የሙዚቃው ጦስ

ልጅነቱ የሚያጓጓ ለግላጋ ወጣት ነው። የ25ቱ ዓመቱ ወጣት ማቲያስ ተፈራ በቀጣዮቹ 18 ዓመታት የጉልምስና ዕድሜውን በእስር ቤት ያሳልፋል ብሎ የገመተ ማንም አልነበረም። ሰውን ሆን ብሎ ያጠቃል ብሎ ለማሰብ ያዳግታል። ቅልስልስ እና ተለማማጭ ነው። ነገር ግን ሲጠጣ ትዕቢቱ ከቁመቱ በላይ ነው። ደረቱን ከነፋ የሚያስተነፍሰው የለም። ብዙ ጓደኞች አሉት፤ የሚውለው፤ የሚያመሸው በጓደኞቹ ተከቦ ነው።

ምንም እንኳ በአዲስ አበባ በምርጥ ትምህርት ቤትነቱ በሚታወቀው የቅድስት ስላሴ ካቴድራል ትምህርት ቤት የተማረ ቢሆንም፤ ቤተሰቦቹ እንደተመኙለት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ አልታደለም። መጨረሻው አላማረም።

የመከኑት ወላጆች

ማቲያስ በ1986 ዓ.ም ይህችን ዓለም ሲቀላቀል፤ እናቱ ወይዘሮ አመለወርቅ ዘለቀ እና አባቱ አቶ ተፈራ ዘለሉ አብዝተው ተደስተው ነበር። ደግሰው ወዳጅ ዘመድ ጠርተው አብልተዋል። አቀማጥለው ለማሳደግ ወስነው እንደፈለገው አሞላቀውታል። በመሃል አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ጥይት ቤት በሚባል አካባቢ ተወልዶ ነው ያደገው ።

ገና በልጅነቱ የጠየቀው ሁሉ እየተሟላለት አንዳንድ ጊዜ ከዕድሜው በላይ ለሚያቀርበው ጥያቄም ምላሽ እየተሰጠው ሳይጎልበት በብዙ እንክብካቤ አደገ። እነወይዘሮ አመለወርቅ ልጃቸውን አብዝተው ይወዱት ስለነበር ከሚገባው በላይ ይንከባከቡት ነበር። አይተው አይጠግቡትም፤ ይወዱታል ብቻ ሳይሆን በልጅነቱ ልዩ ቦታ ስለሚሰጡት እርሱም ከልጆች ሁሉ የተለየ እንደሆነ እየተሰማው ተሞላቆ እና ተንደላቆ አደገ።

ወላጆቹ ሌላ ልጅ ቢወልዱም ለእርሱ የሚሰጠው ቦታ የተለየ ነበር። ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ትምህርት ቤት ገባ። ጎበዝ ተብሎ ሳይሞገስ እንዲሁ ከመውደቅ ለጥቂት እየተባለ እያለፈ 8ኛ ክፍል ደረሰ። ወላጆቹ ብዙ አይጫኑትም፤ ነገር ግን እንደተመኙት ጎበዝ ሆኖ ስላላገኙት ከቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ትምህርት ቤት አስወጥተው መስከረም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገቡት። እርሱም ትምህርቱ ላይ ለማተኮር ፍላጎት የለውም። አያጠናምና ብሔራዊ የ10ኛ ክፍል የማጠቃለያ ፈተናን ማለፍ አቃተው። በዚህ ጊዜ ወላጆች ተፀፀቱ። ነገር ግን ሁሉም ነገር ጅብ ከሔደ ውሻ ጮኸ ሆነባቸው። የወላድ መካን ሆኑ።

በሱስ መጠመድ

ማቲያስ ወደ 11ኛ ክፍል መዘዋወር ባለመቻሉ ከጓደኞቹ ተለይቶ ቤት ዋለ። በተለይ ከልጅነቱ ጀምሮ እስከ 8ኛ ክፍል አብረውት የተማሩ ልጆች በሙሉ 11ኛ ክፍል በመግባታቸው ሞራሉ ተነካ። መጨነቅ ጀመረ። ድጋሚ ለመማር እና እራሱን ለማሳደግ ከመሞከር ይልቅ ድብርት ውስጥ ገባ። ለራሱም ለሌሎችም ግድ የሌለው የባከነ ዜጋ ሆነ።

