በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች ከወንዶች አንጻር ሲታዩ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊውና በፖለቲካው መስኮች ያላቸው ተሳትፎና የተጠቃሚነት ደረጃ አናሳ እንደሆነ ማሳያዎች በርካታ ናቸው። ከተሳትፎና ተጠቃሚነት ባሻገር አሁን ባለንበት በዚሁ ወቅት ሴትነት በራሱ ትልቅ ፈተና እየሆነ እንደመጣ ይነገራል። ሆኖም ይህንን ጎታች አስተሳሰብ ታግለው ያሸነፉና ለሌሎች ሴቶችም መነቃቃትን ፈጠሩ በርካታ እንስቶች በየቦታው አሉ። ለዛሬው የተወሰኑትን እንመልከት።
ሔለን አዳምስ ኬለርን ብዙዎቻችን እናውቃታለን። አይነ ስውር እና መስማት የተሳናት ሆና ውጤታማ የሆነችና ለሌለች አካል ጉዳተኞችም መነቃቃትን የፈጠረች ብርቱ ሴት ናት። ሔለን ልጅ እያለች ልክ እንደሌሎች ልጆች ሁሉ ማየት እና መስማት ትችል ነበር። ነገር ግን ባጋጠማት የጤና ዕክል ማየትና መስማት አቆመች።
ቤተሰቦቿ ከጎበዟ አስተማሪ አን ሱልቪያን ጋር አገናኝተዋት በደንብ ተምራ ዲግሪም ይዛለች። ሔለን 12 መጽሃፍትን የጻፈች፤ ፊልም የሰራች፤ 40 በሚጠጉ አገሮች የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆና ያገለገለች የአካል ጉዳተኞች የተሻለ የትምህርት እና የስራ እድል እንዲያገኙም በጽኑ የተሟጋች ጎበዝ አሜሪካዊት ናት።
ልክ እንደ ሔለን አይነት ታታሪ ሴትም ኢትዮጵያ ውስጥ አለች። ሰላም ትባላለች። ሙሉ ታሪኳን እሷው ታጫውተናለች።
ስሜ ሰላም ይባላል። ማየት፣ መስማት፣ መናገር አልችልም። በዚህ የተነሳም ከሰዎች ጋር ማውራት፣ ሀሳብ መለዋወጥ፣ መጫወት መግባባት አልችልም። እኔን የምታወራኝ፣ የምትረዳኝ፣ የምታጫውተኝ፣ አስተማሪዬ እምነት አየለ ናት። ከአስተማሪዬ እምነት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን በመዳሰስና በመነካካት የምልክት ቋንቋ ነው የምናወራውና የምንጫወተው። እርስዋ በምታደርግልኝ እርዳታ ነው ከሌሎች ሰዎች ጋር መግባባት የምችለው።
ከአስተማሪዬ እምነት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን በመዳሰስ ቋንቋ ለመማር በጀመርኩ ሰሞን በጣም ከብዶኝ ነበር። ለመማርም ፍላጎት አልነበረኝም። ደስተኛም አልነበርኩም። እጅ ለእጅ ተያይዞ በዳሰሳ ማውራት በጣም ከባድ ነው የነበረው። አስተማሪዬን ብዙ አስቸግሬያታለሁ። እርስዋ ግን በጣም ትእግስተኛ ናት። ሳስቸግራት እያባበለችኝ እንድንግባባ አገዘችኝ።
በመዳሰስ መግባባት እንድችል ከረዳችኝ በኋላ ደግሞ አይነስውራን የሚጠቀሙበትን ነጭ በትር (ኬን) አያያዝ አለማመደችኝ። በዚህ ጊዜም በጣም አስቸግሬያታለሁ። አይነስውራን የሚጽፉበትንና ብሬል የሚባለውን እንድጠቀምም አስተማሪዬ ስትሞክር አልቀበላትም ነበር። ይሄን ሁሉ ሳደርግ የነበረው ለምን አላይም፣ አልናገርም፣ አልሰማም ብዬ ስለምናደድ ነው። የተጎዳሁትን ነገር ለመቀበልም ከብዶኝ ነበር።
