ጭፍን ፍረጃ፣ ጥላቻንና አግላይነትን ማስወገድ!

የማኅበራዊ ስነ-ልቦና ሳይንስ አንድ ሰው በሌሎች ኑሮ ምክንያት የሚደርስበትን ተፅእኖ ወይም የእርሱ ኑሮ በሌሎች ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ ያጠናል:: ይህም በማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ በሚፈጠር ግንኙነት የተነሳ አንዱ ሌላው ላይ ወይም ሌላው አንዱ ላይ የሚያደርሱትን ተፅእኖ ያጠቃልላል:: በዚህ ተፅእኖ ምክንያትም ሌሎች ሰዎችን የምናይበት መንገድ የተለያየ ይሆናል:: ማኅበራዊ እይታ ደግሞ በሌሎች ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ ያለን አመለካከት ሲሆን ከዚህ በመነሳት ሌሎች ሰዎች እንዲህ ናቸው፤ እንዲያ ናቸው እያልን እንመድባቸዋለን ወይም እንፈርጃቸዋለን::

አንዳንድ ግዜ ምደባችን ወይም ፍረጃችን በተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተመሰረተና በምክንያት ያልተደገፈ፣ በደፈናው ፊት ለፊት ካገኘነው ነገር በመነሳት የሚሰጥ ሊሆን ይችላል:: ጭፍን ፍረጃ ወይም /stereotype/ ስለ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን በተወሰነ አካላዊ አቀማመጥ ወይም ሌላ እውነታ ላይ የተመሰረተ አመለካከት ነው የሚባለውም ለዚህ ነው:: ለምሳሌ የቆዳ ቀለምን፣ የቋንቋ አጠቃቀምን ወይም የሚያሳየውን ባህሪይ በማየት ስለ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን የሚኖር አመለካከት ጭፍን ፍረጃ ነው::

ጭፍን ፍረጃን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል:: የመጀመሪያው ግለሰብ ተኮር ፍረጃ ሲሆን ይህ የፍረጃ አይነት በግለሰብ ላይ ያነጣጠረ ነው:: ለምሳሌ የሰዎች መጠሪያ ስም ላይ ተንተርሶ የሚኖር አመለካከት ግለሰብ ተኮር ፍረጃ ሊባል ይችላል:: በ1973 እ.ኤ.አ በሀራንና ማክዴቪድ የፅሁፍና የማርክ አሰጣጥ ላይ በተሰራ ጥናት በጣም ሳቢ ስም ያላቸው ተማሪዎች ሳቢ ስም ከሌላቸው ተማሪዎች የተሻለ ማርክ ተሰጥቷቸዋል:: በሌላ በኩል ግለሰባዊ ፍረጃ አካላዊ አቋምን በማየት የሚደረግ ነው:: በዚህም እ.ኤ.አ በ1967 በተሰራ አንድ ጥናት ቆንጆ መልክና ቁመና ያላቸው ሰዎች ከሌላቸው ሰዎች ይልቅ ደስተኞች፣ ጥሩዎችና ጎበዝ ተወዳዳሪዎች ናቸው የሚል የተሳሳተ ፍረጃ ተሰጥቷቸው ነበር::

ሁለተኛው ፍረጃ የቡድን ተኮር ፍረጃ ሲሆን እንዲህ አይነቱ ፍረጃ የሚመነጨው አንድ ግለሰብ የሆነ ቡድን አባል በመሆኑ ምክንያት የተነሳ የሚኖር የተዛባ አመለካከት ነው:: ይህም በአብዛኛው ከጭፍን ጥላቻ ጋር የመመሳሰል ሁኔታ አለው:: ካዝና ብራል የተባሉ ተመራማሪዎች እ.ኤ.አ በ1933 በብሄርተኝነት ላይ ጥናት ለማድረግ መላ ዘይደው ነበር:: በዚህም ለጥናቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ የብሔር ቡድኖችን ለአብነትም አሜሪካውያንና አይሁዶችን እንዲሁም 84 የስብእና መገለጫ ቃላቶችን አቅርበውላቸው ነበር:: ከዚህ በኋላ የጥናቱ ተሳታፊዎች አምስት ወይም ስድስት የስብእና መገለጫ ቃላቶችን ለየብሄሮቹ እንዲሰጡና እንዲገልፁ ተነገራቸው::

