ከኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሠረታዊ ዓላማዎች አንዱ የሆነው በሕግ የበላይነት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ የመገንባት ዓላማ ከግብ የሚደርሰው የግለሰብ፣ የብሔር እና የሕዝብ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች መከበራቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን እንዲሁም ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገቱ እውን መሆን ባካሄደው ረጅም ትግል በከፈለው መስዋዕትነት፣ ሰብአዊ መብቶች ለማናቸውም ዓይነት የተፅዕኖ መዳፍ መጋለጥ የለባቸውም፡፡
የሰብአዊ መብቶቹ በእውን የሚከበሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት በማስፈለጉ፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት የሕዝቦች መብቶችና ነፃነቶች የተከበሩ መሆናቸው በመረጋገጡና በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት አካላትና ባለሥልጣኖቻቸው እነዚህን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታም እንዳለባቸው በመደንገጉ፤ አነዚህን መብቶቹንና ነፃነቶች በማስከበሩ ረገድ የላቀ ድርሻ ይኖራቸዋል ከሚባሉት አካላት አንዱ የሆነውን የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ተቋቁሟል፡፡ ሥልጣኑንና ተግባሩንም ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር በሚስማማ መልክ በሕግ ተወስኖለት ወደ ስራ ከገባም አመታት ተቆጥረዋል።
ኮሚሽኑ በዚህ ደረጃ ላቅ ያለ ስልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶት ይቋቋም እንጂ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በማረጋገጡ በኩል ግን ብዙ ርቀት ተጉዟል ለማለት አያስደፍርም። የሚፈለገውን ያህል በኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎች ሰብአዊ መብትን ማስከበርም ሳይቻል ቆይቷል።
ለዚህ ማሳያው ደግሞ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተገፍፎ አንዳንዶቹ ባላጠፉት ገሚሶቹ ደግሞ ከጥፋታቸው በላይ በእስር ቤቶችና ማጎሪያዎች እድሜያቸውን ያላአግባብ ሲያባክኑ መኖራቸውን መጥቀሱ በራሱ በቂ ነው። ይህንን ሁኔታም ለመቀየር በተለይም ባለፉት ዘጠኝ ወራት አመርቂ የሚባሉ ጥረቶች ተደርገዋል።
በእነዚህ ጥረቶችም በተለያዩ እስር ቤቶች ሲማቅቁ እንዲሁም በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸምባቸው፣ ያለአግባብ በስደት ህይወታቸውን እንዲገፉ ሲገደዱ የነበሩ ዜጎች በሙሉ ማለት ይቻላል ነጻነታቸውን አግኝተው በሰላም ህይወታቸውን ለመኖር እንዲችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። ይህም ቢሆን ግን አሁንም በአገሪቱ ላይ ሰብዓዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተከብረዋል ብሎ ለመናገር ገና የሚቀሩ በርካታ የቤት ስራዎች እንዳሉም መዘንጋት የለበትም ።
ይህንን መልካም ጅምር ካደነቁ አካላት መካከልም ደግሞ ባለፈው ሰኔ ወር 2010 ዓ.ም በጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የምክር ቤት ኮሚሽነር ዜድ ራድ አል-ሁሴኒ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች እያካሔደች ያለችው ለውጥ ውጤታማ ነው ፡፡
የድርጅቱ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ኮሚሽነር ዜድ ራድ አል-ሁሴኒ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ ያለፈውን ታሪኳን ለመቀየር እያካሔደች ያለችውን ለውጥ አድንቀው፣ የህግ የበላይነት ከማስፈን፣ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች መርሆዎችን ከማስከበር፣ ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ፣ የመሰብሰብ መብት እና የሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ በማሳደግ በኩል አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በእርግጥ ኮሚሽነር ዜድ ራድ አል-ሁሴኒ እንዳሉት በኢትዮጵያ የቀድሞውን ያህል አስከፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ከዚህ በኋለ የሚጠበቅ አይሆንም ለዚህ መፍትሔው ደግሞ መንግስት በራሱ ከሚወስደውና የዜጎችን መብት ለማረጋገጥ ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን ህዝቡም ሆነ የፍትህ አካላት የተቀናጀ ስራን መስራት እንዳለባቸው ደግሞ ይታመናል።
ዘንድሮም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመሆን 70ኛ ዓመት የሰብዓዊ መብት ቀንን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ትናንት አክብሯል። በወቅቱም በተለይም ኢትዮጵያ ስሟ በሰብዓዊ መብት ረገጣ መጠራቱ እያበቃ የሚመስልበት ጊዜ ላይ መደረሱን በመግለጽ አሁንም የታዩ ጅምር ተግባራት በተለይም የህጻናትን፣ የሴቶችንና የአካል ጉዳተኛ ወገኖችን ሰብዓዊ መብቶች በማረጋገጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባቸውም ተገልጧል ።
በወቅቱ የኢትዩጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽር ዶክተር አዲሱ ገብረአግዚአብሔር እንዳሉት ከዛሬ 70 ዓመት በፊት ጀምሮ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወጣውን የሰብዓዊ መብት ቻርተር ፈርማለች። በወቅቱም ለሰብዓዊ መብት መከበር የሰጠችው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል ፡፡አሁንም የዜጎች ሰብአዊ መብት ሳይሸራረፍ ይከበር ዘንድ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ትገኛለች ።
