ከትብብር ይልቅ ውድድርና ፉክክር ላይ በተመሰረተችው ዓለም፤ ሀገራት ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ሲፈጽሙ ይስተዋላል። በተለይ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሚዛንን በራስ ፍላጎት ቃኝቶ ለማስጓዝ ባላቸው ከፍ ያለ መሻት፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በኪነ ጥበብና ፈጠራ፣ በታሪክና ባህል፣… የመሳሰሉ ጉዳዮችን ማዕከል አድርገው አንዱ በአንዱ ላይ የራሱን ማንነት ለማኖር ሲታትር ይታያል።
ከዚህ ሁሉ የበዛ ውድድር ባሻገር ግን፤ ሀገራት በባለ ብዙም ሆነ በሁለትዮሽ ግንኙነት ውስጥ የራስን ጥቅም ማዕከል ያደረገ የጋራ ተጠቃሚነትን መርኅ ሲያራምዱ ይታያል። የዚህ መርህ ማስኬጃ መሣሪያው ደግሞ ዲፕሎማሲ ነው። ዲፕሎማሲው ደግሞ በዲፕሎማቶች አማካኝነት ሲከወን፤ የዲፕሎማቶቹ ቀዳሚ ባለድርሻዎች ደግሞ አምባሳደሮች ናቸው።
ለዚህም ነው ሀገራት በዓለም መርኅ መሰረት በመካከላቸው ለሚኖር ማናቸውም ግንኙነት ዲፕሎማቶችን መድበውና አምባሳደሮችን ሾመው ሥራን የሚከውኑት። ይሄ የዲፕሎማሲ ሥራ ደግሞ እንደየሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ በኤምባሲ አልያም በቆንጽላ ጽሕፈት ቤት አማካኝነት የሚከወን ሲሆን፤ በየኤምባሲዎቹ የሚመደቡ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶችም የየተመደቡበትን ሀገርና ሕዝብ ጥቅም ማዕከል አድርገው እንዲሰሩ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያም ባልተቆራረጠውና እድሜ ጠገብ በሆነው የሥርዓተ መንግስት ጉዞዋ፤ ከአንድ ከግማሽ ክፍለ ዘመን የተሻገረ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ስታከናውን ቆይታለች። በዚህም በርከት ያሉ የሁለትዮሽ ግንኙነቶቿን የሚወስኑ፤ የባለ ብዙ መድረክ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ሚናዋን የሚያጎለብቱ ተግባራትት በእነዚሁ ዲፕሎማቶቿ አማካኝነት አስጠብቃ ዘልቃለች።
ይሄ የኢትዮጵያ የሁለትዮሽም ሆነ የባለ ብዙ መድረክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታዲያ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረ የተጓዘ ቢሆንም፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረው አካሄድ ግን ወርቃማ የዲፕሎማሲ ዘመን ተብለው ከሚመደቡት ተርታ የሚቀመጥ ነው። ምክንያቱም በእነዚህ ዓመታት ኢትዮጵያ የበዙ ፈተናዎችን የተጋፈጠችባቸው፤ እጅጉን የሚያኮሩ ስኬቶችና ውጤቶችንም ያስመዘገበችባቸው ናቸው።
ታዲያ እነዚህ የሀገር ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ በተፈተነችና ዓለምአቀፍ ጫናዎች በበረቱባት ወቅት ከችግሮቿ መሻገሪያ መፍትሄን በማፈላለግም ሆነ ዓለምአቀፍ ጫናዎች እንዲረግቡ በማድረግ በኩል እነዚህ ዲፕሎማቶቿ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ከውነዋል። ሥራዎቻቸውም ፍሬ አፍርተው ኢትዮጵያ ከፈተናዎቿ ልቃ እንድትወጣ፤ ነጻነትና ሉዓላዊነቷም ተከብሮ እንዲዘልቅ አቅም ሆነዋል።
