ያልበረደው እሳት!

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በውሳኔ ቁጥር 61/177 እ.ኤ.አ ታኅሣሥ 20 ቀን 2006 በመወያየት አንድ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን አጽድቋል። ዓለም አቀፍ ስምምነቱ የሰው ልጅ በአስገዳጅ ሁኔታ ከመሰወር ለመጠበቅ የወጣ ሕግ ‘Disappearance Convention’ በመባል ይታወቃል። በኮንቬንሽኑ ላይ ሰውን በአስገዳጅ ሁኔታ መሰወር፣ ከሕጋዊ ጥበቃ ውጪ መደበቅ፣ ሰዎችን ከሕግ ጥበቃ ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ፣ አስገድዶ መሰወር እንደሆነ ተቀምጧል። እነዚህ ወንጀሎች በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሆነ በሀገር የውስጥ ሕጎች ላይ በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑ ናቸው።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ፍጡርን የማገት ድርጊት ለየትኛውም ዓላማ ተፈጽሞ ቢገኝ በምንም ዓይነት አመክንዮ ሊደገፍ ወይም ቅጣቱ ሊለዝብ የማይችል ደረቅ ወንጀል እንደሆነ ተደንግጓል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 90 (1) ሥር በስብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል በአስገዳጅ ሁኔታ ሰውን መሰወር ይገኝበታል። የወንጀሉ ደረጃ ከባድ እና ከነጭራሹ አንዳች መንግሥታዊ ምህረትን ወይም ይቅርታን የማያሰጥ እንደሆነም ሕገ መንግሥቱ ላይ በማያሻማ ቋንቋ ተቀምጧል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር (Enforced Disappearance) ወንጀል እየጨመረ መጥቷል።

ሰዎች በታጣቂዎች የመታገት ዜና እንግዳ መሆኑ ከቀረ ሰነባብቷል። ክስተቱም በተወሰኑ መጥፎ ዕጣ በገጠማቸው ሰዎች ላይ የሚከሰት ሳይሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እና በብዛት የሚያጋጥም ስጋት ሆኗል። በሁሉም አቅጣጫዎች፣ በሁሉም አጋጣሚዎችም ሆነ በሁሉም መስኮች እገታ ተፈጸመ ሲባል መስማት የተለመደ ወደ መሆን ተሻግሯል። የጭነትም ሆነ የሰው መጓጓዣዎች ተሽከርካሪዎች የእገታ ሰለባ ስለመሆናቸው በሰፊው ይሰማል። ከኢንዱስትሪዎች እስከ ቤተ እምነቶች የዕገታ ወንጀል ተቃጣባቸው መባሉ ተለ ምዷል።

መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሰዎችን በማገት ገንዘብ መጠየቅ እየተለመደ መምጣቱን አምኗል። ወንጀሎቹ ለገንዘብ ወይም ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ የሚውሉ መሆናቸውን እንዲሁም የፀጥታ መዋቅሩን በገንዘብ በመደለል የራሳቸውን የፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ የሚያደርጉ ግለሰቦች እንደሚሳተፉ ጭምር ተናግሯል። በሀገሪቷ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግሥት በሁሉም አቅጣጫ ያለ ዕረፍት እየሠራ ቢሆንም፤ በታጠቁ ኃይሎች የሚፈጸመው ዕገታ እንደቀጠለ ነው።

ሰሞኑን ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ወደቤታቸው በመመለስ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው ዕገታ በብዙዎች ዘንድ መረር ያለ ስሜት ፈጥሯል። ከእንዲህ ዓይነቱ ሰብዓዊነት የጎደለው ድርጊት የሚጠቀመው ማን ነው የሚለው ምላሽ የሚሻ ጥያቄ አስነስቷል። የወንጀል ድርጊቱ በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች መደጋገም ዜጎች ደህንነት እንዳይሰማቸው፤ በነጻነት ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ለማከናወን እንዲቸገሩ እና ኑሯቸው በስጋት የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል።

