት አኳያ፤ ብሔራዊ ብንክ እንዲህ አይነት የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረጉ እጅጉን የሚያስመሰግነው ነው። ሆኖም በመልካም የሚነሱትን በማላቅ፣ በስጋት የሚጠቃቀሱትንም በማጤን ለፖሊሲው ተፈጻሚነትም ሆነ ውጤታማነት ሁሉም አካል የበኩሉን ሊወጣ ይገባዋል የሚለው መልዕክቴ ነው።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com

Recommended For You