እንግሊዘኛ እውቀት ወይስ ክህሎት?

እንደ ጃፓን እና ቻይና ያሉ የበለፀጉ ሀገራት እንግሊዘኛ ቋንቋ መናገር ግዴታቸው አይደለም። እንግሊዘኛ ቋንቋ ላይ መራቀቅ የሥልጣኔ መገለጫቸው አይደለም። እንዲያውም ጃፓን ውስጥ ከቅርብ ዘመን ወዲህ ተጀመረ እንጂ እንግሊዘኛ አይነገርም ነበር። አሁንም ቢሆን መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጃፓን ውስጥ እንግሊዘኛ የሚሞካክሩ 13 በመቶ ብቻ ናቸው። እዚህ ላይ አንድ የፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴን ገጠመኝ ልጥቀስ።

ለታሪክ ጥናት ጃፓን በቆዩበት ጊዜ በጣም የተቸገሩት በቋንቋ ነበር። በሀገሪቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ የታሪክ ተመራማሪዎችና የዩኒቨርሲቲ ምሑራን እንግሊዘኛ አይችሉም። ይሄኔ ፕሮፌሰር ባሕሩ አንድ ጥያቄ ጠየቁ። ‹‹ለመሆኑ የዓለምን ታሪክ የምታስተምሩት በምንድነው?›› የሚል ነበር። የተሰጣቸው መልስ ‹‹ወደ ጃፓንኛ ያልተተረጎመ ታሪክ ለምን እናስተምራለን?›› የሚል ነበር። የዓለምን ታሪክ ለተማሪዎቻቸው የሚያስተምሩት ወደ ጃፓንኛ አስተርጉመው ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ጥቂት ምሑራንን ያሠለጥናሉ ማለት ነው።

ይህ ለምን ሆነ? ብለን ከጠየቅን የራሳቸውን ማንነትና ምንነት ስለገነቡ ነው። በአሜሪካና አውሮፓ ሀገራት ላይ ጥገኛ ለመሆን ስለማይገደዱ ነው። ከአውሮፓ ሀገራት የኮረጁት አነጋገርና አለባበስን ሳይሆን ራሱን ጥበብን ስለሆነ። የወሰዱት የተሠራውን ቁስ አካል ሳይሆን አሠራሩን ስለሆነ። ስለዚህ እንግሊዘኛ ለመናገር አይገደዱም።

ነገሩን ወደ አፍሪካ እናምጣው። ከኢትዮጵያና ላይቤሪያ በስተቀር የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ የተገዙ ናቸው። ሥር የሰደደ እና የዳበረ የራሳቸው ማንነትና ምንነት የላቸውም። ብዙዎች የሥራ ቋንቋቸው ሳይቀር ቅኝ በተገዙበት ሀገር ነው። እንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ ዋናዎቹ ናቸው። ስለዚህ ሀገራቱ የእነዚህ ቅኝ ገዥዎቻቸው ጥገኛ ናቸው። የአስተዳዳሪዎቻቸው ቋንቋ ነው። የዘመን አቆጣጠራቸውም ሆነ ሁሉ ነገራቸው በቅኝ ገዥዎቻቸው የተቃኘ ስለሆነ እንግሊዘኛ ማወቅ ግዴታ ሆኖባቸዋል ማለት ነው። በብዙ የአፍሪካ አገራት ከአገር መሪ እስከ አርሶ አደር እንግሊዘኛ ይናገራሉ።

አሁን ደግሞ እንግሊዘኛን ከአፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ እናምጣው። ኢትዮጵያ ልክ እንደ ኃያላኑ የአውሮፓ ሀገራት የራሷ ቋንቋና ፊደል፣ የዘመን አቆጣጠር ያላት ናት። እንግሊዘኛ ቋንቋ መስፋፋት የጀመረው በ17ኛው እና በ18ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ዓለም አቀፍ ሰነዶች ያሳያሉ። የአማርኛ ቋንቋ በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥታት ቋንቋ ሆኖ ያገለግል የነበረው ግን ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሊቃውንት የጻፏቸው ሰነዶች ያሳያሉ። በ12ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓውያኑም ቢሆን ከአማርኛ የተለየ የዳበረ ቋንቋ አልነበራቸውም።

