የመመረቂያ ጥናቶች የት ናቸው?

ወቅቱ የተማሪዎች የምርቃት ወቅት ነው:: ከዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን እስከ ማኅበራዊ ገጾች በምርቃት ምስሎች ተጥለቅልቋል:: የዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች አካባቢዎች እና የትራንስፖርት መጠበቂያ ቦታዎች በተመራቂዎችና አስመራቂዎች ደምቀዋል:: መንደሮች በምርቃት ድግስ ደምቀዋል:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የመዋዕለ ሕጻናት ምርቃት ድግስ ሌላኛው ፋሽን ሆኗል:: ለዛሬው ግን ትኩረታችን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁት ላይ ነው::

በመገናኛ ብዙኃን፣ በማኅበራዊ ገጾችና በየአካባቢው የደመቀው ይህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ምርቃት ይህን ያህል ሲደምቅ፤ ዋናው ቁም ነገሩ ግን ተዘንግቷል:: የሠሩት ጥናት የድግሱን ያህል አይደምቅም:: እንኳን የሠሩት ጥናት ይቅርና የተመረቁበት የትምህርት ክፍል ራሱ የምርቃቱን ድግስ ያህል አይታወቅም:: የመጀመሪያ ዲግሪውን እንተወውና ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ የሚመረቁት ላይ እናተኩር::

የመጀመሪያ ዲግሪ ለተማሪዎች ብርቅ ነው:: ከ15 ዓመታት በላይ በትምህርት የቆዩ ናቸው፤ በዚያ ላይ ልጆች ናቸው:: ለልጆችም ለወላጆችም ከፍተኛ የሆነ መጓጓት አለው:: በተለይ ልጆች ከ15 ዓመታት በላይ ትምህርት ላይ ቆይተው ሀገር የመረከብ ኃላፊነት ሊወስዱ ነው:: ከሥራ ዓለም ጋር ሊገናኙ ነው:: ስለዚህ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዎች የቱንም ያህል ብርቅ ቢሆንባቸው ምንም አይገርምም! እንዲያውም ሊሆንባቸው ይገባል!

ከመጀመሪያ ዲግሪ በላይ ያለው የትምህርት ደረጃ ግን በአንድ ጉዳይ ላይ ልዩ ጥናት የሚደረግበት ነው:: ተማሪውም በአብዛኛው በሥራ ላይ ያለ እና ከሥራው ጋር በተያያዘ የምርምር አቅሙን ለማሳደግ የሚማረው ነው:: በአንድ ልዩ መስክ ላይ ትኩረት አድርጎ አንድ ችግር ፈቺ ምርምር እንዲሠራ ነው:: ምርምር የሚለው ቃል ከበድ ቢል እንኳን፤ ቢያንስ በሆነ ልዩ ዘርፍ ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ የሚይዝበት ነው:: በዋናነት ከክፍል ውስጥ ትምህርት በላይ ጥናት ላይ የሚያተኩር ነው::

የምናየው ነገር ግን ከጥናቱ በላይ ትኩረት የሚሰጠው ልብሱ ነው:: በሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ) የሚመረቁ ሰዎች የመላዕክትና የቅዱሳን ስም እየጠሩ ሲጸልዩና ሲያመሰግኑ ከሱናሚ አደጋ የተረፉ እንጂ ለሁለተኛ ጊዜ የሚመረቁ አይመስሉም:: ማመስገኑ ምንም ችግር አልነበረውም፤ ችግሩ ግን የምስጋናው ትኩረት ዋናው ነጥብ ላይ አለመሆኑ ነው:: ‹‹በዚህ ዘርፍ ይህን ጥናት ሠራሁ›› ከማለት ይልቅ ልብሱን በመልበሱ መሆኑ ነው:: በነገራችን ላይ እንዲህ የሚያደርጉት በሁለት ምክንያት ነው::

