በከተሞች ያለውን የድህነት ምጣኔ ለመቀነስ፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የስራ አማራጮችን የመለየት፣ ግንዛቤ የመፍጠርና የማደራጀት ስራዎች በኢትዮጵያ ድህነት ቅነሳ ፕሮግራም በኩል እየተሰሩ ይገኛሉ። ወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግም በየአካባቢው የስራ እድል ለመፍጠር ያሉ አማራጮችንና እድሎችን በመፈተሽ ዜጎች በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተሳታፊ በመሆን ራሳቸውንም ሀገራቸውንም እንዲጠቅሙ ሲደረግ ቆይቷል። በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም እንደ ሀገር ከአንድ ሚሊየን 300 ሺ በላይ ለሚሆኑ ስራ አጦች የስራ እድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን፤ በተለያዩ ምክንያቶች ቁጥሩ በእቅድ ከተቀመጠው ያነሰ ቢሆንም በሀገሪቱ ከነበረው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ጥሩ እንቅስቃሴ የተደረገበት መሆኑ ይገለጻል።
የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጄንሲ የ2011 በጀት ዓመት እስከ ግንቦት ወር የተከናወነው የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እንደሚያመለክተው በዓመቱ በመደበኛና በመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለአንድ ሚሊየን 636 ሺ 392 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ አንድ ሚሊየን 388 ሺ 574 ለሚሆኑት ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን፤ ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ ሴቶች 35 በመቶውን ሲይዙ ፣ 2ሺ411 አካል ጉዳተኞች እና 7ሺ695 ከስደት ተመላሾች መሆናቸውን ያመለክታል። ከነዚህም ውስጥ 96 ሺ 221 የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ተመራቂዎች መሆናቸውን ሪፖርቱ ያሳያል። በእቅዱ በተቀመጠው መሰረት የስራ እድል ለመፍጠር አለመቻሉ በዋናነት በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ሲሆን፤ ከማስፈጸም አቅምና ከስራ ፈላጊዎች አመለካከት ጋር በተያያዘ ተግዳሮቶች እንደነበሩም ተገልጿል። በመሆኑም ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች ያለባቸውን ክፍተት በመለየት ለሱማሌ ክልል የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ በአፋር ክልል ስልጠና በመስጠት ሂደት ላይ እንደሚገኝና የስራ ፈላጊ ዜጎችን አስተሳሰብ ለመለወጥና ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ እንደሆነ ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጿል።
የገንዘብ እንቅስቃሴውንም በተመለከተ በ11 ወራት ውስጥ በሚዘጋጁ ባዛርና ኢግዚቪሽን፣ በሸማቾች ህብረት ስራ ለ166 ሺ ኢንተርፕራይዞች 15 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ ለ109 ሺ ኢንተርፕራይዞች 14 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን። የብድር ስርጭትን በተመለከተም በዚሁ ጊዜ ውስጥ 8ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለ451 ሺ አንቀሳቃሾች ለማሰራጨት ታቅዶ ለ147 ሺ አንቀሳቃሾች 6 ቢሊዮን ብር እንደተሰራጨና 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ውዝፍና የዘመኑ ብድር ለማስመለስ ከታቀደው ውስጥ 4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተመላሽ መደረጉን ሪፖርቱ ያመለክታል። በዚህም ረገድ በክልሎች በኩል የተወሰዱ ብድሮችን ለታሰበላቸው አላማ መዋላቸውንና የአመላላስ ሂደቶችንም አጠናክረው መከታተል እንደሚገበ ተቀምጧል።