አማርኛ የመንግሥታት ቋንቋ በመሆኑ በመላው ኢትዮጵያ የመስፋፋት ዕድል አገኘ። በዚያ ላይ ኢትዮጵያ የብዝኃ ማንነት ሀገር ስለሆነች ብዙ ብሔሮች የየራሳቸው የአፍ መፍቻ ቋንቋ አላቸው። በአጠቃላይ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ያለ ማኅበረሰብ ከእናቱ የሚሰማው ቋንቋ እንግሊዘኛ ሳይሆን የአካባቢውን አፍ መፍቻ ቋንቋ ነው። ወደ ከተሞች አካባቢ ደግሞ አማርኛ ነው። ለዘመናት የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ የሆነውንና የብዙ አካባቢዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ የሆነውን አማርኛን ምሳሌ አድርገን እንቀጥል።

አንድ በአማርኛ አፉን የፈታ ኢትዮጵያዊ በአካባቢው ሲያድግ በአማርኛ የትኛውንም አገልግሎት እያገኘ ነው። በአማርኛ ሙዚቃ እየሰማ፣ የአማርኛ ፊልሞችንና ድራማዎችን እያየ፣ የዳበሩ የአማርኛ ተረቶችን እየሰማ፣ አካባቢውን በአማርኛ እየተረዳ፣ የሀገሩንና የዓለምን ታሪክ በአማርኛ እየሰማ ያድጋል። ይህ ሰው እንግሊዘኛን የሚያገኘው በትምህርት ሂደት ነው። በትምህርት ሂደት የሚያገኘው እንግሊዘኛ ደግሞ አካዳሚያዊ የሆኑ ነገሮችን ለማወቅ ነው። ስለዚህ ይህ ሰው በእንግሊዘኛ ቅኔ የሚቀኝና በእንግሊዘኛ የሚራቀቅ አይሆንም ማለት ነው። ምክንያቱም ቅኔ የሚቀኝበትና የሚራቀቅበት የራሱ ቋንቋ አለው።

አንድ በኦሮምኛ ወይም በትግርኛ ወይም በአፋርኛ ወይም በሶማሊኛ አፉን የፈታ ሰው በራሱ ቋንቋ እምቅ ቅኔና ሥነ ቃል አለው። አካባቢውን የሚያውቀው በራሱ ባሕልና ቋንቋ ነው። ስለዚህ ይህ ሰው በምን አግባብ እንግሊዘኛ ላይ የሚራቀቅ ሊሆን ይችላል? ግዴታስ አለበት ወይ? በራስ ቋንቋ የሚታወቅ እውቀት እንደ ዕውቀት አይቆጠርም ወይ? የዓለምን ጓዳ ጎድጓዳ ታሪክና የተፈጥሮን ምሥጢር በአማርኛ ብናገረው እንደ እውቀት አይቆጠርልንም ወይ?

አንድ የማያከራክር እውነታ አለ። እንግሊዘኛ ማወቅ ብዙ ጥቅም አለው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ግዴታ የሚሆንበት አጋጣሚም አለ። ምክንያቱም ቋንቋው ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው። በቴክኖሎጂ የዳበረ ቋንቋ ነው። ብዙ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እና መተግበሪያዎች የአሠራር መመሪያ (Instruction) በእንግሊዘኛ ነው። ከዚህ የተነሳ ልማድ አድርገነዋል። ለምሳሌ የብር ማውጫ ማሽን (ኤ ቲ ኤም) ቋንቋ ሲያስመርጠኝ የምመርጠው እንግሊዘኛን ነው። የተለየ የእንግሊዘኛ ፍቅር ወይም ችሎታ ኖሮኝ ሳይሆን የእንግሊዘኛ ትዕዛዞችን ስለተላመድኳቸው ነው። የኢሜይል ግድግዳዬ ትዕዛዞች በአማርኛ ሲሆኑ ግራ ይገባኛል። ይህ ቴክኖሎጂው ያመጣው ተፅዕኖ ነው። ስለዚህ እንግሊዘኛን መላቀቅ አይቻልም ማለት ነው።