አንደኛው፤ ያንኑም ቢሆን ለማግኘት ካለው አሰልቺና ተስፋ አስቆራጭ ውጣ ውረድ አንፃር ነው:: በአማካሪና በተማሪ መካከል ያለው ግንኙነት የጌታና የባሪያ የሚመስል ኋላቀር ግንኙነት ስለሆነ ነው:: አማካሪዎችን ማግኘት ራሱን የቻለ ጸሎት ስለሆነ ነው:: በስንት ጸሎት ከተገኙ በኋላም በእርጋታና በትሕትና ከማማከር ይልቅ ማመናጨቅና መቆጣት ስለሚቀናቸው ተመራቂው ‹‹ከዚህ ጉድ አውጣኝ!›› እያለ ፈጣሪውን መማጸኑ አይቀርም:: ጨርሰው ሲመረቁ ከሱናሚ አደጋ የተረፉ የሚያስመስሉበት አንዱና ዋናው ምክንያት ይህ ነው::

ሁለተኛው ምክንያት ግን፤ የሚፈለገው ወረቀቱ እንጂ ጥናቱ ስላልሆነ ነው:: ዲግሪ አለው፣ ማስተርስ አለው፣ ፒ ኤች ዲ አለው… እንጂ ‹‹በምን?›› የሚለው ትኩረት አይሰጠውም:: አንድ በሥራ ዓለም ላይ ያለ ሰው፤ ከሙያው ጋር የሚገናኝ ምን ጥናት ሠራ ከማለት ይልቅ ‹‹ማስተርስ አለው›› የሚለው ይቀድማል:: ‹‹አለው›› የሚለው እንጂ ‹‹በምን?›› የሚለው ዋና ጉዳይ አይደለም:: ቀላል ምሳሌዎችን እንይ::

ለምሳሌ፤ በአገራችን ልማድ ‹‹ዶክተር›› የሚለው ቃል በጣም ይካበዳል:: በዚህም ምክንያት ‹‹ዶክተር›› መባሉን እንጂ ‹‹የምን ዶክተር?›› የሚለውን ልብ አንለውም:: ገጠር ያሉ ቤተሰቦቻችን ለአካዳሚያዊ ጉዳዮች ሩቅ ናቸው:: የሚያውቋቸው የሙያ ዘርፎች በአካባቢያቸው የሚያውቋቸውን ብቻ ነው:: ለምሳሌ፤ አስተማሪ፣ ሐኪም፣ ዳኛ ዋና ዋናዎቹ ናቸው:: ‹‹ዶክተር›› ሲባል ለእነርሱ የሕክምና ዶክተር ብቻ ነው:: እነዚህ ሰዎች ለአካዳሚያዊ ጉዳዮች ሩቅ ስለሆኑ እንዲህ ማሰባቸው አይገርምም:: የሚያስገርመው የተማረ የሚባለውም ከእነርሱ ያልተሻለ መሆኑ ነው:: ‹‹ዶክተር›› የሚል ቃል ሲሰማ ክባድ ይሰጠዋል:: ‹‹የምን ዶክተር?›› ከማለት ይልቅ የሁሉም ነገር አዋቂ አድርጎ ‹‹እሱ እኮ ዶክተር ነው!›› ይላል::

አንድ በቆሎ ላይ ልዩ ምርምር (ስፔሻላይዝድ) ያደረገ ሰው አለ እንበል:: ይህን ሰው እንኳን ጠቅላላ ዶክተር ‹‹የግብርና ዶክተር›› እንኳን ለማለት ይከብዳል:: ምክንያቱም ግብርና ራሱ በውስጡ ብዙ ንዑስ ዘርፎች ያሉት ሰፊ ዘርፍ ስለሆነ:: ይህ ሰው የተዋጣለት የበቆሎ ምርምር ዶክተር ልንለው እንችላለን:: ስለበቆሎ የሚናገረውን ሁሉ ልናምነው እንችላለን:: በቆሎን በተመለከተ መረጃ ሲያስፈልገን መጠየቅ ያለብን ይህን ሰው ነው::

