ትኩረታችን – ወደ መኸር እርሻችን!

በ2016/17 የመኸር እርሻ 20 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል ዘር በመሸፈን፣ 616 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን የግብርና ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል:: ለዚህ እቅድ መሳካት አቅም እንዲሆንም 14 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ለአርሶ አደሩ እየተሠራጨ ነው:: ከዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሩ ኮምፖስት በማዘጋጀት የእርሻ ማሳውን ለዘር የማዘጋጀት ሥራ እየሠራ ይገኛል::

ግብርና የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕይወት መሠረት ነውና ስለግብርናው ዘርፍ ደግሞ ደጋግሞ ማውራት ተገቢ ነው:: በተለይም፣ በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከፍተኛው ዓመታዊ የግብርና ምርት የሚገኝበት የመኸር እርሻ ሥራ በሚከናወንበት በአሁኑ ወቅት፣ ስለግብርናው መጠየቅና መከታተል እጅግ አስፈላጊ ነው::

ከዚህም በላይ የግብርናው ዘርፍ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መሠረት ነው:: እናም የዚህ ወሳኝ ዘርፍ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል:: በመሆኑም የእርሻ ሥራው፣ የግብዓት አቅርቦቱ እና ሌሎች ተያያዥ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ የግብርና ጉዳዮች ዕለታዊ ክትትል ይፈልጋሉ:: ይሄን በማድረግም የጎደለውን መሙላት፤ የተበላሸውን ማስተካከል ያስፈልጋል::

የክረምት ወራት የመኸር እርሻ ሥራ የሚከናወንባቸው ጊዜያት በመሆናቸው አርሶ አደሩ፣ የልማት ጣቢያ ሠራተኛው እንዲሁም አመራሩ ሁሉ ወደ ማሳ ዘልቆ ደፋ ቀና ሲል መታየቱ የተለመደ ተግባር ነው:: ለምን ቢባል፣ አርሶ አደሩ ያርሳል፤ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ሙያዊ/ቴክኒካዊ ድጋፍ ይሰጣሉ፤ አመራሩ ደግሞ ከአርሶ አደሩና ከባለሙያዎች በሚቀርቡ ጥያቄዎች መሠረት የጎደለው እንዲሟላ ትዕዛዝ ይሰጣል፤ ክትትልና ድጋፍም ያደርጋል::

የግብርናውን ዘርፍ በማሳደግ ሀገሪቱ የግብርና አቅሟን ተጠቅማ ከድህነት እንድትላቀቅ ለማድረግ ከሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦች መካከል አንዱ የግብርና ግብዓቶችን አስተማማኝ በሆነ መጠንና ጥራት ማቅረብ ነው:: ከእነዚህ የግብርና ግብዓቶች መካከል አንዱ የአፈር ማዳበሪያ ነው:: በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አርሶ አደር ባለፉት ዓመታት የአፈር ማዳበሪያን መጠቀሙ ሀገሪቱ ከእርሻ የምታገኘው ምርት በየዓመቱ እንዲጨምር አስችሏል::

ይሁን እንጂ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ስለአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ሲሰማ የነበረው ዜና አምራቹን፣ አርሶ አደርም ሆነ ሸማቹን ከተሜ ለጭንቀት የሚዳርግ ሆኖ ተስተውሏል:: ምክንያቱም የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ለእርሻው ዘርፍ ከባድ ፈተና ሲሆን፤ አርሶ አደሩ ለእርሻ ሥራው የሚያስፈልገውን የአፈር ማዳበሪያ በሚገባ እንዳላገኘ በተደጋጋሚ ሲገልፅ ነበር::

በተለይ ባለፈው ዓመት በአንዳንድ አካባቢዎች አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ በማጣታቸው ምክንያት ያለማዳበሪያ ለመዝራት መገደዳቸውን መናገራቸው ይታወሳል:: ይህ አሳፋሪ ተግባርም የማዳበሪያ አቅርቦት ድረስ ዘልቆ ገብቶ አርሶ አደሩንም ሆነ ሸማቹን ከተሜ ለከባድ ችግር ሊያጋልጠው እንደነበር መዘንጋት የለብንም::

