“ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም”

በትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ማህበረሰብ ሰላምን እና ከሰላም የሚገኝ ልማትን እና የተረጋጋ ሕይወትን ይፈልጋል። ይህ የሰው ልጅ ትልቁ ውስጣዊ መሻት ነው። በተለይ አሁን ላይ ዓለምን እየተፈታኑ የሚገኙ ሰው ሠራሽም ሆኑ ተፈጥሯዊ ችግሮችን ለመሻገር የሰላም ጉዳይ ወሳኝ ነው።

ከዚህ የተነሳም ሰላም ዓለም አቀፍ አጀንዳ ከሆነ ሰንብቷል። በየትኛውም የዓለም ክፍል ፤ በየትኛውም ምክንያት የተፈጠሩ የሰላም መታጣቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት እና በድርድር ለመፍታት የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶች የዚሁ እውነታ ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው።

ይህም ሆኖ ግን ጦርነትን እና ግጭቶችን የግለሰባዊ እና የቡድናዊ ፍላጎቶች መግዦ የፖለቲካ መሣሪያ አድርገው መጠቀም የሚፈልጉና ይህንኑ መንገድ የሙጥኝ ብለው የያዙ የሉም ማለት አይደለም። በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያቶች በማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ ልዩነቶችን እና ልዩነቶች የሚፈጥሩትን ተቃርኖ የጦርነት እና የግጭት ምንጭ ለማድረግ የሚተጉ ግለሰቦች እና ቡድኖች አሉ።

የማኅበረሰብ የለውጥ ፍላጎቶችን እና ፍላጎቶቹ የሚፈጥሩትን መነቃቃት ፣ የሥልጣን መወጣጫ አቋራጭ መንገድ አድርገው የሚወስዱ ፣ ለዚህም ማኅበረሰቡን ያልተገባ ዋጋ ለማስከፈል ምንም አይነት የሞራል ጥያቄ የሌላቸው ፣ በህልፈቱ እና በስቃዩ ጭምር የሚፈልጉትን ለማድረግ ወደኋላ የማይሉ ናቸው።

ለእነዚህ ኃይሎች የማኅበረሰብ የሰላም እና የመልማት መፈለግ ብዙም ጥያቄያቸው አይደለም ። ለእነርሱ መሠረታዊ የሕይወት ዘመን ጥያቄያቸው በአንድም ይሁን በሌላ የሚፈልጉትን የፖለቲካ ሥልጣን ማግኘት እና ሥልጣኑን የግል ጥቅም ማሳኪያ መሣሪያ አድርጎ መጠቀም ነው ።

ማኅበረሰብ ሰላም አግኝቶ ወደ ልማት ከገባ ፤ የመልማት ጉዞው ስኬታማ ከሆነ ፤ በግጭት እና በጦርነት፤ በማህበራዊ አለመረጋጋት እና ግራ መጋባት የሚያልሙት የፖለቲካ ሥልጣን በየትኛውም መንገድ እውን ሆኖ የክፉ ሕልማቸው ባለቤት መሆን አይችሉም ። ለዚህ የሚሆን የተከፈተ በር መቼም ሊኖራቸው አይችልም።

ከዚህ የተነሳም በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ማኅበረሰባዊ የፍላጎት ተቃርኖዎችን፤ የአለመግባባት፣ የግጭት እና የጦርነት ምንጭ ለማድረግ የማይፈጥሩት ሴራ እና የጥፋት ትርክት የለም ። ሕዝብን ከመንግሥት፣ ሕዝብን ከሕዝብ ፣ ከዚያም አልፎ ግለሰብን ከራሱ ማንነት ጋር ለማጣላት የሚያባክኑት ጊዜ የለም ።

ለእነዚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች ሀገር የፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ አቅም መሆን ካልቻለች መኖሯም አለመኖሯም የተለየ ትርጉም የለውም። ከዚህ የተነሳም የሀገርን ህልውናን በሚፈታተኑ የጥፋት መንገዶች እና ተግባራት ላይ መገኘታቸው የሞራል ጥያቄ የሚያስነሳባቸው አይደሉም። በሀገር ህልውና የመደራደር ደረጃ ላይ የደረሰ ዝቅጠት ውስጥ የሚገኙም ናቸው።

በእኛም ሀገር እንደዚህ አይነት ግለሰቦች እና ቡድኖች የሀገራችን ሰላም እና መረጋጋት ፈተና መሆን ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል ። ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ ከፍለን ካሳለፍናቸው የግጭት እና የጦርነት ታሪኮቻችን በስተጀርባ የምናገኛቸውም እነዚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች ነው።

ዛሬም ቢሆን ከስድስት አስርት ዓመታት በኋላ ሕዝባችን የጀመረውን አዲስ የለውጥ መነቃቃት ለማደናቀፍ ገና ከጅምሩ አንስቶ በብዙ ሴራ እና የጥፋት ትርክት አደባባዮችን ሞልተዋል። ለትውልዳቸው የሞት ፣ የስቃይ፣ የመከራ እና የስደት ምንጭ መሆናቸውም የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ፣ ዛሬ ላይ ለዚህ ትውልድ ተቆርቋሪ ሆነው ለመታየት ሲዳክሩ ማየት የተለመደ ሆኗል።

እነዚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች በቀደመው ዘመን ለገዛ ትውልዳቸው እንጥፍጣፊ ርህራሄ አጥተው በመልከ ብዙ ሽብር የትውልዱን ተስፋ አምክነው ፣ ሀገርን እንደ ሀገር በተስፋ ዘመን ፣ ጥቁር የታሪክ ካባ አልብሰው ዘመናቸውም በሙሉ ከሚከሳቸው ህሊናቸው ለማምለጥ ከደሙ ንጹህ ነን ሲሉ ውለው የሚያድሩ ፣ የታሪክ እና የትውልድ የደም ባለዕዳዎች ናቸው።

ከትናንት የጥፋት ታሪካቸው ሕዝብን ይቅርታ ጠይቀው ወደ ሰለማዊ የሕይወት ምዕራፍ መመለስ የሚያስችል የማንነት ድፍረት ስለሌላቸው፣ ዛሬም አውሮፓ እና አሜሪካ ተቀምጠው የሕዝባችንን የሰላም እና የልማት ጥያቄ እንደቀደመው ዘመን በግጭት እና በጦርነት ለመቀልበስ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው።

በሀገር እና በሕዝብ ላይ ግልጽ ጦርነት ከማወጅ ጀምሮ ፣ጽንፈኛ እና አክራሪ ኃይሎችን በመደገፍ ለውጡ ወደፊት እንዳይራመድ ብዙ ርቀት ሄደዋል ፣ በዚህም ሕዝብ እና መንግሥትን ብዙ ያልተገባ ዋጋ አስከፍለዋል። ይህ አልበቃ ብሏቸው ባረጀ አሮጌ ማንነታቸው ውስጥ ባልሞተው መፈንቅለ መንግሥት ነፍስ ለመዝራትም ለመንቀሳቀስ ይሞክራሉ።

“ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም” እንደሚባለው በገዛ ወንድሞቻችው እና በሕዝባችን ደም ያደቆነው የጥፋት ማንነታቸው ፣ በሕይወት ዘመናቸው የማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ የጥፋት ቅስና ካባ ለብሶ ብቅ ማለቱ ተጠባቂ ቢሆንም ፣ ይህ ትውልድ ከተረቱ በላይ በሆነ የማንነት ስሪት ውስጥ መሆኑን አለማስተዋላቸው የህሊናቢስነታቸው መገለጫቸው ነው!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You