ይህ ጥናት በወቅቱ ያሳየው እነዚህ ተሳታፊዎች በተወሰኑ ብሄሮች ላይ ጭፍን የሆነ ፍረጃ ወይም ጥላቻ እንዳለባቸው ነበር:: ይኸው ጥናት እ.ኤ.አ በ1951 እና በ1967 ሲደገም ፍረጃውና ጥላቻው በፊት ከነበረው ቀንሶ ታይቷል::

ጭፍን ጥላቻ ወይም /prejudice/ የጭፍን ፍረጃ ወይም /stereotype/ ፅንፍ ወይም ጥግ ነው:: ከላይ በተቀመጡት የአመለካከት ክፍሎች መሰረት ጭፍን ፍረጃ አስተሳሰባዊ፣ ጭፍን ጥላቻ ስሜታዊ፣ እንዲሁም አግላይነት ባህሪያዊ ይሆናል:: የጭፍን ጥላቻ ስሜት የሚያድግና የሚጎለብት ነው:: እንደ እውቁ የማኅበረሰብ ስነ-ልቦና ባለሞያ ጎርደን ኦልፖርት ይህ የጭፍን ጥላቻ እድገት በአምስት ደረጃዎች ይከፈላል::

አንደኛው አጉል ቀልድ ወይም የጥላቻ ንግግር ነው:: አጉል ቀልድ ወይም የጥላቻ ንግግር ስለ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን በፌዝ፣ በቀልድ፣ በስላቅ፣ በሃሜት ወይም በማሾፍ የሚደረግ አሉታዊ ንግግር ነው:: ለምሳሌ አጥንት የሚሰብር ንግግር ተናገረኝ እንደሚባለው አይነት ንግግርና በብሄር ወይም በአካል ጉዳት ላይ የተመሰረተ ቀልድን ጨምሮ ማለት ነው:: ይህ ሁኔታ እንደቀልድ ስለሚቆጠር በግለሰቡ ወይም በቡድኑ ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያመጣ ይቆጠራል:: ነገር ግን እንዲህ አይነቱ ንግግር የሰዎችን ስብእና ከመንካትም አልፎ በራስ መተማመንን የሚያወርድና ስለራስ የሚኖር ምስልን ዝቅ የሚያደርግ ነው::

ሁለተኛው መነጠል ወይም መለየት ነው:: ይህ የጭፍን ጥላቻ እድገት በአንድ ቡድን ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በሌላ ቡድን ከሚገኙ ጋር ይለያሉ ወይም ይነጠላሉ እንደማለት ነው:: በዚህ ግዜ አደጋው የበዛ ይሆናል:: ሌሎች ከቡድናቸው ውጪ ያሉ ቡድኖችን ወይም ሰዎችን የመፍራት ዝንባሌ ያሳያሉ:: ለምሳሌ መጤ ጠል ወይም /xenophobia/ ይከሰታል:: ይህም መገለልን ያስከትላል::

ሶስተኛው አግላይነት ነው:: አግላይነት አንድ ቡድን ሌላውን ቡድን እኩልነት በማሳጣት፣ ፍትህ በመንፈግና በመሳሰሉት መንገዶች ይገለፃል:: ይኸውም የተለያዩ አገልግሎቶችን በመንፈግ፣ በመከልከል እንዲሁም እኩል አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረግን ይጨምራል:: በዚህም የተገለለ ቡድን ስራ፣ ትምህርት፣ ሕክምናና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዳያገኙ ክልከላ ይደረግባቸዋል:: በዚህ የአግላይነት ዘውግ ስር የስልጣን ተዋረድን በመጠቀም የሚደረግ አግላይነት ሲሆን ይህም እውቀትን፣ እድሜን ወይም ፆታንና ባህሪን መሰረት በማድረግ የተወሰኑ ቡድኖች እንዲገለሉ የሚደረግበት ነው::