በዚህ ረገድ፣ በመንግሥት በኩል ለአፈር ማዳበሪያ እጥረት ምክንያት ናቸው የተባሉ ጉዳዮች ሲዘረዘሩ መስማት የተለመደ ነው:: አንዳንዶቹ ለብዙ ዓመታት ተደጋግመው ሲጠቀሱ የነበሩ ጉዳዮች ናቸው:: ግን ምክንያት መደርደሩ የዘር ወቅቱ ላለፈበት አርሶ አደር ምንም እንደማይፈይድለት በተግባር አይተነዋል:: እናም ችግሩን በሚያሻግሩ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መሥራቱ የተገባ ነው::

ከዚህ አኳያ፣ ሰላምና ፀጥታን አስፍኖ የማዳበሪያ አቅርቦቱን ፈጣንና አስተማማኝ ማድረግ፣ ነውረኛ በሆኑ ሌባ ሹማምንትና ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም ርምጃ መውሰድ እንዲሁም የማዳበሪያ አቅርቦቱን ሊያሰናክሉ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ በማሰብና በቂ ዝግጅት በማድረግ ማዳበሪያን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ የማቅረብ ኃላፊነት የመንግሥት ነው:: ባለፉት ዓመታት በማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ረገድ የተስተዋሉ ክፍተቶች ዘንድሮ መፍትሄ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል:: እየታዩ ያሉ ለውጦችም የዚህ አብነቶች ናቸው::

ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ነው:: ለምርት መጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካላቸው ግብዓቶች አንዱ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂ ዘዴዎችን መጠቀም/መተግበር ነው:: በዓለም አቀፍ ደረጃ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈጣንና ከፍተኛ የሆኑ መሻሻሎችን እያሳዩ ይገኛሉ::

እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ጊዜን፣ ገንዘብን፣ ጉልበትንና ሌሎች ሀብቶችን በመቆጠብ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራሉ:: በኢትዮጵያም የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ልምድ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም፣ ሀገሪቱ በግብርና ዘርፍ ካላት እጅግ ከፍተኛ አቅም አንፃር አሁንም በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው::

ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ተስማሚ የሆኑ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ተግባር፣ ቴክኖሎጂዎቹን ለመጠቀም/ለመተግብር ከመወሰን ባሻገር፤ ስለቴክኖሎጂዎቹ ምንነትና አስፈላጊነት ለባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤን የመፍጠር እንዲሁም ቴክኖሎጂዎቹ ያስገኟቸውን ውጤቶች በየጊዜው መገምገምና ማሻሻያዎችን/ማስተካከያዎችን ማድረግን ያካትታል::

ምክንያቱም፣ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ ሀገራት ከማስገባት በተጨማሪ፤ በሀገር ውስጥ ለማልማትና በስፋት ለማዳረስ ብርቱ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል:: ሀገር በቀል የግብርና ቴክኖሎጂዎች የዘርፉ ዘላቂ ዋስትና እንዲሆኑ በዘርፉ ለተሠማሩ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ አልሚዎች ቅድሚያ መስጠት ይገባል:: ቴክኖሎጂዎቹን ከውጭ የሚያስገቡ ኩባንያዎችንም መደገፍና ማበረታታም ችላ ሊባል አይገባም::

በተመሳሳይ፣ የፀረ-አረምና ፀረ-ተባይ አቅርቦትና ስርጭትም ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል:: ሰብሎች በአረምና በተባይ ተጎድተው ምርታቸው እንዳይቀንስ ፀረ-አረምና ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ እንዲሁም ስለአጠቃቀማቸው ግንዛቤ መፍጠር እጅግ አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ተግባር ነው::

በሌላ በኩል፣ በጥሩ ሁኔታ ታርሶ፣ ተዘርቶና ታርሞ የደረሰ ሰብል በጥንቃቄ ካልተሰበሰበ ለብክነት ይዳረጋል:: በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከፍተኛው ዓመታዊ የግብርና ምርት የሚገኝበት፣ የመኸር እርሻ ምርት ስብሰባ ሥራ ብክነትን በእጅጉ በሚቀንስ መንገድ መከናወን ይኖርበታል::

የእርሻ ሥራ በሚከናወንበት በአሁኑ ወቅት ከወራት በኋላ ስለሚከናወን የምርት ስብሰባ ሥራ ማንሳት የፈለግኩት፣ ከዚህ ቀደም በምርት ስብሰባ ወቅት የተፈጠሩት ተደጋጋሚ መዘናጋቶች ከፍተኛ የምርት ብክነት ያስከተሉ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ጉዳዩ ከወዲሁ ትኩረት እንዲያገኝ አፅንኦት ለመስጠት ነው::