ለምን እንደዚህ እንደሆንኩ፣ ማን እንደዚህ እንዳደረገኝ አላውቅም። አሁንም ቢሆን ይህ ሁኔታ ያበሳጨኛል። አስተማሪዬ እምነት ግን በጣም ጎበዝ ስለሆነች በትዕግስት ብዙ ነገር አስተምራ ለውጣኛለች። በጣም አመሰግናታለሁ። በመዳሰስና በመነካካት የምልክት ቋንቋ እንድችል አድርጋኛለች። በብሬልም ከኤ እስከ ዜድ (A Z) ያሉትን የእንግሊዝኛ ፊደሎች መጻፍ ችያለሁ። ስሜንም እጽፋለሁ።
አይኔ እንዲበራልኝ፣ እንድናገርና እንድሰማ እፈልጋለሁ። አንድ አንድ ጊዜ ብቻዬን ቁጭ ብዬ በሃሳቤ በርሬ የሆነ ቦታ ብሄድ እኮ አይን እገኛለሁ እያልኩ አሰላስላለሁ። አንድ ቀን አይኔ ይበራልኛል ብዬ አምናለሁ። እስከዚያው ድረስ ግን መነጽር ባገኝ ደግሞ ጥሩ ነው። ንፋሱ በጣም እያስቸገረኝ ነው። ሀኪም ቤትም ሄጄ መመርመር እፈልጋለሁ። ወደፊትም እንደ ጤናማ ሰዎች መማርና ደስተኛ መሆን እንደልቤ መጫወት እፈልጋለሁ።
አስተማሪዬ በክር ዳንቴል መሥራት ስላስተማረችኝ ማታ ማታ ዳንቴል እሰራለሁ። የምሠራቸው ዳንቴሎች ለስኒ ረከቦትና ለተለያዩ ነገሮች መሸፈኛ የሚውሉ ናቸው። ወደፊትም በብዛት መሥራት እፈልጋለሁ።
እኔ ይህንን ታሪክ መጻፍ የቻልኩት መምህሯ እና ሰላም በእጅ በመነካካትና በመደባበስ ባደረጉት መግባባት አማካኝነት መምህሯ የሰላምን ሃሳብ መልሳ እየነገረችኝ ነው።
ሰላም ከአስተማሪዋ ጋር ለመግባባት የሚያደርጉትን የእጅ መነካካት ምንነት ላልተረዳ ሰው ጨዋታ እየተጫወቱ ነው የሚመስለው። እነሱ ግን በዚህ መንገድ ነው የሚግባቡት። የሰላም መምህር የሆነችው መምህርት እምነትም መስማትና መናገር አትችልም። መምህርት እምነት ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው የኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ውስጥ እንደ ሰላም ያሉ ልጆችን እያገዘች በመምህርነት ለ14 ዓመታት ሰርታለች።
ሰላም የምትኖርበት ማህበር መስራች ወይዘሮ ሮማን መስፍን ሰላም ወደ ማህበሩ እንዴት እንደመጣችና አሁን ያለችበትን ሁኔታም ያስረዳሉ።
ሰላም የሚለውን ስም ያወጣሁላት እኔ ነኝ። ምክንያቱም ስሟን፣ ቤተሰቧን፣ በአጠቃላይ ስለ ራስዋ ምንም አታውቅም። ሰላም ብዬ ስም ያወጣሁላትም ትኖርበት በነበረው አሶሳ ከተማ ውስጥ በአንድ ወቅት ላይ በነበረ ግርግርና ሰላም ማጣት ምክንያት ለአደጋ እንደተጋለጠች ስለሰማሁ ነው።
አንድ ሀኪም ጠይቄ እንደተረዳሁት በከባድ ስለታማ መሳሪያ ተመትታ፤ አገጯ ሁለት ቦታ ተሰንጥቆ እንደነበርና በጉዳቱም ማየትና መስማት አቁማለች። ሆስፒታል ረጅም ጊዜ ሕክምና ተከታትላለች። ከሕክምናው በኋላ ግን የምትሄድበት ቤተሰብ አልነበራትም። ወደ ማህበራችን ከመጣች በኋላ ግን የክህሎት ስልጠና እንድታገኝ አድርገናል። ዛሬ ሰላም በጣም ተቀይራለች። አእምሮዋ ፈጣን ነው። በባህሪዋም መብቷን ለማስከበር ወደ ኋላ የማትል ጎበዝ ሆናለች።