ዳሩ ግን ቋንቋውን ከቋንቋነት ባለፈ የእውቀት መለኪያ ማድረግ አላዋቂነት ነው። ቋንቋ በባሕሪው እውቀት ሳይሆን ክህሎት ነው። አፈጣጠሩም ሆነ ዕድገቱ ዘፈቀዳዊ ነው። የሚያገለግለውም ለመግባቢያ ነው፤ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ግን እንግሊዘኛን የእውቀት መለኪያ አድርጎ ማየት ነው። ወቀሳው ደግሞ በተቃራኒው መሆኑ ነው። ለምሳሌ፤ ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ የሚናገራቸው ቃላት በብዙኃኑ የሚታወቁ የተለመዱ ቃላት ሊሆኑ ይገባል። አሻሚ፣ ውስብስብ፣ ዘይቤ እና ፈሊጣዊ ቃላት የበዙበት ቃላትን መጠቀም ለጋዜጠኛና ፖለቲከኛ አይመከርም። በዚህም ምክንያት ፖለቲከኞች በእንግሊዘኛ ሲናገሩ ግልጽ እና የተለመዱ ቃላትን መሆን አለበት።

ብዙ ጊዜ ግን እንደ ብቁ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ የሚታየው በቃላት ላይ ቃላት እየደራረቡ በፍጥነት መንጣጣት እና በእንግሊዘኛው ‹‹Idiomatic›› የሚባለውን ከመዝገበ ቃላት ተፈልገው የሚገኙ ፈሊጣዊ ቃላትን መጠቀም ነው። ሲጀመር እንዲህ አይነት ቃላትን መጠቀም ለጋዜጠኛና ፖለቲከኛ አይመከርም። ‹‹ምን ማለት ይሆን?›› የማይባሉ ቃላትን ነው መጠቀም ያለባቸው። በቋንቋ ባለሙያዎች ‹‹ከባዱ ነገር ቀላል ማድረግ ነው›› ይባላል። ቀላል ማድረግ ማለት ለሁሉም የሚገባ ማድረግ ማለት ነው። በቃላት መራቀቅና መፈላሰፍ ለጋዜጠኛና ፖለቲከኛ ሳይሆን ለልቦለድ ደራሲና ለኪነ ጥበብ ሥራዎች ነው። ምክንያቱም የኪነ ጥበብ አንዱ ውበት የቃላት ጨዋታው ሊሆን ይችላል። ገለጻዊ ለሆኑ ነገሮች ግን የሚመከረው በተቻለ መጠን አሻሚ ቃላትን ማስወገድ ነው።

ሌላው ችግር ደግሞ የቃላት አጠራር (Pronun­ciation) ነው። የቃላት አጠራር (አነባበብ) ከአገር አገር ብቻ ሳይሆን ከግለሰብ ግለሰብ ይለያያል። ብዙ ጊዜ እንደ እንግሊዘኛ ችሎታ የሚታየው ምላስን ቆልፎ አፍ መፍቻቸው የሆኑትን እንግሊዝና አሜሪካን ለመምሰል መታገል ነው። በነባራዊ ሁኔታዎች ምክንያት እንግሊዘኛ መናገር ግዴታ ሊሆን ቢችልም የእንግሊዝ ተወላጅ ዜጎችን ለመምሰል መታገል ግን ግዴታ አይሆንም። ምክንያቱም ዓረቦችም፣ ሕንዶችም፣ ቻይናዎችም የሚታወቁበት የየራሳቸው የእንግሊዘኛ ዘዬ (አክሰንት) አላቸው።

በሌላ በኩል አፋቸውን በእንግሊዘኛ የፈቱ ሀገራት (እንግሊዝና አሜሪካ) ራሱ የአጠራር (አነባበብ) ልዩነት አላቸው። ስለዚህ ‹‹እገሌ ትክክለኛ እንግሊዘኛ ተናጋሪ ነው›› ሊባል ይችላል ወይ? እንዴት ሲሆን ነው ትክክለኛ እንግሊዘኛ ተናጋሪ የሚባለው? ማንን ሲመስል ነው?

በአጠቃላይ እንግሊዘኛ ክህሎት እንጂ እውቀት አይደለም። አንድ ጃፓናዊ ወይም ቻይናዊ እንግሊዘኛ የማይችል (ምናልባትም የማይፈልግ) ሆኖ በአስተርጓሚ ሲናገር እንደ ኩሩ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ እንግሊዘኛ ካልተናገረ ግን እንደ መሐይም የሚታየው በምን አግባብ ነው? ኢትዮጵያዊው በራሱ መኩራት አይችልም እንዴ?

ልብ ማለት ያለብን ነገር፤ ማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ያደገ ኢትዮጵያዊ በራሱ ቋንቋና ማንነት ያደገ መሆኑን ነው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You