ፊርማው፣ የኢትዮጵያን በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ የተቃኘ ዲፕሎማሲ ለፍሬ ያበቃ ነው!

የጋራ ተጠቃሚነትን መርኋ አድርጋ የምትሠራው ኢትዮጵያ፤ ከጎረቤት ሀገራት ጀምሮ ካለ የሁለትዮሽ ትብብር እስከ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘለቀ የባለ ብዙ መድረክ ግንኙነቶች ሁሉ የሚኖራት የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን የምትመራው በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ ነው። ለዚህም ነው በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ኢትዮጵያ የምታራምደው የዲፕሎማሲ መንገድ፤ አንዱ አንዱን በሚጫንና በሚያስገድድ ሳይሆን፤ ሁሉም አካል በሚኖረው የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ ሰጥቶ በመቀበል ውስጥ የሚገኝ የጋራ ተጠቃሚነትን እውን በማድረግ ነው።

ኢትዮጵያ በዚህ መርሕ መሠረት በሁሉም ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን አከናውናለች፤ በዚያው ልክም ውጤቶችን አስገኝታለች። ለአብነት፣ አፍሪካዊ ጉዳዮች በአፍሪካ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲታዩ የተደረገበት አካሄድ እውን እንዲሆን እና አፍሪካ በሌሎች ጫና ስር እንድትወድቅ የተዘረጋውን የሴራ መረብ በማስወገድ ረገድ የኢትዮጵያ ሚና ቀላል አልነበረም። የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በሚል የሚታወቀው ተቋም ሳይቀር የአፍሪካ መሪዎችን በማሳደድ የቅኝ ገዢዎችን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሆኖ የተገለጠበትን አካሄድ በመግታት በኩል ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት በኩል የቀዳሚነት ሚናዋን ተወጥታለች።

ከዚህም ባሻገር እንደ ሀገርም፣ እንደ ቀጣናም፣ እንደ አሕጉርም የሚታዩ ኢ-ፍትሐዊ አካሄዶችና አሠራሮች መስመር እንዲይዙ ረጅም ርቀትን ተጉዛለች፤ እልህ አስጨራሽ የዲፕሎማሲ ሥራዎችንም ሠርታለች። በዚህ ረገድ የሚጠቀሰው የዓባይ (ናይል) ወንዝ ላይ ያለው ያልተገባና የተዛባ እሳቤና አጠቃቀም ነው።

ይሄን ያልተገባና የተዛባ እሳቤና አጠቃቀም ወደ መስመር ከማምጣት አኳያ ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትታገል ኖራለች። ከሃሳብ እስከ ተግባር የዘለቀንም ርምጃ ወስዳለች። በተለይ የዓባይ ግድብ እውን ከመሆኑ ቀደም ብሎም ሆነ በኋላ፤ የዓባይ (ናይል) ወንዝ የአንድ ወይም የሁለት ሀገራት የብቻ ሃብት ሳይሆን የተፋሰሱ ሀገራት በጋራ አልምተው ሊጠቀሙበት የሚገባ እና ሁሉም ወሳኝም ባለቤትም የሆነበት ሊሆኑ ይገባል የሚል አቋሟን አንፀባርቃለች። ይሄ በሕግ ታግዞ እውን እንዲሆንም ሠርታለች።

ለዚህም የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ እና ማዕቀፉም በተፋሰሱ ሀገራት ተፈርሞ ሕግ እንዲሆን፤ ይሄን ተከትሎም የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን እንዲቋቋምና የተፋሰሱ ሀገራት ከውሃ ሃብታቸው በፍትሐዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ 14 ዓመታት የተሻገረን ትግል አድርጋለች። ምክንያቱም፣ ስምምነቱ በውሃው አመንጪ ሀገራት ዘንድ የተፈረመ እና በየሀገራቱ ሕግ የሆነ ቢሆንም፤ የተፋሰሱ ሀገራት የሚገዙበት ሕግ ሆኖ በአፍሪካ ኅብረት ሊመዘገብና የተፋሰሱ ኮሚሽን ተቋቁሞ ሊተገበር የሚችልበት የአንድ ሀገር ፊርማ ይጠበቅ ነበር።

በዚህም ኢትዮጵያ ያልፈረሙ ሀገራትን የማግባባት ሰፊ የዲፕሎማሲ ሥራን ስታከናውን 14 ዓመታትን አሳልፋለች። ዛሬ ላይ የዲፕሎማሲ መንገዷ ቀንቶ ደቡብ አፍሪካ ማዕቀፉን ፈርማለች። ይሄ ደግሞ የትብብር ማዕቀፉ ሕግ ሆኖ እንዲፀድቅ እና በአፍሪካ ኅብረት ተመዝግቦ ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚያደርግ እንደመሆኑ፤ በአንድ በኩል ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ፍሬ ማፍራት ማሳያ፣ በሌላ በኩልም ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት እውን መሆን መተማመኛ የሚሆን ነው።

የደቡብ ሱዳን የትብብር ማዕቀፉን መፈረም አስመልክቶ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ደቡብ ሱዳን የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን ተቀብላ ማፅደቋ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአካባቢው ሀገራት ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ይህ ዲፕሎማሲያዊ እመርታም በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ቀጣናዊ ትብብርን ለማሳደግ ላለው ፍላጎት ጉልህ ርምጃ ነው። በጥቅሉም፣ የደቡብ ሱዳን ስምምነቱን ተቀብላ ማፅደቅ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽንን በማቋቋም የሕዝባችንን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መነቃቃትን ይፈጥራል። ” ሲሉ መግለጻቸውም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You