አራተኛው አካላዊ ጥቃት ሲሆን በአብዛኛው የጥላቻ ጥቃት በመባል ይታወቃል:: በዚህም የተወሰኑ የቡድን አባላትን ለይቶ ማጥቃት፣ ንብረታቸውን ማቃጠል ወይም ግለሰቦቹን በመንጋ ማጥቃትና ጅምላ ጭፍጨፋ ማድረግን ያጠቃልላል::

አምስተኛውና የመጨረሻው የጭፍን ጥላቻ እድገት አይነት ጭፍጨፋ ማካሄድ ሲሆን የዘር ማጥፋት፣ የብሄር ማፅዳትንና የመሳሰሉትን ያካትታል:: ጎርደን ኦልፖርት እንደሚገልፀው ጭፍን ጥላቻ በተሳሳተ መንገድ በተወሰኑ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች የሆነ ቡድን አባል በመሆናቸው ብቻ እነርሱ ላይ ያነጣጠረ ተለዋዋጭና ተጣጣፊ የሆነ ጥቅል መገለጫ ነው:: እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ግን ጭፍን ጥላቻ እንዴት ሊኖር ቻለ? የሚለው ነው::

ስለ ጭፍን ጥላቻ መኖርና አለመኖር ጥናት የማያስፈልገው ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በርካታ ጥናቶች ተሰርተዋል:: ለምሳሌ አሮንሰንና ኦሽሮው ጃን ኦልዌት የምትባል አስተማሪን አሳትፈው ተማሪዎቿን ቡናማ የአይን ቀለም ያላቸው ሰማያዊ የአይን ቀለም ካላቸው ልጆች የተሻለ ጎበዝ ናቸው ብላ እንድትነገርላቸው ካደረጉ በኋላ በውጤቱ ሰማያዊ የአይን ቀለም ያላቸው ልጆች ቡናማ የአይን ቀለም ካላቸው ልጆች ያነሰ ውጤት ማስመዝገብ ጀምረው ነበር:: ምክንያቱም ቡናማ የአይን ቀለም ያላቸው ልጆች ይህ ንግግር ከተነገራቸው በኋላ አግልለዋቸው ስለነበር ነው::

በአብዛኛው ጭፍን ጥላቻ እንዴት ለብዙ ግዜ በውስጣችን ይቆያል የሚል ጥያቄ ይነሳል:: በመሰረቱ ጭፍን ጥላቻ ሳይናወጥ ለብዙ ግዜ መቆየት የሚችል ነው:: ይህም ማለት አንድ ግዜ በውስጣችን ካለ እንደነበር ለብዙ ግዜ ይቆያል ማለት ነው:: ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች ስለ ጭፍን ፍረጃ የነበሩ እውነታዎችን ከሌሎቹ ይልቅ በተሻለ ያስታውሳሉ:: ጭፍን ፍረጃ ያልተለመዱ ወይም ወጣ ያሉ ሁኔታዎችን ስለሚያደርግ አንድ ግዜ በጣም ከፍ ካለ ለማውረድ ከባድ ይሆናል::

ሌላው ነገሮችን አውነት አድርጎ መቀበል ነው:: ሰዎች ብዙውን ግዜ ለተደረገባቸው ፍረጃና ጥላቻ በምላሹ እነርሱም ያደርጉታል:: ይህ ጥላቻን በጥላቻ የመመለስ ሂደት ጥላቻን ይበልጥ ያባብሰዋል እንጂ አይቀንሰውም:: የሆነው ሆኖ ጭፍን ጥላቻን በተመለከተ ምሁራን የተለያዩ አስተያየቶችን ይሰነዝራሉ:: ከነዚህም ውስጥ ሁለቱ ይጠቀሳሉ::

