አባት ወይስ ጠላት?

‹‹አባት›› የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ የአንድ ነገር ምንጭ ወይም ጀማሪ የሚል ትርጓሜን ይይዛል:: አባት ምንጭ ቢሆንም አባትነት እምነት እናትነት እውነት ይባላል:: ልጅ ሲወለድለት አባት መሆኑን አምኖ ተቀብሎ ለልጆቹ ጥላ ሆኖ ከመከራ ከልሎ ያሳርፋል:: ልጆቹ ማደጋቸውን በጉጉት እየተመለከተ ነጋቸውን በአይነ ሕሊናው ይቃኛል:: በእርጅናው ደግሞ በፀሎት የልጆቹን ቀና መንገድ ሲመኝ የሚኖር ታላቅ ሃብት ነው አባትነት።

ታዲያ ይህ አባትነት የግድ በስጋ ከመዋለድ ጋር ብቻ የተሳሰረ አይደለም:: ብዙዎች በስጋ ያልወለዷቸውን ልጆች እንደአብራካቸው ክፋይ አባት ሆነው አሳድገው ለቁም ነገር አድርሰዋል:: ጠባቂ መደገፊያ ማምለጫ በመሆን የአባትነት ግዴታን ተወጥተዋል:: በተቃራኒው ደግሞ እንደአባት ታምኖ በስጋ ወልዶም ሆነ ሳይወልድ አባትም ሆነ የእንጀራ አባት ሆኖ እንደአባት ግዴታውን የማይወጣም ሞልቷል:: የአባትነት ግዴታውን መወጣት ሲገባው በተቃራኒው ጠባቂ ሳይሆን እራሱ አራጅ ሆኖ ሲገኝ ምን ይባላል? ይህን የአባትነት ምስጥር ያፈረሰ ትስስሩን ባልተገባ መንገድ የበጠሰ አባት ሲገኝ አባት ወይስ ጠላት ያሰኛል:: ለዛሬ ተናጋሪ ዶሴ አምዳችን የ8 ዓመት የእንጀራ ልጁን አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ ታሪክ ልናካፍላችሁ ወደድን።

ይህን የወንጀል ታሪክ ህብረተሰቡን በሚያስተምር መልኩ ይቅረብ ዘንድ የፈቀዱልንን የአዲስ አበባ ፖሊስ መዝገብ ቤት ሰራተኞችን እያመሰገንን ታሪኩን በዚህ መልኩ አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።

እናትና ልጅ

ከተወለደችባት ቀዬ የወጣችው ገና በአፍላ የወጣትነት ዘመኗ ነበር። ያኔ ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ሠርታ ከድህነት ለማመለጥ አቅዳ ነበር። ከድህነት አመልጥበታለሁ ያለችበት ሥራ የልጅነት ልጇን እስኪ ያሳቅፋት ድረስ ያገኘቻትን ገንዘብ እየቆጠበች ሕይወቷ ለማሻሻል ቀን እየጠበቀች በአገኘችው አጋጣሚ ትታር ነበር።

በአንዲት ክፉ ቀን በሰራተኝነት የተቀጠረችበት ቤት የሚኖር የዘመድ ልጅ በክፉ አይኑ ተመለከታት። በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረው ወጣት የአስራ አምስት ዓመቷ የገጠር ጉብል ላይ አይኑን ከማሳረፍ አልፎ፤ አብሯት ሊተኛ ተመኛት:: ምኞቱ አብሮ ለመኖር እና የትዳር ጓደኛው ለማድረግ ሳይሆን ጊዘያዊ ስሜቱን ከማርካት ያለፈ አልነበረም:: ከእለታት በአንዱ ቀን ለዓመታዊ ክብረ በአል የቤቱ ሰው በሙሉ ተለቃቅሞ ለንግስ ጉዞ ሄደ። ያኔ እሷና የዘመድ ልጅ ተብዬው ብቻቸውን ቤት ቀሩ። ይህች የዋህ የገጠር ልጅ እንደለመደችው ስራዋን ሰርታ ለልጁ እራት አቅርባ ወደ መኝታዋ ሄደች። ከዛም መአድ ቤት ውስጥ ፍራሽ አንጥፋ ጋደም ከማለቷ እንቅልፍ ይዟት ጭልጥ አለ።