የትግራይ ክልል የከተሞች ስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረመድሀን ሀጎስ በክልሉ ያለውን የስራ ፈጠራ እንቅስቃሴ ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ፤ በ2011 ዓ.ም በተያዘው እቅድ መሰረት 75 በመቶ ወጣቶች ለሆኑ 104 ሺ 803 ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፈው 11 ወር 97 ሺ 151 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል። ከእነዚህም 57 በመቶ የሚሆኑት በማኑፋክቸሪንግ፤ በኮንስትራክሽን፤ በከተማ ግብርና፤ በንግድና አገልግሎት ዘርፍ ጊዚያዊ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ሲሆን፤ በተለይም በኮብልስቶን መንገድ ግንባታ 408 ሚሊየን ብር በጀት በመመደብና 60 ኪሎ ሜትር መንገድ በመስራት ከ11 ሺ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ ሲቻል በገጠር መንገድ ጥገናና ግንባታ ደግሞ 1ሺ 357 ለሚሆኑ ወጣቶች ስራ መፍጠር ተችሏል። የስራ ፈጠራው ዋና አላማ ዜጎችን የቋሚ ስራ ባለቤት ማድረግ እንደመሆኑ በቀጣይ በጀት ዓመት ስራ ከሚፈጠርላቸው ዜጎች አብዛኛዎቹን ቋሚ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ለመስራት እቅድ መያዙን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ በስራ እድል ፈጠራ ረገድ የተሻለ አፈጻጸም ነበር የሚሉት ዳይሬክተሩ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊየን ብር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታስቦ በተለያየ ደረጃ አንድ ነጥብ 75 ቢሊየን ብር በመፍጠር 37 ሺ የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል። የብድር አቅርቦትንም በተመለከተ 2 ቢሊየን ለማቅረብ ታቅዶ ለ36ሺ 367 ተጠቃሚዎች አንድ ነጥብ 91 ብር ማቅረብ የተቻለ ሲሆን ብድር በመመለስና በቁጠባም በኩል የተሰሩት ስራዎች አበረታች እንደነበሩ ተናግረዋል። 43ሺ 967 ለማሸጋገር እቅድ ተይዞ 39ሺ 876 ከጀማሪ ወደ ጥቃቅን እንዲሁም ከጥቃቅን ወደ ታዳጊ ማሸጋገር መቻሉን የገለጹት ዳይሬክተሩ ከፍተኛ የግንዛቤ እጥረት በመኖሩም ለ74 ሺ ኢንተርፕራይዞች ተግባር ተኮር ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።
ከመንግስት ተቋማት ጋር ያሉ ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ማነቆዎችን ለመቅረፍ፣ በኢንተርፕራይዞችና ግለሰቦች በኩል ያለውን ጠባቂነትና ብድር በመመለስ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለቀጣይ ለማስተካከል ግንዛቤ መፍጠር ላይ እንደሚሰራም ተናግረዋል። በክልሉ የስራ አጥነት ችግሩ ሰፊ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ከ2009 እስከ 2010 በተደረገ ጥናት ከ20ነጥብ ስድስት በመቶ ስራ አጥ መኖሩን ያሳያል የድህነት ደረጃውም 29 በመቶ ነው። በመሆኑም አሁን እየተሰራ ካለው በላይ መስራት ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው በተያዘው በጀት ዓመት ለ351 ሺ ስራ አጦች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ከ90 በመቶ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ 42 ሺ ኢንተርፕራይዞች እንደሚገኙ ይናገራሉ። እንደ አቶ ተፈሪ ማብራሪያ ከፌደራል መንግስት ተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር 209 ቢሊየን ብር የተሰራጨ ሲሆን፤ የክልሉ መንግስትም 600 ሚሊየን ብር ተጨማሪ በጀት መድቧል። ከ352 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከሶሰት ሺ በላይ ሼዶች ተገንብተዋል። ከእቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነበር፤ ይህ ሊሆን የቻለው በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ዘግይቶ በመጀመሩ ነው። የማምረቻና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት በቂ አለመሆን፤ በፍላጎት ልክ የብድር ገንዘብ ማቅረብ አለመቻልና በወጣቱ በኩል ሰርቶ የመለወጥ አመለካከት አለመዳበር ተጨማሪ ተግዳሮቶች ነበሩ። እንደ ተቋምም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በኩል የታዩ ክፍተቶች ነበሩ።