በምርት አሰባሰብ ወቅት የሚፈጠሩ ችግሮች ከፍተኛ የምርት ብክነት እንዲከሰት ያደርጋሉ:: የምርት ብክነት መከሰት ደግሞ በኅብረተሰቡና በሀገሪቱ ላይ ተራዛሚ ተፅዕኖዎችን የሚያስከትሉ ችግሮችን ይፈጥራል:: የምርት አሰባሰብ ሥራ ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶት በሚገባ ካልተከናወነ፣ የምርት እጥረት እንዲፈጠርና የዋጋ ንረት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑ አይቀርም::

ሀገሪቱ ከበቂ በላይ የምታመርታቸው ምርቶች ጭምር ዋጋቸው ሰማይ ነክቶ በተደጋጋሚ እንታዘባለን:: ለአብነት ያህል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከበቂ በላይ ተመርተው ከማሳ የሚያነሳቸው አጥተው ለብክነት እንደሚዳረጉ የምርቶቹ ባለቤቶች ሲናገሩ ደግመን ደጋግመን ሰምተናል:: በከተሞች ያለው የእነዚህ ምርቶች ዋጋ ግን ‹‹ጆሮ አይስማ›› የሚያሰኝ ነው::

የአትክልትና ፍራፍሬን ዋጋ ለችግሩ ማሳያነት ያህል ጠቀስኩ እንጂ፣ በሌሎቹም ምርቶች ላይ ተመሳሳይ ችግር መከሰቱ አይቀርም:: የዚህ ችግር ስር ቢመዘዝ የምርት አሰባሰብ ድረስ እንደሚደርስ አያጠራጥርም:: አሁን ባለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ላይ ተጨማሪ የዋጋ ንረት ከተፈጠረ ደግሞ የኅብረተሰቡ የኑሮ ፈተና ከድጡ ወደ ማጡ ይሆናልና ለመኸር ምርት አሰባሰብ ትኩረት በመስጠት ተጨማሪ ችግር እንዳይፈጠር መትጋት ይገባል::

የምርት ስብሰባ ሥራው ምርትን ሰብሰቦ በጥንቃቄ ለፍጆታም ይሁን ለገበያ የማቅረብ ተግባርን ያካተተ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ይገባል:: ይህን በማድረግ እያደገ ለመጣው የምግብና የገበያ ፍላጎት በጊዜ እና በጥራት ተወዳዳሪ የሆነ ምላሽ መስጠት እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ በቂ የሰብል ምርት ማቅረብ፣ እና ዋና ዋና የምግብ ሰብሎች ለዘላቂ የግብርና ልማት ያላቸውን ሚና ማሳደግ ይቻላል::

የምርት ብክነትን ከሚቀንሱ ዘዴዎች መካከል አንዱ፣ ምርትን በዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ መሣሪያዎች መሰብሰብ ነው:: ይህ ግብርናውን በቴክኖሎጂ የማዘመን ተግባር የግብርናውን ዘርፍ በማሳደግ ሀገሪቱ የግብርና አቅሟን በመጠቀም ከድህነት እንድትላቀቅ ለማድረግ ከሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦች መካከል አንዱ ነው:: በተለይ ትርፍ አምራች በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የማጨጃና የመውቂያ ማሽኖችን የሚያገኙባቸውን አሠራሮችን መዘርጋት እጅግ አስፈላጊ ነው:: ይህን አሠራር በመተግበር የምርት ጥራትን መጨመርና ብክነትን መቀነስ ይቻላል::

በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል:: በመንግሥትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ትብብር በተተገበሩት ተከታታይነት ያላቸው የግብርና ልማት እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ያሳደጉና የሕዝቡን፣ በተለይም የአርሶ አደሩን፣ ሕይወት ያሻሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል:: ከግብርና የሚገኘው ምርት በየዓመቱ ጭማሬ አሳይቷል፤ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍልም ከድህነት መላቀቁንና ብዙ ባለሀብት አርሶ አደሮች ማፍራት መቻሉን መረጃዎች ያመለክታሉ::