ድብን ያለ እንቅልፍ ውስጥ መግባቷን የተመለከተው ወጣትም ቀድሞ አይኑ ያረፈባትን ልጅ ተመኘ። ወጣቱ እንዳትነቃነቅ አድርጎ ካሰራት በኋላ ልጅቱ ከእንቅልፏ ነቃች:: እኩይ ተግባሩን ለመፈፀም አቅዶ የነበረው ወጣት ቀድሞ በተዘጋጀው መንገድ እጇን አስሮ አፏን በጨርቅ ጠቅጥቆ ግንኙነት ፈፀመባት።

ያላሰበችው ነገር የደረሰባት ወጣት ቤታቸውን አደራ ሰጥተዋት የሄዱት ሰዎች ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ ጨርቄን ማቄን ሳትል ማልዳ ተነስታ እንደ ወፍ በራ ጠፋች። ጠፍታ ሕክምና ወስዳ እራሷን አጠንክራ ወደ ሥራዋ ለመመለስ ስታስብ ነፍሰ ጡር መሆኗን ሰማች። ይህንን ስታውቅ ሰማይ ተደፋባት:: ሥራ ሠርታ ራሷን የመቀየር ዕቅዷ ተበላሸ:: ነፍሰ ጡር ሆና የሚቀጥራት ባለመኖሩ ዘመድ ጋር ተጠግታ ለመኖር ተገደደች:: ዘመድ ቤት እየሰራች እና እየበላች ልጅ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ:: በሰላም ሴት ልጅ ተገላገለች::

ልጅ ከወለደች በኋላ ሕይወት ቀላል አልሆነችም:: በብዙ መከራ ውስጥ አለፈች:: በመከራ ውስጥ ስታልፍ ለጇን ለማንም ሳትሰጥ ጉያዋ ውስጥ ሸሽጋ እና አዝላ በየሰው ቤቱ እየሰራች እስከ አምስት ዓመት እድሜዋ ድረስ ብቻዋን አሳደገቻት። ከዛ በኋላ ግን ኑሮ እየከበዳ መጣ:: የልጇም ፍላጎት አየጨመረ ሄደ:: በዚህ መሃል ልጅ ቢኖርሽም አገባሻለሁ፤ የሕይወትን ፈተና አብረን እንጋፈጥ ብሎ ደጋግሞ ለሚጠይቃት ሠው ምላሽ ሰጠች:: ጥያቄውን ተቀብላ አብራ ለመኖር መፍቀዷን አሳወቀች።

ትዳር ፈላጊው ሙዓዝ ከፈለኝ ባሳየችው ፈቃደኝነት ተደሰተ:: የሞቀ የደመቀ ትዳር መስርተው ኑሮን ማጣጣም ጀመሩ:: የትዳር አጋሯ ልጇን እንደ ልጁ እየተንከባከበ ማሳደጉ እጅግ አስደሰታት። አዲሱ ባልና ሕፃኗን አብረው ለተመለከታቸው በስጋ አባትና ልጅ እንጂ፤ የእንጀራ አባትና ልጅ አይመስሉም ነበር። ያበላታል፣ ያጠጣታል፣ ያለብሳታል፣ ወደ ትምህርት ቤት ያደርሳታል:: ብቻ ማንኛውም ወላጅ ለልጁ ሊያደርግ የሚገባውን እንክብካቤ በሙሉ ያደርግላታል::

ያልታሰበው ጥቃት

ባሏ ለልጇ መልካም አባት መሆኑ ያስደሰታት ሴት ሙሉ ትኩረቷን ወደ ስራ አድርጋ ለእድገታቸው ደፋ ቀና ማለቷን ቀጠለች። ባልም በትርፍ ጊዜው በሙሉ ልጅቷን መንከባከብ ስራው ነበር። እንደ አባት አስፈላጊውን ነገር በሙሉ እያሟላለት ያስተምራት ጀመር። ልጅቷ የቅድመ መደበኛ ትምህርቷን አጠናቃ አንደኛ ክፍል ገባች። በእንክብካቤ በመያዟ ቁመቷ አድጎ ቆንጆ ልጅ ሆነች።

አባዬ የምትለው አባትም የልጅቷ ቁመት ሲያድግ እድሜዋን ረስቶ ክፉ ሃሳብ በአይነ ሕሊናው ይመላለስ ጀመር። የሁለተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ልጅም በትምህርቷ ጎበዝ ቀልጣፋና ታዛዥ ነበረች። እናት የራስዋን ቁስል ዋጥ አድርጋ ልጇን ለማሳደግ አቅም የሰጣትን ባለቤቷን እጅግ ከማመኗ የተነሳ ልጇ ላይ እንኳን ጥቃት ቁንጥጫ ያሳርፍባታል ብላ አታስብም ነበር።

ነገር ግን ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚባለው እናቷ የቀመሰችውን ፅዋ ልጅቷም ባመነችው ሰው እንድትቀምስ ተፈረደባት። አባትየው ሙዓዝ ታህሳስ 1 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 6፡00 ስዓት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ካራ ጋቢሳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤት ውስጥ አባትና ልጅ አንደ ሁልጊዜው ተቀምጠው እየተጫወቱ ነበር።

ይህች የ8 ዓመት ዕድሜ ያላትንና በራሱ ቁጥጥር ስር የሚያሳድጋትን የእንጀራ ልጁን ከትምህርት ቤት ስትመጣ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተቀምጦ ያገኘችውን አባቷን ስማ አጠገቡ ተዝናንታ ተቀምጣ ነበር። የእናቷን አለመኖር የተመለከተው ሙአዝ ከፈለኝ የልጅቷን አፍ አፍኖ አስገድዶ ደፈራት። አባት ለድጋፍ ለእቅፍ እንጂ ለጉዳት ሳይታሰብ የልጅቷን ሕልም አጨለመው።

ድርጊቱ እንዳይታወቅበት ልጅቷን ቢላዋ ይዞ “ብትናገሪ እንችንም እናትሽንም እገላችኋለሁ“ በማለት ዝም እንድትል አስጠነቀቃት። ልጅቷ ከዛን ቀን አንስቶ ደስታዋ መጥፋቱን እናት ብታስተውልም የልጅ ነገር ነው በማለት ቸል ትላታለች። ሰውየው ግን የሰራው ጥፋት ሳይነቃበት በመቆየቱ ሕፃኗን እየደጋገመ ይደፍራት ጀመር።

ከእለታት አንዱ ቀን እናት ሥራ ውላ መጥታ እንደተለመደው ልጇን ውሃ ስጪኝ ስትላት፤ ልጅቷ አስገድዶ ደፋሪ የተጫወተባት በመሆኑ መንቀሳቀስና ከመቀመጫዋ መነሳት አለመቻሏን ትመለከታለች። እናቷም ስትጠይቃት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ አባቴ የምትለው ሰው ያደረገባትን ነገር በዝርዝር ትነግራታለች።

ሙዓዝ የተባለው የሴትየዋ ባለቤት በተደጋጋሚ እንደሚደፍራት እና ቢላዋ ይዞ “ብትናገሪ አንችንም እናትሽንም እገላችኋለሁ::” እያለ ያስፈራራት እንደነበር ለእናቷ ትናገራለች። ከሥራ ደክሟት የመጣችው እናት በራሷ የደረሰው ቁስል በልጇ መድረሱን ስትሰማ እንደ እብድ እያደረጋት ወደ ፖሊስ ጣቢያ በረረች።

ለፖሊሶቹ በልጇ ላይ የደረሰባትን ነገር በሙሉ በእንባ በማጀብ ታስረዳለች:: ፖሊሶቹን ወደ ቤት ይዛቸው ስትመጣ አድብቶ አራጁ አባት የሠራውን ሠርቶ አገር ሠላም ብሎ ቤት ቁጭ እንዳለ ተገኘ:: ፖሊስ ያለብዙ ውጣ ውረድ ግለሰቡን በቁጥጥር ሰር አዋለው። እናት ወንጀለኛው መያዙን አረጋግጣ፤ በማታ ልጇን ይዛ ወደ ሕክምና ቦታ ሄደች። በሆስፒታሉ በድንገተኛ ክፍል ተቀብለው ያስተናገዷት ሀኪሞችም ጉዳቱ የከፋ ባይሆንም የስነ ልቦና ጉዳቷ ከፍ ያለ መሆኑን ነግረው፤ ክትትል እንደታደርግ መክረው ወደ ቤት ላኩዋት። ባመነችው የተከዳችው እናት እንባዋን እያፈሰሰች ልጇን አቅፋ ፍትህ እስክታገኝ መጠባበቅ ቀጠለች።

የፖሊስ ምርመራ

የፖሊስ ምርመራ ቡድኑ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ወዲያው ምርመራውን ቀጠለ። የልጅቷን ቃል፤ የሕክምና ምርመራ ወረቀትን ይዞ የተጠርጣሪውን የእምነት ክህደት ቃሉን ለመቀበል ቁጭ አለ። ድርጊቱን የፈፀመው ሰው መጀመሪያ ጉዳዩን ማመን ባይፈልግም ምርመራው እየጠነከረ ማስረጃዎች እየወጡ ሲሄዱ፤ ጥፋቱን አምኖ መቀበል ግድ ሆነበት። አዎ በተደጋጋሚ ድርጊቱን ፈፅሜያለሁ ሲል አመነ::

ተጠርጣሪው ጥፋተኛ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ ቁጥር 627/1/ እና 627/4/ሀ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ለአካለ መጠን ያልደረሰችን ልጅ በተለያዩ ቀናት እና ጊዜ በተደጋጋሚ አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ የመርማሪ ፖሊስ ቡድኑ ለዐቃቤ ሕግ አቀረበ::

የአቃቤ ህግ ክስ ዝርዝር

የዐቃቤ ሕግም ከፖሊስ የምርመራ ቡድን የቀረበለትን ማስረጃ ከተመለከተ በኋላ አስፈላጊውን ስርዓት ይዞ አጥፊው ለፍርድ የሚቀርብብት አካሄድ ላይ መሥራት ጀመረ። አቃቤ ሕግ ያገኘውን ማስረጃ በመጠቀም በእዚህ መልኩ የክስ ዝርዝሩን አቅርቧል።

ሙዓዝ ክፍሌ የተባለው ተከሳሽ ታህሳስ 12 ቀን 2016 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 5፡00 ስዓት በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ካራ ጋቢሳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የ8 ዓመት ዕድሜ ያላትንና በራሱ ቁጥጥር ስር የሚያሳድጋትን የእንጀራ ልጁን ከትምህርት ቤት ስትመጣ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ አፏን አፍኖ አስገድዶ ደፍሯታል:: ድርጊቱን ከፈፀመ በኋላም እናቷ ከስራ መጥታ ውሃ ስጪኝ ስትላት መንቀሳቀስና ከመቀመጫዋ መነሳት ባለመቻሏ እናቷም ስትጠይቃት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ እንደሚደፍራት እና ቢላዋ ይዞ “ብትናገሪ እንችንም እናትሽንም እገላችኋለሁ“ እያለ ያስፈራራት የነበረ መሆኑን ተናግራ እናት ለፖሊስ ጥቆማ ሰጥታለች:: ጥቆማውን ተከትሎ በተካሔደው ምርመራ ተከሳሽ ሙዓዝ ድርጊቱን ይፈፅም እንደነበር እና የሕፃኗን ቃል፣ የተከሳሹን የእምነት ክህደት ቃል እና የሕክምና ማስረጃውን በማጠናቀር ዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝሩን አቅርቧል::

በክስ ዝርዝሩ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ ቁጥር 627/1/እና 627/4/ሀ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ለአካለ መጠን ያልደረሰችን ልጅ በተለያዩ ቀናት እና ጊዜ በተደጋጋሚ አስገድዶ በመድፈሩ ተከሶ ፍርድ ቤት መቅረቡ ተመላክቷል::

ውሳኔ

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ቢሰጠውም ተከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበበትን ክስና ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ሙዓዝ በተከሰሰበት ወንጀል የጥፋተኝነት ብይን አስተላልፎበታል:: በመሆኑም የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የካ ምድብ 7 ኛ ወንጀል ችሎት ተካሣሹን ያስተምራል፣ ያርማል ሌላውንም የማኅበረሰብ ክፍል ያስጠነቅቃል በማለት በ15 (አስራ አምስት) ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል::

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You