ታሪክ፣ እውነት እና እምነት- ተደምረው የተገለጡበት ጎርጎራ፣ ሰላምን አብዝቶ ይሻል!

ኢትዮጵያ የገናና ታሪክ፣ የባለጸግነት እውነት፣ የሕዝቦች ማንነት የተቀረጸበት እምነት፣… ባለቤትነት ለዘመናት ሲነገርም ሲዘመርለትም ኖሯል፡፡ ይሁን እንጂ ታሪኳ ለከፍታዋ አቅም ከመሆን ባሻገር ለሕዝቦቿ መናቆሪያ ተረክ ተበጅቶለት ማጋጫ ተደርጎም ዘልቋል፡፡ የባለጸግነቷም እውነት በተግባር ሳይገለጥ በወሬ ብቻ ተተርኳል፡፡ የእምነት አምባነቷም ዛሬ ዛሬ ከንግግር ማሳመሪያነት የዘለለ ትውልዱን በእምነት ልዕልና ቀርጾ ከመግለጥ አኳያ የበዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት ሆኗል፡፡

የእነዚህ ሦስት ጥምረቶች፣ ግን ደግሞ ከመኖራቸው ተረክ የዘለለ በሚገባቸው ልክ ለሀገርና ሕዝብ ፋይዳ ሳይሰጡ የኖሩ ጉዳዮች ማዕከልም፣ የሀገር ምልክትም ሆና የምትገለጠው ደግሞ ጎርጎራ ናት፡፡ ምክንያቱም፣ ጎርጎራ – የሚነገርም የሚናገርም ታሪክ አላት፤ ጎርጎራ- የምትገልጠውና ለሕዝቦቿ የምታተርፈው ሀብት ባለቤትነቷን የምትገልጥበት እውነት አላት፤ ጎርጎራ – ትውልዱን በሥነምግባር ገርታ የምታኖርበት፣ ለሀገር የሚተርፍ እሴትና ቅርስ ያበለጸገችበት እምነትም አላት፡፡

በዚህ መልኩ ጎርጎራ የሀገር ምሳሌ ናት፡፡ ኢትትዮጵም የታሪክ ባለቤት፣ የባለጸግነት እውነት፣ የእምነት አምባነቷ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ግን ደግሞ እነዚህ ከራሷ አልፈው ለዓለም የሚተርፉ ሀብቶቿን ምን ያህል አውቃቸዋለች፤ ምን ያህልስ አልምታ አስተዋውቃቸዋለች፤ ምን ያህል ተጠቅማባቸዋለች፤… የሚሉት ጉዳዮች ሲፈተሹ እምብዛም ሳይታይ ቆይቷል፡፡ ምክንያቱም አንድም እነዚህን ሀብቶቿን ለይታ አላወቀቻቸውም፤ ብቻውቃቸውም እንዴት አልምታ መጠቀም እንዳለባት ለዘመናት አልተገለጠላትም፡፡

ሁለተኛም፣ እነዚህን ሀብቶቿን በልካቸው አልምታ እና ገልጣ እንዳትጠቀም እንቅፋት የሚሆኑ የሰላም እና ሌሎችም ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ ፈተናዎች አንቀዋት ቆይተዋል፡፡ ዛሬ ላይ ግን ጊዜውን የሚዋጅ እሳቤን በመያዝ በለውጥ ታግዞ ወደሥልጣን የመጣው የለውጥ መንግሥት ይሄንን ታሪክ የሚቀይር ተግባር እያከናወነ ይገኛል፡፡ ሀገር ታሪክ አላት ከማለት ባሻገር ታሪኳን በልኩ ገልጦ የመጠቀም፤ ሀገር እምቅ አቅምና ሀብት አላት የሚለውን እውነት የማረጋገጥ፤ የሀገር የእምነቶች አምባነት በሚገባው ልክ የሠብዓዊ ግንባታ ማዕከል የማድረግ አካሄድን እየተከተለ ይገኛል፡፡

