መቻል ከዩጋንዳው ክለብ ኪታራ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል

መቻል ከዩጋንዳው ክለብ ኪታራ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል

መቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር የክለቡን የቀደመ ገናናነት በሚያስታውሱ እና ከአፍሪካ ምርጥ ክለቦች አንዱ ለመሆን የሚያስችሉትን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። በበርካታ ኩነቶች የምሥረታ በዓሉን እያከበረ የሚገኘው መቻል፣ በነገው እለትም አንጋፋና የቀድሞ የዓለም እግር ኳስ ኮከቦች የሚታደሙበትን የወዳጅነት ጨዋታን ከዩጋንዳው ክለብ ኪታራ ጋር ያካሂዳል።

መቻል ከሰኔ 1-2016 ዓ.ም ጀምሮ በክለቡ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሰይፉ ጌታሁን እና የመከላከያ ሚኒስቴር የሥነ-ልቦና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጀነራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን በሚመራው ኮሚቴ በተለያዩ የምሥረታ በዓሉን እንዲከበር እየሠራ ነው። ከነዚህም መካከል ሕዝባዊ የፓናል ውይይት፣ የሩጫ ውድድር እና የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ክለቡን ለማጠናክር እና ውጤታማ ለማድረግ ታስበው ተካሂደዋል። ሌላው የክብረ በዓሉ አካል የሆነውን እና ትላልቅ የእግር ኳስ ኮከቦች የሚታደሙበትን የወዳጅነት ጨዋታውን የወንዶች እግር ኳስ ቡድኑ በነገው እለት 10፡00 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስቴድየም እንደሚያደርግ ይፋ ተደርጓል።

በተጠናቀቀው የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ አስደናቂ አቋም አሳይቶ በሁለት ነጥብ ልዩነት ዋንጫውን ማንሳት ያልቻለው መቻል፣ የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን ለማድመቅ ከዩጋንዳው ክለብ ኪታራ ጋር የወዳጅነት ጨዋታውን እንደሚያደርግ አሳውቋል። የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አሸናፊው ክለብ ኪታራ የወዳጅነት ጨዋታውን ለማድረግ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ መድረሱም ታውቋል።

ሁለቱ ክለቦቹ ከሚያከናውኑት የወዳጅነት ጨዋታ በፊት አርቲስቶች እና የቀድሞ የመቻል ተጫዋቾች የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርጉ ሲሆን ይህም ለቀድሞ ተጫዋቾች ክብር ተብሎ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል። በባለሀብቶችና በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መካከል እንዲሁ የወዳጅነት ጨዋታ ሲደረግ መንግሥት ለስፖርት የሰጠውን ትኩረት ከግንዛቤ በማስገባት እና የሥራ ኃላፊዎቹ ለስፖርቱ ትኩረት እንዲሰጡና ባለሀብቶችም ያላቸውን አበርክቶ እንዲያጎለብቱ በማሰብ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

በጨዋታው ታዋቂና ትልልቅ ስፖርተኞችና የመንግሥት ከፍተኛ በለሥልጣናት የሚታደሙ ሲሆን የስፖርት ቤተሰቡ ጨዋታውን ስታድየም ገብቶ በነጻ መከታተል እንደሚችል አዘጋጅ ኮሚቴው ገልጿል። በዓሉን ለማድመቅና የሀገር ገጽታን ለመገንባት እንዲረዳ የቀድሞ የዓለም የእግር ኳስ ክዋክብት የሆኑት ሁለት ተጫዋቾች ጨዋታውን እንደሚታደሙ ተጠቅሷል። ፖርቹጋላዊው የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ ኮከብ ሉዊስ ካርሎስ አልሜይዳ (ናኒ) በጨዋታው ላይ እንደሚገኙ ቀደም ብሎ መገለፁ ይታወቃል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት አምባሳደር ተደርጎ የተሰየመው ናይጄርያዊው የቀድሞ ንዋንኮ ካኑም እንደሚታደም ይጠበቃል።

የመቻል እግር ክለብ የቴክኒክ ዳይሬክተር ኢንስትራክተር አብረሃም መብራቱ ክለቡ በዓሉን ሲያከብር በ80 ዓመታቱ በስፖርት ሲያገለግሉ የነበሩ በሕይወት ያሉትንም የሌሉትንም ስፖርተኞች እያወደሰና እያመሰገነ እንዲሁም ለቀጣይ ጠንካራ መሠረት በመጣል መሆኑን ገልጸዋል።

ዋናው የመቻል የሴቶችና ወንዶች እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች የእግር ኳስ ቡድኖች በተመሳሳይ በፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ከ17 ዓመት በታችም አራት ውስጥ ገብቶ ቀጣይ ጨዋታን እየተጠባበቀ ነው። በዚህም ዘንድሮ በእግር ኳሱ የታቀዱ እቅዶች የተሳኩ መሆኑን ቴክኒካል ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። ይህም የሆነው የቦርድ አመራሩ በሰጠው አቅጣጫ፣ በአሠልጣኝ ክፍሉ ላይ በተሠራው ጠንካራ መዋቅር እና የተጫዋቾችና አሠልጣኞች የጋራ ህብረት እንደሆነ ገልጸዋል። ክለቡ ለቀጣዮቹ ዓመታት ዘመናዊ እና በታዳጊዎች ላይ ሊከተል ለፈለገው አቅጣጫ ስፖርተኞቹ እና ክለቡ ካላቸው ልምድ እንዲያካፍሉ ታስቦ ነው። ከክለቡ የቦርድ አመራር፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር የበላይ ኃላፊዎች እና ስፖርቱ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር የውይይት መድረክም ይካሄዳል። በቀጣይም ከሰሜን እና ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ካሉ የሚሊተሪ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

መቻል ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር እንዲሁ የካፍ ዲ ላይሰንስ የአሠልጣኝነት ሥልጠናን የሚሰጥ ሲሆን በክለብ ደረጃ የመጀመርያው እንደሚሆን ተነግሯል። በዚህም ከዋናው የሁለቱ ቡድን ተጫዋቾች እና የሠራዊቱ አባላት ሆነው የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ሥልጠናን የወሰዱ ይሳተፋሉ። ሥልጠናውን የሚወሰዱት 60 ከ መቶ ከክለቡና 40 ከመቶ ከተለያዩ ክለቦች ተጋብዘው ይሆናል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያለባትን የግብ ጠባቂ ችግር ለመቅረፍ ባለሙያዎችን ከደቡብ አፍሪካና ዴንማርክ ጋብዞ ሥልጠና ለመስጠት ታቅዷል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You