ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ እነሆ ስድስት ዓመታት ተቆጠሩ። በእኚህ ስድስት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች ከኢኮኖሚውና ከሌሎች ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ባሻገር በከተማ ማስዋብ ሥራ ላይ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል.. እየተሠሩም ይገኛሉ። እንደሚታወቀው አብዛኛው የሀገራችን ከተሞች የከተማነትን መስፈርት ያሟሉ ናቸው ብሎ መናገር ይከብዳል። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተሠራው የግንዛቤ ለውጥ ግን በብዙ ከተሞች ላይ ከፍተኛ መሻሻልን እያየን የመጣንበት ሁኔታ ነው ያለው። ያለፉትን ስድስት ዓመታት ‹የጽዱ ከተማ የኑሮ በጤናን› ንቅናቄ እንደ ማሳያ በመጠቀም የሀገራችንን የከተሞች አሁናዊ መልክ ማየት ይቻላል።
ሁሉንም እንቃኝ ብንል ጊዜ ስለማይበቃን ለዛሬ የመዲናችንን የአዲስ አበባን የበጎ ዐሻራ የከተማ ውበት ላስቃኛችሁ። መዲናችን አዲስ አበባ ከዋና ከተማነት ባለፈ የአፍሪካ መዲናም ጭምር ናት። በዚም ሳያበቃ የዓለም የዲፕሎማሲ መቀመጫ፣ የአፍሪካ ህብረት ቢሮ መገኛ እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስብሰባዎች የሚካሄዱባት ትልቅ ከተማ ናት። እንደ መዲናችን የአገልግሎት ስፋትና አይነት ግን ዜጎችን የሚመጥን በቂና አስተማማኝ የመዝናኛም ሆነ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ሥፍራዎች በጥራትና በአይነት የሉንም። ይሄ ብቻ አይደለም መቶ ሃያ ሚሊዮን የሕዝብ ቁጥር ላላትና ከሰባ በመቶ በላይ ወጣት ለሆነባት ሀገር የወጣቱንም ሆነ የአብዛኛውን ማህበረሰብ ፍላጎት ያሟላ ሁሉን አቀፍ የመዝናኛ ሥፍራ የላትም።
ይሄ የታያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተአምር በሚመስል ሁኔታ ለዛውም በጥቂት ጊዜ ውስጥ የአዲስ አበባን ገጽታ የሚያጎሉ ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ሀገራት ጎብኚዎች መደነቂያ የሆኑ የተለያዩ ከመዝናኛ ስፍራ እስከ ኮሊደር ልማት ድረስ የዘለቀ በጽዳትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሠርተዋል። እያንዳንዱ ፓርክና የመዝናኛ ሥፍራ ኢትዮጵያዊነትን በሚያጎሉ ሀበሻዊ ቁሶች የተሠሩ ከመሆናቸውም በላይ በኢትዮጵያዊ ለዛና ቀለም የተበጁ የአብሮነት ጥግ ማሳያ መሆናቸው ሌላው ድምቀት ነው። ይሄም ብቻ አይደለም በእያንዳንዱ የከተማ ገጽ ውስጥ፣ በእያንዳንዱ ፓርክና መዝናኛ ሥፍራ ውስጥ የሀገርን ታሪክ የሚናገሩ፣ ጥንታዊና ዘመናዊ ሀገር በቀል ትውፊቶች መኖራቸው ነው።
በኮሊደር ልማት ረገድም በአጭር ጊዜ ውስጥ አስገራሚና ለከተማችን የሚመጥኑ መንገዶችንና ተያያዥ ሥራዎች ተከናውነዋል። በትናንትና በዛሬ ውህድ ቀለም እየነከርን የጻፍናቸው የአብሮነት ገጾች በውብ ከተማችን ላይ ተገልጠው ውበትን ከዘመናዊነትና ከጤና ጋር አቆራኝተው ለከተማችን ውበትን ለሕዝቡ ደግሞ ጤናንና ዘመናዊነትን ጀባ ብለዋል። እኚህ ውብ ገጾች ስለ ኢትዮጵያ የሚዘምሩ፣ ስለ ታላቅ ሀገርና ታላቅ ሕዝብ የሚናገሩ የአብሮነት ዐሻራዎች ናቸው። እኚህ ውብ ገጽታዎች ኢትዮጵያን አንድ አድርገው ያቆሙ፣ ዘመኑን የዋጁ የተስፋ ምልክቶች ናቸው።