በአካባቢው ከሚውሉ የመንደሩ ቦዘኔዎች ጋር መወዳጀት ጀመረ። ልክ እንደእነርሱ ጫት መቃም፣ አረቄ መጠጣት፣ ሺሻ ማጨስ መለያው ሆነ። ቀስ በቀስ ከሚቅሙት በላይ ቃሚ፣ ከሚሰክሩት በላይ ሰካራም፣ ሺሻውንም ከሚያጨሱት በላይ አጫሽ ሆነ። በጓደኞቹ ተከቦ ይውላል፤ ተከቦ ያመሻል። ቀስ በቀስ ቤተሰቦቹ አገለሉት፤ ገንዘብ የሚሰጠው አጣ። ስለዚህ ለሰዎች ጉዳይ እያስፈፀመ ገንዘብ ማግኘት ጀመረ። ገቢ ማግኘት ሲጀምር ልቡ ግን ተመልሶ ከሱስ አልወጣም። እንደነበረው እየቃመ፣ እየጠጣ እና እያጨሰ ሕይወቱን መግፋት ቀጠለ።

ክፋ ምሽት

ማቲያስ እንደለመደው ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ቤት ተቀምጦ አረቄ ይጠጣል። እየተሳሳቁ፣ እያውካኩ፣ እየጠጡ እየተጨቃጨቁ እየተገፋፉ እና እየተላፉ ሌላኛው ጓደኛቸው ሳሙኤል ፈረደ ወደ ቤት ገባ። ማቲያስ ሳሙኤልን ሙዚቃ እንዲከፍት አዘዘው። ማቲያስ ግን ‹‹ጓደኛችን የተቀበረው ትናንት ነው። እንዴት አሁን ሙዚቃ ይከፈት ትላለህ? ›› ሲል ጠየቀው። ማቲያስ ለሳሙኤል አስፀያፊ ስድብ ሰደበው፤ ሳሙኤል ብቻ ሳይሆን የሳሙኤል እናትም ተሰደቡ። የማቲያስ ጓደኛ ሳሙኤል እጅግ ተበሳጭቶ ከቤት ወጣ።

ሶስቱ ጓደኛሞች ሲያውካኩ ቆይተው ሁለቱ ወጥተው ወደ ቤታቸው ሔዱ። ማቲያስ ምንም እንኳ ጠጥቶ ከሞቅታ ወደ ሥካር ቢንደረደርም ብቻውን ቤቱ ውስጥ መቀመጥ አስጠላው። ተነስቶ ወደ ለቅሶ ቤት ሔደ። ለቅሶ ቤት ሲሔድ ያስቀየመውን ጓደኛውን ሳሙኤልን አገኘው። አጠገቡ ሔዶ ተቀመጠ። ሳሙኤል በንዴት አይኑን አፈጠጠ። ‹‹ሳያዝኑ ሙዚቃ እየከፈቱ እና እየተዝናኑ ለቅሶ ቤት መሔድ ምን ዋጋ አለው?›› ብሎ ከማቲያስ አጠገብ ተነስቶ ከድንኳኑ ወጥቶ ወደ ቤቱ ሔደ።