አንደኛው የምሁራን ወገን ጭፍን ጥላቻ በተፈጥሮ አብሮን የሚወለድ ነው ሲል ሌላኛው ወገን ደግሞ ጭፍን ጥላቻ ከማኅብረሰብ ግንባታ ጋር የሚመጣ እንጂ በተፈጥሮ የሚገኝ አይደለም ሲል ይሞግታል:: ይህ ክርክር ጭፍን ጥላቻን ማስወገድ እንችላለን ወይስ አንችልም የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ ለመመለስ መነሻ የሚሆን ነው:: በዚህም ላይ እንደተጠቀሰው ጭፍን ጥላቻ በተፈጥሮ የሚመጣ ነገር ከሆነ ማስወገድ ከባድ ነው የሚለውን ምላሽ ሲሰጥ በማኅበረሰብ ግንባታ ወቅት የሚመጣ ከሆነ ደግሞ የማኅበረሰቡን አተያይ በተለያየ መንገድ በመቀየር ማስወገድ ይቻላል ወደሚለው መደምደሚያ ይወስደናል::

ከላይ የተቀመጡትን ክርክሮች በመውሰድ ስነ ልቦናዊ አስተያየቶች እንዲህ ይላሉ፡- ቀደም ብሎ እንደተቀመጠው በተፈጥሮም ይሁን በማኅበረሰብ የመጣን ጭፍን ጥላቻ በቀላሉ ለማስወገድ በጣም አስቸጋሪና ከባድ ነው:: የሚያስቸግርበት አንዱ ምክንያት ጭፍን ጥላቻ አስተሳሰባዊና ስሜታዊ ክስተት በመሆኑ ነው:: እናም ጭፍን ጥላቻ ከዚህ የሚፈልቅ አመለካከት ነው:: አመለካከት ደግሞ በውስጡ በርካታ ነገሮችን ያቅፋል:: አመለካከት ካለን እውቀትና ልምድ የተነሳ ይመጣል:: ይህም የምናየውን ብቻ እንድንረዳ ያደርገናል:: ሌላው አመለካከት ሌሎች ከሚሰጡን ጥሩ ወይም መጥፎ አስተያየት ጋር ይገናኛል:: ይህም ማለት ሌሎች ሰዎች ያላቸው አመለካከት እኛ ካለን አመላካከት ጋር ከተመሳሰለና ያንን የምንጋራ ከሆነ ለነዛ ሰዎች ወይም ቡድኖች ያለን አመለካከት የተለየ እንዲሆን ያነሳሳናል::

በሌላ በኩል ደግሞ አመለካከት ስለራሳችን ያለንን ዋጋ ከፍ እንዲል የማድረግ ስራ ይሰራል:: ይህም የሆነ አይነት አመለካከትን ማዳበር ለራሳችን የሚኖረንን ዋጋ ከፍ እንዳርጋለን፤ በመጨረሻም አመለካከት ራሳችንን ካላስፈላጊ ትችት የመከላከል ሥራ ይሰራል:: በዚህም ጭፍን ጥላቻ ያለምንም በቂ ምክንያት በሌሎች የተገለሉ ቡድኖች ላይ የበላይነትን የማሳየት ዝንባሌ እንዲይዝ ያደርጋል::

እውቁ የስነ- ልቦና ምሁር ሲግመንድ ፍሮይድ እንደሚለው ሰዎች ጠበኝነታቸውንና ፍርሃታቸውን በትክክለኛው ምክንያት ላይ ንዴታቸውን ከመግለፅ ይልቅ በሌላ ነገር ላይ ያስወጡታል:: በሌላ በኩል በዚህ የፍርሃት ጠበኝነት አዙሪት ውስጥ መግባታቸው ሰዎች ፍርሃታቸውንና ጠበኝነታቸውን እንደምክንያትና ውጤት ይጠቀሙበታል:: ይህም ማለት ፍርሃት ለጠበኝነት መንስኤ፤ እንዲሁም ጠበኝነት እንደገና ፍርሃትን ይወልዳል::