በከተማ ውበትና በኮሊደር ልማት ሥራዎች ላይ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆንንና በቀጣይም በላቀና በበረታ መልኩ ከተማችንን ከአፍሪካ ቀዳሚዋ የማድረግ ተልዕኮ እንዳለ ብዙ ማሳያዎች አሉ። የማይቻሉ የሚመስሉ የተለያዩ ሥራዎችን በጋራ ሠርተን የላቀ ውጤት አምጥተናል። በመጥፎ ጠረንና እዛም እዚም በሚጣሉ ቆሻሻዋ የምትታወቀው መዲናችን አምራና ተውባ እንደሙሽራ የታየችበት አሁናዊ ገጽታዋ ‹ጽዱ ከተማን ከማህበረሰብ ጤና ጋር አስተሳስረን የተነሳንበትን ዓላማ በጉልህ የሚያሳይ ነው። እያወራን ያለነው በአዲስ አበባ እየተሠሩ ካሉ የልማት እቅዶች አንዱን መዘን ነው። የተጀመሩትንና ሊጀመሩ የታሰቡትን እንዘርዝር ካልን ጊዜ ላይበቃን ይችላል።
በሸገር ገበታ የተጀመረው የልማት መነቃቃት ወደኮሊደር ልማት አድጎ አዲስ አበባን ተሻግሮ በክልልና በወረዳ ድረስ ተግባራዊ በመሆን ላይ ነው። እንደአብነት ባህርዳር፣ ሃዋሳ፣ አርባምንጭ በኮሊደር ልማት እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ከተሞች ናቸው። በቅርቡ በርካታ ከተሞች የዚህ ንቅናቄ ተሳታፊ ይሆናሉ። አዲስ አበባችን የመጀመሪያ ፓርኳን ያየችው በጠቅላይ ሚኒስተራችን የላቀ መነሳሳት አንድነት ፓርክን ነው። አንድነት ፓርክ ከፓርክነቱ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ድሮአዊና አሁናዊ ታሪኮችን የያዘ ራሱን የቻለ ሙዚየም ነው። እኔና እናተ ከነውበታችን፣ ከነቀለማችን፣ ከባህልና ሥርዓታችን ጋር በአንድ ሥፍራ በአንድነት ፓርክ ውስጥ ታሪክ እያወራን አለን።
ታሪክና ትውፊትን በእንደዚህ አይነት ዘመን ተሻጋሪ በጎ ሥራ በኩል ለትውልድ ማስቀመጥ እጅግ ብልህነት ነው። ህብረብሄራዊነትን በአንድ ቦታ ለዛውም በሚስብና ለእይታ ምቹ በሆነ ሥፍራ ማግኘት ይበል የሚያሰኝ ነው። ከዚህ በተጨማሪ አንድነት ፓርክ ቤተመንግሥት ጊቢ ውስጥ መሠራቱ ልዩ ያደርገዋል። ከልዩነቱ አንዱ ቤተመንግሥትን ለሕዝብ ክፍት ከማድረግ ጋር የሚመሳሰል ትርጉም ያለው ነው።
ስለ አንድነት ፓርክ አውርተን ሳንጨርስ፣ ተገርመንና ተደንቀን ሳናበቃ ሁላችንንም በአንድ ያስገረመ እንጦጦ ፓርክ ተመረቀ። እንጦጦ ፓርክ ፓርክ ብቻ አይደለም ለዚህ ደግሞ ፓርኩን ሄዳችሁ ያያችሁ ምስክሮች ናችሁ። እንጦጦ ፓርክ የኢትዮጵያዊነት አለላ መልኮች የተጣመሩበት ከመዝናኛ ባለፈ ብዙ ትርጉም ያለው መናፈሻ ነው። ፓሪስና ዱባይን፣ አውሮፓንና ኢሲያን የሚስተካከል አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ የሚያስንቅ ኢትዮጵያዊ መልክ ነው። ይህ ውብ መልክ ደግሞ ዝም ብሎ አልመጣም ለውበትና ለጤና ከሰጠነው የገዘፈ ቦታ የፈለቀ ነው።
አሁን ላይ እንጦጦ ፓርክን ለብዙ ነገር እየተጠቀምነው እንገኛለን። የከተማችን ቁጥር አንድ መዝናኛ ከመሆኑም በተጨማሪ ሰርግና መሰል የደስታ በዓላትን እናሳልፍበታለን። ለፊልምና ለተለያዩ ቀረጻዎች እየተጠቀምንበት እንገኛለን። ለተለያዩ ስብሰባዎች እያገለገለን ያለ ዘመናዊና ታሪካዊ፣ የብዙ ሃሳቦች፣ የብዙ ህልሞች ውብ ሥፍራ ነው ብል አጋነንክ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። የከተማ ውበት ግሳጋሴአችን ወደ ሌላም ይወስደናል..በአንድነት ፓርክ ጀምረን በእንጦጦ ቀጥለን በወዳጅነት ፓርክ አሰልሰናል።