ንፋስ በማግኘቱ ስካሩ ለቀቅ ያደረገው ማቲያስም ከጥቂት ቆይታ በኋላ እርሱም ከለቅሶ ቤት ወጥቶ ወደ ቤቱ መሔድ ጀመረ። ሳሙኤል በማቲያስ ስለተበሳጨ ቢላዋ ይዞ በመንገዱ ቅያስ ላይ መጠበቅ ጀመረ። ሀገር ሰላም ብሎ ወደ ቤቱ ሲሔድ የነበረው ማቲያስ ሳያስባው ሳሙኤል ግራ እጁን በቢላዋ ወጋው። ማቲያስ ፈጠን ብሎ የሳሙኤልን እጅ ጠምዝዞ ቢላዋውን ነጠቀው። ምኑ ላይ እንደወጋው አያውቅም፤ እጁ የሰነዘረለትን ያህል ቢላዋውን ሳሙኤል ላይ ደጋግሞ ሰነዘረ። የተለያየ ቦታ በቢላዋ የተወጋው ሳሙኤል ጉልበቱ ተብረክርኮ በደረቱ ወደቀ።

ሳሙኤል መውደቁን እና ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰበት የተረዳው ማቲያስ በነበረበት ቢላዋውን እና ወዳጁን ሳሚን መሬት ላይ ጥሎ ወደ ቤቱ ሮጠ። እየተርበተበተ ቤት ሲገባ ወንድሙን አገኘው። ጓደኛው ሳሚ ላይ ጉዳት ማድረሱን እንደውም ‹‹ገድዬዋለሁ›› ብሎ መገመቱን ሲነግረው፤ አራት ኪሎ ፖሊስ ጣቢያ ሔደህ እጅህን ስጥ አለው። ማቲያስ እጁን ሊሰጥ ፖሊስ ጣቢያ ሲሔድ፤ ራሱም የግራ እጁ ላይ በመወጋቱ ደሞ እየፈሰሰ በመሆኑ ለመመለስ አሰበ።

ማቲያስ ሳሙኤል አለመሞቱን እና ሆስፒታል መወሰዱን ሲሰማ፤ ለፖሊስ እጁን ሳይሰጥ ወደ ቤት ተመለሰ። የሚፈሰውን ደሙን ለማስቆም እጁ ላይ ጨርቅ አስሮ ተቀምጦ ሲርበተበት የቤቱ በር ተንኳኳ።

ሳሙኤል አጠቃለሁ ብሎ ተጠቃ። እገድላለሁ ብሎ ከቤቱ ቢላዋ ይዞ ቢወጣም። የሰነዘረው ቢላዋ ወደ እርሱ ተመለሰ። በተደጋጋሚ ግራ ደረቱን፣ የግራ ጡቱን እና የግራ ታፋውን ተወጋ። ደሙ እንደወራጅ ውሃ ፈሰሰ። ሰዎች እርሱን ለማዳን ተረባረቡ። በደም እየተጨማለቁ ተሯሯጡ። ነገር ግን የተሰነዘረበት ቢላዋ ደረቱን እና ጡቱን ብቻ ሳይሆን ልቡ እና ሳንባው ላይ ዘልቀው ጎድተውታልና ደሙ በቀላሉ አልቆም አለው። ሆስፒታል ቢደርስም ታህሳስ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ40 ላይ እስከ ወዲያኛው አሸለበ፤ ገና በለጋነት እድሜው ሕይወትን ሳያጣጥም ሁሉም አለፈ።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ቀበሌ 18 አካባቢ ወንጀል መፈፀሙ ጥቆማ ደረሰው። የዕለቱ ተረኛ የምርመራ ቡድን ወዲያው ቦታው ላይ ሲደርስ፤ ሰዎች የሳሙኤልን ሕይወት ለማትረፍ እየተሯሯጡ መሆኑን አረጋገጠ። ሳሙኤል ሆስፒታል ሄዶ ሕይወቱ ማለፉን ሲያውቅ ወንጀሉን ማን እንደፈፀመ ጠየቀ። ድርጊቱን የፈፀመው ማቲያስ መሆኑ ታወቀ።

የዕለቱ ተረኛ የፖሊስ የምርመራ ቡድን በግምት ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ55 ሲል ወደ ማቲያስ ቤት አመራ። ማቲያስ ቤቱ ቁጭ እንዳለ ተያዘ። ለማምለጥ፣ ለመካድ እና ለመከራከር አልሞከረም። እየተንቀጠቀጠ እጅ ሰጠ። ፖሊስ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን አሰባሰበ። የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አደራጅቶ ለአቃቤ ሕግ አቀረበ።