በክልሉ ተዘዋዋሪ ፈንድ በማስመለስ ረገድ አበረታች እንቅስቃሴ ተደርጓል የሚሉት ሃላፊው ለዚህ ሲባል የተቋቋመው ግብረ ሀይል ከቢሮ እስከ ቀበሌ በየአስራ አምስት ቀኑ እየተገናኘ እንደሚሰራና የአመላለስ ምጣኔው 97 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል። አንዳንድ የብድር አጠቃቀም ችግር የተስተዋለባቸውን ወጣቶች ለመቆጠጣጠር እቅድ መያዙን በመጠቆም ለቀጣይ አመት የተያዘውን እቅድ እንደሚከተለው ገልጸዋል። በ2012 በጀት አመት 716ሺ 123 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠርና 70ሺ ኢንተርፕራይዝ ለማቋቋም እቅድ ተይዟል። ከመካከለኛ፣ አነስተኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች የገበያ ትስስር ለመፍጠር የተጀመረውም ስራ የሚቀጥል ይሆናል። የብድር አቅርቦት፤ የሼድ ግንባታ፤ የመስሪያ ቦታ፤ ስልጠናና ድጋፍም አሁን ካለው በተሻለ ለማቅረብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት እቅድ መያዙንም ተናግረዋል።
በበጀት አመቱ አስራ አንድ ሺ 398 መቶ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ቢታቀድም ማከናወን የተቻለው ግን ሁለት ሺ 478 ብቻ ነው። የሚሉት ደግሞ የአፋር ክልል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተር ፕራይዞች ቢሮ የእቅድና ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ አሊ ከሌይታ ናቸው። አቶ አሊ እንደሚያብራሩት በክልሉ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋትና እሱን ተከትሎ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዲሁም ከዚህ ጋር ተያይዞ በቢሮው የአመራር ለውጥ በተደጋገሚ በመደረጉ ስራዎች በተፈለገው ደረጃ እንዲከናወኑ ማድረግ አልተቻለም። ባለፈው አመት ብቻ በቢሮው ሶስት ግዜ የአመራር ለውጥ ተደርጓል። የብድር አቅርቦት በወቅቱ አለመድረስም አንዱ ችግር ነበር።በወቅቱ ተቋቁመው የነበሩት የስትሪንግ ኮሚቴዎች በመበተናቸው ከማይክሮ ፋይናንስ ብድር ማውጣት አልተቻለም። የብድር አመላለሱም የተጓተተ መሆኑ ማይክሮ ፋይናንስ ብድር እንዲከለክል አንዱ ምክንያት ሆኗል። እስካሁን ከተወሰደው አርባ ሚሊየን ብር መሰብሰብ የተቻለው 400 ሺ ብር ብቻ ነው። በዚህም የተነሳ ለክልሉ ከተመደበው 200 ሚሊየን ብር መጠቀም የተቻለው አርባ ሚሊየኑን ብቻ ሲሆን፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዘርፉ ኪራይ ሰብሳቢነት የሚስተዋልበት ሆኗል።
የቦታ አቅርቦትም አንዱ ችግር ነው። በተለይ በክልሉ ሼዶች ሲገነቡ የሚሰጣቸው ቦታ ከከተማው ወጣ ያለና ለማምረትም ለመሸጥም የማይመች ነው። በዚህም የተነሳ እንደ አማራጭ የወሰዱት መከራየትን ነው። ሲከራዩ ደግሞ አከራዮቹ በብድር እንደሚከፈል ስለሚያውቁ የሚከራዩት ቤት በጣም ውድና ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ነው። በተደረገ ፍተሻም አንድ ሺ 500 ብር የሚያወጣ ቤት አራት ሺ ብር ድረስ ተከራይተው የተገኙ አሉ። በመሆኑም ለቀጣይ ዓመት የሼድ ግንባታዎችን በማቆም በከተማው መሀል 120 የኮንቴነሮች ግንባታ ለማከናወን ከክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በሌላ በኩል በክልሉ ሰፊ የአመለካካት ችግርም አለ። ወጣቶች ግንዛቤ ስለሌላቸው ለመደራጀት ፈቃደኛ አይደሉም፤ ተስፋ መቁረጥ በስፋት ይስተዋልባቸዋል። በመሆኑም ክልሉ ከፌደራል ጋር በመቀናጀት የወጣቱን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በስፋት ለመስራት በዝግጅት ላይ ይገኛል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክልሉ ከ250 በላይ ኢንተርፕራይዞች ቢኖሩም በርካታ ኢንተርፕራይዞች ገንዘብ ከወሰዱ በኋላ ለቁጥጥር ሲኬድ የከሰሙ ሆነው ተገኝተዋል፤ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት በትክክል እየተንቀሳቀሱ ያሉት ስላልተለዩ በቀጣይ ዓመት ቁጥጥር ለማድረግ እቅድ መያዙን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