ይህ ሰው ግን አትሌቲክስን በተመለከተ ከአንድ የመጀመሪያ ዲግሪ ካለው ሰው በምንም አይለይም:: የመንገድ ግንባታን በተመለከተ አንድ የመጀመሪያ ዲግሪ ኢንጂነር ይበልጠዋል:: በአገራችን ልማድ ግን ‹‹ዶክተር›› የሚል ማዕረግ ያለውን ሁሉ የሁሉ ነገር አዋቂ አድርጎ ማየት የተለመደ ነው:: በዚያ ነገር ላይ ‹‹አላውቅም›› ካለ ‹‹እንዴት ዶክተር ሆኖ አያውቅም?›› ሊባል ነው ማለት ነው::

ይህ ችግር ማኅበረሰባዊ ልማድ ብቻ ቢሆን ቢያንስ ይሻል ነበር:: ችግሩ ተቋማዊ ባሕሪም እየተላበሰ መሆኑ ነው:: ለአንድ የሙያ ዘርፍ ባለሙያ ሲቀጠር በዚያ ሙያ ላይ ያደረገው ምርምር፣ ያለውን የሥራ ልምድና ቅርበት ከማየት ይልቅ በሌላ ዘርፍ የያዘው ተደራራቢ የትምህርት ደረጃ እንደ ክብደት ይታያል:: ‹‹እገሌ ፒ ኤች ዲ›› ያለው ነው ከማለት ይልቅ፤ የያዘው ፒ ኤች ዲ ወይም ሁለተኛ ዲግሪ ለዚያ ለሚፈለገው የሥራ መደብ (ሙያ) ምን የሚጨምረው ነገር አለው? በዚያ ሙያ ላይ ምን ጥናት ሠርቷል የሚለው ነው መታየት ያለበት::

ብዙ ጊዜ ‹‹እገሌ እኮ ይህን ያህል ዲግሪ አለው!›› ሲባል እንሰማለን:: ይህን የተናገረው ሰው ግን ‹‹በምን? በምን?›› ቢባል ‹‹እኔ እንጃ!›› ሊል ይችላል፤ ምክንያቱም ዋናው ጉዳይ ቁጥሩ እንጂ በምን ጉዳይ ላይ የሚለው አይደለም ማለት ነው:: ‹‹ምን ችግር ፈቱበት?›› የሚለውን እንተወውና ቢያንስ ግን በምን ጉዳይ ላይ የሚለው እንኳን መታወቅ ነበረበት::

ሌላኛው ችግር የመመረቂያ ጥናቶች የት እንዳሉ አይታወቅም:: ለሕዝብ ተደራሽ የሚሆኑበት ዘመናዊ የዲጂታል አማራጭ የለም:: በእርግጥ ጥናቶቹም ወረቀቱን ለመያዝ ተብሎ የሚሠሩ ስለሆነ ያን ያህል ተፈላጊ ላይሆኑ ይችላሉ:: ቀደም ሲል እንዳልነው፤ በተማሪው ችግር ብቻ ሳይሆን አማካሪዎች በጸሎት የሚገኙ ናቸው:: ከአሠራር መመሪያ ይልቅ በግል ስሜት የሚጠቅሙና የሚጎዱ ናቸው:: ይህ ሁሉንም እንደማይወክል ግልጽ ነው:: አንዳንድ ተማሪዎች ደግሞ ዋና ዓላማቸው ወረቀቱን ማግኘት ላይ ብቻ ነው:: በእነዚህ ምክንያቶች የሚሠራው ጥናት ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ የማያጓጓ ይሆናል ማለት ነው:: ቢሆንም ግን ጥናቶች በዲጂታል አማራጭ በቀላል መንገድ የሚገኙ መሆን አለባቸው:: ለሌሎች ሰዎች የጥናት መነሻ ይሆናሉ::

ስለምርቃት ስናስብ ስለሚሠሩ ጥናቶችም እናስብ:: የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ጥናቶች ትኩረት ይሰጣቸው:: ጥናቶች ከድግሱ በላይ ይሁኑ!

ሚሊዮን ሺበሺ

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም

Recommended For You