ሌላው ጭፍን ጥላቻን ከውስጣችን እንዳይወገድ ከባድ ከሚያደርጉ ስነ -ልቦናዊ መላምቶች የታችፌልና ተርነር ማኅበረሰብ ማንነት መላ ምት ነው:: ይህ ማለት ሰዎች በተፈጥሮ ለራሳቸው መልካም ገፅታ ለመገንባት ይታገላሉ:: በዚህ ሂደት ውስጥ ማኅበራዊ ማንነት ሰዎችን ቡድን ውስጥና ከቡድን ውጪ በሚል በመከፋፈል ይገለፃል:: ይህ ማኅበራዊ ማንነትን የመገንባት ሂደት ጭፍን ጥላቻ እንዲፈጠር ያደርጋል::

ሰዎች ለራሳቸው መልካም ግምትን በመገንባት ሂደት ውስጥ ሁለት አይነት ገፅታዎች ይኖራሉ:: አንደኛው የግላዊ ማንነትን መገንባት ሲሆን ሌላኛው ማኅበራዊ ማንትን መገንባት ነው:: በሌላ በኩል አዶርኖ የተባለ ተመራማሪ በበኩሉ ጭፍን ጥላቻን ሊፈጥር የሚችል ማግነናዊ ስብእና አለ ብሎ ይከራከራል:: ይህ የስብእና አይነት ዝቅተኛ የማኅበረሰብ ክፍሎች ወይም ቡድኖችን የመናቅና ዝቅ አድርጎ የመመልከት እንዲሁም ከፍ ያሉ ማኅበረሰቦችን የማጉላትና ለእነሱ የማጎብደድ የስብእና አይነት ሲሆን ይህ አይነት ስብእና ያላቸው ሰዎች እጅግ ግትርና የማይተጣጠፉ ናቸው ይላል::

አዶርኖ እንደሚለው ይህ የስብእና አይነት ከአስተዳደግ ችግርና ከማኅበረሰብ ጫና የሚመጣ ነው:: ይህም ማለት በአስተዳደግ ወቅት ቤተሰቦቻቸው በጣም ወግ አጥባቂ፣ ሃይለኛና ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ልጆች በወላጆቻቸው ላይ እልህና ቁጭት ውስጥ ይገባሉ:: ነገር ግን በወቅቱ ስለማያወጡት ተደብቆ ይቆይና ኋላ ላይ በነዚህ ዝቅተኛ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ያወጡታል:: ዋናው ጥያቄ ጭፍን ጥላቻን ለመቀነስ ምን ይደረግ? የሚለው ነው::

ከዚህ በፊት ጭፍን ጥላቻን ፈፅሞ ለማስወገድ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ አይተናል:: ነገር ግን ማስወገድ እንችላለን ብለን ካሰብን የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል:: በዘርፉ ምርምር ያደረጉ ሰዎችም የሚከተሉትን እርምጃዎች በመውሰድ ጭፍን ጥላቻን ማስወገድ እንችላልን ይላሉ::

1ኛ. በቡድን በተደራጁና ባልተደራጁ ወይም በሌላ ቡድን ውስጥ ባሉ መካከል ምንም አይነት የተወዳዳሪነት መንፈስ እንዳይኖር በማድረግና እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ::

2ኛ. በሁለቱም የቡድን አባላት የሚሰራና መሳካት የሚችል የጋራ ዓላማ ማቀድና ለዛም በእኩልነት እንዲሰሩ ማድረግ::

ከላይ የተጠቀሱት መንገዶች ጭፍን ጥላቻን ማስወገድ የሚችሉ ቢሆንም በተለያዩ ሀገራት እስካሁን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባይቻልም በመቀነሱ ረገድ ግን መልካም ውጤት ተመዝግቧል:: በተለይ የጋራ ዓላማ ላይ መስራት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምሮበታል:: በዚህም ከተለያዩ የቡድን አባላት የመጡ ሰዎችን በመቀየጥና በጋራ ለሚመዘን ውጤት እንዲሰሩ በማድረግ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You