የእነዚህ የበዙ ሀገራዊ ተግባራት ድምር ውጤቶች አንድ ማዕከል ሆና የምትገለጠው ደግሞ ጎርጎራ ናት፡፡ ምክንያቱም ጎርጎራ ለዘመናት የታሪክ አውድነቷ ቢታወቅም ሳይገለጥ ኖሯል፡፡ የእምቅ ሀብት ባለቤትነቷ እውነትም ተሰውሮ ኖሯል፡ ፡ ለሠብዓዊ ግንባታም፣ ለታሪክ እሴት ማዕከልነት የሚታትሩት የእምነት አደባባዮቿም ብርሃናቸው ወደ ሌላው ከባቢ ሳይፈነጥቅ በዛው በደሴቶቿ ጉያ ተወስኖ ኖሯል፡፡ ዛሬ ግን ይሄ ሁሉ ተለውጧል፤ ጎርጎራም የሀገር ሁለንተናዊ ከፍታ ተምሳሌትነቷን የገለጠችበትን ገጽ ተላብሳለች፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመሩት የገበታ ለሸገር፣ የገበታ ለሀገር እና ለትውልድ ፕሮጀክቶች አንድ አካል ሆና፤ የአስር ዓመቱ የልማት ስትራቴጂ እቅድም አንድ አዕማድ ለሆነው ቱሪዝም ማሳኪያነት ታልሞ በተሠራው ሥራ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ መልክና ልክ ተገልጣለች፡፡ ይሄ ሲሆን ግን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ አይደለም፡፡

ምክንያቱም ፕሮጀክቱ በገበታ ለሀገር ሲጀመር የነበረው ሰላምና መነሳሳት ባለበት አልቀጠለም። ለምን ቢባል፣ ይሄን መሰል መንገድ ፋይዳው ለሕዝብ፣ ገጽታው ለሀገር ነውና፤ ሕዝብ ሲጠቀም የማይሹ፤ ሀገር ስትደምቅ የሚጨልም እሳቤ ያላቸው ኃይሎች ከውስጥም ከውጭም ውዥንብር መፍጠራቸው አልቀረም፡፡ ይሄ ደግሞ ከቃል ልፈፋ እስከ ጦር ሰበቃ የሚዘልቅ የአደናቃፊነት ሥብዕና ባላቸው አካላት የሚፈጸም ነው፡፡ ጎርጎራም እንደ ኢትዮጵያ መንገድ ሁሉ ገጹን ለመግለጥ በሚደረገው ግስጋሴ ውስጥ እነዚህን ፈተናዎች አስተናግዷል፡፡

የሀሰት ውንጀላዎች ተስተጋብተዋል፤ ክልሉን የጦርነት ቀጣና እስከማድረግ የዘለቁ ሰላምን የማደፍረስ እና ክልሉንም ሀገርንም ከልማት መንገዳቸው ለማስተጓጎል ብርቱ ትግሎችን አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ላይፈጸም የተወጠነ ሥራ ባለመኖሩ በችግር ውስጥም ተሆኖ ለማጠናቀቅ ተቻለ፡፡ እናም ጎርጎራ በፈተና ውስጥ የማለፍ ጽናትንም፤ እንደ ሀገር ያሉ አቅሞችን ደምሮ መግለጥ፣ ማልማትና መጠቀም መቻልንም ለኢትዮጵያውያን አበሰረ፡፡

ሆኖም ጎርጎራ የሀገር አንድ ምሳሌ ነው ካልን ዘንዳ፤ ሀገር ዛሬ ላይ ጸጋዎቿን ለይቶ የሚያለማት፤ በረከቶቿን ለሕዝቦቿ እንዲውሉ የምታደርግበትን ዕድል የፈጠረላት እሳቤና አመራር ባለቤት ሆናለች፡፡ ይሄ ግን ብቻውን ሀገርን አያበለጽግም፤ የሕዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎን ይሻል፡፡ ይሄ የሕዝብ ተሳትፎ ደግሞ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ብልጽግና እውን የመሆን ሂደት ላይ ትልቅ ተስፋ በሆነው የሰላም መሻት አውድ ላይ ከፍ ብሎ መገለጥ አለበት፡፡

ለዚህ ደግሞ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያን መልክና ልክ ይዞ በተገለጠው ጎርጎራ መገኛ አካባቢ ወይም አማራ ክልል ያለው የሰላም ሁኔታ አብይ ማሳያ ነው፡፡ ጎርጎራ ንግባታው በችግር ውስጥ ሆኖ መድመቅ ቻለ፡፡ ይሁን እንጂ የተገለጠውን መልክ ማጣጣምም መጠቀምም የሚቻለው የጸና ሰላም ሲኖር ነው፡፡ በጎርጎራ የተገለጠው ታሪክም፣ እውነት እና እምነትም የኢትዮጵያ መልክ ከሆነ፤ በጎርጎራ መልክ ውስጥ የተገለጠው የኢትዮጵያ መልክ የበለጠ እንዲደምቅ ዛሬ ላይ ጎርጎራ ከመቼውም ይልቅ ሰላምን አብዝታ በመሻቷ ለዚህ ሰላም ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You