ወደ ሌላዋ ታታሪ እንስት ታሪክ እንመለስ። ለአንድ ጉዳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከሚገኙ ስድስት ዞኖች አንዱ በሆነው ኮንታ ዞን ገንጂ በሚባል አካባቢ ተገናኝተናል። ኢሞታ ልዩ ትምህርት ቤት በትምህርታቸው ጎበዝ የሆኑ ተማሪዎች ተመርጠው የሚማሩበት አዳሪ ትምህርት ቤት ነው። በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አርባ ዘጠኝ ተማሪዎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን ሁሉም የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው። ከጠቅላላው ተማሪ ሴቶች 17 ብቻ ናቸው። ከሴቶቹ መካከል ተማሪ ረድኤት ታደለ አንዷ ናት።
ተማሪ ረድኤት እንደነገረችን፣ ኢሞታ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ለመግባት አንድ ተማሪ በስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ይጠበቅበታል። በውጤቱ ከተመረጠ በኋላ ደግሞ ትምህርት ቤቱ ያዘጋጀውን የመግቢያ ፈተና ማለፍ ይኖርበታል። ሥነ-ምግባርና ሌሎችም መስፈርቶች ይታያሉ።
መስፈርቱን እንደምታሟላ እርግጠኛ ብትሆንም ዜሮ ነጥብ አንድ እንኳን የሚያበላልጥ በመሆኑ እድሉን አላገኝ ይሆን ብላ ተጠራጥራ ነበር። የ8ኛ ክፍል ውጤቷ 93 እንደሆነና በምትማርበት አመያ ደጀኔ ደድኖ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃን እንዳስገኘላት ነግራናለች። የትምህርት ውጤቷ ኢሞታ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ያወጣውን መስፈርት እንድታሟላ እንዳስቻላትና የመግቢያ ፈተናውንም በጥሩ ውጤት አልፋ በትምህርት ቤቱ ለመማር እድሉን ማግኘቷን ነው የነገረችን።
ተማሪ ረድኤት በትምህርቷ ከፍተኛ ነጥብ ለማስመዝገብ ጠንክራ በመማሯ እንደሆነ ትናገራለች። እርስዋ እንዳለችው ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ስትማር ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ነው የምትወጣው። በአነስተኛ ውጤት ተበልጣ ነው ወደ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ የምትወርደው። ከሶስተኛ ደረጃ ወርዳ ግን አታውቅም።
ተማሪ ረድኤት እስካሁን ያላትን ጥሩ ውጤት ማስጠብቅ ብቻ ሳይሆን፣ ደረጃዋን ማሻሻል ነው የምትፈልገው። በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚማሩት ሁሉም ከፍተኛ ውጤት ያላቸው፣ ጠንካሮችና ፉክክሩም ከፍተኛ ነው ትላለች። እርስዋም በውድደሩ አሸናፊ መሆን ነው የምትፈልገው።
በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ውስጥ የሴቶች ቁጥር አነስተኛ መሆኑም ተማሪ ረድኤትን ቁጭት ውስጥ ከቷታል። ጠንክራ ለመማርም ሌላው ምክንያት ሆኗታል። ሴቶች በትምህርታቸው ጎበዝ እንደሆኑ ማሳየትና ተምሳሌት መሆን ትፈልጋለች። ይህን እቅዷን ለማሳካትም አዳሪ ትምህርት ቤቱ ምቹ እንደሆነላትም ትናገራለች። እርስዋ እንዳለችው ንጽህናቸውን ከመጠበቅ ውጭ ሌላ የሚሰሩት ሥራ የላቸውም። ምግብም መኝታም ተመቻችቶላቸዋል። ሀሳበቸውን የሚሰርቅ ነገርም የለም። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያለው ፀጥታ ግቢው ለመማር ማስተማር ምቹ ሆኖ ነው ያገኘችው። ሁሉም ተማሪ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት የሚፈልግ ስለሆነም በትምህርቱ ላይ ነው የሚያተኩረው። አስተማሪዎቻቸውን በቅርብ ስለሚያገኟቸውም በፈለጉት ጊዜ የሚከብዳቸውን ይጠይቋቸዋል።