ዓቃቤ ሕግ ክስ

ዓቃቤ ሕጉ ለፍርድ ቤት እንዳሳወቀው፤ ወንጀሉ 1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 539 (1) (ሀ) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የተፈፀመ አስነዋሪ ተግባር ነው። ዕድሜው 25 ዓመት የሆነው ወጣት ማቲያስ ተፈሪ ጨካኝነቱ እና ነውረኝነቱን በሚያሳይ መልኩ፤ በቢላዋ ደጋግሞ ሟች ሳሙኤልን የግራ ደረቱን፣ የግራ ጡት ላይ እና የግራ ታፋው ላይ በመዋጋት እንደቅደም ተከተላቸው በ2 ነጥብ 1 ሳንቲ ሜትር፣ 2 ነጥብ 1 ሳንቲ ሜትር እና 2 ሳንቲ ሜትር ድረስ ወደ ውስጥ የገባ፣ ቁስል እንዲፈጠርበት በማድረግ በስለት ልቡን እና የግራ ሳምባው ላይ በደረሰበት ጉዳት ብዙ ደም እንዲፈሰው አድርጓል። ሟች ወጣት ሳሙኤል በደረሰበት ጉዳት ምክንያት የደም ዝውውሩ እና የትንፋሽ ሥርዓቱ በመቆሙ ምክንያት ወዲያው ሕይወቱ ያለፈ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የሰው ግድያ ወንጃል ሊፈረድበት ይገባል ሲል አቃቤ ሕግ የክሱን ጭብጥ ለፍርድ ቤቱ አስረዳ።

ጨምሮም ማቲያስ ሆን ብሎ ሰውን ለመግደል በማሰብ ከሟች ከሳሙኤል ጋር ሲጨቃጨቅ መቆየቱን ይዞት በነበረው ስለት ባለው ቢላዋ ወግቶት ሕይወቱ እንዲጠፋ አድርጓል ሲል የሰው 10 ምስክር አቀረበ። ህዳር 8 ቀን 2015 ዓ.ም በቁጥር 3515/44/15 ከዳግማዊ ምንሊክ ሪፍራል ሆስፒታል፣ ፎረንሲክ ህክምና ሥነ-መርዝ ትምህርት ክፍል የቀረበ የአስክሬን ምርመራ ውጤት በማስረጃነት አያያዘ።

ተከሳሹ ማቲያስ በበኩሉ ‹‹ወንጀሉን የፈጸምኩት ሕጋዊ የመከላከል መብቴን በመጠቀሜ ነው። ሆን ብዬ ለመግደል ሳይሆን ሊገድለኝ የመጣ ሰውን ስከላከል ሕይወቱ አለፈ። ›› ሲል በወንጀል ሕጉ 179 መሠረት ቅጣት ይቅለልልኝ በማለት ጥያቄ አቀረበ። ሆኖም አቃቤ ሕግ ወንጀሉ ራስን ከመከላከል ገደብ በመተላለፍ የተከናወነ በመሆኑ የቀረበው የቅጣት ማቅለያ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ አስረዳ። ግድያውም ቀላል ወንጀል ሳይሆን ከባድ የግድያ ወንጀል በመሆኑ ተከሳሹ ማቲያስ ተገቢውን ቅጣት ሊያገኝ ይገባል አለ።

 ውሳኔ

ተከሳሽ የተከሰሰበትን ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል መፈፀሙን ማስረጃዎች ተስምተው በበቂ ያስረዱ በመሆናቸው ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ ስር ያለውን ፍርድ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ሰጠ።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ማቲያስ ተፈሪ ላይ የቀረበውን ሰው የመግደል ወንጀል በተመለከተ ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ወንጀል ፈፃሚውን ያርማል ሌሎችንም ያስተምራል ብሎ ባመነበት 18 (አስራ ስምንት) ዓመት ፅኑ እስራት ይቀጣ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You