ከዚህም ባሻገር በሚገለጸው የስኬትና የውጤት መንገዷም ውስጥ ቢሆን፤ እነዚህ ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ የችግርና ግጭት ሀገር ሳትሆን፤ እየተፈተነችና ጫና እየተደረገባትም ቢሆን ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን እያስመዘገበች ያለች ሀገር መሆኗን በዓለም አደባባይ በመግለጥ ገጿን አድምቀዋል። በዚህም ከየአቅጣጫው እንዲጫንባት የሚፈለገውን ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ በማለዘብ ሂደት ውስጥ ከፍ ያለ ሚናቸውን ተወጥተዋል።
ይሁን እንጂ አምባሳደርነት ወይም ዲፕሎማትነት የአንድ ወቅት ስራ አይደለም። በተወሰኑ ግለሰቦች ላይም ተንጠልጥሎ የሚዘልቅ ሁነት አይደለም። ይልቁንም በየጊዜው አቅም መፍጠርን፤ አዳዲስ አቅሞችን ማካተትን፤ የዜጎችን ተሳትፎና ድጋፍ ማሳደግን፤… በጥቅሉ ከፍ ያለ አቅም፣ ክህሎትና የዲፕሎማትነት ልዕልናን የተጎናጸፈ አውድና አካሄድን መላበስን ይጠይቃል።
ከዚህ አኳያ ከሰሞኑ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በዓለም መድረክ ከፍ አድርገው የሚገልጡ፤ የሀገርና ሕዝቦቻቸውን ጥቅም አስቀድመው የሚሰሩ አዳዲስ አምባሳደሮችን ከቀድሞዎቹ ጋር የሚያቀናጅ ተግባር ተከናውኗል። በዚህም አዳዲስ አምባሳደሮች ተሹመው፣ በተለያየ ጉዳዮች ላይ አቅም መፍጠር የሚያስችላቸው ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል።
ይሄ ስልጠና ደግሞ አዳዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች፣ በሚሰማሩባቸው ቦታዎችና መስኮች ሁሉ ምን እንዴትና መቼ መሥራት እንዳለባቸው በልኩ ግንዛቤ እንዲይዙ የሚያስችል ነው። በተለይ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በብዙ ፈተና ውስጥ እንዳለች እና በፈተና ውስጥም ከፍ ያለ ድልና ስኬት እያስመዘገበች እንዳለች ሀገር፤ ይሄንን በልኩ ተገንዝቦ የሚያስገነዝብ ዲፕሎማት ትሻለች።
በመሆኑም እነዚህ ዲፕሎማቶች ከምንም በላይ የሀገራቸውን እውነት አውቀው በማሳወቅ፤ ለሀገራቸው ልዕልና፣ ለሕዝባቸው ክብር፣ በጥቅሉም ሀገር እና ሕዝብ ለሚፈልገው ሁለንተናዊ ብልጽግና እና ልዕልና መሳካት የማይተካ ሚናቸውን መወጣት ይገባቸዋል። አምባሳደሮችም ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ ሀገራት ሲሾሙ የመጀመሪያ ተግባራቸው ይሄው መሆኑን ተገንዝበው ሊሰሩ፤ አምባሳደርነታቸው የሚገለጸውም ስለ ሀገራቸውና ሕዝባቸው ጥቅም በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ውስጥ መሆኑን አውቀው ሊሰሩ ይገባል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ፣ “አምባሳደሮች ከፍ ያለ የሀገር ፍቅር ብሎም፣ ሀገርንና ሕዝብን የማገልገል ስሜት ሊኖራቸው ይገባል፤ የሀገርንና የሕዝብን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር መትጋት ይጠበቅባቸዋል፤ ምክንያቱም አምባሳደር ሆኖ መመረጥ ሀገራዊ ኃላፊነትንና የሕዝብ አደራን በትጋት ለመወጣት የሚሰጥ ትልቅ ኃላፊነት ነው። በዲፕሎማት ሥራ ዋናው ቁም ነገርም የሕዝብና የሀገር አገልጋይነትን ከፍ ማድረግ ነው። ” ሲሉ፣ በሥልጠና መርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ የተናገሩትም ለዚሁ ነው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም