የሆርቲካልቸር ዘርፉን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በመምራት የኢኮኖሚው አቅም ማድረግ ይገባል!

ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ሀብቶች ባለቤት ናት። በተለይ የግብርናው ዘርፍ ዛሬም በኢኮኖሚው ቀዳሚ ባለድርሻ እንደመሆኑ፤ ይሄንን ዘርፍ በተገቢው መልኩ ተገንዝቦና አልምቶ የሀገርን ኢኮኖሚ ማላቅ እና የኢንዱስትሪውንም ሽግግር እውን ማድረግ የተገባ ነው።

ከዚህ አኳያ በሰብል ልማት የታየው ከፍ ያለ ውጤት፣ ግብርናው ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ ከተሠራበት እውነትም ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ መበልጸግ የምትችልበት አቅም እንዳላት ያመላከተ ነው። በተለይ በስንዴ ልማት ዘርፉ የተከናወነው ተግባር ኢትዮጵያን ከስንዴ ለማኝነት ወደ ስንዴ ላኪነት ያሸጋገራት ተግባር ነው።

በተመሳሳይ በሩዝ፣ በሻይ ቅጠል፣ በአቮካዶ፣ በቡና… በጥቅሉ በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ውጤት፤ እንደ ሀገር በግብርናው ዘርፍ የልማት አቅሞችን ለይቶ መሥራት ከተቻለ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ከፍ ያለ የውጭ ምንዛሬ የገቢ ምንጭ መፍጠር እንደሚቻል በተግባር የገለጡ ናቸው።

ከእነዚህ አንዱ ደግሞ የሆልቲካልቸር ዘርፉ፣ በተለይም የአበባ ልማት ተጠቃሽ ነው። እንደሚታወቀው የአበባ ምርት በዓለም ገበያ ትልቅ ተፈላጊ እና ከፍ ያለ ገቢም የሚያስገኝ ነው። በዚህ በኩል በርካታ ሀገራት በአበባ ገበያው ላይ ጉልህ ስፍራን ይዘው፤ የሀገራዊ ገቢያቸውን ሲደጉሙ ይታያል።

ኢትዮጵያም በዚህ ዘርፍ ሩቅ የሚባል ታሪክ ባይኖራትም ላለፉት ሁለትና ሦስት አስርት ዓመታት በአበባ እርሻ ዘር ትልልቅ ሥራዎችን እየሠራች ትገኛለች። ለዚህም የአበባ እርሻ ስፍራዎችን በመለየት እና ባለሀብቶችን (አልሚዎችን) በመጋበዝ በሚፈለገው ልክም ባይሆን አበረታች ውጤት ማየት ተችሏል።

በዚህም በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከአበባ ምርት ሽያጭ እየተገኘ የዘለቀ ሲሆን፤ እንደ ሀገር ከሚታዩ የሰላም ብሎም ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ጋር ተያይዞም ዘርፉ በበርካታ ውጣ ውረዶች ታጅቦ መዝለቁ፣ የገቢ መጠኑም በዚያው ልክ መውጣት መውረዱ አልቀረም። ከሰሞኑ የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተውም እንደ ሀገር ከሆልቲካልቸር ዘርፉ በ2015 ዓ.ም 658 ሚሊዮን ዶላር፣ በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ 535 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ከዚህ ውስጥ የአበባ ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።

ዘርፉ በዚህ መልኩ ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍ ያለ ፋይዳ ያለው መሆኑ እሙን ቢሆንም፤ የአበባ እርሻ በአግባቡ እና በጥንቃቄ ካልተከናወነ ግን ከፍ ያለ አካባቢያዊም ሆነ የጤና ጉዳቶች እንዳሉት የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ጥናቶችም ይሄንኑ ያሳያሉ። ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያም በተለይ ሥራው በአብዛኛው በሐይቆች አካባቢ የሚከናወን እንደመሆኑ፤ በሐይቆች ሥነሕይወታዊ ገጽታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማድረሱ አልቀረም።

ለዚህ አንድ አብነት መጥቀስ ቢቻል፣ የባቱ (ዝዋይ) ሐይቅ አንዱ ሲሆን፤ በአካባቢው ያለ የአበባ እርሻም ሆነ ሌሎች ተያያዥ የግብርና ግብዓቶች ጋር ተያይዞ ወደ ሐይቁ አካል የሚገቡ ኬሚካሎች፣ በሐይቁ ውስጥ የሚገኙ የዓሳ ዝርያዎች ላይ ስጋት መደቀናቸው በተለያየ ጊዜ ሲገለጽ ቆይቷል።

ይሄ የሚያሳየው ደግሞ የአበባ እርሻ ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍ ያለ ፋይዳ ያለውን ያህል፤ በአግባቡ ካልተመራ እና በጥንቃቄ ካልተሠራበት አካባቢያዊ ጉዳቱም የማይናቅ መሆኑን ነው። ከዚህ አኳያ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ባለድርሻዎች ሃሳብና ሙያዊ አስተያየት ሲሰጡ ቆይተዋል። በመንግሥት በኩልም፣ በተለይ ዘርፉን በሚመራው አካል በኩል ጉዳዩን በማጤን፤ የሆልቲካልቸር ዘርፉ ጉዳት በመቀነስ እና ከፍ ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ለመቋደስ የሚያስችል ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

ለዚህ ደግሞ ተጠያቂነትን በሚያስከትል መልኩ ዘርፉን አንድም በሕግ፣ ሁለትም በጠንካራ የተናበበ አሠራር መምራት የተገባ በመሆኑ፤ ብሔራዊ የሆርቲካልቸር ረቂቅ ስትራቴጂ ሰነድ፤ እንዲሁም በዘርፉ ያሉ አንኳር ችግሮችንና የመፍትሔ ሃሳቦችን ያጠቃለለ ብሔራዊ የ10 ዓመት ረቂቅ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ውይይት ተደርጎበታል።

በዚህ ስትራቴጂ መሠረት የሆርቲካልቸር ዘርፉን ዓመታዊ ገቢ ማሳደግ ቁልፍ ተግባር ሲሆን፤ በዚህም በ10 ዓመታት ውስጥ ሦስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ የማግኘት ግብ ተቀምጧል። ከዚህ በተጓዳኝም የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማሟላት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማሳደግና የከባቢ ተጽዕኖውን መቀነስ የትኩረት አቅጣጫው ነው።

እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ በአበባ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በሥራ ስር ልማት እምቅ አቅም አለ። የሆርቲካልቸር ዘርፉም የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው። ይሁን እንጂ ዘርፉ በብዙ ችግሮች ውስጥ እየዳከረ እንደመሆኑ፣ የሆርቲካልቸር ብሔራዊ ስትራቴጂ መዘጋጀቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት፣ ዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የሚያስችል ነው። በመሆኑም የሆልቲካልቸር ዘርፉን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በመምራት ዘርፉን የኢኮኖሚው አቅም ማድረግ ይገባል!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You