የወዳጅነት ፓርክ እንደስሙ አንድነትንና አብሮነትን የሚገልጥ፣ የውህደትና የትስስር ምልክት ነው። ኢትዮጵያዊነት ከመልክና ከወዙ ጋር የሚታይበት የፍቅርና የመቻቻል ፓርክ ነው። ከስሙ ጀምሮ እስከግብሩ ድረስ አያይዞና አሰባስቦ በጋራ የሚያማክር ቦታ ነው። በርካታ ብሄር ብሄረሰብ በአንድነትና በወዳጅነት እጅ ለእጅ ተያይዘው አንድ ሃሳብ የሚያስቡበት፣ አንድ ህልም የሚያልሙበት የጥቁርነት ቀለም ነው። እኚህ ፓርኮች ከመዝናኛነት ባለፈ አብሮነትን ከማስቀጠል ረገድ ሚናቸው የላቀ ነው። ውበትን ከምቾትና ከከተማ ገጽታ ጋር አስተሳስረው ያሉ የትጋት ውጤቶች ናቸው።
በነዚህ ፓርኮች አማካኝነት ለብዙዎች የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል። በእነዚህ ፓርኮች አማካኝነት የይቻላል በጎ መንፈስን በውስጣችን አስርጸናል። እኚህ ፓርኮች እንደብሄራዊ ድል አንድነታችን የታየባቸው ከሕዝብ በሕዝብ ለሕዝብ አንድምታን የሚያንጸባርቁ ናቸው። ሌላው ከዚህ ጋር አብሮ የሚነሳውና የአዲስ አበባን ገጽታ በትልቁ ከቀየሩ አጋጣሚዎች አንዱ መስቀል አደባባይ ነው። ሀገር ትናንምትና ዛሬ ነገም የራሷ የሆነ መልክና ደም ግባት አላት። የዛሬ የከተማ ልማቶች ለነገው ትውልድ ምቾትና የጤና መድህን ሆነው መቀመጣቸው እሙን ቢሆንም እንደሀገር ትርፋቸውም የት የሌለ ነው።
መስቀል አደባባይ የከተማዋ ትልቁ አደባባይ ከመሆኑም ባሻገር ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ መንፈሳዊና ዓለማዊ በዓላት ሲካሄዱበት ቆይቷል። የመስቀል በዓልን ጨምሮ፣ የተለያዩ የሕዝብ በዓላት፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ መንግሥታዊ ዝግጅቶች ከተስተናገዱበት ዝግጅቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። ይሄን በዓይነቱ ትልቅ የሆነ አደባባይ መንግሥት ከዘጠኝ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ 2.6 ቢሊዮን በሆነ የገንዘብ ወጪ እጅግ ዘመናዊ በሆነ መልኩ አሰርቶ ለአገልግሎት ክፍት ካደረገው ዓመታት ተቆጥረዋል። እስከ ማዘጋጃ ቤት ድረስ የሚዘልቀው ይሄው የመስቀል አደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት መንግሥት ለከተማ ውበት የሰጠውን ዋጋ በግዝፈት የሚያሳይ ነው።
አዲስ አበባ ከተማ እንደ ሀገሪቱ ዋና ከተማነት፣ እንደ አፍሪካ መዲናነቱ፣ እንደ ዓለምአቀፍ እውቅናው ከዚህም በላይ ማማርና መበልጸግ የሚገባው እንደሆነ ይታመናል። በዚህ ግዙፍ የዋና ከተማ አደባባይ ላይ የከተማውን ገጽታ የሚጨምሩ እጅግ ሰፊና ማራኪ የሆኑ እስከ አንድ ሺ አራት መቶ ሃምሳ (1450) የሚደርሱ መኪናዎችን መያዝ የሚችል ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንጎች ተሠርተዋል። በተጨማሪው የተለያዩ ሱቆች፣ መጸዳጃ ቤቶች የተካተተበት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የከተማዋን ውበት የሚያጎሉ የተለየዩ ስክሪኖችም የተገጠሙለት አውሮፓ ስታንዳርድ አደባባይ ነው። ይህ እንግዲህ ለከተማ ውበትና ለማህበረሰብ ጤና ቅድሚያ ተሰጥቶ የተሠራ የባለፈው ዓመታት የታሪክ ሰነድ ነው።
