ኢትዮጵያ የወጪ ምርትን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት አተኩራ ከምታከናውናቸው ተግባሮች አንዱ የቡና ልማትና ግብይት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቡና ልማትና ግብይት እየተገኘ ያለው ውጤትም ከዚሁ ጠንካራ ሥራ የወጣ ነው፡፡
የቡና ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የቡና መጠን እንዲጨምር ትኩረት ሰጥታ ትሠራለች፡፡ አዳዲስ የቡና ችግኞችን በመትከል፣ ነባሮቹን በመጎንደል ይበልጥ ምርታማ እንዲሆኑ የሚደረገው ርብርብ በዘርፉ ከሚከናወኑ ተግባሮች አንዱ ነው፡፡ ልማቱን የቡና ልማት ወደማይካሄድባቸው አካባቢዎች ጭምር ልማቱ እንዲስፋፋ እየተደረገ ነው፡፡
የቡና ልማት ብቻውን ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም እንደማያስገኝ ይታወቃል፡፡ ቡና በዋናነት ለውጭ ገበያ የሚመረት እንደመሆኑ ከግብይት አኳያ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ በዚህም በቡና ግብይት ውስጥ ይታዩ የነበሩ ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፤ ይህን ተከትሎም መመሪያዎች ተሻሽለዋል፡፡ በቡና ልማቱና ግብይቱ ውስጥ ምንም ሚና የሌላቸው ደላሎችን በማስወጣት ቡና አልሚ አርሶ አደሮችን ጨምሮ ላኪዎች፣ አቅራቢዎች ቡና በቀጥታ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡበት መንገድ ተፈጥሯል፡፡
የሀገሪቱን የተለያዩ አካባቢዎች ቡናዎች ሊያስተዋውቁ የሚችሉ መድረኮችን በሀገር ውስጥም በውጭ በማዘጋጀት የዘርፉ ተዋንያን እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው፡፡ የሀገሪቱን የተለያዩ ቡናዎች የሚገዙ ሀገሮችን ቁጥር ለማሳደግ፣ ልዩ ቡናዎች በገበያው ሰፊ ድርሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ መድረኮች ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡
ሀገሪቱ የቡና ምርት በመጠን እንዲያድግ፣ ግብይቱ እንዲስፋፋ ብቻ አይደለም የምትሠራው፡፡ ቡናው ጥራቱ የተጠበቀ እንዲሆንም አጥብቃ ትሠራለች፡፡ በማምረት፣ በክምችት፣ በማጓጓዝና በመሳሰሉት ወቅቶች ሁሉ ለቡናው ጥራት መጠበቅ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡
እነዚህ የሀገሪቱ ጥረቶች ከቡና የምታገኘውን ጥቅም እንዲጠበቅ አልፎም ተርፎም የላቀ እንዲሆን አስችለዋል፡፡ ከዓመት በፊት ሀገሪቱ በቡና የውጭ ገበያ ታሪኳ አይታው የማታውቀው የውጭ ምንዛሪ ማግኘቷ ይታወቃል፡፡ ይህም በዘርፉ የተደረገው ርብርብ ውጤት ነው፡፡
ዘንድሮም ይህን ስኬት መድገም ያስቻለ የውጭ ምንዛሪ ከቡና ማግኘት ተችሏል፡፡ ሰሞኑን የወጣው የቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ ዋቢ ያደረገ ዘገባ እንዳመለከተው፤ ሀገሪቱ ባለፈው ሰኔ ወር ብቻ ለውጭ ገበያ ያቀረበችው የቡና መጠን ክብረ ወሰን የሰበረ ሆኗል፤ በዚህ ወር ከቡና ሽያጭ ብቻ 218 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ችላለች፡፡
በ2016 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከአምናው የላቀ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል፤ በበጀት ዓመቱ 298 ሺ 500 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ፣ አንድ ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ይህ አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ለውጭ ገበያ በቀረበው የቡና መጠን የ20 በመቶ እንዲሁም በገቢ የሰባት ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ አለው፡፡
አፈጻጸሙ በቡና የውጭ ንግድ ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት እንደመሆኑ፣ ይህ ውጤት እንዲመዘገብ አስተዋፅዖ ያደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ስኬት በብዙ መልኩ ሊታይ ይችላል፡፡ ሀገሪቱ አርሶ አደሮቿንና መላውን የቡና ቤተሰብ በማስተባበር ተሠርቶና ተደክሞ የተገኘ ውጤት ነው፡፡
ቡና ዘንድሮ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት የቻለው እንደ አውሮፓ ኅብረት ያሉ አካላት ከጫካ ቡና ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳደር ጥረት እያደረጉ ባለበት ወሳኝ ዓመት ላይ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ይህን ጫና በመሻገር የተመዘገበው ስኬት ሀገሪቱ እንደ ቡና ልማቷ ሁሉ በቡና ግብይቷም ጠንክራ እየወጣች መሆኗን ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወጪ ምርትን በማሳደግ እንዲሁም የገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ በማምረት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ የወጪ ምርትን በሀገር ውስጥ በማምረት በኩልም ውጤቶች እየታዩ ናቸው፡፡ በበጀት ዓመቱ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊያስወጡ የሚችሉ ተኪ ምርቶች ተመርተውባታል፡፡
ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ እንደ ግብርና ምርቶች ያሉትንም እንዲሁ በስፋትና በዓይነት እያመረተች ለውጭ ገበያ እያቀረበች ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተገኘበት ቡና ከእነዚህ ምርቶች አንዱ ነው፡፡ ሀገሪቱ የወጪ ምርቶችን በስፋትና በዓይነት ለማምረት እያከናወነች ባለችው ተግባር ቡና ውጤታማ ተግባር የተከናወነበት መሆኑ የተላከው የቡና መጠንም የተገኘው የውጭ ምንዛሪም ያመለክታል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች ምርት ተገኝቶ ገበያ የሚጠፋበት ሁኔታ ሰፊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለቡና ይህን ያህል ገቢ ሊያስገኝ የሚችል ገበያ ማግኘት መቻሉ በገበያው ላይም ምን ያህል ከፍተኛ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
የገበያ መገኘት የሚያመለክተው ሌላም ጉዳይ አለ፤ ከገበያው ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን በምርት ቀጣይነት ላይ መሥራትን በእጅጉ ይጠይቃል፡፡ ገበያው ድንገት የመጣ አይደለም ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በዓመታት ሂደት ውስጥ የተገኘ ነው፡፡ ይህን ገበያ አሟጦ ለመጠቀም፣ በምርትና ምርታማነት እንዲሁም በግብይት ላይ አሁንም ሰፊ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በቡናው ዘርፍ የምትሠሩ አካላት በሙሉ የተገኘውን ስኬት ማጣጣማችሁ እንዳለ ሆኖ የዘርፉ እምቅ አቅም ገና ብዙም ያልተነካ እንደመሆኑ በልማቱም በግብይቱም ለሚመዘገብ የላቀ ውጤታማነት አሁንም ርብርባችሁ ተጠናክሮ ይቀጥል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም