የስፖርት ጉዳይ ከስፖርትነት ያለፈ ትርጉም ከተላበሰ ዓመታት ተቆጥረዋል። በተለይም የኦሊምፒክ ስፖርት ከመዝናኛነት ባለፈ የብሄራዊ ክብር እና ኩራት ምንጭ በመሆን፤ ሀገራት ለውድድር መድረኩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው፤ ሰፊ ጊዜ እና ሀብት መድበው ውጤታማ ለመሆን በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀሱ እያስገደዳቸው ነው።
በውድድር መድረኩ የሚመዘገቡ ውጤቶችም፤ ሀገራትን እንደ ሀገር በአደባባይ ከፍ ያለ ክብር እና ሞገስ የሚያጎናጽፍ፤ ሰንደቅ ዓላማቸው እና ብሔራዊ መዝሙራችው በአደባባይ ጎልቶ እና ደምቆ እንዲታይ ፤ እንዲሰማ የተሻለ ታሪካዊ ዕድል የሚፈጥር፤ ዜጎች በዓለም አቀፍ መድረኮች አንገታቸውን ቀና አድርገው መሄድ እንዲችሉ የሚያስችልም ነው። በሀገር ገጽታ ግንባታም አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ነው።
በመድረኩ የሚገኝ ውጤት በብዙ ድካም እና ልፋት፤ በብዙ የሀገር ፍቅር እና ከዚህ በሚመነጭ የይቻላል መንፈስ የሚገኝ ነው፤ ሰፊ የዝግጅት ምዕራፍ የሚፈልግ፤ የስፖርተኛውን ብቻ ሳይሆን የስፖርት ባለሙያውን፤ የስፖርት አመራሩን፣ የመንግስት እና የመላውን ሕዝብ ርብርብ የሚጠይቅ ነው።
በተለይም የስፖርተኛውን ብቃት፣ የአሸናፊነት ስነ ልቦና ለመገንባትም ሆነ ውጤታማነትን ተጨባጭ ለማድረግ የስፖርት አመራሩ ድርሻ ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል። ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ አመራሩ ስፖርቱ ለሚገዛበት ሕግ እና ስርዓት ታማኝ መሆንና ለዚያ የሚሆን ስብእና ማጎልበት ይጠበቅበታል።
የኦሊምፒክ የስፖርት መድረክ ለኛ ለኢትዮጵውያን ከስፖርት ያለፈ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፤ ከቀደሙት ጊዜያት ጀምሮ የብሔራዊ ክብራችን አንዱ መገለጫ ነው። ዛሬ ዜጎች መድረኩን እንደ አንድ የብሄራዊ ክብር መገለጫ አድርገው ይጠብቁታል። በመድረኩ ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ ሲውለበለብ እና ብሔራዊ መዝሙራችን ሲሰማ ማየትና መስማትን ይናፍቃሉ።
አበበ በቂላ በሮም በባዶ እግሩ፣ በቶኪዮም ጫማ አጥልቆ፤ ማሞ ወልዴ በሜክሲኮ፣ ምሩፅ ይፍጠር በሞስኮ፣ ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ በባርሴሎናና ሲድኒ፣ ሻላቃ ኃይሌ ገብረስላሴና ፋጡማ ሮባ በአትላንታ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ሚሊዮን ወልዴ በአቴንስ፣ ጥሩነሽ ዲባባና መሰረት ደፋር በቤጂንግና ለንደን፣ አልማዝ አያና በሪዮ፣ ሰለሞን ባረጋ በቶኪዮ ያስመዘገቡዋቸው ድሎች ፤ ከስፖርት ውድድር ድል በላይ ከሀገር አልፈው ለጥቁር ሕዝቦች የመንፈስ ልዕልና ያጎናጸፉ፤ ወደ ፊትም ለሚመጡ ትውልዶች የተመሳሳይ የመንፈስ ልዕልና ምንጭ የሚሆኑ ናቸው።
ከፊታችን ያለውን የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ውድድርን ስናስብም፤ ይህንን እውነታ ታሳቢ ባደረገ፤ በዚህ ደረጃ የሚመዘን ዝግጁነት እየፈጠርን መሆን አለበት። ከዚህ ውጪ የሆነ ዝግጁነት፤ ሊመጣ የሚችለውም ውጤቱ የቱንም ያህል ከፍ ያለ ቢሆን፤ በራሱ ምሉዕ ሆኖ በመድረኩ ያለንን የተወዳዳሪነት እና የአሸናፊነት ታሪክ ሊያስቀጥል አይችልም ።
አሁን ላይ ያለው ሀገራዊ የኦሊምፒክ ዝግጅታችን፤ በአንድም ይሁን በሌላ ችግሮች ሊኖሩበት፤ ለችግሮቹ እንደ ምክንያት ሊጠቀሱ የሚችሉ የሕግ፣ አሰራር፣ የአመለካከት ..ወዘተ ክፍተቶች ሊኖሩም ይችላል። ከቀረን ጊዜ አንጻር ያለን አማራጭ በችግሮቹ እና በምንጮቻቸው ዙሪያ መነታረክ ሊሆን አይገባም።
ከዚህ ይልቅ ባለችው ጊዜ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ካሉ በሰከነ መንፈስ፣ አሸናፊነትን እና አሸናፊነቱ በስፖርቱ መድረክ ሊያጎናጽፈን የሚችለውን ብሔራዊ ክብር ታሳቢ ባደረገ መንገድ ማረም እና ማስተካከል ላይ ቅድሚያ ሰጥተን ልንቀሳቀስ ይገባል።
አሁን አደባባይ የሞላው ጭቅጭቅ እና ንትርክ ከሁሉም በላይ እንደ ሀገር ሊጎዳን የሚችለው እኛን ነው። በጭቅጭቅ እና በንትርክ የምንፈታው ችግር የለም፤ ከዚያ ይልቅ መረጋጋት መስከን ያስፈልገናል “ከመጀመሪያው ስህተት የሁለተኛው “እንደሚባለው ስህተት ለማረም በሚል የበለጠ ስህተት እንዳንሰራ መጠንቀቅ ይጠበቅብናል።
ሌላውን ሁሉ ለሌላ ጊዜ አስቀምጠን አሁን ከሁሉም በላይ አትሌቶቻችንን የአሸናፊነት መንፈስ በሚያጎለብት፤ የይቻላል መንፈስን በውስጣቸው ሊያሰርጽ እና ሊያጸና በሚችል መንገድ ላይ ቆመን ልንደግፋቸው፤ ልናበረታታቸው እና ተጨማሪ የጉልበት ምንጭ ልንሆናቸው ይገባል። ድል ለኢትዮጵያ !
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም