የኢትዮጵያውያን መለያ እየሆነ የመጣው አረንጓዴ ዐሻራ

ከዓለም አቀፍ የመሬት ስፋት ውስጥ 31 በመቶ የሚሸፍነው ደን ነው። ዋነኛው ደግሞ የአማዞን ደን በመባል ይታወቃል። ይህ በብራዚል ውስጥ የሚገኘው የአማዞን ደን በምድር ላይ ካሉ ትልልቅ ደኖች ሁሉ የላቀ ስለመሆኑ ይነገርለታል። በአፍሪካም ትልልቅ ደኖች የሚገኙ ሲሆኑ፤ በዋናነት ተጠቃሹ የአፍሪካ ደን በኮንጎ የተፋሰሶች ምድር ላይ ያለው እና በ 500 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ገዝፎ የሚታየው ደን ነው።

ይህ በዓለም የሁለተኛ ደረጃን የያዘው የኮንጎ ትልቅ ደን እንደአማዞን ሁሉ ለዓለም ከፍተኛ ጥቅም እያስገኘ መሆኑ ይገለፃል። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ምንም እንኳ ደኗ ተመናምኖ መጠኑ እጅግ ቀንሷል እየተባለ ቢነገርም፤ በስፋቱ የሚነገርለት ትልቁ የኢትዮጵያ ደን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኘው የባሌ ተራራ ደን ነው። በእርግጥ በማያከራክር መልኩ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አጠቃላይ ከመሬት ስፋቷ ከ35 በመቶው በላይ የነበረው የደን ሽፋን በ2000ዎቹ መጀመሪያ ወደ 4 በመቶ የቀነሰ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለመመለስ በተደረገው ጥረት እ.ኤ.አ. በ 2010 የኢትዮጵያ መሬት 12 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር በተፈጥሮ ደን እንዲሸፈን ማድረግ ተችሏል። ከ2010 በኋላ በተሠሩ ሥራዎች በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴው ሌጋሲ ተነሳሽነት በኢትዮጵያውያን ዘንድ የችግኝ ተከላ ባሕል እንዲሆን በተሠራው ሥራም ከዓመት ወደ ዓመት ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ ይገኛል።

ሰሞኑን ይፋ በተደረገው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ሪፖርት እንደተመላከተው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በ2011 ዓመተ ምሕረት ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ አሁን በ2016 ዓ.ም ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ብሏል። እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የተቻለው በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ30 ሚሊዮን ሰዎች በላይ የሚሳተፉበት የችግኝ ተከላ በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ሌጋሲ በሚሊዮን የሚጠጋ ብዛት ችግኝ ተከላ በመካሄዱ ጭምር ነው። ባለፈው ዓመት ማለትም መንግሥት በአንድ ጀንበር 569 ሚሊዮን ችግኞችን መተከሉን ያሳወቀ ሲሆን፤ ዘንድሮም የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ዘንድሮ በአንድ ጀንበር 150 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል።

ይህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው በአንድ ቀን በሚሊዮን የሚቆጠር ችግኝ እንትከል ዘመቻ የተሳካ መሆኑ እየተነገረለት ነው። ይህ ተከላ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የደን ሽፋን ከማሳደግ በተጨማሪ የካርበን ልቀትን በመከላከል በኩል የሚያበረክተው አስተዋፅዖም ከፍተኛ እንደሚሆንም እየተጠቆመ ይገኛል።

ችግኝ ተከላን እንደባሕል መውሰድ እና የደን ሽፋንን ማስፋት ለኢትዮጵያውያን ቅንጦት ሳይሆን ግዴታ ነው የሚሉት ምሑራኑ፤ መነሻቸው ኢትዮጵያ ከዓለም አገራት መካከል ለአየር ንብረት ለውጥ በጣም ተጋላጭ ከሆኑ ሀገሮች አንዷ በመሆኗ ነው። ራሷን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ከአረንጓዴ ልማት ጋር ተያይዞ የሚያከናውኑት ደንን የማስፋት ተግባር እጅግ እንደሚጠቅማት ምሑራን ትንታኔ በመስጠት ላይ ናቸው።

ከሚገኙት ጥቅሞች መካከል ዛፎች ካርቦን ዳይኦክሳይድን ከአካባቢ አየር ውስጥ ስለሚወስዱ የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ይረዳሉ። በዚህ ረገድ ይህ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን ሕዝብ በመጥቀም በኩል የሚኖረው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ስለመሆኑም የዘርፉ ምሑራኖች ያስረዳሉ።

ጠቅለል ባለ መልኩ እንደሚጠቆመው ለሰው ልጆች ዛፎች በአካባቢ አየር ውስጥ ያለውን የግሪንሃውስ ተፅዕኖ እንዲዋጋላቸው ከማስቻል ባሻገር፤ ዛፎች ውሃ በመቆጠብ፣ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ እንዲሁም ኃይልን በመቆጠብ ረገድ የሚኖራቸው ፋይዳም የጎላ መሆኑ እሙን ነው። ይህ ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ አፈሯ በገፍ በጎርፍ እና በወንዝ እየተሸረሸረ ወደ ጎረቤት አገር የሚኮበልልባት ኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ ጉዳይ ወይም ደንን ማስፋት ቀለል ተደርጎ የሚወሰድ አይሆንም።

የዛፎች መኖር የዝናብ መጠንን መጨመሩ አንደኛው ጥቅም ሲሆን፤ በሌላ በኩል ዛፍን ለማገዶ በማዋል ሰዎች በእንጨት ምግብ ማብሰልን ጨምሮ ሌሎች በእንጨት የሚሠሩ ጥቅሞች እንዲያገኙ እንደሚያግዝ ይነገራል።

ይህም ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለማገዶ እና ለሌሎች በእንጨት አገልግሎት ለሚሰጡ ቁሳቁሶች በዋሉ ዛፎች ምክንያት ደኗ ከ35 በመቶ አሽቆልቁሎ 4 በመቶ ላይ ደርሳ ለነበረች ሀገር ችግኝ ተከላን ማስፋት ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም። በተለይ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የፍላጎት መጨመር የሚኖር መሆኑን ታሳቢ በማድረግ አስቀድሞ ችግኝ ተከላው ላይ ማተኮር እንደሚገባ አያጠያይቅም።

ዛፎች ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን በመፍጠር በኩል ሚናቸው የሚናቅ አለመሆኑም በጥናት ተረጋግጧል። ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ዛፎች የፍራፍሬ ምርት በስፋት እንዲኖር ከማገዝ በተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭን፣ የነዳጅ ሽያጭን ለማረጋጋት ያግዛሉ። በተጨማሪ የግንባታ ዕቃ ሽያጭን፣ የቤት ቁሳቁስ ሽያጭ ላይም በግብዓትነት የሚውሉ በመሆናቸው ገበያውን በማረጋጋት በኩል የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑም ይነገራል።

ይህ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጋርም የተያያዘ ሲሆን፤ 120 ሚሊዮን አካባቢ የሚገመት ሕዝብ ከዛፍ እና ከእንጨት ጋር ተያይዞ ቤት ለመሥራትም ሆነ፣ የቤት ቁሳቁስ ለማሟላት እንዲሁም ሌሎች ከዛፍ ጋር ተያይዞ ለሚኖረው ፍላጎት አስቀድሞ ለሟሟላት ችግኝ ተከላ ማካሔዱ እጅግ አስፈላጊ እና ተገቢ መሆኑ አያጠያይቅም።

ዛፎች የአየር ብክለትን ለመቀነስ እና የአካባቢውን የአየር ሁኔታ ከመለወጥ ባሻገር የድምፅ ብክለትን እንደሚቀንሱም ጥናቶች ያመላክታሉ። ይህ በአጠቃላይ ለሁሉም ከሚሰጡት ጥቅሞች መካከል አንዱ ሲሆን፤ የግል ጤናን በማሻሻል በኩልም ዛፎች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ይነገራል። ሰዎች ከሚስቡት አየር ጀምሮ ከውሃ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት የዛፎች በስፋት እና በብዛት መኖር የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ሳይታለም የተፈታ ነው።

ይህ ሁሉ ሲታይ ኢትዮጵያውያን ከመንግሥት ጎን ሆነው የችግኝ ተከላውን ማካሔድ እና የሀገሪቷን የደን ሽፋን ማሳደግን ከስንት አንድ ጊዜ የሚደረግ ቀላል ተግባር ሳይሆን በየጊዜው ትኩረት ተሰጥቶት ሊተገበርበት የሚገባ ባሕል መሆን እንደሚኖርበት የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ጥናት ያካሄዱ ምሑራን ይመክራሉ።

ፌኔት ኤሊያስ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You