አገሪቱ የምትተዳደርበት ህገ መንግስት አንድ ሶስተኛው የያዘው የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ነው ያሉት ኮሚሸነሩ ይህ ቢዘረዘር ምናልባትም በርካታ ትልልቅ መጽሀፍት ሊወጡት እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡መብቶቹን በህገ መንግስቱ ከማካተት ባሻገር ግን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች የዜጎች መብት መሆናቸው ታውቆ በእለት ተዕለት ኑሯችን እንዲተገበሩ ማድረግ ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡
በአገሪቱ የሚታዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመታገል ሁሉም ድርሻ እንዳለው መታወቅ አለበት ምክንያቱም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አሉ፤ ብዙ ተቋማትም ስላሉ ሰብአዊ መብትን የማክበርና የማስከበር ተልዕኮው ቀላል ባይሆንም በተቻለ መጠን ግን የእለት ተእለት አጀንዳችን በማድረግ መስራትም ውጤቱን እሩቅ እንዳይሆን ያደርገዋል ይላሉ።
እንደ ዶክተር አዲሱ ገለጻ፤ ባለፉት ጊዜያት በኢትዮጵያ ውስጥ ተከስተው የነበሩ የመብት ጥሰቶች መኖራቸው በኮሚሽኑም ምርመራም ተረጋግጧል፤ ወደፊት ግን እነዚህ ጥሰቶች መቀነስ የሚችሉት የእያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሲጎላ በመሆኑ በዚህ በ70 ዓመት ክብረ በዓል ላይም ጎልቶ መውጣት ያለበት ከዚህ በፊቱ ምን ተምረናል ወደፊትስ ለልጆቻችን ምንድነው የምናቆይላቸው የሚለው ሊሆን ይገባል።
«የዜጎች መብት የተከበረባት እንደ ሰው የተቆጠሩባት አገር የመፍጠር ተልዕኮ ቀላል አይደለም፤ ብዙ አባጣ ጎርባጣ ሁኔታዎችና ፈታኝ ነገሮች አሉት፤ እነዚህን የመፈተሽ ተፈጻሚነታቸውን የማረጋገጥ በፍትህ አካላት በኩል ያለውን አካሄድ ቆም ብሎ ማየት የሁሉም ተቋማት ድርሻ ስለሚያስፈልገው ወደፊትም ግንዛቤን ከመፍጠር ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት ይከወናሉ።›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ኮሚሽኑ በተለይም በአገሪቱ ሲፈጠሩ የነበሩ ኢ- ሰብአዊ ድርጊቶችን እንዲሁም የድብቅ እስር ቤቶችን ያውቅ ነበር ወይ? ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱም « ኮሚሽኑ የሚያውቀውን ያውቃል፤ ያወቀውንም አሳውቋል፤ ሆኖም ድብቅ እስር ቤቶች እንደነበሩ አያውቅም፤ ምናልባት ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሚሰራው ስራ የወንጀል ምርምራም በመሆኑና የተለያዩ ውስብስብ ኬላዎችን አልፈው ያገኙትን አሰምተውናል» ካሉ በኋላ ከእዚህ ግን ምን እንማር ወደፊትስ ምንድን ነው መደረግ ያለበት የሚለውን ኮሚሽኑ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ተቋም ጥንቃቄ የሚወሰድበትና የሚማርበት መሆኑን እንገነዘባለን በማለትም ይናገራሉ።
የጸጥታ አካላት ስራቸው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማረጋገጥና ተገፎም ሲገኝ ማስከበር ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በዚህ መሰረት ስራቸውን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ሊሰሩ ይገባቸዋል። ሆኖም አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የመንጋ ፍትህ እየታየ ነው ይህ ሁኔታ ደግሞ በዚሁ ከቀጠለ የመብት ጥሰት ላይ ነውና የሚያርፈው ይህ እንዳይሆን መንግስት በየቀኑ ክትትል እያደረገና የተለያዩ መግለጫዎችን እየሰጠም ይገኛል ሁኔታውን እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እጅግ የሚደነቅና የሚበረታታ አድርገን ነው የምናየው ብለዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ፈራማለች፤ በተለያዩ አለም አቀፍ ትብብሮች ላይም ትሰራለች። በመሆኑም እነዚህም መሰረታዊ ድንጋጌዎች በተለይም የሰላምንና የደህንነት ጉዳዮችን ትቀበላለች።
ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ውስጥ ስትታይ በታላቅ በቁርጠኝነት ነው ቀሪዎቹን ስራዎች ለመስራት የተዘጋጀችው ያሉት አቶ ታገሰ፣ ይህንንም ቁርጠኝነት በሙሉ ልብ ወደ ስራ በማስገባት ሁሉም ዜጎች ያላቸውን የተፈጥሮ መብትና ክብር ያለምንም መድሎ እንዲጠበቅላቸው እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
እንደ አቶ ታገሰ ገለጻ፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የአመራር ስርዓት ለመዘርጋት ይሰራል ፡፡በዚህም ህብረተሰቡን ማዕከል ባደረገ የምክር ቤት እንቅስቃሴ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች እንዲከበሩ ለማድረግና ተጥሰው ሲገኙም ተጠያቂነት ያለው አሰራር ለመዘርጋት ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጅት ተደርጓል ።
በሌላ በኩልም በአገሪቱ ተጓድሎ የነበረው ፍትህ እንዲሰፈን ለማድረግ ምክር ቤቱ እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ በቅንጅት ለመስራት እንዲሁም አሳታፊ ለማድረግና የህብረተሰቡን ህመም በማስታገስ በኩል መሰረታዊ የሆኑ ለውጦችንም ለማምጣት መታቀዱንም አፈ ጉባኤው አስረድተዋል።
‹‹በሺዎች የሚቆጠሩ አስረኞች መለቀቃቸውን ጠቅሰው፣አብዛኞቹም መታሰር ሳይገባቸው የታሰሩም መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ወደፊት እንዳይደገም በደሉን የፈጸሙ አጥፊዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ እንደ ህዝብ ተወካይነታችን ሰፊ ስራንም እንሰራለን ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 2/2011
እፀገነት አክሊሉ