ቤተሰብ ጋር ሆነው ቢማሩ ኖሮ ይሄን ሁሉ እድል እንደማያገኙም ተማሪ ረድኤት ያለውን ልዩነት ነግራናለች። ተማሪ ረድኤት በዚህ አጋጣሚ ቤተሰቦችዋን አመሰግናለች። አዳሪ ትምህርት ቤቱ የበለጠ ለትምህርት የተሻለ ሆኖ ብታገኘውም ቤተሰቦችዋ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን ስትከታተል ለትምህርቷ ትኩረት እንድትሰጥ እንደሚያበረታቷትና የሚያስፈልጋትንም እንደሚያሟሉላት ነው የነገረችን።
ተማሪ ረድኤት ወደፊት ቤተሰቧም ሀገርም ከእርሷ ብዙ ነገር እንደሚጠብቁ በማሰብ በኃላፊነት ጭምር እንደምትማር ነው የነገረችን። እርስዋ እንዳለችው ቤተሰቦችዋ ለእርስዋ የተለያዩ ወጭዎች አድርገው ሲያስተምሯት እርስዋ ደግሞ ውጤት ማምጣት አንዳለባት ታስባለች። አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥም እድሉ ሲመቻችላት እርስዋም በእድሉ መጠቀም እንዳለባት ታምናለች። በጥሩ ውጤት ትምህርቷን አጠናቅቃ በሥራ ዓለም ደግሞ የሕግ ባለሙያ ወይንም ሀኪም ሆና ሀገሯን ማገልገል ነው ፍላጎትዋ። ይሄን ለማሳካትም ቃል ገብታለች።
ኢሞታ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲቋቋም ዓላማው እንደነ ተማሪ ረድኤት ጎበዝ ተማሪዎችን በማፍራት ለሌሎችም አርአያ እንዲሆኑ እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ነው። ትምህርት ቤቱን ያቋቋመው ደግሞ የኮንታ ዞን ልማት ማህበር ነው። ማህበሩም በትምህርት ጥራት ላይ የራሱን ድርሻ ለመወጣት ያደረገው ጥረት ያስመሰግነዋል።
ትምህርት ቤቱ በ2016 ዓ.ም ነው ትምህርት መስጠት የጀመረው። አዲስ በመሆኑ ብዙ ተማሪዎች በሳይንስ ትምህርት በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ ቤተ-ሙከራ ክፍሉን ማደራጀት ይቀረዋል። ትምህርት ቤቱ የሚገኝበት የተለያየ ዝርያ ያላቸው ዛፎችና ሣር የአካባቢው መልክዓምድር ውበት ከማላበስ ባሻገር ንፁህ የሆነ አየር እንዲኖረው አድርገዋል።
በአጠቃላይ ሴቶች በየትኛውም ችግር ውስጥ ሆነው አሸናፊ መሆን እንደሚችሉ ነው። ወጣት ሰላም ተደራራቢ አካል ጉዳት ሳያግዳት ሕይወትን እየተጋፈጠች ትገኛለች። ረድኤትም በበኩሏ በትምህርቷ ጠንክራ በመማር ካሰበችው ለመድረስ መንገዷን በማቃናት ላይ ትገኛለች።
ስለሆነም ከእነዚህ ሁለት እንስቶች ታሪክ የምንረዳው ሴቶች መጠነኛ ድጋፍ ከተደረገላችው በተሰማሩበት መስክ ሁሉ አሸናፊ መሆን እንደሚችሉ ነው።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም