ግንዛቤና የባህሪ ለውጥ ለወባ መከላከል ስራ

በኢትዮጵያ የወባ በሽታ አዲስ ክስተት አይደለም:: ወባን የማያውቅ የማኅበረሰብ ክፍል የለም:: ይህም ሊሆን የቻለው የወባ በሽታ በአብዛኛው ቆላማ አካባቢዎች ላይ የሚከሰት በመሆኑ ነው:: አሁን ባለበት ሁኔታና የዓለም ጤና ድርጅት በሚሰጠው ሪፖርት መሰረት በሽታው ከብዙ ሀገራት ቢጠፋም አሁንም ቆላማ በሆኑ የአፍሪካና እስያ አካባቢዎች እንዲሁም የላቲን አሜሪካን ሀገሮች ስርጭቱ እንዳለ ይታወቃል::

ባለፈው ዓመት ከዓለም ጤና ድርጅት በወጣ ዓመታዊ ሪፖርት መሰረት 245 ሚሊዮን የሚሆን የዓለም ሕዝብ በወባ በሽታ ተይዟል:: ከ600 ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በዚህ በሽታ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል:: ኢትዮጵያም ከፍተኛ የወባ ስርጭት ከሚታይባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት:: ይሁንና የወባ በሽታ ባለፉት አስር ዓመታት ስርጭቱ በተከታታይ እየቀነሰ መጥቷል:: ስርጭቱን በመቀነስ ረገድ ጠንካራ ስራዎች በመሰራታቸው ተከታታይነት ያለው ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል::

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሕይወት ሰለሞን እንደሚናገሩት፣ የወባ ስርጭትን በመቀነስ ረገድ ሁለት አይነት መስፈርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ ይውላሉ:: አንዱ የታማሚ ቁጥር መቀነስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሞት ምጣኔን ማውረድ ነው:: ከዚህ አኳያ ለተከታታይ ዓመታት ስኬቶች ተመዝግበዋል:: በኢትዮጵያ በተለይ በ2009 ዓ.ም ከ1 ሚሊዮን በታች የወባ ኬዝ የተመዘገበበትና ትልቅ ስኬት የታየበት ሲሆን ከዚህ ዓመት በፊት ከነበሩ ሪፖርቶች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ለውጥ የመጣበት ነው::

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በወባ በሽታ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ነበር:: በወባ በሽታ የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ በተሰራ ስራ ግን ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ተችሏል:: ይሁንና ከቅርብ ግዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የወባ ወረርሽኝ እያንሰራራ መጥቷል:: በዘንድሮው በጀት ዓመት 4 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በወባ በሽታ ስለመያዛቸውም ሪፖርት ተደርጓል:: ይህም ለመንግስትም ሆነ ለማኅበረሰቡ አሳሳቢና የማንቂያ ደውል ሆኗል::

የወባ በሽታን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ለማጥፋት ስትራቴጂክ ሰነድ በጤና ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ስራዎች እየተሰሩ ነው:: ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግ ቁልፍ ነጥቦች ተዘጋጅተዋል:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ትክክለኛ የሆኑ መረጃዎችን መሰረት ያደረጉ ሲከናወኑ ቆይተዋል:: አሁንም ቢሆን ስራዎቹ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ ይገኛሉ:: ወባን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር ስልጠና መስጠትና መመርመሪያ መሳሪያዎችን ማቅረብ ብቻውን በቂ አይደለም:: መረጃዎችን በደምብ ማጠናቀር በጣም አስፈላጊ ነው:: ለዚህም ይህን የሚያግዙ ነገሮች ከግዜ ወደግዜ በአቅምም፣ በሀብትም እየተሟሉ የተሻለ ስራ እየተከናወነ ይገኛል::

መሪ ስራ አስፈፃሚዋ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ በየግዜው ወባን ለመከላከል የፕሮግራም ስልቶች ይወጣሉ:: ከነዚህ የፕሮግራም ስልቶች ውስጥ አንዱና ጥቅም ላይ የሚውለው የትንኝ ቁጥጥር ስራ ነው:: የወባ ትንኝ ቁጥጥር ስራ ሲሰራ በርካታ አማራጮች አሉ:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ለወባ ትንኝ ቁጥጥር ስራ ሚመከረው አንዱና ዋነኛው የአልጋ አጎበር መጠቀም ነው:: እንዲሁም ለርጭት ምቹ የሆነ ግድግዳ ካለ ኬሚካል መጠቀም ነው:: ትንኟ እጭ ሆና ወደጉልምስና የምትቀየር እንደመሆኗ እዚህ ላይም የሚሰሩ ስራዎች አሉ::

ለዚህም ወባን ለመከላከል የሚያግዙ ግብዓቶች ፍትሁነታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል:: ምክንያቱም ሁሉም ኬሚካል ሁልግዜ መፍትሄ ያመጣል ማለት አይደለም:: ስለዚህ በየዓመቱ የግባቶችን ውጤታማነት መፈተሽ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል:: ይህን ለማድረግ ደግሞ ጤና ሚኒስቴር ለወባ መከላከል የሚያግዙ ግብአቶችን እንደሚያቀርብ ሁሉ ጥናቶችን ለማድረግ በቂ የሆነ ሀብት ይመድባል:: የተለያዩ የምርምር ተቋማትም በተለይ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የአርማወር ሀንሰንና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ጥናቶች ይሰራሉ:: እነዚህን ወደ አንድ በማምጣት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው መረጃ ይታያል:: በሌላው ሀገር ላይ ያለው ችግር ነገ ወደ ኢትዮጵያ ምንም ምክንያት የለምና እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ድምበር ተሻጋሪ ጥናቶችም ይታያሉ:: ለምሳሌ በዚህ ሳምንት ከኢጋድ አባል ሀገራት ጋር የጋራ እቅድ ታቅዶ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ::

እንደወባ ያሉ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ቅንጅት እንጂ የተናጠል ስራ ውጤት ሊያመጣ አይችልም:: በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚሰሩና የሚሰበሰቡ ጥናቶችም ወደ ዋናው ሀገር አቀፍ የመከላከል፣የመቆጣጠርና ማጥፋት ላይ ያላቸው አንድምታ ላይ ትንታኔዎች ይሰራሉ:: ከዚህ በተጨማሪ ወባን ለማከምና ለመመርመር ጥቅም ላይ የሚውሉ ግብአቶች አሉ:: ለምርመራ ፈጣን የመመርመሪያ መሳሪያ/RDT/ ጥቅም ላይ ይውላል:: ይህን እ.ኤ.አ ከ2004 ጀምሮ ስራ ላይ መዋል ጀምሯል:: ይህ መሳሪያ በማኅበረሰብ ደረጃ በተለይ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች እንዲመረምሩና ወዲያው ደግሞ አስፈላጊውን መድሃኒት ይዘው እንዲያክሙ ያገዘ ነው:: በዚህ ስራም ብዙ ለውጥ መጥቷል::

ሕብረተሰቡ የወባ ምልክቶች ከታዩት በኋላ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ርቆ መሄድ የለበትም:: በማኅበረሰብ ደረጃ የወባ ሕክምና አገልግሎቱን በማግኘቱ በርካታ ሰዎች የወባ በሽታ የከፋ የጤና ጉዳት ሳያስከትልባቸው ታክመው እንዲድኑ አስችሏቸዋል:: ይህ ስራ አሁንም ቀጥሏል:: ወባን ለመመርመር የሚያስችለው መሳሪያም በየግዜው ይፈተሻል:: በዚሁ መሰረት አንዳንድ ማስተካከያ በሚያስፈልጉ ቦታዎች ላይ የተሰሩ ስራዎች አሉ:: ከዚህ ባለፈ ሌላኛው ወባን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውለው መድሃኒት ሲሆን በመድሃኒት ፍቱህነት ላይ በየሁለት ዓመቱ ፍተሻና ጥናት ይደረጋል:: ይህን ለማድረግ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ‹‹ሴንትናል ሳይቶች›› አሉ:: ከነዚህ በተጨማሪ ደግሞ እንደአስፈላጊነቱ ተጨማሪ ጣቢያዎችን በመምረጥ ጥናት ይደረጋል:: ይህም ሳይቆራረጥ እየተሰራ ያለና ጥሩ ግብአት እየሰጠ የሚገኝም ነው:: ጥቅም ላይ የሚውለውን መድሃኒት ብቻ ሳይሆን ነገ ደግሞ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ መጠባበቂያ መድሃኒቶችንም ማስቀመጥ ያስፈልጋል:: እደነዚህ አይነት ስራዎችም በጥናት ተደግፈው እየተከናወኑ ይገኛሉ::

ትልቁና ቁልፉ ነገር በባለፈው ዓመት የወባ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ተፈትሾ የመጠቀሚያ ግዜው ገና ሳይጠናቀቅ የመከለስ ስራ ተሰርቷል:: የኢትዮጵያ የወባ ቁጥጥር ስራ ምን እንደሚመስልና መታየት ያለበት ቦታ ካለ እንዲታይና እንዲሻሻል ተደርጓል:: በዚህ መሰረት አዲሱ በጀት ዓመት ሲጀመር ግብአቶች፣ ግዢዎች ይህን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲሆኑ ተደርጓል:: የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች አገልግሎትን ሊያቋርጡ ይችላሉ:: ይህ ችግር ደግሞ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ዓለምን የሚያሳስብ ነው::

ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው የወባ ሕክምናና ሌሎችንም የጤና አገልግሎቶችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በቅርበት መስራት እንደሚገባ በተለያዩ ጉባኤዎች ላይ በመሳተፍ ግንዛቤ ለመውሰድ ተችሏል:: የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የወባ መከላከል ስራ በጤና ሚኒስቴርና በሕክምና ተቋማት ብቻ የሚሰራ ስራ አይደለም:: የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና ርብርብ ይጠይቃል:: ከግለሰብ ጀምሮ በቤት ውስጥ የምናደርጋቸው ጥንቃቄዎች ለወባ መከላከል ስራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው:: የታቆረ ውሃን ማፍሰስ ብቻ ሳይሆን በባልዲ ውስጥ ሁለትና ሶስት ቀን የተተወ ውሃ ለወባ መፈልፈል ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ስለሚችል ከቤት ውስጥ ጀምሮ የጥንቃቄ ስራዎችን ማከናወን ይገባል::

ስለዚህ በማኅበረሰብና በግለሰብ ደረጃ የሚሰሩ ስራዎች ለወባ መከላከል ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው በመረዳት እዚህ ላይ አተኩሮ መስራት ያስፈልጋል:: ለምሳሌ የወባ ስርጭት ከፍ ባለባቸው አካባቢዎች የአልጋ አጎበሮች ለሌላ ስራ ሲውሉ ይታያል:: ከዚህ አንፃር በኅብረተሰቡ ዘንድ የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ ተከታታይነት ያለው ስራ መሰራት ያስፈልጋል:: ለዚህ ደግሞ የሚዲያ አካላት ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይገባል:: ለወባ መከላከል ስራ የሚውሉ የአልጋ አጎበሮች፣ ኬሚካሎችና መድሃኒቶች በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እንደመሆናቸው ኅብረተሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀምባቸው ሰፊና ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ስራዎችን መስራት የግድ ይላል::

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፣ ኢንስቲትዩቱ የጤና ሚኒስቴር ቴክኒካል አማካሪ ነው:: በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውስጥ ካሉ ተቋማት ውስጥም አንዱ ነው:: በመደበኛነት የወባ በሽታን ክትትልና ሕክምና የሚያደርገው ጤና ሚኒስቴር ቢሆንም ቁጥሩ ከፍ ሲል ወይም ወደ ወረርሽኝ ደረጃ ከፍ ሲል በቀጥታ ስራውን ወስዶ የሚሰራው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነው:: ስለዚህ በተለየ መልኩ ለዚሁ ስራ የተቋቋመ ተቋም ነው::

ኢንስቲትዩቱ ከወባ አንፃር በኅብረተሰብ ጤና አደጋ ዙሪያ ስልጠና ይሰጣል:: የምርምር፣ የላብራቶሪና የብሄራዊ ዳታ አስተዳደር ስራዎችን ያከናውናል:: በኅብረተሰብ ጤና አደጋ በተለይ በሽታዎች ከሚፈለገው ቁጥር ወይም ደግሞ ከመደበኛ ሕመሞች በላይ ሲሆን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን የሚሰራ ስራ ነው:: የወባ ስርጭትም በአሁኑ ግዜ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ በመደበኛ ስራ የሚመለስ አይደለም:: በተለይ ደግሞ የክልል ጤና ቢሮዎችን፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶችን ሁሉንም እስከ ቀበሌ ድረስ በተዋረድ አብሮ መስራትን ይጠይቃል:: የአደጋ ምላሽ ማእከሉም የሚሳተፍበት ነው:: ከአደጋ ምላሽ ማእከሉ ከሚሰራቸው ዋነኛ ስራዎች ውስጥ ደግሞ አንዱ የተግባቦት ስራ ነው::

ምክንያቱም ወባን ልዩ ከሚያደርጉት ውስጥ አንዱ ብዙ አካላትን የሚነካና የሚያሳትፍ መሆኑ ነው:: ከነዚህ ውስጥ የመጀመሪያዎቹና አስፈላጊዎቹ ሰዎች ወይም ማኅበረሰቡ ናቸው:: ለምሳሌ ጤና ሚኒስቴር የወባ መከላከያ ኬሚካሎችን ታች ወርዶ ሊረጭ ይችላል:: ነገር ግን ግድግዳዎች መልሰው ቀለም ወይም ጭቃ አልያም እበት የሚለቀለቁ ከሆነ በታሰበው ልክ የወባ በሽታን መከላከል አይቻልም::

ስለዚህ ማኅበረሰቡ የወባ በሽታ መከላከያዎችን አውቆ ራሱን ከበሽታው እንዲከላከል በየግዜው የግንዛቤ ማስጨበጫና የተግባቦት ስራ መስራት ያስፈልጋል:: በተመሳሳይ በአካባቢው የታቆሩ ውሃዎችን ማፍሰስ ልምድ ኖሮት ይህንን ተግባር በየግዜው ያለመሰልቸት እንዲተገብርና ለወባ ሕክምና የሚውሉ መድሃኒቶችን በአግባቡ እንዲጠቀም ያለመታከት የግንዛቤ ስራዎችን መስራት ተገቢ ይሆናል:: ማኅበረሰቡ በወባ መከላከል ዙሪያ እውቀት እንዲኖረውን ያን እውቀት ሁልግዜ ተግባባዊ እንዲያደርግ ማስገንዘብ ያስፈልጋል::

በዋናነት ደግሞ ማኅበረሰቡ በወባ መከላከል ዙሪያ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጣ ተመሳሳይ ስራዎችን መስራት ይገባል:: በማኅበረሰቡ ላይ የሚሰራው የግንዛቤና የባህሪ ለውጥ ስራ ደግሞ ቀጣይነትና ድግግሞሽ ያለው መሆን አለበት:: የባህሪ ለውጥ ስራው የድግግሞሽ ስራ ብቻ ሳይሆን ቁርጠኝነትም ይጠይቃል:: በሌላ በኩል ደግሞ ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች አሉ:: ለምሳሌ የአየር ንብረት ለውጥ አንዱ ነው:: የአየር ንብረት ለውጥ ሲባል ታዲያ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የአየር ንብረት ለውጥም ነው የሚታየው:: ስለዚህ ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ለውጥን ቀድሞ በመማንበብ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል::

ከዚህ ባሻገር አመራሩ ከጤና ሚኒስቴር ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ በተግባቦት መስራት አለበት:: በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ችግሩ የሰፋ ሊሆን ይችላል:: አመራሩም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ሊያደርግ ይችላል:: ማኅበረሰቡ እንደተዘናጋ ሁሉ አመራሩም ሊዘናጋ ይችላል:: ስለዚህ ወባ ክረምት ብቻ ተጠብቆ የሚሰራ ስራ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ በተከታታይ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው:: በዚህ ስራ ውስጥ ጥናቶች፣ የአመራር ስራዎች፣ ሕክምና፣ ላብራቶሪ፣ የመድሃኒት አቅርቦት ይካተታሉ:: ስለዚህ ወባን የመከላከል ስራ የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ነው::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You