በየአካባቢያችን ላሉ ድጋፍ ለሚሹ የኅብረሰተብ ክፍሎች እጃችንን ልንዘረጋ ይገባል

አዲስ አበባ፡- በየአካባቢያችን ላሉ ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች እጃችንን ልንዘረጋ እንደሚገባ ተገለጸ።

የተባበሩት ዓረብ ኢምሬት ኤምባሲ ለአራት የተለያዩ መረዳጃ ማኅበራት የ3 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር የአልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍ አበርክቷል።

በድጋፍ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሐረጓ ማሞ፣ ኤምባሲው ከዚህ ቀደምም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ልዩ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ሁላችንም በየአካባቢያችን ላሉ ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች እጃችንን ልንዘረጋ ይገባልም ብለዋል። ኃላፊዋ እንዳሉት፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሐሳብ ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በርካታ የበጎ አድራጎት ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

ኤምባሲው ድጋፍ ያደረገላቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለበርካታ ድጋፍ ለሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መጠለያ መሆን የቻሉ ናቸው ብለዋል።

ወቅቱ ልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች የሚሠሩበት መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ሐረግ ባለሀብቶችና በተለያየ ሙያና እድሜ ላይ ያሉ ዜጎች የክረምቱን ወራት ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግ እንዲያሳልፉም ጥሪ አስተላልፈዋል።

እርስ በእርስ መደጋገፍ የኢትዮጵያውያን መገለጫ ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ ድጋፍ ማድረግን በአቅራቢያችን ከሚገኙ ድጋፍ ከሚሹ አረጋውያን፣ ሴቶችና ሕጻናት በመጀመር ይህን እሴት ማጠናከር ይገባናል ብለዋል።

ኤምባሲው ድጋፍ ካደረገላቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል የ “የወደቁትን አንሱ የነዳያን የበጎ አድራጎት ማኅበር” ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቀሲስ ሳምሶን በቀለ ለተደረገላቸው ድጋፍ ኤምባሲውን አመስግነው፣ ማኅበሩ ለዛሬ የደረሰው ከተለያዩ አካላት በሚደረግለት ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ማኅበሩ ከተመሠረተበት ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ደጋፊና ተመልካች ያልነበራቸው አረጋውያንንና ሕሙማንን በመጠለያ ልብስና በምግብ ሲያግዝ መቆየቱንም አንስተዋል። በአሁኑ ወቅትም 300 ያህል አረጋውያንና ሕሙማንን በቋሚነት እየደገፈ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሌላውን በመደገፍና የወደቀውን በማንሳት ረገድ ያለው ልምድ ትልቅ ነው ያሉት የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ፣ በየአካባቢው ያሉ ደጋፊና ጠያቂ የሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ ሁኔታ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም

Recommended For You