በሀገራችን የድርጊቱ መደጋገም እየፈጠረ ካለው ውስጣዊ ችግርና ተፅዕኖ ባሻገር ውጫዊው ተጽዕኖው ከፍተኛ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ኢንቨስተርም ሆነ ቱሪስት ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ሲያቅዱ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ሰላም እንደሆነ ይታወቃል። ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት የሚያስፈልጋቸው ትልቁ ነገር ሰላማዊና የተረጋጋ ከባቢ ነው። ፖለቲካዊ ሆነ ገንዘብ በመፈለግ በየአካባቢው የሚፈጸሙ የእገታ ወንጀሎች ዕገታዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ፀር ናቸው። ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር (Enforced Disappearance) ወንጀል መጨመር ውስጣዊም ውጫዊም ተፅዕኖ ያለው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ተረድቶ መሥራትን ይጠይቃል።

መንግሥት ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን የሚያደርገው ጥረት ላይ ጥላሸት እየቀባም ጭምር ነው። የፌዴራል ፖሊስ ሆነ መከላከያ የኅብረተሰብ ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር ኃላፊነቱን ለመወጣት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም የጸጥታ አካላት ወንጀሎቹን ለመከላከል በቅንጅት ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ በተጨባጭ አሳይተዋል። ለምሳሌ በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው ዕገታ ተከትሎ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ተሞክሯል።

ለአብነት ይህን ጠቀስን እንጂ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባደረገው ተጋድሎ በተለያዩ አካባቢዎች በታጠቁ ቡድኖች የታገቱ ዜጎችን በማስለቀቅ ሕዝባዊነቱን አስመስክሯል። በመጠኑም ቢሆን በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ተከታትሎ በመያዝ ተጠያቂ ሲሆኑ አይተናል። ነገር ግን የዕገታ ወንጀሉ እየተስፋፋበት ባለበት ልክ የመከላከልና መቆጣጠር ሥራው እየሄደ ነው ለማለት ያዳግታል። የዕገታ ድርጊቱ በተደጋጋሚ የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ባለመሰጠቱ በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ሰዎች የእገታ ሰለባ እስከመሆን መድረሱ በምክንያትነት ይነሳል። በመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦችን በመጠቀም የሚፈፀም ስለመሆኑም መንግሥት በተደጋጋሚ በተደረገ ምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል። መንግሥት የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ያለውን ክፍተት በአግባቡ ባለመፈተሹ ችግሩ እንዲባባስ እንዳደረገው ይታመናል።

ስለሆነም መንግሥት በሀገራችን አሳሳቢ እየሆነ ለመጣው ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር (Enforced Disappearance) ወንጀል አፋጣኝ መፍትሔ በመስጠት መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ባሳተፈ መልኩ የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በመንግሥት ፀጥታ መዋቅር ውስጥ ሆነው በድርጊቱ የሚሳተፉ ግለሰቦችን በአፋጣኝ ተጠያቂ ማድረግም ይጠበቅበታል። እንዲህ ያሉ ግለሰቦች እሽሩሩ ሊባሉ የሚገባቸውም አለመሆናቸው መታወቅ አለበት።

በሕገ መንግሥቱ ላይ እንደተቀመጠው የወንጀሉ ደረጃ ከባድና ከነጭራሹ አንዳች መንግሥታዊ ምህረትን ወይም ይቅርታን የማያሰጥ መሆኑ ነው። በዚህ የወንጀል ድርጊቱ ተሳትፎ የሚያደርግን ማንኛውንም አካል መንግሥት ለሕግ ማቅረብ ግዴታ አለበት። የፌዴራል መንግሥት ሆነ የክልል የጸጥታ አካላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚፈጸሙ እገታዎችን ለመከላከል የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

ኅብረተሰቡም መንግሥት ወንጀሉን ለመከላከል እና በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያደርገውን ጥረት መደገፍ አለበት። ወንጀሉ በሚፈጸምበት ጊዜ ድርጊቱ የተፈፀመባቸው ግለሰቦች መረጃውን በሰዓቱ ለፖሊስ በማሳወቅ ወንጀለኞችን ተከታትሎ የመያዝ ጥረቱን አስቸጋሪ እንዳይሆን በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

በጥቅሉ ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር (Enforced Disappearance) ወንጀልን የመከላከል እና መቆጣጠር ተግባር የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ፣ ቁርጠኝነት እና የጋራ ርብርብ ይጠይቃል። የዕገታ ድርጊቱ በተደጋጋሚ የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ላይ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ይገባል።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You