ይሁን እንጂ እነዚህ ተግባራት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ካላት አቅም አንፃር ሲመዘኑ ለሀገሪቱ የምግብ ዋስትና፣ የሥራ እድል ፈጠራና የምጣኔ ሀብት እድገትም ሆነ ለዘርፉ ችግሮች አስተማማኝ መፍትሄ የሰጡ አይደሉም:: አሁንም ግብርናው በዘላቂነት ከኋላ ቀር አስተራረስና ከዝናብ ጥገኝነት አልተላቀቀም፤ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በብዛት ከመጠቀም የራቀ ሆኖ ይታያል:: ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች እየኖሩ ነው:: በአጠቃላይ የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ለውጥን እስካሁን ድረስ እውን ማድረግ አልተቻለም:: የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ በሌሎች የግብርና ግብዓቶች ላይ የሚስተዋለው የአቅርቦት እጥረት እና የስርጭት ችግር በዘርፉ እየተገኙ ያሉ ውጤቶችን ወደ ኋላ እንዳይመልሳቸው መጠንቀቅ ይገባል::

ምክንያቱም የሀገሪቱ ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች የተሻለ ምርታማና ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የግብርና ግብዓቶች እጥረት ነው:: የግብዓቶቹ አቅርቦት መዘግየት እና የዋጋ ውድነት አርሶ አደሩን ከግብዓት በማራቅ ምርቱ ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርጉታል:: ይህ የአርሶ አደሩ ውድቀት ደግሞ የሀገር ውድቀት ይሆናል:: በግብርናው ዘርፍ የምትፈፀም አንዲት ቅንጣት ስህተት እጅግ አደገኛ ሀገራዊ ውድቀትን እንደምትጋብዝ መዘንጋት አይገባም!

ስለሆነም የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ ለግብርናው ዘርፍ ስኬት አስፈላጊ ለሆኑ ግብዓቶች አቅርቦት ሁሉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል:: አለበለዚያ ግብዓት ሳያቀርቡ ምርት እንዲያድግና ሀገር እንድትሻሻል መጠበቅ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› ይሆናል::

ከዚህ አኳያ የዘንድሮው ግብርና ቀደም ባሉትም ሆነ በአሁኑ ወቅት በተከሰቱት ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች (ድርቅና አለመረጋጋት) ምክንያት ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው:: በእነዚህ ፈተናዎች ምክንያት ባለፈው የምርት ወቅት ምርት የቀነሰባቸውን አካባቢዎች ዘንድሮ የተሻለ ምርታማ በማድረግ ማካካስና ከዘርፉ የሚጠበቀውን ሀገራዊ የምርት መጠንም ማሳደግ ያስፈልጋል::

በአጠቃላይ ከመኸር እርሻ የታቀደውን ምርት ለማግኘት ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት ስብሰባ ድረስ የሚከናወኑ ተግባራትን በከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ መፈፀም ይገባል:: የመኸር እርሻ በሚከናወንበት በዚህ ወቅት አርሶ አደሩ፣ የልማት ጣቢያ ሠራተኛው እንዲሁም አመራሩ ሁሉ ወደ ማሳ ዘልቆ ያለመታከት መሥራት አለበት:: አርሶ አደሩ ይረስ፤ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ሙያዊ/ቴክኒካዊ ድጋፍ ያድርጉ፤ አመራሩ ደግሞ ከአርሶ አደሩና ከባለሙያዎች በሚቀርቡ ጥያቄዎች መሠረት የጎደለው እንዲሟላ ትዕዛዝ ይስጥ፤ ክትትል ያድርግ!

ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ አጨዳና ድህረ ምርት አያያዝ ድረስ ለሰብሎች ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ በግብርና ሚኒስቴር የብርዕና አገዳ ሰብሎች አመራረት ኤክስቴንሽን ማኑዋል ላይ በዝርዝር ተብራርቷል:: የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ይህን የምርት አመራረት መመሪያ ከአርሶ አደሩ ልምድና ተሞክሮ ጋር በማቀናጀት እንዲተገበር በብርቱ መትጋት ይኖርባቸዋል::

ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት ስብሰባ ድረስ የሚከናወኑ ተግባራትን በከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ መፈፀም ካልተቻለ፣ ነገሩ ሁሉ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› መሆኑ አይቀርም:: ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግብርና ዘንግተው መኖር ስለማይችሉም፤ የግብርናው ዘርፍ ለአፍታም ቢሆን ትኩረት ሊነፈገው አይገባም:: ለዓመታት በምኞት ላይ የኖረው ‹‹ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ›› እውን እስከሚሆን ድረስም ግብርናውን መዘንጋት አንችልም::

ወንድይራድ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You