በስተመጨረሻም የጉዳዬ አንደኛ ወዳደረኩትና ይሄንንም ጽሁፍ እንድጽፍ ወዳነሳሳኝ ትልቅ ቁም ነገር ልለፍ። ከላይ እንዳየንው ያለፉት ዓመታት በከተማ ገጽታ እና ውበት በኩል ብዙ ሥራዎችን የሠራንባቸውና እንደስኬት የምናወሳቸው ዓመታት እንደነበሩ በድፍረት መናገር ይቻላል። ለዚህ ነጻ ሃሳብ እንደማሰሪያና እንደዋና ማጠንጠኛ የሚሆነው አሁናዊው የኮሊደር ልማት አፈጻጸም ነው። ስድስትና ሰባት ወራት የተያዘለት በአምስት የኮሊደር ልማት የተጀመረው አዲስ አበባን የማስዋብ ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ከተማችንን ልዩ ድባብ ሰጥቷታል።
ይሄ መንፈስ ወደመላው ኢትዮጵያ ተስፋፍቶ በአሁኑ ሰዓት በርካታ ከተሞች በኮሊደር ልማት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ። የኮሊደር ልማትም ሆነ የከተማን ውበት የሚመለከቱ ሌሎች ሥራዎች ዘመናዊነትን ከሥልጣኔና ከኑሮ ምቹነት ጋር የሚገልጡ ናቸው። ሀገር ለማህበረሰብ ምቹ ከባቢ ሳይኖራት በዋና ከተማ መጠራቷና የዓለም የዲፕሎማት መቀመጫ መሆኗ ብቻውን ትርጉም የለውም። በነገራችን እኛ ብቻ አይደለንም ለተለያየ ጉዳይ ከውጭ ወደሀገራችን የሚመጡ ነጮች ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ባለመኖሩ፣ አረንጓዴ የለበሰ መዝናኛ ሥፍራ ባለመኖሩ ቅሬታ የሚያነሱ ናቸው።
እሱ ብቻ አይደለም ከአፍሪካ ምርጡን ኤርፖርት ይዘን ምርጥ እና ለኑሮ እንዲሁም ለጎብኚዎች ተስማሚ አዲስ አበባን ካልፈጠርን ምቹ ኤርፖርት ብቻውን ገጽታችንን አይገነባም። ከኤርፖርት የወረደ አንድ የውጭ ዜጋ የሚያርፍበት ምቹ ሆቴል፣ የሚዝናናበት ምቹ መዝናኛ ሥፍራ፣ ወጣ ብሎ የሚያየው አረንጓዴ ከባቢ ያስፈልጋል። ሥልጣኔን ከረጃጅም ፎቅ ጋር አስተሳስረን ግራ ተጋባን እንጂ በውጭው ዓለም የዘመናዊነት ልኬት ከሆኑት ውስጥ እንደ ፎቅ ሁሉ አረንጓዴ ከባቢዎች ቀዳሚዎቹ ናቸው። ስለሆነም የኮሊደር ልማቶች ዘርፈ ብዙ ጥቅም አላቸው እንደሀገር ከውበትና ከጤና ጋር የተሳሰሩ ሲሆኑ በተጨማሪም የውጭ ጎብኚዎችን በመሳብ፣ የሥራ እድሎችን በመፍጠር በጎ ዐሻራ ማሳረፍ የሚችሉ ናቸው።
ልቀንና በርትተን በቀጣይም የተሻሉና የበለጡ ኢትዮጵያዊነትን በላቀ መልኩ የሚያጎሉ ሥራዎች እንደሚሠሩ ተስፋ አለ። ሁልጊዜም ካለፈው ይልቅ የሚመጣው ይበልጣል። ያሉትን እንደመንደርደሪያ በመውሰድ ለላቀ ክዋኔ የምንበረታባቸው እንደሚሆኑ እናምናለን። በብዙሃን ተሳትፎ፣ በቀን ሃያ አራት ሰዓት፣ በሳምንት ሰባት ቀን በሚሠሩ ትጉ እጆች በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲሳባንና አካባቢዋን በዚህ ልክ ማሳመር ከተቻለ ቀጣዩ ጊዜ ምን እንደሚመስል መገመት አይከብድም። በከተማ ማስዋብ ሥራ ያለፉት ጥቂት ወራት የአምስትና አስር ዓመታትን ያክል ዋጋ ያላቸው እንደሆኑ ውጤታቸው ይመሰክራል።
ከምንም በላይ ቃል በተግባር የታየበት፣ የእውነት፣ የጽናትና የይቻላል መንፈስ ተንጸባርቆ ያለፈበት ጊዜ ነበር። በዲዛይንና በፈጠራ፣ በአብሮነትና በቅንጅት አክሱምንና ላሊበላን ያነጹ እጆቻችን ዛሬም ተአምር መሥራት እንደሚችሉ በተግባር አይተናል። ‹ጽዱ ከተማ ኑሮ በጤና› ዘመናዊነትና የኑሮ ዋስትና የሚረጋገጥባቸው የተሀድሶ መሪ ሃሳቦች ናቸው። አበቃሁ። ሰላም ለእናተ ይሁን።
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም